ስለ አንበሳና ስለ አይጥ

Lion Mouseአንበሳ በዱር ውስጥ ወዲያና ወዲህ እየሮጠ ምግቡን ሲፈልግ ውሎ ደከመውና ባንድ ዛፍ ሥር ተኛ። በዛፉም ሥር አንዲት አይጥ ከጉድጓድዋ ወጥታ በአንበሳው ላይ እየዘለለች ትጫወት ጀመረች። አንበሳው ግን ከድካሙ ብዛት የተነሣ አልሰማትም። ከዚህ በኋላ ባፍንጫውና ባይኑ ላይ ትዘል ጀመረች። በዚያ ጊዜ አንበሳው ከእንቅልፉ ነቃና አፈፍ አድርጎ ያዛት። ሊውጣትም ያንን የሚያስፈራ አፉን ከፈተ። አይጢቱም ያራዊት ንጉሥ ሆይ፣ ማረኝ፤ በድዬሃለሁ፤ የዛሬን ብቻ ማረኝ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ቸርነትህን ለዘላለሙ አልዘነጋም። ደግሞም ምንም ትንሽ ፍጥረት ብሆን አንድ ቀን በተቻለኝ ነገር እረዳሃለሁ እያለች ትቀባጥር ጀመረች።

አንበሳውም አይጢቱ እረዳሃለሁ ባለችው ነገር ሳቀና ለቀቃት።

አይጢቱም እግዚአብሔር ይስጥልኝ ብላ ወደ ጉድጓድዋ ጥልቅ አለች።

ከጥቂት ቀን በኋላ አንበሳው በጨረቃ ብርሃን ላደን ወጥቶ ሳለ አዳኞች ያንን የሚተኛበትን ዛፍ አይተው ኑሮ ወጥመድ አጥምደውበት ሔዱ። አንበሳውም ከስፍራው ሀያ ኪሎ ሜትር ርቆ ሔዶ ነበረና ሲመለስ በድንገት ወጥመዱ ያዘው።

ከዚህም በኋላ ወጥመዱን ለመበጠስ ቢዘል፣ ቢያገሣ፣ የማይሆንለት ሆነ። አዳኞቹም ባንድ ስፍራ ተቀምጠው ይመለከቱ ኑረው ወጥመዳቸው እንደ ያዘላቸው አይተው አንበሳውን ወስደው ለንጉሥ ለመስጠት የብረት አጥር ያለው ሠረገላ ለማምጣት ወደ ከተማ ሔዱ።

በዚያን ጊዜ ያች አይጥ አንበሳው ሲያገሣ ሰምታ ኑራ ከጉድጓድዋ ብቅ አለችና ያራዊት ንጉሥ ሆይ፣ አንድ ቀን እረዳሃለሁ ብዬህ አልነበረምን አለችው። አሁንም አንበሳው በብርቱ ጭንቀት ተይዞ ሳለ ባይጢቱ ንግግር ሳቀ። አይጢቱ ግን አትሳቅ እመነኝ። አሁን ባሁን ከዚህ ከጭንቀትህ አወጣሃለሁ አለችው። ይህንም ከተናገረች በኋላ አንበሳው የታሰረበትን የወጥመዱን ገመድ ባንድ አፍታ ቀረጣጥፋ ጨረሰችው። አንበሳውም ከወጥመዱ አምልጦ በወጣ ጊዜ አይጢቱ ቀርባ ያራዊት ንጉሥ ሆይ፣ እኽ፣ እኔ እውነተኛ አይደለሁምን አለችውና ወደ ጉድጓድዋ ጥልቅ አለች።

ከወዳጄ ልቤ፣ ገጽ 112-113 የተወሰደ። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ከኢዞፕ ተረቶች ተርጉመው በ1922 ዓ.ም. እንዳሳተሙት። አአ ዩኒቨርሲቲ ማተሚያ እንደገና በ2 ሺህ ዓ.ም. አሳተመው።  Illustration credit: americanliterature.com