gabiso2

ርዕስ፦ የተስፋዬ ጋቢሶ መዝሙሮች፤ ካሴት ቁጥር 1 እስከ 7። በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ። አዘጋጅና ተርጓሚ - ወ/ሮ ላይላ ባልስኪ [በኢትዮጵያ ከ40 ዓመት በላይ ሚሲዮናዊት ሆነው ያገለገሉ]። 1ኛ እትም 2004፤ 120 ገጽ፤ ኤስ አይ ኤም ማተሚያ፤ አ/አበባ፣ ኢትዮጵያ።

ላይላ ባልስኪ የተስፋዬ ጋቢሶን ዝማሬዎች በመጽሐፍ መልክ ለማሳተም የተነሳሱበትን ዓላማ፣ 1/ በኢትዮጵያ ላይ ጥናት ለሚያደርጉ ምሑራንና ለትውልዶች ጥቅም እንዲውል፤ 2/ “ስብሐት ለአምላክ” የመዝሙር መጽሐፍ ለርሳቸው የአማርኛ መማርያ እንደነበረ ሁሉ አማርኛ ለሚያጠኑ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች [እንግሊዝኛ ለሚያጠኑ አማርኛ ተናጋሪዎች] መማርያ እንዲውልና በሩቅና በቅርብ ላሉ ሁሉ መንፈሳዊ በረከት እንዲሆን ነው ሲሉ ገልጸውታል።

አዲስ ሚሲዮናዊት ሆነው ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜ በአለታ ወንዶ ወጣቱን ተማሪ ተስፋዬን እንደተዋወቁት። በዚያን ዘመን፣ ወጣቶች ከስዊድንና ከእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ከተተረጎሙት መዝሙራት [ከስብሐት ለአምላክ] ውጭ አዳዲስ መዝሙሮችን ይዘምሩ እንደነበረ። ተስፋዬም እቤታቸው እየመጣ በብስራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ የሚተላለፈውን ያዳምጥና ግጥሞቹን በደብተር ይጽፍ እንደነበረ። ከያኔ ጀምሮ ስለነዚህ አዳዲስ መዝሙሮች ሲያብላሉ ከኖሩ በኋላ ጠለቅ ያለ ጥናት ለማድረግ በ1983 ዓ.ም ገደማ ከባለቤታቸው ጋር ወደ ኤድንብራ ዩኒቨርስቲ ስኮትላንድ እንደተጓዙ ይናገራሉ። ጥናታቸውም “ሥነ መለኮት በዝማሬ፦ ኢትዮጵያዊው ተስፋዬ ጋቢሶ” የሚል ጽሑፍ እንደወጣው በመግቢያው ላይ አስፍረዋል። ላይላ ለጥናታዊ ጽሑፉ የሰጡት ርዕስ የመዝሙራትን ምንነት ለመገምገም አቅጣጫን የሚጠቁሙ ሆነው አግኝተናቸዋል። የተስፋዬ ጋቢሶ መዝሙራት ዓይነተኛ ሊሆኑ የቻሉበት ምክንያት በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና በጸሎት የተገኙ በመነበራቸውና ጠለቅ ያለ ሥነ መለኮታዊ ይዘት ስላላቸው ነው። መነሻቸው፣ ማጣቀሻቸውና ግባቸው እግዚአብሔር መሆኑ ላይ ነው። “አከበረኝ” ሳይሆን፣ “ክብር ላንተ ይሁን” ማለት ስለሚያበዙ ነው። በአጠቃላይ ሲታዩ፣ የመዝሙራት ሥነ መለኮታዊ መልእክት ዛሬ ምን ይመስል ይሆን? የቃል አመራረጥና የቅኔ ውበታቸውስ?

