Download Geez Unicode Font if unable to read Amharic text.

 

የቤተ ክርስቲያን የመሠረት መልሕቆችና መሪነት

በፍራንሲስ እስጢፋኖስ

 

ክፍል ሁለት

የቤተ ክርስቲያን የመሠረት መልሕቆች

አስቀድመን የመልሕቅን ትርጉም እንመልከት፣

መልሕቅ በጠንካራና ረዥም ገመድ ጫፍ ላይ የሚንጠለጠል እጅግ ከባድ ብረት ነው፤ ሆዱ ገባ ብሎ ሦስት እጆቹ አንድን ትልቅ ነገር ለመሰብሰብ የተዘጋጁ የሚመስል፣ በባሕር ላይ የሚጓዙ ቀላልና ከባድ መርከቦች ረግተው እንዲቆሙ የሚያደርግ መሣርያ ነው። ብረቱ በገመዱ ጫፍ ወደ ውሃው ጥልቅ ይወረወራል፣ ከክብደቱም የተነሳ የመርከቡን እንቅስቃሴ ይገታል። መልሕቅ መርከቡን ባንድ ሥፍራ የሚያቆም፣ የሚያቆይ ብረት ነው።

የቤተ ክርስቲያን የመሠረት መልሕቅም እንዲሁ ቤተ ክርስቲያን በመሠረታዊ አስተምህሮ ላይ የቆመች፣ ያረፈች ናት እንደ ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ የያዘችው የቆመችበት አስተምህሮ ማለት ነው። እንዳትወድቅ፣ እንዳትፍገመገም የያዛት ፅኑ ነገር ወይም መሠረት ነው ማለት እንችላለን።

የቤተ ክርስቲያን የመሠረት መልሕቆች የተባሉት ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ቃል የተቀበለቻቸውና የምትመራባቸው መሠረታዊ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አድርገን በመውሰድ እላይ የጠቀስናቸውን “የእግዚአብሔር ቃል፣ ቅዱስ ጥምቀትና ቅዱስ ቁርባንን” ጨምሮ ዋና ዋናዎቹን ከዚህ በታች እንመለከታለን።

1.  እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ። 

እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ እራሱን በሦስት ማለትም በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ አድርጎ የገለጠ መሆኑን አምኖ መቀበል።

  • እግዚአብሔር አብ ሁሉን ቻይ ሰማይንና ምድርን በውስጡም ያሉትን ሁሉ ፈጣሪ ነው፤ የፈጠረውን ሁሉ ይጠብቃል፣ ይመግባል፣ ያቆያል።
  • እግዚአብሔር ወልድ ኃጢአተኞችን ለማዳን በመንፈስ ቅዱስ ከድንግል ማርያም የተወለደ ስለ ሰዎች ኃጢአት የተሰቃየና የተሰቀለ፣ የሞተ፣ የተቀበረ፣ የተነሳ፣ በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ እንደሚመለስ እናምናለን። ድነትም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ በፀጋ የሚሆን እንጂ ሰው በሥራው እንደማይድን እናረጋግጣለን።
  • እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም ሰዎችን ስለ ኃጢአት የሚወቅስ፣ የሚያስተምር፣ የሚያጽናና፣ የሚቀድስ፣ እምነትን በሰው የሚፈጥር፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችና ኃይልን የሚሰጥ መሆኑን እናምናለን።

2.  መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የጻፉት የእግዚአብሔር ቃል ነው። ሰዎችን ወደ ደኅንነት የሚመራ ለክርስትና ሕይወት ትክክለኛ የእምነት መሠረት ሙሉ ሥልጣን ያለውና የማይጨመርበት መደምደሚያ ቃል መሆኑን እናምናለን። 2ኛ ጴጥ 1፡ 20-21፤ 2ኛ ጢሞ 3፡ 16

መጽሐፍ ቅዱስ የድህነትን መንገድ ለማግኘት፣ በጌታ ኢየሱስ ስም አምኖ የዘላለም ሕይወት ለመቀበል ብቁ ስለሆነ ማንም በዚህ ቃል ላይ ሊጨምር ወይም ከዚህ ቃል ሊቀንስ አልተፈቀደለትም። በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ የተጻፈውን ማስጠንቀቂያ ምዕመን ሁሉ በጥንቃቄ ሊፈጽመው የሚገባው ነው ማለት ነው።

“የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚሰማውን ሁሉ አስጠነቅቃለሁ፤ ማንም በዚህ ቃል ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤ ማንም በዚህ የትንቢት መጽሐፍ ከተጻፈው አንዳች ቢያጎድል፣ እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ ዕድሉን ያጎድልበታል።” ራእይ 22፡ 18-19

3.  ቅድስና


እያንዳንዱ አማኝ በተጠራው አጠራር ከኃጢአት በመለየትና ኃጢአትን በመቃወም በቅድስና መኖርና መመላለስ መንፈሳዊ ፍሬም ማፍራት ይጠበቅበታል። ኤፌሶን 5፡ 26፤ 2ኛ ጢሞ 2፡ 21፤ 1ኛ ጴጥሮስ 1፡ 15-16፤ 2ኛ ጢሞ 2፡ 20-21

ሰዎች ወንጌልን ሰምተው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ጌታን የግል አዳኛቸው አድርገው ከተቀበሉት በኋላ ክርስቶስን ባለማወቅ የኖሩትን የቀድሞ የኃጢአት ኑሮ በዝሙት፣ በስካር፣ በማታለል፣ በጣኦት አምልኮና በሌሎችም ኃጢአት “የጎደፈውን አሮጌ ሰውነታቸውን” አውልቀው እንዲጥሉ ታዝዘዋል። ኤፌሶን 4፡ 20-32

ሰዎች ጌታ ኢየሱስን ከተቀበሉ በኋላ በለበሱት ሥጋ ምክንያት ወደ ኃጢአት ከሚስባቸው የሰይጣን ኃይል በጌታ መንፈስ ቅዱስ ድጋፍ እየታገሉ ዕለት ዕለት ከኃጢአት መራቅና መለየት አለባቸው። መቀደስ ማለት መለየት ማለት ነው። ምዕመናን ሁሉ በግልጽ ከኃጢአትና ከክፉ ሥራ እንዲለዩ ተጠርተዋል። 1ኛ ጴጥሮስ 1፡ 13-17

በመቀደስ ምዕመናን ሁሉ መላ አካላቸውና አእምሮአቸውን እንዲያነጹ ተጠርተዋል። በተቀደሰ አካልም እግዚአብሔርን ማምለክ ለርሱም ክብርና ገናናነት መስጠት እርሱንም ማገልገል ይቻላል።

ባሁኑ ጊዜ ምዕመናንና መሪዎች በብዛት ሲቀደሱ አይታዩም። የሚዋሸው፣ የሚሰርቀው፣ የሚያመነዝረው፣ የሚጠላውና በገንዘብ ፍቅር የተነደፈው የወንጌል ተከታይ ቁጥር ትንሽ አይደለም። ይህ የሚያሳየው ከዓለም፣ ከኃጢአት አለመለየትን ነው። የቅድስና ሕይወት አስፈላጊነት በቤተ ክርስቲያን በጥብቅ ሊሰበክ ይገባል። መሪዎች በቅድስና ሕይወት ኑሮ ምሳሌ መሆን አለባቸው።

ሐዋርያው ጳውሎስ መሪዎች ምሳሌ መሆን እንዳለባቸው ሲናገር የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቶአል፦ “ወጣትነትህን ማንም አይናቅ፤ ነገር ግን ለሚያምኑት በንግግር፣ በኑሮ፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽህና አርአያ ሁንላቸው። 1ኛ ጢሞ 4፡ 12

4.  ቅዱስ ጥምቀት*

ቅዱስ ጥምቀት ጌታ ኢየሱስ እራሱ ያጸናውና ደቀ መዛሙርት እንዲፈጽሙት የታዘዙት ሥርዓት ነው። ጥምቀትም በኃጢአት የተወለደና የተሞላ አካል መቀበርንና በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ የታጠበና የታደሰ ሕይወት ትንሳኤን ያመለክታል። በውሃ ጥምቀት የኃጢአት ሥርየት፣ ከኃጢአት መንጻትና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ይገኛል። ከዚህም የተነሳ ይህ ጥምቀት ዳግም ልደት፣ መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ በመባል ይታወቃል። ቅዱስ ጥምቀት ወደ ቅዱሳን ሕብረት ለመጨመርም የሚያገለግል ሥርዓት ነው። ማቴዎስ 28፡ 18-20፤ ቲቶ 3፡ 5-7፤ ዮሐንስ 3፡ 3-5፤ ማርቆስ 16፡ 16፤ ሮሜ 6፡ 3-5

