የ “ሐዋርያ” ዘላለም ትምህርት ሲመረመር

በዘላለም መንግሥቱ

ካለፈው የቀጠለ

"ሐዋርያ" ዘላለም ወይም "ፖዝ" ኢየሱስን፥ 1. ፖዝ አስደራጊው ኢየሱስ፤ 2. ሰይጣኑ ኢየሱስ፤  ብሎ እንደገለጸው በክፍል አንድ ተመልክተናል። በዚህ በመጨረሻው ክፍል 3. ሰው ብቻ ኢየሱስ፤  4. ታጃቢው ኢየሱስ፤ ያለውን እንመለከታለን  

3/ ሰው ብቻ ኢየሱስ። ኢየሱስ እንደ ሰው ብቻ ነው የተመላለሰው? ፖዝ ይህን በግልጽ ተናግሮአል። ይህ ጠማማ የስሕተት ትምህርት ኢየሱስ በምድር በተመላለሰባቸው 33 ዓመታት ከቶም አምላክነቱን አልገለጠም፥ አልተለማመደም፥ "በምድር ሲመላለስ የመለኮትን ኃይል አልተጠቀመም" እንደ ፍጹም ሰው ብቻ ሆኖ ነው ትምህርቶቹን ያስተማረውና ተአምራቱንም ያደረገው የሚል ሆኖ እኛም እንደ እርሱ ፍጹም ሰው በመሆን እነዚህን እናደርጋለን ወደሚል ድምዳሜ የሚያመራ ስሕተት ነው። ወደ ምድር ሲመጣ፥ ፊልጵስዩስ ምን አለ? በምስሉ እንደ ሰው ተገኘ፤ ራሱን አዋረደ፤ ራሱን ባዶ አደረገ፤ የባሪያን መልክ ይዞ ለሞት ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። ሙሉውን ቅድምም እርግማን ሆነ የሚለውን እዚህ ላይ ማምጣት ትችያለሽ። ለሞት፥ ይኸውም የመስቀል ሞት፤ እሷ ፊደል ናት ኋላ የምመልስልሽ። አሁን ክርስቶስን ላሳይሽ፤ ሰው ሲሆን ክርስቶስ ሁለተኛ አዳም ነው የሆነው። እግዚአብሔር ሆኖ አይደለም በምድር የተመላለሰው። እግዚአብሔርነቱን እያሳየ አይደለም በምድር የሠራው። ክርስቶስ በምድር ሲመላለስ፥ ማንነቱ የማይቀየር

[ቤተልሔም፣ በምድር ሲመላለስ ክርስቶስ መለኮትነቱን ገልጧል? ተጠቅሟል?]

ገልጧል፥ ተጠቅሟል፤ አልተጠቀመም ብዬ ነው የማምነው። ክርስቶስ በምድር ላይ መለኮታዊ ማንነቱን አልተጠቀመም። የተመላለሰው በሰው ማንነት፥ በመንፈስ ቅዱስ ቅባትና ኃይል ነው።

ጋዜጠኛዋ ደጋግማ ያቀረበችውን የኃጢአት ስርየት መስጠት እና አብሮት ለተሰቀለው ሰው፥ 'ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ' የሚለውን ቃል በመንገር እነዚህ የመለኮት ባሕርያት መሆናቸውን ልታሳይ ብትጥርም፥ ይቅርታ ማድረግ ለተከታዮቹም የተሰጠ ሥልጣን መሆኑን እና በመስቀል ላይ የተሰቀለው እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ማመኑ ሊያስገባው እንደቻለ፥ እኛም የዳንነው 'በዚያ ፕሪንሲፕል' መሆኑንና እርሱም ራሱ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ እንደሚችል ሊያስረዳ ሞክሮአል። “ . . . ኢየሱስ አምላካዊ ኃይሉን እየተጠቀመ ከሆነ እየሠራ ያለው፥ እኛ አሁን በመንፈስ ቅዱስ የምንኖረውን ኑሮ መሥራት አንችልም ማለት ነው። . . .  “