ላይላና ሌሎች ሚሲዮናውያን ወንጌልን ይዘው አገራችን በመምጣታቸው ብዙዎች በክርስቶስ በኩል የተሰጠውን ተስፋ እንዳገኙና አዲስ ሕይወት እንደተቀዳጁ አጠያያቂ አይሆንም። በብዙ መከራ ውስጥ የእግዚአብሔር ጸጋ የተሰጣት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ተራዋን ለዓለም የምታካፍለው አላት ማለታቸው የላይላ ልብ ቀና መሆኑን ያመለክታል። ጸጋን የሚሰጥ ብቻውን ባለጸጋ የሆነ እግዚአብሔር ነውና፣ የጸጋ ሥራ በኢኮኖሚ ከለሙት ወደ አልለሙት ብቻ ሊሆን አይችልም። ተቀባዩ ሰጭ የሚሆንበትም ዘመን አለ [2ኛ ቆሮንቶስ 8፡13-15]። ሚሲዮናውያን ላኪ የነበረው ምዕራቡ ዓለም፣ ዛሬ በከፍተኛ የሞራል ውዥንብር ውስጥ ወድቋል። ሁሉን ዓይነት ማስተናገድ እየፈለገ ዋነኛውን ጥሏል። የኢትዮጵያስ ቤተክርስቲያን ያካበተችውን ጸጋ በእነዚህ ሃያ ዓመታት ምን ያህሉን አካፍላ ምን ያህሉን አባክና ይሆን?

የዚህ መጽሐፍ መታተም ዘማሪ ተስፋዬ ከተሰጠው መገለጥ ውጭ የተዘባረቀ ትርጉም እንዳይኖር ያግዳል። በተለይም አንዱን አዝማች ከሌላው ጋር ማደራረብ በበዛበትና አብዛኛው  በቃል በሚዘመርበት ሁኔታ። የመዝሙሮቹ ቀዳሚ አሳብ እንዳይለወጥ መከላከያ ይሆናል። “ኤልሻዳይ” የሚለውን አጠራር ሰምታ የማታውቅ፣ “ኤልሻዳይ የሠራዊት ጌታ”ን “ይሻላል የሠራዊት ጌታ” አለች ተብሎ እንደተተረተባት እንዳይሆንብን ማለት ነው። “ይሻላል የሠራዊት ጌታ”ም ለነገሩ አያስከፋም። ሆኖም “ኤልሻዳይ፣ ሁሉን ቻይ” የሚለውን ትርጉም ሳይገነዘብ ይቀራል።

ላይላ የተነሡበትን ዓላማ ምን ያህሉን እውን አደረጉ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከአርትኦት፣ ከትርጉሙ ጥራት አኳያና ተስፋዬ ጋቢሶን ለይተው ለማጥናት ካደረጉት ሙከራ አንጻር እንመልከት።

1. የአርትኦት ጥራት። ሀ/ “ተዋወቅን” ለማለት “ወደ ሕይወታችን መጣ” ተብሏል [ገጽ4]። በእንግሊዝኛ “ኬም ቱ አወር ላይፍ” መሆኑ ነው። ለ/ “ልብን ኩላሊትን የምትመረምረው” የሚለው፣ “ዩ ሰርች ዘ ሃርት ኤንድ ኪድኒስ” ተብሏል። ይኸም አማርኛ ለማያውቁ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ትርጉም አይሰጥም። “ውስጥን የምትመረምር አምላክ ነህ” ለማለት “ዩ ሰርች ዘ ሃርት” በቂ ነበር፤ መ/ የጽሕፈት ግድፈቶች፣ በተለይ የ “አ” ና የ “ተ” ዘሮች በብዛት ይታያሉ። መጽሐፉ ከመታተሙ በፊት ረቂቁን ሌሎች እንዲመለከቱት ማድረግ እነዚህን ችግሮች በቀላሉ በፈታው ነበር። በሁለተኛው እትም ይህ ሁሉ ሊታረም ይገባል። የጥራት ነገር ሲታሰብ፣ ባጠቃላይ ጠንካራ አርታኢ እንደሚጎድለን እንገነዘባለን። ይኸ ሲሆን የሚበደለው ሥራው ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚው ጭምር ነው። አማርኛ ለሚያነብቡ እንግሊዝኛ ቃላት ሸንቁሮ፣ የእንግሊዝኛ አባባሎችን ደግሞ በጥሬው በአማርኛ መናገርና መጻፍ የባሕል ተስቦ ሆኖብናል። “ትንሽ ስሕተት ምንም አይጎዳም። ከሚሠራ ሰው ስሕተት አይጠፋም። የማይሳሳት የማይሠራ ብቻ ነው። መተቸትማ ቀላል ነው። አንባቢው አስተካክሎ ያንብበው” የሚሉ የከረሙ አባባሎች ሊወገዱ ይገባል። ባጭሩ፣ ከተጠያቂነት ለመሸሽ የምንደረድራቸው ምክንያቶች በአስተሳሰብ ወደ ፊት እንዳንገሠግሥ ደንቃራ ሆነውብናል።

