ርዕሰ አንቀጽ
የጥበብና የሰላም መጀመሪያ ዛሬም እግዚአብሔርን መፍራት ነው
ሃይማኖት የጠብና የጦርነት መንስዔ ነው አፅንቶ መባል ከጀመረ ይኸው መቶ ዓመት አለፈው።
ሃይማኖት አክራሪነትን ያጸናል፤ የዓለማትን ታሪክ
ለድርድር ሥፍራ የለውም፤ ቅራኔን ያሰፋል፤ ወደ ጠብ ያመራል፤ ይሉናል።
ስለ ሕይወት፣ ስለ ጽድቅ፣ ስለ እውነት “እርግጠኛ መሆን ይቻላል” ስለሚል በሰላም አብሮ መኖር እንዳይቻል ጋሬጣ ሆኗል።
ለዚህ መፍትኄው ሃይማኖትን ችላ ማለት ነው፣ ይሉናል።
ሰው መረን እንዳይወጣ፣ ከአራዊት እንዲለይ ሃይማኖት ያበረከተውን ሥነ ምግባርና ገደብ እነዚሁ ይዘነጋሉ፤ ማስታወስ አይፈቅዱም።
እርግጥ በሃይማኖት ስም በደል አልተፈጸመም አንልም። ሕዝብን ለማነሳሳት ሃይማኖታዊ ሽፋን አልተበጀም አንልም።
እውን ግን ሃይማኖት ለሰላም መጥፋት ምክንያት ነው?
የታሪክ ማኅደር ሲገለጥ በተለይ በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታየው አሣር መነሻው ሃይማኖታዊ ሳይሆን ብሄራዊ፣ ፖለቲካዊና ኤኰኖሚያዊ ሆኖ እናገኘዋለን።
የሶቭየት ኅብረቱ ጆዘፍ ስታሊን ብቻውን ከሃያ ሚሊዮን ያላነሰ ሰው አስፈጅቷል። በዚህ ላይ የመጀመሪያውን የዓለም ጦርነት ይጨምሩ፣
· ሁለተኛውን ይድገሙ።
· የእስራኤልና የፍልስጤምስ?
· የኰሪያ ጦርነት ለምን ይረሣ?
· ቪየትናምስ?
· የቻይና ሽብርና የባሕል አብዮት?
· የኢትዮጵያስ የ 6/66 ግርግር?
· የኢትዮጵያና የኤርትራ ውጊያ
· ሩዋንዳ-ቡሩንዲ
· ኰንጎ፣ ወዘተ
የአንዳቸውም መንስዔ ሃይማኖት እንዳልሆነ እንረዳለን።
እኛ ግን የጦርነት ምክንያት ሰው የራሱን ክብር መፈላለጉና ፈሪሃ እግዚአብሔር መጥፋቱ ነው እንላለን። አያቶቻችንና አባቶቻችን ሲጠሩት የኖሩት አምላክ መረሣቱ ነው፤ ችግሩ ያለው የሰው ልብ ጋ ነው፣ እንላለን፤
ከልብ ክፉ አሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣልና (ማቴዎስ ወንጌል 15፡ 19)
· · ·
ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲጠፋ ወጣቱ ለአዛውንቱ ከተቀመጠበት አይነሳም። ነጋዴው በሚዛን ይበድላል። የአገር መሪው ለሕዝብ አይራራም። ልጅ ወላጁን ያዋርዳል። ወልዶ ይጥላል፣ ችላ ይላል። ጫማ አስጠርጐ ጥፊ ይከፍላል፣ ካልቾ ይመርቃል። ሰውን በቋንቋና በቁመና ያገላል ወይም ያቀርባል። በአደባባይ ለሴቶች መብት ይከራከራል፤ ቤት ገብቶ ሚስቱን ያንገላታል።
ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲጠፋ ጓዳው ከእግዚአብሔር ቤት ይበልጥበታል። ራሷን አላስደፍር ያለች ሴት ተማሪ ከትምህርት ገበታዋ ላይ ትፈናቀላለች። ይኸኛው ቃል ይገባል፣ ያፈርሳል። አማና ይበላል። ያኛው ፍቅረ-ንዋይን በረከት፣ ጮሌነቱን ጥሪ ይለዋል። መማለጃን የፍቅር ስጦታና መብት፣ የቡድን ስሜቱንና አንጀኛነቱን ደግሞ አንድነትና ኅብረት ብሎ ይሰይማቸዋል።
ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲጎድል ምሑሩ ለእውነት አልገዛ ይላል። አብሮ የኖረ ወዳጅ ይከዳል። ሸክም ያንገላታት አህያ ዱላ ይጨመርላታል። ሕግ የሚያስከብረው ይሰርቃል። ቄሱ ያታልላል። ሐኪሙ ቃለ መሃላውን ያፈርሳል። ፈላስፋው፦ አመጽም እኰ ወደ ጽድቅ ያደርሳል ይላል።
