ለዚህ እኔም ምስክር ነኝ

በሚሊዮን በለጠ

atoMillionየመምሬ ወልደ ሰንበት የልጅ ልጅ ነኝ። እናቴና አባቴ መሃይማን ቢሆኑም ከእናቴ ጋር ወደ ዳሩ ማርያም ቤተክርስቲያን እሄድ ነበር። እናትና አባቴ ይህን እመን ያን አትመን ይህን ተከተል ያን አትከተል ብለው ባያስተምሩኝም በአኗኗራቸው እንድከተለው የሚገባኝን መንገድ አስጀመሩኝ። ስለ አጀማመሬ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። በአጀማመሬ እኮራለሁ። ፈሪሃ እግዚአብሔርን የተማርኩት ከወላጆቼ ነው። ከእናቴ አባት ከመምሬ ወልደ ሰንበት የተላለፈልኝ በግዕዝና በአማርኛ የተጻፈ የዮሐንስ ወንጌል ነበር። ወንጌሉን ሳነብ ባይገባኝም የመጀመሪያው የንባብ መማሪያ መጽሐፌ ግን እሱው ነበር። ያን መጽሐፍ በክብር ነበር የያዝኩት።

የኔታ አልፎ አልፎ ዛፍ ሥር፣ አንዳንዴም ቤታቸው ጣራ ሥር ቁጭ ብለው የሚያነቡትና፣ በማያነቡበት ጊዜ ሳጥን ውስጥ ሽፍንፍን አድርገው የሚያስቀምጡት መጽሐፍ ነበራቸው። አልፎ አልፎ ከዚያ መጽሐፍ ያነቡልን ነበር። ስለ ፍጥረትና ስለ ዳዊት የነገሩን ትዝ ይለኛል። ያ መጽሐፍ በግሌ ኖሮኝ ማንበብ የምችልበትን ጊዜ እናፍቅ ነበር። በትምህርት ይበልጠኝ የነበረ ጓደኛዬ “ብዙ ነገር የሚገኝበት መጽሐፍ” እንደ ሆነ ይነግረኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ያለው መሆኑ በአእምሮዬ የተፀነሰው ያኔ ነበር።

ከቄስ ትምህርት ቤት ወጥቼ ለሁለት ዓመት ከብቶች ከጠበቅሁ በኋላ ደደር መንግሥት ትምህርት ቤት ገብቼ መደበኛ ትምህርት ጀመርኩ። ከትምህርቶቹ ክፍል አንዱ ግብረ ገብ ነበር። በዚህ ትምህርት መልካም ማድረግ ማሸለሙን፣ ክፉ ማድረግ በምድርም በሰማይም እንደሚያስቀጣ፣ ስለ አሥርቱ ትዕዛዛትና ስለ ስድስቱ ቃላተ ወንጌል በሚገባ ተማርን። በተለይ በማቴዎስ ምዕራፍ ሃያ አምስት የሚገኘው በዓለም መጨረሻ ስለሚሆነው ፍርድ የተጻፈች ትንሽ መጽሐፍ ተሰጥታን ስለ ነበር ደጋግሜ አጥንቼአት ነበር። አንድ ቀን እግዚአብሔር ፊት እንደምቀርብ፣ ያን ለት በእድሜዬ ሙሉ የሠራሁት ሁሉ በሚዛን ላይ ባንድ በኩል ደጉ ሥራዬ፣ በሌላው ክፉ ሥራዬ በሚዛን እንደሚቀመጥ አነበብሁ። የቱ ያመዝን ይሆን በማለት እጨነቅም አስብም ነበር።

ከዚያን ዘመን ገጠመኞቼ የማልረሳው አንዱ በአስራ ሰባት ዓመት እድሜዬ በጠና ራሴን አሞኝ ከሁለት ሳምንት በላይ ትምህርት ማቋረጤን ነበር። የመጀመሪያውን ሕክምና ያደረገችልኝ እናቴ ናት። ካደረገችልኝ ሕክምና አንዱ ለጋ ቅቤ በእንሰት ቅጠል አድርጋ ራሴን በሻሽ ማሠር ነበር። መታሠሩ ግውግው የሚለውን ራሴን ሸብ ስላደረገው ራስ ምታቱን ያሻለው ይመስለኝ ነበር። ያልተደረግልኝ ነገር አልነበረም። የምንኖረው ገጠር ስለ ነበር አባቴ ወደ ከተማ ወጥቶ ከጤና ጣቢያ ነጫጭ እንክብሎችን ይዞ መጥቶ ሁለት ሁለቱን በቀን አራት ጊዜ መዋጥ እንዳለብኝ ነገረኝ። የታመመው ራሴ ሆኖ የሚዋጥ ነገር ለእኔ መስጠቱ ግር አለኝ። የታመመው ራሴ ነው እንጂ ሆዴ አልነበረም። ሌላው የተደረገልኝ የወዳጃ ሥርዓት ነበር። በወዳጃ ጊዜ በመንደር ያሉት አዋቂ ሰዎች [ቆቱዎች ይባላሉ] ከማታ ጀምሮ ዶሮ እስኪጮህ ድረስ ጫት እየቃሙ ሆጃ እየጠጡ ያዜማሉ። አልፎ አልፎ እኔን ከመካከላቸው በማስቀመጥ ከወገቤ በላይ ራቁቴን አድርገው በጉንጫቸው ውሃ ይዘው እንትፍ እንትፍ እያሉብኝ በእኔ ውስጥ ያለው በሽታ ለቆኝ እንዲሄድ ለማድረግ ይጥሩ ነበር።