2. የትርጉም ጥራት። “ግጥምን ከአንዱ ቋንቋ ወደ ሌላው መተርጎም በጣም አስቸጋሪ ነው። ይህ የትርጉም ሥራ የመዝሙሮቹን ፍሬ ነገርና ትርጉም ለመጠበቅ ሞክሯል፤ ቢሆንም በእንግሊዝኛ ሊዘመር የሚችል ትርጉም አይደለም” ተብሏል [ገጽ 6]። እርግጥ ነው ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ መመለስ ቀላል አይደለም። የተስፋዬን መዝሙሮች ለመተርጎም ግን ቁልፍ የሚሆኑንን ነገሮች ለይቶ ማወቅ ይጠቅማል።

ሀ/ ዝማሬዎቹ በሙሉ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የተቆራኙ ናቸው። መዝሙሮቹ ከአርባ ዓመት በኋላም እንኳ ብርቱና አዲስነት ያልተለያቸው ምክንያቱ፣ ብርቱና ዘላለማዊ በሆነው ቃል ላይ ስለተመሠረቱ ነው፤ በጸሎት ኃይል ስለተገኙ ነው፤ ከተደመጡ በኋላ ልቡናንና አሳብን ለጸሎት የሚያነሳሱት ከዚሁ የተነሳ ነው። ቤት አመታታቸው ሚዛናዊና ስዕላዊ ስለሆኑ ነው፤ [“ዕንባቸውን ሲያፈሱ ለምተው አየዋቸው” ካሴት 1 ቁ.1፡1]። በመጨረሻም፣ ለጌታና ለሕዝቡ መታነጽ እንዲሁ በመሰጠታቸው ነው። “በነጻ የተቀበላችሁትን፣ በነጻ ስጡ” ብሏልና [ማቴ 10፡8]። መዝሙሮቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘዬና ጥራት ተቀዳጅተዋል ላልነው፣ ካሴት 1 ቁ.2ን እንይ።

በከፍታ ሥፍራ [ኢሳ 57፡15፤ 2ዜና 20፡6] / በሰማይ ያለኸው [ማቴ 6፡9፤ መዝ 123፡1]

ምንም አይሳንህም [2ዜና 14፡11፤ ዘፍ 18፡14፤ ሉቃስ 1፡37] / ሁሉን ቻይ የሆንከው [ዘፍ 35፡11፤ ኢዮብ 42፡2] / ልብን ኩላሊትን የምትመረምረው [ኤር 17፡10]

ጌታ ሆይ፣ ጓዳችንን አጽዳ አጥበህ አስተካክለው [1ዜና 23፡28፤ ነህ 13፡19፤ ኤር 35፡2፤ ኢሳ 40፡3፤ ሕዝ 45፡19]

ወደ እንግሊዝኛ ለመተርጎም፣ ጥሬ ቃሉን ወይም መስመር በመስመር መተርጎም አጥጋቢ ሊሆን የማይችለው ለዚህ ነው። “የመዝሙሮቹን ፍሬ ነገርና ትርጉም ለመጠበቅ” ሲባል የማይገቡ ሐረጎችን መጠቀም ለምን ተመረጠ? የአተረጓጎሙ ጥራት በእንግሊዝኛ ለመዘመር ካላስቻለስ መንፈሳዊ በረከት ማካፈል እንዴት ይቻላል? መተርጎሙስ ለምን አስፈለገ? ወደ መዝሙራቱ አሳብ ጠልቆ ለመግባት ይልቅ፣ በቅድሚያ መዝሙሮቹን ደጋግሞ ማንበብና አዝማቾቹ ላይ ማተኮር ያሻል። ለምሳሌ፦ ለካሴት 1ቁ.1፡1 የተሰጠውን አተረጓጎም [ገጽ 13] እንመልከት።