[ቤተልሔም፥ እኔ ክርስቶስ መለኮት መሆኑን አምናለሁ፤]

እነማን ያምናሉ? መጽሐፉ ይላል ወይ? እነማን መለኮት ነበር ይላሉ? የአምላክ እናት የሚሉ እኮ አሉ፤ . . . ኃጢአት ማሰተሰረይ ይችላል ወይ ሰው ላልሽው መልሱ አዎን ነው። ለምን አዎ ሆነ? ጌታ ኢየሱስ እዚያው አንቺ የጠቀስሽው ጥቅስ ላይ ሲናገር እስራኤሎች የተቆጡበት ላይ ሲናገር ምንድነው ያለው ጌታ ኢየሱስ፥ 'የሰው ልጅ ኃጢአትን ማሰረይ እንደሚችል እንድታውቁ'”

[ቤተልሔም። የሰው ልጅ ያለው ስለራሱ ነው፤]

የሰው ልጅ ማንን ወክሎ ነው ያለው? በአብ ቀኝ የተቀመጠ ስብዕና አይደለም የሰው ልጅ የተባለው? . . . ክርስቶስ ኃጢአትን አሰተሰረየ የምንልባቸው ነገሮች አምላካዊ ማንነትን አያሳዩም። . . . አንዳንዶች ስግደትን ተቀብሏልና አምላክ ነው ይላሉ፤ ለዳዊትና ሰሎሞንም ተሰግዶአል። . . . አንዳንዶች በውኃ ላይ ሄዶአል ይላሉ፤ ስንቶች አስማተኞች አሉ በውኃ ላይ የሚሄዱ . . . መለኮት ናቸው ወይ? . . . የኛ ጌታ በውኃ ላይ ሲሄድ 'መለኮት ስለሆንኩ ሄድኩ' አላለም። ጴጥሮስም በውኃ ላይ ሄዶአል። ውኃ ላይ መሄድ መለኮት አያሰኝም።”

ፖዝ የሚነግረን ኢየሱስ ሰው የሆነውን ኢየሱስን ነው። ሊያስተሰርይ ስለሚችለው ኃጢአት ሲያብራራ በበሽታ ምክንያት የመጣ ኃጢአትን እና ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ይቅር ይባልላቸዋል የተባለውን በማቅረብ፣ ከሐዋ. 2 22 እና 36 በመጥቀስ ጌታ ሰው እንደነበረ ብቻ ከትንሣኤው በኋላ ግን ጌታና ክርስቶስ እንደሆነ አብራራ። ከልደቱ በፊት አምላክ፥ ከትንሣኤው በኋላ ሰውና አምላክ፥ በመካከል ግን (መሰይጠኑንም ሳንዘነጋ) ሰው ብቻ ነበር ነው የሚለን። ይህ የትውልድ መርዝ የሆነ አጋንንታዊ ትምህርት ነው። ጌታ ኢየሱስ፥ 'መለኮት ስለሆንኩ ይህን አደረግሁ' እያለ መለከት እያስነፋ ምንም አለማድረጉን ወንጌላት ይነግሩናል። ኢየሱስን ሰው ብቻ የሚሉ እንደ ኢስላም ያሉ ሃይማኖቶች ትልቅ አድርገው የሚያቀርቡት ማስረጃ ይህ ነው። ጌታ ኢየሱስ እንዲያውም ማንነቱን፣ ሰዎችም አጋንንትም ሲረዱ፣ እንዳይገልጡ ይነግራቸው ነበር፤ ማቴ. 1215 ማር. 312 830 ሉቃ. 921-22 ወዘተ። ኢየሱስ እንዳይናገሩ የተከላከለው ሥጋ የለበሰ እግዚአብሔርን ስላልሆነ ሳይሆን የመጣበት ተልእኮ በመርሐ ግብሩ መፈጸም ስለነበረበት ነው።

