አሁን መቼ ይሁን?

ትናንትን አየሁት፣ ጓዙ ተሸካክፎ፣ ጭልጥ ብሎ ሲነጉድ

አምናንም ቃኘሁት፣ ብዥታ ታቅፎ፣ እንከፍ እንከፍ ጎርደድ

ዘንድሮን ደገምኩት፣ ሲስገመገም ጎርፎ፣ ድንፋታው እስኪበርድ

ነገንም ታዘብኩት፣ ከከርሞ ተራርፎ፣ ጭላንጭሉን ሲሰድ

የሄደውን ሸኘሁት፣ ሲሳለም ተጣድፎ፣ አዲሱ ሲወደድ

የመጣውን አቀፍኩት፣ ገልፍጦ ለፍፎ፣ ደሞ እስከሚሰደድ

ግና መቼ ይሁን 

የማየው አሁንን

እምሰማው ድምጹን 

ስለቴ ሰምሮልኝ

ቤት ለእምቦሳ ብሎኝ

ናፍቆቴ በረካ፣ እቅፍ አርጎ ስሞኝ

አሁን ሚሉት ደርሶ

ሁሉን አተራምሶ

ገደብ ኬላውን ጥሶ

ገመዱን በጥሶ

ድንበሩን አፍርሶ 

ወይም ጉድጓድ ምሶ

ክምሩን ደርምሶ

ደንቃራውን ገርስሶ

መች ይሁን ሚሆነው?

አሁንን አይቼው

አሁን አሁን ባየው

ናፍቆቴ ምነው ጃል?

አሁን ሚሉት የታል

የማይደርስ ገደል

ቢጠበቅ ኮሽ የማይል

የማይጨበጥ ላመል

የሰማይ መሰላል

የጨረቃ አፍላል

የጉም ክምር ቁልል

አይታችሁዋል ልበል?

አሁንን አይቼው

አሁን አሁን ባየው

መች ይሁን ሚሆነው?

መክረሙ ሳያንሰው

ትዕግስት እንዳይከብደው

ጥብቅ አርጌ ይዤው

ላልለቅ ተጠምጥሜው

እንድኖር አብሬው

ሽቶኝ ተመችቼው

የቀረው ቀርቶብኝ አሁንን አግኝቼው

ባሁን ተከልዬ፣ አሁን አሁን ባየው

“በትክክለኛው ሰዓት ሰማሁህ፤

በመዳንም ቀን ረዳሁህ” ይላልና።

እነሆ፤ ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው፤

የመዳንም ቀን አሁን ነው። (2ኛ ቆሮንቶስ 5፡2) 

ጎዳና ጎግያጎ (c) 2017