· · ·
ፈጣሪ እንግዲህ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ነው። ፍጡር ደግሞ ዓለማት፣ ሰውና የሰው ሥራ ውጤቶች ናቸው። ፍጡር ፈጣሪውን ማምለክና በሥርዓቱ መተዳደር ድርሻው ነው።
ሰው ሳያመልክ መኖር አይችልም። ፈጣሪውን ካላመለከ ራሱን ያመልካል ወይም ተመልሶ ለገዛ እጁ ሥራ ይሰግዳል።
ለፈጣሪው የተለየውን የሕይወቱን ክፍል በተለያዩ ተግባራትና የኑሮ እንቅስቃሴዎች መሙላት ይሞክራል፤ ግን አይረካም። ለአምላክ ሥፍራ እስከሚለቅለት ድረስ ዕረፍትን አያይም። ይህን እውነት መፋቅ አይቻልም።
ፍጡር የፈጣሪን ሥፍራ ሲይዝ፣ ሁሉን መቆጣጠር ሲሻ፣ ያኔ ማኅበራዊ ቀውስ ይከተላል። ይኸ የዓለም ሕዝቦች ጥንትም ሆነ ዛሬ የሚያልፉበት የተመሰከረ ታሪካቸው ነው። ኃጢአት በመሠረቱ እግዚአብሔርን፦ “አታስፈልገኝም፣ እኔ በራሴ ብቁ ነኝ” ማለት ነው። ኃጢአት ከእግዚአብሔር መሸሽ ነው፤ ወደ መቅበዝበዝ ወደ ፍርሓትና ወደ ሞት ክልል ማዝገም ነው።
ወደ እግዚአብሔር መሸሽ ግን ጽድቅና ሰላም ሕይወትም ነው።
የኤኰኖሚ ስልት የሰው አዕምሮ ውጤት ነው፣ ስለዚህም ፍጡር ነው። አዕምሮ የተሰጠን ለምድራዊ ኑሮአችን እንድናውቅበት እንጂ ሰጭውን እንድንዘነጋበትና እርስ በርስ እንድንናናቅበት አይደለም። እውቀታችን የማኅበረ ሰብን ኅልውና መቆጣጠር ሲጀምር ለፈጣሪ የሚገባውን ቦታ ይዟልና አምላክ ሆነ ማለት ነው። ሰው አምልኰውን ወደ ፈጣሪው ሳይሆን ወደ ራሱ ሲያቀና በዚያው ልክ በስነ ልቡናውና በማኅበራዊ ግንኙነቱ ላይ ቀውስ መታየት ይጀምራል።
የኤኰኖሚ ሥርዓት ምን ያህል ቢሠምር በአምላክ ልክ የሰውን ሁለንተናዊ ፍላጐት ሊያረካ አይችልም። አሜሪካኖች ይመስክሩ። ጃፓኖችም ይጠሩ። ሰው ለእግዚአብሔር እንጂ
ለእንጀራ አልተፈጠረም፤ በእንጀራ ብቻ አይኖርም። ፍላጐቱ ከእንጀራ የሰፋና የጠለቀ ነው። የሰውን ኅልውናዊ ፍላጐት የሚያውቅለትና ፈጽሞ ሊሞላለት የሚችል አሁንም ፈጣሪው ብቻ ነው።
ፍላጐትን ደግሞ እንደ ኤኰኖሚ ሥርዓት መቀየስ አይቻልም፤ ዘመን ሲለዋወጥ ስሜትም ትውልድም መለዋወጡ አይቀርምና። ማኅበራዊ ድንጋጌዎች ብቻቸውን ውስጣዊ ማንነትን ሊያረኩ አይችሉምና። ስለዚህም ሰው ሌላ ይሻል፤ ያምጻል።
የኤኰኖሚው ስልት ኅብር ወዳድ ወይም ግለኛነትን የሚያገንን ይሆናል። ኅብር ወዳዱ ግላዊነትን ስለሚጫነው ፍጥጫ ይጀመራል። ፍጥጫው ወደ ማኅበራዊ አብዮት ይቀየርና የነበረውን ይሽረዋል።
የሰው ታሪክ ጐዳናው ፏፏ የሚባልበት ጥርጊያ ሳይሆን ባልተብላሉና በተፈረካከሱ ማኅበራዊ ፍልስፍናዎች የሰረጓጐጠ ነው።
በሶቪየት ኅብረት ለሰባ ዓመት የሶሻሊዝም ሥርዓት አምላክ ሆኖ ሲያስገብር ኖረ። ሶሻሊዝም
ፍጡር ነው። የሰው አዕምሮ ውጤት ነው። ጅማሬው ተስፋና ፍትሕ እንዳለ የሚለፍፍ በመሆኑ ይማርካል፣ ያዘናጋል። ሌላ ይሆናል ብሎ አያስጠረጥርም። ፍጻሜውን ከጅምሩ ማወቅ አይቻልም ነበር ማለት ነው።
ከአምላክ ተነጥሎ ኑሮ ድንግዝግዝና ዳበሳ ነው። ሶሻሊዝም የፈጣሪን ቦታ ይዞ ኖረ። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ንብረትና ሕይወት ተሰዋለት። ከባሕር የጠለቀ ዕንባ ረገፈለት። ካፒታሊዝም የሚባል ሌላ አምላክ ደርሶ አንኰታኰተው።
