አዲስ መጽሐፍ

እውነት ግድ ይለናል

በመጋቢ በለጠ ደሳለኝ [2013፣ ዋጋው 7 ዶላር፤ አታሚ Ethiopianchurch.org]

GebreBeleteBkመጋቢ በለጠ ደሳለኝ “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ” የሚለውን በማብራራት የመልእክቱን አስፈላጊነትና ወቅታዊነት እንድናስተውልና እንድንታዘዝ ያስገነዝበናል። መጽሓፍ ቅዱስ የተጻፈው ለትምህርታችን ነው (ሮሜ 15:4)፣ የማያሳፍሩ ሠራተኞችና (2ጢሞ 2:15) ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀን እንድንሆን ነው (2ጢሞ 3:16)። ይህ እንዲሆን ቃሉን ማንበብ፣ ያነበብነውንም ማስተዋልና መታዘዝ ይኖርብናል። “እውነት ግድ ይለናል” ን በጥሞና ብናነብ መጽሓፍ ቅዱስን እናነባለን። “እውነት ግድ ይለናል” ያነበብነውን እንድናስተውል ያግዘናል፣ ልንታዘዝባቸው የሚገቡ አቅጣጫዎችን ይጠቁመናል። መታዘዙ ግን የእያንዳንዳችን ድርሻ ነው።

መጽሓፉ 25ቱን የይሁዳ መልእክት ጥቅሶች መሠረት አድርጎ ከብሉይ፣ ከአዲስከታሪክና ከዘመናችን ሁኔታ ጋር እያገናዘበ ለምዕመናንና ለአገልጋዮች የሚጠቅም ግልጽና፣ ተነባቢ ማብራሪያ ያቀርባል። ጥቅስ በጥቅስ ሆኖ ከይሁዳ መልእክትና ከመላ መጽሓፍ ቅዱስ ጋር ያለውን ግንኙነት ስለሚያሳይ መጽሓፍ ቅዱሳዊ ነው። የሓሰት አስተማሪዎች ባህርያት ምን እንደሚመስልና እንዴት መከላከል እንደምንችል ጠቃሚ ትምህርት አለው። በተጨማሪ በካልቪኒስቶችና በአርሚንያኖች መካከል ላለው ክርክር መጽሓፍ ቅዱሳዊ መልስ ይሰጣል።

ድነትየሚለው ቃልደህንነትማለት እንደሆነና በመጽሓፉ መጨረሻ ላይ ያሉ የማጣቀሻ ጥቅሶች ከመጽሓፉ ጋር እንዴት እንደሚገናኙ ቢገለጽ የበለጠ ይጠቅማ። መጽሓፍ ቅዱስ እያነበብን፣ ያነበብነውንም እያስተዋልንና እየታዘዝን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት ተጠብቀን እንድንኖር፣ ተካራካሪዎችን እንድንወቅስ፣ አንዳንዶችን ከእሳት እንድናድን ሌሎችንም እንድንምር የምንፈልግ ሁላችን፣ “እውነት ግድ ይለናል” ይህን እንድናደርግ የሚረዳ ስለሆነ ገዝተን እናንብብ። የሚለንን እንድንሰማ፣ እንድናስተውልና እንድንታዘዝ እግዚአብሔር ይርዳን።

መጋቢ ገብረእግዚአብሄር ካሕሳይ

ናይሮቢ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን፣ ኬንያ