5.  ቅዱስ ቁርባን

ቅዱስ ቁርባን ወይም የጌታ እራት ከኅብስትና ከወይን ጭማቂ ወይም ከተመሳሳይ የሚዘጋጅ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን የወሰደውን ሥቃይ፣ ሞትና ትንሣኤ የምንካፈልበትና የምናስታውስበት እስከ እርሱም ዳግም ምጻት ድረስ ሞትና ትንሣኤውን ለማወጅ ቃል በመግባት እንድንፈጽመው የታዘዝነው ቅዱስ ሥርዓት ነው።

ቅዱስ ቁርባን ጌታ ላደረገው መስዋእትነትና ለሰጠን ታላቅ የድነት ስጦታ የምናመሰግንበት፣ በንስሃ ራሳችንን በመመርመር የምንወስደው፣ ከእግዚአብሔርና ከምዕመናን ጋር ሕብረት የምንፈጥርበት፣ በትሕትና፣ በምስጋናና በአክብሮት የምንፈጽመው ሥርዓት ነው። ቅዱስ ቁርባን የክርስቶስን ሥቃይ ሞትና ትንሣኤ ያመለክታል። የርሱ ሞት በብሉይ ኪዳን ይፈጸም የነበረውን የኃጢአት ስርየት መስዋእት አንዴ ለመጨረሻ ጊዜ ተክቶአል። ማቴዎስ 26፡ 26-29፤ ማርቆስ 14፡ 22-25፤ ሉቃስ 22፡ 19-20፤ ዕብራውያን 10፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 10፡ 16-17፤ 11፡ 23-33

6.  ፀሎት

ቅዱስ አውጉስጢኖስ ባንድ ወቅት “ፀሎት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ነው” ሲል ተናግሮ ነበር። ፀሎት ከእግዚአብሔር ጋር በመነጋገር የምንፈልገውን የምንገልጽበት፣ ልመናና ምስጋና የምናቀርብበት፣ ከእግዚአብሔር አብ ሰማያዊ ፈቃድ ጋር መተባበራችንን የምንገልጽበት የመገናኛ መስመር ነው።

ፀሎት እንድናደርግ ጌታ ኢየሱስ ያበረታታናል። እርሱም እራሱ ወደ አብ በመፀለይ እንዴት መፀለይ እንደሚገባንም ያስተማረበት ነው። ማቴዎስ 6፡ 5-17፤ ሉቃስ 11፡ 2-4

ፀሎት ለአንድ ምዕመን ለቤተሰብና ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆነ የሕይወት መስመር ነው። ማቴዎስ 26፡ 36-44፤ ማርቆስ 14፤ ሉቃስ 22

ሁሉን ቻይ፣ በጎና ባለ ሙሉ ፀጋ ወደ ሆነው እግዚአብሔር መሻታችንን ይዘን ስንቀርብ መልካም አባት ለልጁ የሚያደርገውን በጎ ነገር ሁሉ ያደርግልናል። ፀሎት እግዚአብሔር ፈቃዱን የሚገልጽበት እኛም ፈቃዱን የምናውቅበት ነው። ማቴዎስ 7፡ 7-12፤ ሉቃስ 11፡ 9-13፤ ገላትያ 4፡ 5-6 

7.  ፍቅር ወይም መዋደድ

የመዳናችን መሠረቱ የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ነው። እግዚአብሔር በመለኮታዊ ፍቅር ተነሳስቶ እኛ ገና ኃጢአተኞች ሳለን አንድ ልጁን ኢየሱስን ልኮ ከኃጢአት ውጤት ከሞት አዳነን። ዮሐንስ 3፡ 16

አብ ወልድን እንደ ወደደ እኛም እርሱ በወደደን ፍቅር እንድንወደውና እርስ በርስ እንድንዋደድ በፍቅሩም እንድንኖር ታዝዘናል። ዮሐንስ 14፡ 5-17፤ 17፡ 20-25፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 13፤ 1ኛ ዮሐንስ 3፡ 4፤ ማርቆስ 12፡ 31፤ ሉቃስ 10፡ 27፤ ሮሜ 13፡ 9