1 መዋረዳቸውን አይተህ፣ አንተ ባርከሃቸው / 2 የቤትህን ልጆች አንተ ሰብረሃቸው

1 Seeing that they are humiliated, bless them / 2 Making the children of Your house humble

3 ትዕቢታቸው ጠፍቶ ከትሑት ልባቸው / 4 ዕንባቸውን ሲያፈሱ ለምተው አየኋቸው

3 With pride destroyed and a meek heart / 4 I saw them simply shedding their tears

መስመር 1 ላይ፣ መዋረድ “penitent, humbled” እንጂ “humiliated” አይስማማውም። ጠላት ስላዋረዳቸው እግዚአብሔር ሕዝቡን አይባርክም፤ ቀድሞውኑ ጠላት ያዋረዳቸው ስላልታዘዙ መሆን አለበትና። ባለመታዘዛቸው ሲጸጸቱ ነው የሚባርካቸው። መስመር 4 “[ከትሑት ልባቸው] ዕንባቸውን ሲያፈሱ ለምተው አየኋቸው።” ያለፉበት ሁኔታ ለጥቅም ሆናቸው ነው አሳቡ። ተክል ውሃ ሲጠጣ እንደሚመቸው፣ እንደሚለማ እንደሚለመልም ማለቱ ነው። ዕንባ ሲወርድ፣ ፍሬው ይበሰብስና ችግኙ ይወጣል፣ ያድጋል። መውረድ ከመውጣት ይቀድማል። ዝቅ ማለት፣ ወደ ከፍታ ያወጣል። ይህ ውብ ቅኔ፣ “I saw them simply shedding their tears = እንባቸውን ሲያፈሱ አየኋቸው” ብቻ በማለቱ የዕንባውን ዘላቂ ተልእኮ አባክኖታል። ቃል በቃል ሳይሆን፣ አሳብ በአሳብ፣ penitent, you blessed them; humble, tears caused them to grow” አማራጭ ትርጉም ሊሆነው ይችል ነበር።

ለሌሎች የምናካፍለው ጸጋ መኖርና ያንኑ እንደሚገባ መግለጥ መቻል ለየቅል ናቸው። ጳውሎስ በቆላስይስ 4፡4፣ “እንደሚገባኝ ያህል እንድገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ” ማለቱ መልእክቱ ኖሮ ከአገላለጽ ጉድለት ሊዛባ እንደሚችል ለማስገንዘብ ነው። ከአያያዝ ይቀደዳል፤ ከአነጋገር ይፈረዳል። በተረፈ፣ የዘማሪያን ርዕስ አሰጣጥ ራሱን የቻለ ጥናት የሚጠይቅ ነው። ርዕስ የመዝሙሩ መልእክት ጭማቂ ነው ካልን። እነዚህን ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት።

ሀ.1. ካሴት 1 ቁ.7፤ ርዕስ፦ ልጅነቴ ያላለቀ፣ በእንግሊዝኛ፦ ማይ እንፈንሲ ኢዝ ኖት ዬት ኦቨር፤

የመዝሙሩ ትኩረት ግን ጨቅላነቱ ላይ ሳይሆን “ሙሉ ሰው አድርገኝ” በሚለው ላይ ነው።

“ልጅነቴ ያላለቀ፣ ነኝና ብላቴና / ሙሉ ሰው አድርገኝ ጌታ፣ ቃልህን አብላኝና”

ሀ.2. ካሴት 3 ቁ.8። ርዕስ፦ ዘመኑ ፈጠነ። ትርጉም፡- ዘ ሲዝን ስፒድድ።

ዘመኑ ፈጠነ፣ ሮጠ ገሰገሰ / የጌታችን መምጫ፣ ጊዜያቱ ደረሰ

ሰዎች ቶሎ በሉ፣ መከሩን ሰብስቡ / የተጣለብንን አደራ አስቡ።

ቃላት በአስተሳሰባችን ላይ በጎና በጎ ያልሆነ ተጽእኖ ያሳድራሉ። ከእንስሳ የሚለየን ይኸው በቋንቋ መግባባት መቻላችን ነው። በ ሀ.1.፣ጨቅላነቱን ሳይሆን፣ ሙሉ ሰው ለመሆን መፈለጉ የመዝሙሩ ቀዳሚ አሳብ ነው። በ ሀ.2.፣ ትኩረቱ ከዘመኑ መፍጠን ይልቅ አደራን ስለመፈጸም ነው፤ የዘመኑን መፍጠን ማሰብና የጌታን መምጫ ማሰብ እኩል ተጽእኖ ይኖራቸዋል ማለት አይደለም።  