ሶሻሊዝም እኛም አገር ለአስራ ሰባት ዓመት አንገላታን። በጐሣ ፖለቲካ ተተካ። የጐሣ ፖለቲካ እንደ ቀደመው ሥርዓት ፍጡር ነው። ሰዎች የቀመሙት ነው። ያለ ፈሪሃ እግዚአብሔር የቀመሩት ነው። ሰው ከፈጣሪው ላይ ዓይኑን አንስቶ ፍጡር በሆነው ላይ አደረገ። ራሱንና ጐሣውን አስበለጠ። ራሱን ከሌላው ጋር አስተያየ፤ ሌላውን ናቀ። ከዚህም የተነሳ በወዳጆች መካከል ጠብና ጉስቁልና ነገሠ።
ካፒታሊዝም ሌላ ፍጡር ነው። የሰውን ቀማኛነት ይቀሰቅሳል፣ ያንጻል። ሰው በተፈጥሮው ንፉግ ነው፣ ራስ ወዳድ ነው። ይህን ባሕርዩን ሕጋዊ ዕውቅና ያጐናጽፈውና ያንቀሳቅስዋል። ፉክክር ያይላል፤ አብሮ ተጋርቶ መኖር ይዳከማል። በዚያው መጠን የኑሮ ልዩነት እየጐላ ይሄዳል።
የሶሻሊዝም አዝማሚያው ብዙሃንን እኩል ማደህየት ነው። የካፒታሊዝም ደግሞ ጥቂቶችን ማቅበጥ ነው። ይህን ለማቃናት ማኅበረ ሰቡ መነቃነቅ ይጀምራል፤ ሲያስፈልግም ያምጻል።
ሌላም ስም ያለው ቢኖር ያው የአዕምሮ ጥበብ ፍጡር ነው። ሁሉን በአዕምሮ ብርታት መፍታት ይቻላል ይላል። ገደብ እንዳለ ይዘነጋል። ትሕትና ይጐድለዋል፤ የትዕቢት መንገድ ነው።
ብዙ ሳይቆይ መፍታት የማይችለውም እንዳለ መገንዘብ ይጀምራል። ብዙ ካበላሸ በኋላ ማለት ነው። ላለመረታት፣ እጅ ላለመስጠት ይታገላል።
እግዚአብሔርን መፍራት ክብር እንጂ ውርደት እንዳልሆነ አይገነዘብም። ሙሉነት እንጂ ጉድለት እንዳልሆነ አያስብም። የመከባበሪያ ጐዳና እንደ ሆነ አያይም። የሰዎችን በደል በእግዚአብሔር ያላክካል። የሰዎችን በደል ሲኰንን እግዚአብሔርንም አብሮ ይኰንናል። ሰው መሆኑን፣ በሌሎች ላይ ያየው ጉድለት የርሱም ዕጣ መሆኑን ይክዳል።
እምነትና እውቀት እንደማይቃረኑ፣ እንዲያውም እንደሚጠባበቁ ይዘነጋል።
በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ በሳይንስ ጥበብ ለሰው የሚጠቅሙ ብዙ ግኝቶች በጊዜው ለነበሩትና ዛሬም ላለነው የተስፋ ጮራ ፈንጥቋል። ለምሳሌ፦ ፔኒሲሊን ለብዙ ስውር ቀሳፊዎች መፍትሔ አስገኝቷል። ትንሽ ነች የምንላት አስፕሪን እንኳ በመቶ ዓመት ዕድሜዋ ስንቱን ራስ ምታትና ቁርጥማት ፈንግላለች። ስንት ፍላትና ትኩሳት አብርዳለች። ባጭሩ፣ እነዚህና የመሳሰሉት ግኝቶች ለኑሮ ቅልጥፍናን አስገኝተዋል።
አንዱን ችግር መፍታት ግን ሁሉን መፍታት ይመስለውና ሰው ይታለላል። እንደ ልጅ ቸኩሎ በጥቂቱ ይፈነድቃል። ጽኑ ተስፋና እምነት ካልተጨመረበት በስተቀር ነገ እንደሚያታግለው አያስብም። የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ነው የተባለው ለዚህ ነው።
ሰው የራሱ ተስፋ ሰጭ ሊሆን አይችልም። የተገባው አይደለምና። አምላክ አይደለምና። ተስፋ ሰጭ ያለው ከሰው ውጭ ነው፤ እግዚአብሔር ብቻ ነው።
በጥበብ የገሰገሱት ለምድር ሁሉ መሪና ሚዛን አድርገው ራሳቸውን በአምላክነት ሾሙ። ወደዚህ የሥልጣኔ ደረጃ ያልደረሱትን ማስገበር መግዛት ፈለጉ። ሁሉም በተገኘበት ከበታቹ ያለውን ማንበርከክ ተግባሩ ሆነ። ራሱን ማግነን ለሰው የማያቋርጥ ምኞቱ ሆነ። ከአምላክ ሥልጣን በታች መሆኑን ዘነጋ።