መለኮትን ገልጧል? ተአምራት መለኮት አይደለም። ተአምራት መሥራትሽ፥ የሆነ ነገር ማድረግሽ መለኮትነትሽን አያሳይም። . . . ለምሳሌ በምድር ላይ ሠላሳ ዓመት ሲመላለስ መለኮት ተገልጦበታል? ወይንስ መንፈስ ቅዱስ ተገልጦበታል? በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት በጥበብም በሞገስም ያድግ ነበር ነው የሚለው።”

ከላይ ፖዝ ከተናገረው ውስጥ ያሰመርኳቸውን አሳቦች ስናጤን ክርስቶስ በምድር ሲመላለስ እንደ ሰው ብቻ በመንፈስ ቅዱስ ቅባትና ኃይል የተመላለሰ ብቻ ነው። ይህ ወደ ምን እንደሚመራን ለመረዳት አይከብደንም። እኛም በመንፈስ ቅዱስ ቅባትና ኃይል ኢየሱስ እንደተመላለሰው መመላለስ፥ እንደሆነው መሆን፥ እንዳደረገው ማድረግ ይቻለናል ወደሚል ወደ ዘመናዊው የቃል-እምነት ትምህርት የሚወስደን ስሕተት ነው። ይህ ትምህርት ደግሞ በፖዝ አልተጀመረም፤ ይህንንን ስሕተት በማሰራጨትም እርሱ የመጨረሻው የዚህ መርዘኛ ትምህርት ደቀ መዝሙር አይሆንም።  ኢየሱስ ሰው ብቻ ሆኖ ኖሮ ሲጠመቅ ክርስቶስ ሆነ፤ ከአብ ድምጽ ሲመጣ ክርስቶስ ሆነ፤ በተራራው የአብ ድምጽ ሲመጣ ክርስቶስ ሆነ፤ በትንሣኤው ክርስቶስ ሆነ እያሉ ሊያስረዱ የሚሹ ከኒቅያ ጉባኤ ዘመን በፊት አንሥቶ እስከ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የቅባት እና የጸጋ ልጅ አስተማሪዎች፥ እስከ ዘመነኞቹ የቃል-እምነት አስተማሪዎች ድረስ አሉ። እግዚአብሔር የነበረው ቃል (ዮሐ. 11) ሥጋ የሆነውና በእኛ ያደረው (ዮሐ. 114) መለኮትነቱን ጥሎ ወይም ሽሮ አይደለም። በድንግል ማርያም ማኅጸን ከነበረበት፥ በቤተ ልሔም በረት እስከተኛው ሕጻን፥ በመስቀል ላይ እስከተሰቀለው ድረስ ኢየሱስ ሰው ብቻ አልነበረም።

ቤኒ ሂን ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ ባይረዳው ኖሮ ኃጢአት ሊያደርግ የሚችል ሰው ብቻ ነበረ ይላል። ሰው ብቻ። ይህንን የሚለው ሂን ብቻ ሳይሆን ብዙዎች የቃል-እምነት ሰባኪዎች ናቸው። በመስቀል ላይ የፈሰሰው ደም የአንድ ተራ ሰው ብቻ ደም ነው። ሂን የሚለው ሲመላለስ ሰው ብቻ ሳይሆን በመስቀል ሰይጣን ሆኖ መሸነፉንና በሲዖል ድል ማድረጉንና ዳግም መወለዱንም ነው። ፖዝም የሚለን ይህንን ይመስላል። ኢየሱስ፥ 'እኔ አምላክ ስለሆንኩ ይህን አደረግሁ' እንዳላለ፥ 'እኔ ሰው ብቻ ስለሆንኩ ይህን አደረግሁ ወይም አላደረግሁም' አለማለቱን እግምት ውስጥ ሳያስገባ የራሱ ድምዳሜ ላይ ደርሶ ኢየሱስ ከጽንሰቱ እስከ ስቅለቱ ሰው ብቻ ነበረ፤ እንዲያውም ከሰውም የወረደና የሰየጠነ ነበረ ይለናል። ኢየሱስ ሰው ብቻ ነበረ ማለት አንድ ባሕርይ ብቻ ነበረው ማለት ነው። መለኮታዊነት የሌለው ሰብዓዊ ብቻ የሆነ ነው ማለት ነው። ኢየሱስ አንድ ባሕርይ ብቻ ነው የሚሉ፥ ሰው ብቻ ነው የሚሉ፥ ሰውና አምላክ ተቀይጦ አንድ አዲስ ባሕርይ ተፈጥሮአል የሚሉ፥ አምላክነቱ ሰውነቱን ውጦት ተዋሕደው ተዋሕዶ ሆኖአል (እንደ ኢኦተቤ/) የሚሉ፥ ሌሎችም በታሪክ ውስጥ የመጡና የሄዱ፥ እስከዛሬም ተጋቦታቸው ያልጠፉ ትምህርቶች ኖረዋል። ፖዝ የሚያቀነቅነው ይህ ከነአርዮስ ዘመን ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲያውክ የኖረና የታደሰ አሮጌ ኑፋቄ ነው። ግራ ቀኙን የማያውቀው የዋኅ መንጋ ባለማወቅ እየተጋተ ያለው መርዘኛ ትምህርት ነው።