3. ዘማሪ ተስፋዬ ጋቢሶ። ስለ ዘማሪ ተስፋዬ ጥቂት ነገሮችን መጥቀስ ያሻል። “በዚያን ጊዜ” በተሰኘው መጽሐፉ [2002 ዓ.ም፤ አሳታሚ ሙሉ ወንጌል ቤተ/ክ፣ አ/አበባ] እንዳሳወቀን፣ የአገልግሎቱን እድሜ፣ ላይላም እንደገለጹት በቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን እንደጀመረና፣ በመካነ ኢየሱስና ኋላም በሙሉ ወንጌል አብያተክርስቲያናት እንደቀጠለ ጠቅሷል። ይህም ከውጭ ለተተረጎሙ መዝሙራትና ከሙዚቃ ስልቶች ጋር እንዳስተዋወቀው ማስተዋል ይቻላል። የሚያገለግሉትን ለማዘጋጀት፣ የእግዚአብሔር ብልሃትና አካሄድ ሁሌም አስገራሚ ነው። ዘማሪ ተስፋዬ እግዚአብሔር ለሰዓቱ ካስነሳቸው ዓይነተኛ አገልጋዮች መካከል ነው። በዚሁ ድረ-ገጽ ላይ ባተምነው ቃለ-ምልልስ፦ “መዝሙር የምታወጣው በምን በምን መንገድ ነው?” ተብሎ ተጠይቆ፦ “ዮሐንስ [ራእይ] ‘በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርኩ’ ይላል። እኔም በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ በመንፈስ ሆኜ ነው የማገኘው። ስጸልይ፣ ቃሉን ሳነብ፣ በመንገድ ስሄድ፣ ያን ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር፣ ስለ እግዚአብሔር ሥራ አስባለሁ። ይህንን ወደ መዝሙር እለውጣለሁ፤ ብቻ ብዙ ጊዜ ብቻዬን ስሆን ነው የሚታየኝ። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ፣ አእምሮዬ በአንድ መልእክት ይሞላል” ብሏል። በሌላ አነጋገር፣ ከታች እንደሚታየው፣ መዝሙሮቹ ጥቅሶችን ሰብስቦ ቤት እንዲመቱ ከማድረግ ያለፈ እንደሆነ ነው። ሦስተኛ፣ ለቤተክርስቲያን የተገዛ ዘማሪ ነው። በቃለ-ምልልሱ ላይ ቀጥሎ፣ “እንዴት ጀመርክ በካሴት ማውጣት?” ብሎ ለቀረበለት ጥያቄ፦ “የመዝሙሮቹ መልእክቶች ተቀርጸው ከበዙ ለብዙዎች ትምህርት እንደሚሆን ብዙዎች ስላመኑበት ቤተክርስቲያን አዘጋጅታ አወጣች። እኔ መዘመር ብቻ ነው። የቀረውን ሁሉ የምታደርገው ቤተክርስቲያን ነች” ሲል መልሷል።

ዘማሪ ሁሉ እንደዚህ ያድርግ ብለን መደንገግ አንችልም። ይኸ ለመንፈስ ቅዱስ እና ለቤተክርስቲያን እንደዚሁም ለአገልጋዮቹ የሚተው ክፍል ነው። ሁሉም በፍሬው ይታያል። በተጨማሪ፣ ዘማሪዎችም መተዳደሪያ ያስፈልጋቸዋል። ይህን ነጥብ ያነሳነው፣ ለቤተክርስቲያን መገዛት ራስን መጠበቂያ ብቻ ሳይሆን የሳተ ሥነ መለኮታዊ አስተምርሆን ከማራባትና ከቅኔያዊ ውበት ከመጉደል እንደሚጠብቅ ለማስገንዘብ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ሳይሆን፣ በገበያ መንፈስ የሚመራ ዝማሬ ለዘማሪው የበዛ ገቢና ሙገሣ ሊያስገኝ ይችላል፤ ለዘማሪው ሕይወትና ለሰሚው ግን ኪሳራ ሊሆን እንደሚችል ማሰብም ይበጃል። ከተዘባረቀ ሕይወት ቅዱስ ዝማሬ ማፍለቅ ደግሞ እጅግ ይቸግራል። የገበያን ነገር ካነሳን፣ ዛሬ በአንድ ሲዲ የሚታተሙት መዝሙሮች ቁጥር ከ 8 እስከ 12 ነው። የገበያን ተጽእኖ ለማየት ከታች እንደተመለከተው ተስፋዬ ካሳተማቸው 7 ካሴቶች ጋር እናነጻጽር፦