ለፈጣሪ የሚገባውን ክብር ለአዕምሮው ውጤት፣ ለሥልጣኔውና ለወገኑ ክብር አዋለ። ከዚህ የተነሣ ዘላቂ የሆነ ስምምነት ሊገኝ አልቻለም። ራስን ማግነን ድሮም ቢሆን ውጤቱ ከዚህ አያልፍም። ቅድም እንዳመለከትነው መቆራቆስና ምድርን ማወክ ተጀመረ። ሰው ራሱን ስላነገሠና ሌላው ሁሉ እንዲሰግድለት ስለሻ ብዙ ቀውስ ተከተለ።
በዚህም የሰው አዕምሮ ብቻውን ሁሉን ቻይ አለመሆኑን በራሱ ላይ መሰከረ።
የሰው ብልሃት የፈጣሪን ሥርዓት አይቀይርም። የፈጣሪን ሥርዓት የሚቀይር ተአምር ብቻ ነው፤ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ተአምር የማድረግ ሥልጣን ደግሞ ለአምላክ እንጂ ለሥጋ ለባሽ አልተሰጠም።
የሰው ብርታት የአምላክን ድካም አይረታም። አምላክ ድካም አለው ከተባለ ማለት ነው። የጥበብና የሰላም መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው። የራስን ክብር መፈላለግ ዛሬም እንደ ጥንቱ የውድቀት መጀመሪያ ነው:: ራስን ማክበር እግዚአብሔርን አለመፍራት ነው፤ ሰውን መናቅ ነው። ራሳቸውን የሚያከብሩ ይዋረዳሉ፤ ለከንቱነትም አልፈው ይሰጣሉ።
* * * * *
የእግዚአብሔርስ
ክንድ ለማን ተገልጦአል? በፊቱ እንደ ቡቃያ ከደረቅም መሬት እንደ ሥር አድጎአል። መልክና ውበት የለውም፥ ባየነውም ጊዜ
እንወድደው ዘንድ ደም ግባት የለውም። የተናቀ ከሰውም የተጠላ፥ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው፤ ሰውም ፊቱን
እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፥ እኛም አላከበርነውም። በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ
ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው። እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም
ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን
ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ
ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደ ተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?
ከክፉዎችም ጋር መቃብሩን አደረጉ፥ ከባለጠጎችም ጋር በሞቱ ሆኖም ግፍን አላደረገም ነበር፥ በአፉም ተንኮል አልተገኘበትም
ነበር። እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈከደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም
ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ
ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሰከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤
ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና፤ እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥ ስለ
ዓመፀኞችም ማለደ … Top art credit: www.stailbe.org

Copyright © 2006 ethiopianchurch.org