ፍቅር እግዚአብሔርን እንድንወድ ያደርገናል። ዘዳግም 6፡ 5 ፍቅር ጎረቤታችንን እንድንወድ ያደርገናል። ዘሌዋውያን 19፡ 18፤ ፍቅር እግዚአብሔርን ከሰው፣ ሰውን ከሰው ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ነው። ፍቅር በደልን አይቆጥርም፣ ፍቅር ይቅር ባይ ነው። የእግዚአብሔርና የሰው ግንኙነት መሠረቱ ፍቅር ነው። ፍቅር የሰላምና የሕብረት መሠረት ስለሆነ አጥብቀን ልንሻው ይገባል። ያለንበት ዘመን ፍቅር በጣም የተመናመነበት ዘመን ነው። ሰይጣን በአማኞች መካከል እንዲኖር የታዘዘውን ፍቅር ከተቻለ ጨርሶ በማጥፋት አልያም እንዲዳከም በማድረግ ቤተ ክርስቲያን ተልእኮዋን እንዳትወጣ እየጣረ ነው። ለምዕመን፣ ለቤተሰብ፣ ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንና ለቤተ እምነት ፍቅርን መለማመድ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን መፈጸም ያለባቸው ትእዛዝ ነው። ቤተ ክርስቲያንና መሪዎቿ ይህንን ታላቅ ትእዛዝ አጥብቀው ሊለማመዱት ይገባል።

8.  የወንጌል ስብከት

ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን ስለ ወደደ ሊያድናቸው ሕይወቱን በመስጠት የኃጢአትን ዋጋ ከፍሏል፤ ሰዎች ሁሉ ይህን እንዲያውቁና ከሞት እንዲያመልጡ፦ “ሂዱ ይህን የምስራች ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፣ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አዝዟል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ፣ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል፤ ሆኖም ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ሰባኪ ሳይኖር እንዴት መስማት ይችላሉ? ሰዎች ካልተላኩ ደግሞ እንዴት መስበክ ይችላሉ?” ብሎ በመጠየቅ ለመዳን ሰዎች በወንጌል ስብከት ስለ ኢየሱስ አዳኝነት መስማት እንዳለባቸው ያረጋግጣል። ሮሜ 10፡ 13-14

ለራሱም ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 9፡ 16። አንተ ግን ጢሞቴዎስ የመንፈስ ልጄ ሆይ፣ “ቃሉን ስበክ፣ ጊዜው ቢመችም ባይመችም ዝግጁ ሁን፤ በታላቅ ትዕግስትና በማስተማር አቅና፣ ገሥጽ፣ አበረታታ… የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፣ አገልግሎትህንም ፈጽም፤” ብሎ ያበረታታዋል። 2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡ 1-5

ከኢትዮጵያ ጠቅላላ ሕዝብ አብዛኛው ከኢየሱስ ስም በስተቀር ለመዳን ሌላ ለሰዎች የተሰጠ ስም እንደሌለ ገና ያላወቀ ስለሆነ ልንደርስለት፣ ወንጌልንም ልናደርስለት ከባድና አጣዳፊ ኃላፊነት እንዳለብን መረዳት አስፈላጊ ነው። በመሆኑም መሪዎች ጊዜአቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ኃይላቸውንና ዕውቀታቸውን በወንጌል ስብከት ዙሪያ ማቀናጀት የጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ልንረዳ ይገባናል።

የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረትና ታላቁ ተልእኮ እግዚአብሔር የጣለባቸውን ከባድ አደራ በመረዳት አገር አቀፍ ሰፊ ራእይ ይዘው ከፍተኛ የወንጌል ስርጭት ሥራ እየሠሩ ነው፤ ለዚህም እግዚአብሔርን የመከሩን ባለቤት ልናመሰግን ይገባል። በተጨማሪ ግን ቤተ እምነቶችና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት የበለጠ ሥራ ለመስራት የወንጌልን ሥራ ማቀናጀትና ማስተባበር አስፈላጊነቱ እየጎላ በመምጣቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ከቀድሞ ይልቅ ሊተጉ ይገባል።

9.  የማስታረቅ ተግባር

ሰዎች በፈቃዳቸው በሠሩት ኃጢአት ምክንያት በእግዚአብሔር ላይ አምፀዋል። “ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ አመፅን ያደርጋል፤ ኃጢአትም አመፅ ነው” 1ኛ ዮሐንስ 3፡ 4