ሰባቱ ካሴቶች በጠቅላላው፣ 103 መዝሙሮች ይዘዋል። ካሴት ቁ.1 እና 2 = እያንዳንዳቸው 14 x 2 = 28 መዝሙሮች። ካሴት ቁ.3፣4 እና 5 = እያንዳንዳቸው 16 x 3 = 48 መዝሙሮች። ካሴት ቁ.6 = 15 መዝሙሮች። ካሴት ቁ.7 = 12 መዝሙሮች።

አራተኛ፣ ለጌታ መቀኘትና ‘ሰሌብሪቲ አርቲስት’ መሆን በባህሪም በውጤትም ለየቅል ናቸው። ትኩረቱ፣ በግለሰቡ ላይ ሳይሆን፣ በሚተላለፈው መልእክት ጥራት ላይ ሲሆን ያንጻል፣ እድሜውም ይበረክታል። ሙዚቃው እንደማጀብ፣ እየተጋረጠ መልእክቱን የሚሻማ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው። ሙዚቃ አጨዋወቱና ድምፃዊነቱ እንጂ መልእክቱ ካልተያዘ ምን ዋጋ አለው? የሰሚውን አሳብ የሚይዘው ማንነትና አጃቢ እንቅስቃሴዎች ከሆኑ ግቡን ስቷል። መልእክቱን ከመልእክተኛው መነጠል አዳጋች ነውና፣ ብዙ ጸሎት፣ ጥንቃቄና ጥረት ይጠይቃል። በዚህ ዘመን ለአገልጋዮች ወጥመድ የሆነው የራስን ባሕል ክዶ በብልጭልጭ ዘመናዊነት መወሰድ ነው። በተረፈ፣ ተስፋዬ ጋቢሶ በ “በዚያን ጊዜ” መጽሐፉ እንደጀመረልን፣ባጭር ባጭሩ ለመዝሙሮቹ መነሻ የሆኑ ሁናቴዎችን እንደመግቢያ አድርጎ ቢጽፋቸው ከላይላ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው መጽሐፍ በሚቀጥሉት እትሞች የበለጠ ይዳብራል እንላለን።

የመዝሙሮች ዋነኛ ተግባር እግዚአብሔርንና ቃሉን ማሳወቅ ነው። ይህም ተግባር የዛሬዎቹን ብቻ ሳይሆን የቀደሙትንም ዝማሬዎች ማካተት ይኖርበታል። የሚተላለፈው ሥነ መለኮታዊና ታሪካዊ ዕውቀት ከተዛነፈ ብዙ ጉዳት ይከተላል። በ“የጥንት አምባ ዶት ኦርግ” ድረ-ገጽ የቆዩ መዝሙሮችን ማሰባሰብ የጀመሩ ወገኖች ሥራቸውን በጅምሩ ማቆም የለባቸውም። ምክንያቱም፣ ከ40 ዓመት በፊት ይዘመሩ የነበሩ መዝሙሮች በጊዜአቸው አዲስ ነበሩና ነው። መንፈስ ቅዱስ ለቤተክርስቲያኑ የሰጠው ነውና፤ የጸኑ ትዝታዎቹን መቀስቀስ ትውልድን ከማያያዝ አልፎ የጌታን ኃይል ሥራ ያውጃል፤ ለምስጋና ያበቃል። ከዛሬዎቹ አዳዲስ መዝሙሮች ግን አንዳንዶቹ የአንድ ዓመት እድሜ ከኖራቸው ረጅም ነው። ለምን ይሆን? ወደ ተነሳንበት እንመለስና “ስብሐት ለአምላክ”ን ከቄስ ባድማ ያለው ጋር ተቀኝተን እንጨርስ።

ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር / ስብሐት ላንት በሰማይ ለምትኖር

ይገባናል ምስጋናህን ልንዘምር / በልባችን ቅዱስ ቃልህ ይደር። [1943 ዓ.ም፣ ቁ.6፣ገጽ 7-8]  6/26/12