ስለ አንበሳና ስለ ነብር፤ ስለ ጅብና ስለ አህያ ባልንጀርነት

ethiopianTales

አንበሳና ነብር፣ ጅብና አህያ፣ ባልንጀርነት ይዘው ባንድነት ሲኖሩ ምግብ ተቸገሩ። አንድ ቀን ባንድነት ተሰብስበው ስለ ምግባቸው ምክር ጀመሩ። ከቶ እግዚአብሔር ምግብ የነሣን በምን ምክንያት ይሆን፤ ምናልባት ከመካከላችን ትልቅ ኃጢአት የሠራ እንዳለ ሁላችንም እንናዘዝ፤ ትልቅም ኃጢአት ሠርቶ የተገኘውን ከመካከላችን እናጥፋው ተባባሉ።

መጀመሪያ አንበሳን ተናዘዝ አሉት። አንበሳም ሊናዘዝ ቀረበ። እኔ አንድ ቀን ተርቤ ውዬ ነበርሁ። ዘላኖች ብዙ ከብት ይዘው በዱር ውስጥ በረት ሠርተው ተቀምጠው ነበረና ቀኑ ሲመሽ አይቼ በበረቱ ውጭ ቆሜ አንድ ጊዜ ባገሣ ሰንጋው ሁሉ በረቱን እየዘለለ ወጣ፤ እኔም አንዱን ሰንጋ ሰብሬ ደሙን ጠጥቼ ሥጋውን በላሁት፤ ይህ ኃጢአት እንደ ሆነ ፍረዱብኝ አለ። ባልንጀሮቹ መለሱ፤ ወዲህ ተርበህ ወዲህ ደግሞ በዱር ውስጥ የሚኖሩ ከብቶች አግኝተህ እንኳን አንድ ሰንጋ ብዙውንስ ብትበላ ምን ኃጢአት አለብህ ብለው ፈረዱለት።

ነብር ቀረበ፤ እኔም አንድ ቀን እጅግ ተርቤ በዱር ውስጥ ወዲያና ወዲህ እያልሁ ምግብ ስፈልግ፣ አንዲት ፍየል ከእረኛዋ ጠፍታ ብቻዋን ቅጠላ ቅጠሉን ስትለቃቅም አገኘኋት። ወዲያው አንቄ ይዤ ደምዋን ጠጥቼ ሥጋዋን በላሁት። ይህ ኃጢአት እንደ ሆነ ፍረዱብኝ አለ። ባልንጀሮቹ መለሱ፤ ወዲህ ተርበህ ወዲግ ደግሞ ከእረኛዋ የጠፋች ፍየል አግኝተህ፤ እንኳን አንዲት ፍየል ብዙስ ብትበላ ምን ኃጢአት አለብህ አሉት።

ጅብ ቀረበ፤ እኔም አንድ ቀን እጅግ ተርቤ ውዬ ነበረ። ማታ ከጉድጓዴ ወጥቼ ምግቤን ስፈልግ ነጋዶች ቢደክማባቸው ጥለውት የሔዱ አንድ የፈረስ አጋሠሥ፣ ከመንገድ ዳር ወድቆ መነሣት አቅቶት ሲገላበጥ አግኝቼ እርሱን በልቻለሁ፤ ይህ ኃጢአት እንደ ሆነ ፍረዱብኝ አለ። ባልንጀሮቹ መለሱ፤ ወዲህ ተርበህ ወዲህ ደግሞ ነጋዶች ጥለውት የሔዱ አጋሠሥ አግኝተህ፣ እንኳን አንድ አጋሠሥ ብዙስ ብትበላ ምን ኃጢአት አለብህ አሉት።

ከዚህ በኋላ አህያን ነይ ተናዘዢ አሏት። አህያም ቀረበች፣ አንድ ቀን ጌታዬ ብዙ ጭነት ጭኖብኝ ስሔድ፣ ጌታዬ በመንገድ ላይ አንድ ሰው አገኘና ከዚያ እየተነጋገረ ቆመ። እኔም እጅግ ተርቤ ነበረና እነዚያ እስቲነጋገሩ ድረስ በመንገዱ ዳር ሠርዶ መሳይ አግኝቼ ያንን እየነጨሁ ቆየሁ፤ ወዲያው ጌታዬ መጣና መጫኛውን አጠባብቆልኝ መንገዳችንን ተጓዝን። ይህ ኃጢአት እንደ ሆነ ፍረዱብኝ አለች። ባልንጀሮችዋም መለሱ፤ ከዚህ የበለጠ ምን ኃጢአት አለ፤ ጌታሽ ከሰው እስቲነጋገር ከመንገድ ወጥተሽ ሠርዶ እየነጨሽ የቆየሺው ትልቅ ኃጢአት አይደለምን፣ እግዚአብሔር ምግባችንን የነሣን ለካ ባንች ኃጢአት ኑሮዋል። አንችን ከመካከላችን ካላጠፋን እግዚአብሔር አይታረቀንም ብለው ወዲያው ገነጣጥለው በሏት።

ምንጭ፦ ወዳጄ ልቤ እና ሌሎችም፤ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ እንደ ጻፉት፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዳሳተመው፤ 2 ሺህ ዓ.ም.፤ ገጽ 118-119።          2010/2012