ሰዎችም በእግዚአብሔር ላይ በማመፃቸው ምክንያት እግዚአብሔር ሞት ፈርዶባቸዋል። “የኃጢአት ዋጋ ሞት ነውና።” ሮሜ 6፡ 23

ምንም እንኳን ሁሉም ኃጢአትን ቢሠሩ “በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት” በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ “እንዲያው በፀጋው ብቻ ይጸድቃሉ… እግዚአብሔር ይህን ማድረጉ የቀድሞውን ኃጢአት እንዳልነበረ በመቁጠር የራሱን የጽድቅ መንገድ ለመግለጥ ነው።” ሮሜ 3፡ 24-25

በዚህ የኢየሱስን መስዋእትነት በጠየቀው የማስተሠርያ ሥራ ከእግዚአብሔር ጋር የተጣሉት ሊታረቁ ችለዋል። ይህንንም የማስታረቅ ሥራ የፈጸመው ጌታ ኢየሱስ ነው። ይህንኑ የማስታረቅ ሥራ ቤተ ክርስቲያን እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ድረስ በምድር እንድትቀጥል ኃላፊነት ተሰጥቶአታል። ለዚህም ቃል ማረጋገጫ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ጽፎአል፦

“ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፏል። እነሆ፣ አዲስ ሆኖአል። ይህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው። እርሱ በክርስቶስ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታረቀን፣ የማስታረቅንም አገልግሎት ሰጠን፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር ሲያስታርቅ የሰዎችን በደል አይቆጥርባቸውም ነበር። ለእኛም ደግሞ የማስታረቅ ቃል ሰጠን፤ ስለዚህ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ እግዚአብሔርም በእኛ አማካይነት ጥሪውን ያቀርባል፤ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን በክርስቶስ እንለምናችኋለን። 1ኛ ቆሮንቶስ 5፡ 17-20

የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛው መልእክት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው ሰዎችን ወድዶ ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን ከኢየሱስ የታዘዘችውን የማስታረቅ ተግባር ለአፍታም ችላ ልትል አይገባትም። 

 

ክፍል ሦስት ይቀጥላል...


 

* በቅዱስ ጥምቀት አተረጓጎም ላይ የተለያዩ የእምነት ክፍሎች የተለያየ አቋም አላቸው። በዚህ ጽሑፍ ላይ የሠፈረው አተረጓጎም በዚህ መልኩ ይነበብ።

 


 

ተራራ እንውጣ

 

ዞትር በሸለቆ ዞትር በየሜዳ

እንሸሽበት ባይኖር እንዴት ይዘለቃል

ልብ እንዲበረታ ከጭንቅና ጣጣ

ኑ እንደ ጌታችን ተራራ እንውጣ

 

ለብቻው እንዲቆም ቁልቁል ተዘርግፎ

ከሥር በፈፋና በወንዝ ተደግፎ

ንጹህ አየር ከብቦት ሃሳብ እንዲያጠራ

እንውጣና እንየው ይህንን ተራራ

 

ይህንን ተራራ ጸንቶ የቆመውን

እንዲህ እፊታችን የተከመረውን

ተነሡ እንዝለቅ ይልቅ አናመንታ

ሕይወት እንደ ሆነች ሁሌም መንታ መንታ

 

ፀሐይዋ ልትጠልቅ ልትወጣ ጨረቃ

ዋኖስ ቤቷ ልትደርስ ሥራችን ሊያበቃ

እደጅ የዋለ ከብት በረቱ ሲከተት

ይህን ተከትሎ ዐይን ይረፍበት

 

ሰው ከምድርም ቢሆን ፍጻሜው ነው ሰማይ

እዚህ እንዳልተወሰን እላይ ደርሰን እንይ

ተራራ ‘ሚወጣ ልቡ ተራራ ነው

ምኞቱም ተራራ እንደዚሁም ሥራው

 

ስለዚህ በኑሮ እጅጉን ተዋክበን

እንዲህ ተርመስምሰን እንዲህ ዐመድ ለብሰን

ይልቅ እንዳንቀር አጥርተን እንድናይ

ኃይላችን ይታደስ እንውጣ አምባ ላይ

 

ብዙ አመንትተን ብዙ ተስፋ ቆርጠን

ባይመችም ቅሉ በልማድ ተይዘን

እየተጠራጠርን ልባችን እየሻ

የለት ኑሮ አስሮ ነጥሎ ካኖረን

 