በዚያን ጊዜ ልሞት ነው ወይ? ብሞት የት ነው የምሄደው? ለፍርድ ስቀርብ የሚያመዝነው መልካም ሥራዬ ነው? ወይስ ክፉ ሥራዬ? ብዬ እጨነቅ ነበር። ቃል ኪዳንም ገብቼ ነበር። ልዳን እንጂ ክፉ ላላደርግ መልካሙን ብቻ ላደርግ ቃል ገብቼ ነበር። እግዚአብሔር ይመስገን! ዳንሁ። መልካም ሰው የመሆኑ ጉዳይ ግን፣ በተግባር የማዋሉ ነገር ተረሳ። ለካስ! ሰው በራሱ ኃይል ኃጢአት አለማድረግም ሆነ መልካም መሆን አይችልም።

ይህን ገጠመኜን የጠቀስሁበት ዋናው ምክንያት ሁለት ነው። አንደኛው፣ በሕይወቴ እንደ ተረዳሁት፣ ሰው በራሱ ኃይል ራሱን መልካም ሊያደርግ እንደማይችል ለመግለጽ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎአል። “እኔ የማደርገውን አላውቅም፣ ምክንያቱም የምወደውን ነገር ማድረግ ትቼ፣ የምጠላውን አደርጋለሁ … ማድረግ የምፈልገውን መልካም ነገር አላደርግም፣ ዳሩ ግን የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁ” [ሮሜ 7፡15-19]። እውነተኛ ክርስቲያን ኃጢአት ላለመሥራት፣ መልካም ለማድረግ መለኮታዊ ኃይል ያስፈልገዋል። ይህን ኃይል ደግሞ የሚያገኘው ኢየሱስ ክርስቶስን በመከተል እንደ ሆነ ነው።

ሁለተኛው ምክንያቴ፣ ያኔ ስለ ሞት የነበረኝን እይታና በኋላ ያለኝን እይታ ልዩነት ለመግለጽ ነው። ይኸውም ከዓመታት በኋላ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኜ አድርጌ ከተቀበልኩ በኋላ የተከሰተ ነው። ከተግባረ ዕድ ትምህርት ቤት ተመርቄ ዓመታት ከሠራሁ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ሄድሁ። እዚያ እንዳለሁ ሃይለኛ የሆድ ቁርጠት ይዞኝ ወደ ሐኪም ቤት ተወሰድሁ። ስመረመር የትርፍ አንጀት መሆኑ ታወቀና ወዲያው የቀዶ ጥገና እንዲደረግልኝ ተወሰነ። ከቀዶ ጥገናው በፊት አንዲት ነርስ እርሳስዋን አሹላ አንድ ቅጽ ልትሞላ አልጋዬ አጠገብ ቁጭ አለችና የቅጹን ክፍት ቦታዎች መሙላት ጀመረች። “ሙሉ ስምህ ማነው? መቼ ተወለድህ? የት ተወለድህ? …የመኖሪያ አድራሻህ?” እያለች ጠየቀችኝ። ለሁሉም መልስ ሰጠሁ። በመጨረሻ “የቅርብ ዘመድ ስም?” አለችኝ። “የት የሚገኝ?” አልኳት። “በዚህ በሰጠኸኝ አድራሻ” አለችኝ። “እንኳን በዚህ አድራሻ በመላው አሜሪካ ዘመድ የለኝም። ለመሆኑ ይህ ለምን አስፈለገ?” ስላት፣ “እንደምትመለከተው ነገሩ ቀላል ቢሆንም ኦፕራስዮን ልትሆን ነው። ማን ያውቃል?” ስትል “ትሞት ይሆናል ማለትሽ ነው እንዴ?” አልኳት። እርስዋም “ኦፕራስዮኑ ቀላል ቢሆንም …” አለች። የጓደኛዬን ስም ሰጠኋትና ሄደች። ከሄደች በኋላ ነገሩ አሳሰበኝ። እሞት ይሆን እንዴ? አልሁ። ብሞት እናቴ በጣም እንደምታዝን ገመትሁ። ለሀገሬ፣ለጌታዬ ምንም ሳልሠራ ልሞት ነው? አልኩኝ። በአንደኛ ዮሐንስ 5፡13 የተጻፈውን “በእግዚአብሔር ልጅ ስም የምታምኑ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ያላችሁ መሆኑን እንድታውቁ ይህን ሁሉ ጽፌላችኋለሁ” የሚለውን ቃል አስታወስሁ። ብሞት የምሄደው ወደ ኢየሱስ መሆኑን ተገነዘብሁ። ቅር የተሰኘሁት ምንም ሳልሠራ በመሞቴ እንጂ ሞትን አልፈራሁም። ወጣት በነበርኩበት ጊዜ በራስ ምታት ምክንያት ከዚህች ዓለም ብለይ የምሄድበትን ቦታ ባለማወቄ የፈራሁት ያ ፍርሃት አልነበረም፤ ሕይወቱን ለጌታ ኢየሱስ የሰጠ ሞትን አይፈራም። ለዚህ እኔም ምስክር ነኝ።

አቶ ሚሊዮን በለጠ በተባበሩት መጽሐፍ ቅዱስ ማህበራት የአፍሪካ አህጉር ዋና ፀሐፊ ሆነው 17 ዓመታት አገልግለዋል። ይህ ጽሑፍክርስትናበሚል ርዕስ 2000 .. ካሳተሙት መጽሐፍ ከገጽ 9-12 በፈቃድ የተወሰደ ነው። ሙሉውን መጽሐፍ ለማግኘት ራእይ መጽሐፍት መደብር፣ ፓሣቁ 2332 አዲስ አበባ፤ ኢሜይል፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ጠይቁ | photo credit:archives.mhsc.ca