“. . . በምድር ላይ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ አልተመላለሰም። አሁን በሰማይ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው። ዱሮ ወደ ምድር ሳይመጣ በፊት ፍጹም አምላክ ብቻ ነበር። በምድር ላይ ቤዛ ሲሆን በሰው ማንነት ሁለተኛው አዳም ሆነ። የአዳምን ቤዛነት በሚጨርስ ማንነት እራሱን ባዶ አድርጎ በምስሉ እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋርዶ ነው ሚለው። ጳውሎስ ነው ሚለው፤ የጳውሎስ መረዳት ነው ያለን”  

ከዚህ የፖዝ የድፍረት ንግግር በግልጽ የምንረዳው ከመምጣቱ በፊት ፍጹም አምላክ፥ አሁን ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ እንደሆነ ሲሆን፥ በመካከል ግን መለኮትነት የሌለው ፍጹም ሰው ብቻ እንደነበር ነው። ክርስቶስን በየተለያዩ ዓመታቱ ገነጣጥሎ እንደተለያየ አድርጎ እንደሚያስተምር ለተጠየቀው ጥያቄ የመለሰው መልስ ይህንን ግልጽ ያደርገዋል፤

“ . . . እስከ 30 ዓመቱ ማንኛውም ሰው የሚኖረውን ነው የኖረው፤ አናጢ ነበር ነው የሚለው፤ በቃ ኖርማል ነገር ነው። 30 ዓመቱ በኋላ ግን የጌታ መንፈስ በኔ ላይ ነው ብሎ የተቀባው መሢሕ አገለገለ ማለት ነው። ጌቴሴማኒ ጽዋውን ከጠጣ በኋላ ቤዛ ሊሆነን እያንዳንዷን የኃጢአተኛ ዋጋና ሥርዓት ከፈላት ማለት ነው፤ እስከ መስቀል። ከሙታን ሲነሣ 30 ዓመቱ ኢየሱስ ነው? 3 ዓመቱ አገልግሎት ነው? መስቀል ላይ ያለው ነው? አይደለም። አሁን በሌላ ክብር አይደል ምናውቀው? እስኪ ጳውሎስ ያለውን ጥቅስ ልጥቀስና ልጨርስልሽ፤ 2ቆሮ. 5 ማለት ነው፤ ክርስቶስን በሥጋ ያወቅነው ብንሆን እንኳ ከዚህ በኋላ እንደዚህ አናውቀውም ይላል። በሌላ መልክ እናውቀዋለን ማለት ነው። ስለዚህ መገነጣጠል ለምን አስፈለገ?”