አንጋጠን እንዳየን ቁልቁል እንመልከት

ዝምታን እንማር ጸጥታን እንቅመስ

ራእያችን ይጥራ ለምንሠራው ሥራ

ኑ እንደ ጌታችን እንውጣ ተራራ

 

Copyright©2008 by Mitiku Adisu

 

 

 

ርዕሰ አንቀጽ

እውነተኛውን ለይቶ ስለ ማወቅ

 

ከእግዚአብሔር ዘንድ መጣን የሚሉ አያሌ ሰዎች በታሪክ ውስጥ ተነስተዋል። አንዳንዶችም “አምላክ ነን” ብለዋል።

“አምላክ ነን” ስላሉ ሁሉም ይታመናሉ ማለት ግን አይደለም። ሁሉም የማይታመኑ ከሆነ ታዲያ እውነተኛውን እንዴት ለይቶ ማወቅ ይቻላል?

እውነተኛው በቅድሚያ እግዚአብሔር እንደሚልከው ያስታወቀው ሰው መሆን ይኖርበታል። የዚህንም ሰው ማንነት፣ የት፣ መቼና እንዴት እንደሚወለድ፣ ምን መልእክት አስይዞ እንደሚልከው፣ አኗኗሩንና አሟሟቱን በዝርዝር መግለጽ ይኖርበታል። ይኸ ሲሆን ከብዙዎች መካከል ያንን እውነተኛውን ለይቶ ማወቅ ይቻላል ማለት ነው።

በዚህ ሚዛን መሠረት ኢየሱስን ከሁሉ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን። ሌሎቹ ሁሉ ሲመሳሰሉ፤ ኢየሱስ ብቻ ያለ አምሳያ ያለ አቻ ይቀራል ማለት ነው። ያለ አምሳያ ለመሆኑ እነዚህን ጥቂት ማስረጃዎች ማስታወስ ይበቃል፦

  • ሰው ሁሉ የሚወለደው ለመኖር ነው። ኢየሱስ ግን የተወለደው ለመሞት ነው። በመሞቱም ላመኑበት ሁሉ አዳኝ ሆነ። ለተቀበሉት የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው። የኃጢአትን ይቅርታ፣ የዘላለምን ሕይወት አጎናጸፋቸው። ዓለም የማያውቀውንና የማይሰጠውን ሰላም ሰጣቸው። የማያልቅ የማይደክም ተስፋ ሆናቸው። ኃጢአትን ይቅር ለማለት ሆነ የእግዚአብሔርን አባትነት ለማቀዳጀት የተቻለውና የደፈረ ሌላ ማንም የለም።
  • ስለ ራሱ ሲናገር፦ እውነተኛው የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ፤ ከእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ ማንም የለም፤ ደግሞም፣ እኔን ያየ አብን አይቶአል፣ አለ። ሌሎች ስለ ራሳቸው እንዲህ ማለት አልቻሉም!
  • ታሪክን ለሁለት ገመሰው። የታሪክ ራስና መጋጠሚያ እርሱ ሆነ፤ “ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ ከክርስቶስ ልደት በኋላ” መባል ተጀመረ። ወዘተ። እርሱ ብቻ ሕያው ነው።

“አምላክ ነን” ወይም “ከአምላክ ዘንድ ተልከናል” የሚሉ ሰዎችን ታሪክ በጥሞናና በቅንነት ለመረመረ ከዚህ ከጠቀስነው መደምደሚያ ማምለጥ አይቻለውም። ኢየሱስን፦

  • መላእክት አውጀውታል
  • ጠቢባን መስክረውለታል፤ እረኞች አውቀውታል
  • ነገሥታት ዝናውን ሰምተው ደንግጠዋል፤ ያዩትና የሰሙት አምነውታል
  • ማኅበረሰብ ያገለላቸው፣ ሕመም ያሠራቸው፣ የኅሊና ወቀሳ የኃጢአት እሥራት ያሠቃያቸው ሽተውታል፤ ፈዋሽነቱን መስክረውለታል
  • ሳያዩት ወድደውታል
  • ሕጻናት ቀርበውታል፤ ቆነጃጅትና ጎበዛዝት አወድሰውታል
  • ሁሉም ሰግደውለታል፤ ፈቅደው አገልግለውታል

˛˛˛

የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች… እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ [አሉት]… ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ… በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች። ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ። ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፣ የበኩር ልጅዋንም ወለደች። ማቴ 1፡ 18፣ 21። 2፡ 1-2። ሉቃስ 2፡ 1-7።

ወዳደገበቱም ወደ ናዝሬት መጣ፣ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገባ፤ ሊያነብም ተነሣ። የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፣ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ፦ የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛል፣ ለታሰሩትም መፈታትን፣ ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፣ የተጠቁትንም ነጻ አወጣ ዘንድ፣ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል፣ ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ። መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኩራብም የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር። እርሱም፦ ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ ይላቸው ጀመር። ሁሉም ይመሰክሩለት ነበር። ሉቃስ 4፡ 16-21

እነሆ፣ የእግዚአብሔር በግ፣ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ… የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷል። ዮሐንስ 1፡ 29፣36። ሉቃስ 19፡ 10

ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። ኢሳይያስ 53።

መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረም፣ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ 1 ቆሮንቶስ 15፡  

ይህ እንዴት ይሆናል?

ማርያም ሆይ፣ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፣ ትፀንሻለሽ፣ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ… ማርያምም መልአኩን፦ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል አለችው። ሉቃስ 1፡ 30፣ 34።

እውነትም፣ ይህ እንዴት ይሆናል? የሚያሰኝ ነው። ተሰምቶም ታይቶም የማይታወቅ ስለሆነ እንኳንስ ለሰሚው ለማርያምም ግራ ያጋባ ጉዳይ ነው። የተነገራት በሰው ልማድ ውስጥ ያልታየ ስለሆነ ጥያቄ መፍጠሩ አስገራሚ አይደለም። ብዙዎቻችን ይህን የመሰለ ጥያቄ ጠይቀናል። ይህ ዓይነት ጥያቄ እግዚአብሔርን አያስገርመውም። እግዚአብሔር ሰዎች እንደ ሆንን ያውቃልና!

በአንጻሩ ይህን አስገራሚ ታሪክ መርምሮ የመዘገበው ሉቃስ ሐኪም እንደ ሆነ መዘንጋት የለብንም!

˛˛˛

ዝግ ብሎ ላሰበ በዘመናት ሁሉ “ይህ እንዴት ይሆናል?” ያሰኘ ብዙ ብዙ ነገር ተሰምቷል። “ሊሆን አይችልም” የተባለው አንዳንዱ ከመቆየት ብዛት ሆኖ ተገኝቷል። በአንዱ ትውልድ ጥያቄ የፈጠረው በቀጣዩ መልስ አግኝቷል።

ያለፈውን ታሪክ ማወቅ ከብዙ ስሕተት ያድናል ማለት ነው። ያለፈው ያሁኑን ይተረጉመዋልና፤ ለሚቀጥለው ደግሞ ያዘጋጃል።

መልአኩም መልሶ እንዲህ አላት፦ መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል… ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም። ሉቃስ 1፡ 45

ከዚህ በኋላ ማርያም ጥያቄ አላነሳችም። “እነሆኝ፣ የጌታ ባሪያ፣ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ አለች” (ሉቃስ 1፡ 46)። አንዳንዶቻችን እንደ ማርያም ለእግዚአብሔር “እሺ” ከማለት ይልቅ በጥያቄ ዳርቻ ላይ ቆመን ቀርተናል። መልሱ ቀርቦ ሳለ ርቆብናል። እርምጃ እስክንወስድ ድረስ ከጥያቄና ከማመንታት ምጥ አንገላገልም።

“መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል።” ምሥጢሩ ያለው መንፈስ ቅዱስ ዘንድ ነው። ይህም መንፈስ አይታይም። በሚፈቅዱለት ውስጥ ግን ይኖራል፤ አብሮአቸውም ይሆናል። ወደ እውነት ሁሉ ይመራቸዋል። ለሰው የማይቻለው ይቻለዋል። ፈቅደው ለሚጠጉት እርግጠኛነትን ያጎናጽፋቸዋል። የጥርጥርን ድንበር አሻግሮ የእርግጠኛነትን ርስት ያወርሳቸዋል።

˛˛˛

“እንዴት እንደሆነ ሳላውቅ ይህን ወንጌል ማመን አልችልም” የሚል ከአምላክ ሕይወት ይጎድልበታል። እግዚአብሔር ይግለጥልኝ እንጂ እኔስ አምነዋለሁ ለሚለው ደግሞ ምሕረትና ሞገስ ይለቀቅለታል። ወንጌል፦ እመን፤ ታውቃለህ። እመን፤ ትድናለህ፣ ይለናል። አምኖ ማወቅ፣ አምኖ መዳን ስለሚቻል ነው። ለማመን ደግሞ ከበቂ በላይ ምክንያት አለ። እግዚአብሔር ልንቀርበው፣ ልናየው፣ ልንሰማው፣ ልንዳስሰው እንድንችል “ሥጋ ሆነ፣ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በኛ አደረ፤ አንድ ልጅም ከአባቱ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን።” ለማመን በቂ ምክንያት ባይኖር እግዚአብሔር ጻድቅ አይሆንም። ሰዎች እርሱን ወደ ማመን እንዳይደርሱ መንገዱን እየዘጋባቸው ተመልሶ ሊፈርድባቸው አይችልም።

ሰው ሌላውን ብዙ ነገር እንዴት እንደሆነ ሳያውቅ ሲቀበል ወንጌል ላይ ሲደርስ የሚያቅማማ ከሆነ በደል ይሆንበታል። ራሱን ይበድላል። ፈጣሪውን ያሳዝናል።

·        ነፋስ አይታይም፤ ነፋስ የለም ማለት ግን አይደለም። ነፋስን ሥራው ይገልጸዋልና

·        ፍቅር አይታይም፤ ፍቅር የሚባል የለም ማለት ግን አይደለም።

ኢየሱስም ለሚመረምሩት እንዲህ ብሏል፦ እኔ (የላከኝን) የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ባደርገው ግን እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ… አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፣ ይህ የማደርገው ሥራ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና። የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም፣ መልኩንም አላያችሁም… መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው… እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና፣ እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው። ዮሐንስ 10፡ 37። 1፡ 18። 5፡ 36፣39  

˛˛˛

እንግዲያስ ምሕረቱን የቀመሱ እውነቱን ይመስክሩ። “ይህ እንዴት ይሆናል?” ሲሉ የነበረ፦ “አይሆንም ያልነው ሆኗል፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው የለም!” ይበሉ!! ጳውሎስ ምሕረቱን የቀመሰ ሰው ነበረ። ጴጥሮስም። ምሕረቱን የቀመሱ የምናውቃቸው ዛሬም እንኳ በዙሪያችን አሉ። አንዳንዶቹ ጓደኞቻችን ዘመዶቻችን ናቸው። እነዚህ ሁሉ በሞት ይሁን በሕይወት ኢየሱስ እውነተኛ እንደ ሆነ ያውጁ።

በቤተ ልሔም ይሁዳ በግርግም የተወለደው ሕፃን የዓለም አዳኝ እንደ ሆነ ይንገሩ። ለሰው ኃጢአት ሞቶ ጽድቅን ለማውረስ ከሙታን ለተነሳው ይዘምሩ። ከአምላክ ዘንድ ለመጣው እራሱም አምላክ ለሆነው ለኢየሱስ ይስገዱ!

መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ይናገሩ፣ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ምንም የለም ይበሉ!

እንደ ሰጠው ተስፋ ቃል የሚኖረውን ያክብሩ። እንዲህ ብሎ ነበርና፦ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፣ እነሆ፦ ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች… በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፣ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ። የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ። ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፣ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፣ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፣ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፣ ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። ኢሳይያስ 7፡14። ሉቃስ 2፡ 8-14። 

 


 

»»»>

 

Copyright © 2006 ethiopianchurch.org All Rights Reserved

picture

 

 


ፍትሕና ምሕረት
ዝም የማትለው እስከ መቸ ነው?
ፍትሕና ምሕረት
የቤተ ክርስቲያን የመሠረት መልሕቆችና መሪነት
የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም
የእምነት አቋም መግለጫ ምንነትና አስፈላጊነት
ቃልህ እንዳይባክን
መልካም ቀን ቶሎ ና
ርዕሰ አንቀጽ
እግዚአብሔር አስገረመን

ሞት ጅማሬ ነው ወይስ ፍጻሜ? [ክፍል 2]
እውነተኛ ክርስቲያን ማን ነው?
ማስታወቂያ
የመለኮቱ ኃይል፥
ሞት ፍጻሜ ነው ጅማሬ?

ይድረስ ለቴዲ አፍሮ