እንግዲህ የሰነፍ አሳብ ነው።  የፖዝ ኢየሱስ በምድር ባገለገለበት ዘመን ሰው ብቻ ኢየሱስ ነው። ተወልዶ እስከሚሞት እንደ ሰው ብቻ ኖሮ ከሞት ሲነሣ ግን እንደገና አምላክና ሰው ሆነ። በሥጋው ወራት መለኮት ያልነካው፤ አማኑኤልነትን ያልተቀዳጀ፤ መንፈስ ቅዱስ እኛን እንደሚረዳን ብቻ የረዳው፤ ነፋሱ፥ ማዕበሉና ተፈጥሮ የታዘዘው በመለኮትነቱ ያልሆነ፥ 'እወዳለሁ ንጻ' ብሎ ያነጻው በመለኮት ያይደለ፥ ደካሞችን ወደራሱ የጠራ ወደ ሰውነቱ ብቻ የሆነ፥ የሰንበት ጌትነቱ የሰው ጌትነት ብቻ የሆነ፥ ቃል ተናግሮ በውኃ ላይ የሚያስኬድ የሰውነቱ ቃል ብቻ የሆነ፥ በፊታቸው ተለውጦ እንደ ፀሐይ የበራ፥ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስነቱና የአይሁድ ንጉሥነቱ ሲጠየቅ እውነቱን የገለጠው ሰውየው ብቻ ኢየሱስ ነው ወይ? ዮሐ. 11-2 በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ይላል። ኋላ በቁ. 14 ይህ ቃል ሥጋ መሆኑ ተጽፎአል። ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። መጀመሪያ ቃል የነበረው ቃልን አውልቆ አስቀምጦ ነው ሥጋ የሆነው? ወይስ ቃል ራሱ ነው ሥጋ የሆነው። ጥያቄውን በሌላ መልክ ልበለው፤ ቃል ቃልነቱን ይዞ ነው ሥጋ የሆነው ወይስ ቃልነቱን ትቶ ነው ሥጋ የሆነው? ትንሽ ዝቅ ብለን የምናየው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የተነሡ በኢየሱስ ማንነት ላይ የተፈጠሩ የማንነት ጥያቄዎች አሉ። አንዳንዱ ኢየሱስን አምላክ ብቻ፥ ሌሎቹ ሰው ብቻ፥ ሌሎቹ ግማሽ አምላክና ግማሽ ሰው፥ ሌሎች ብዙው ክፍል አምላክና ጥቂት ሰው፥ ሌሎች ከሁለቱም ልዩ የሆነ ሦስተኛ አካል የያዘ ያደርጉታል። ሁለት ሰውና ሁለት ባሕርይ፥ አንድ ሰውና አንድ ባሕርይ የሚያደርጉትም አሉ። የኢየሱስ ማንነት ሰውም አምላክም በመሆኑ ልዩ ነው። 

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረን ኢየሱስ ሥጋ የለበሰ እግዚአብሔር ወልድ ነው። የሥላሴ ሁለተኛ አካል ነው ሥጋ የለበሰው። የሥላሴ ሁለተኛ አካል የሆነው እግዚአብሔር ሥጋ ለበሰ ማለት የሥላሴ ሁለተኛ አካልነቱን ደመሰሰ፥ ተወ፥ ከመሆን አቆመ፥ አውልቆ የነበረበት አስቀምጦ አምላክነቱ እዚያ ሰማይ፥ ሰውነቱ ደግሞ እዚህ ምድር ሁለት አካል ሆኖ ተመላለሰ ወይም ኖረ ማለት አይደለም። ኢየሱስ አንድ አካል ነው፤ በዚያ አንድ አካል ውስጥ ሁለት ባህርያት አሉ። ኢየሱስ በአንድ አካል ፍጹም ሰው እና ሙሉ አምላክ ሆኖ ተመላልሶአል። አንድ አካል ሁለት ባሕርያት። ፖዝ የሚነግረን ኢየሱስ አንድ አካልና አንድ ባሕርይ ኢየሱስ ነው። ፖዝ ሊመልስልን የሚገባው የሥላሴ ሁለተኛ አካል የሆነው እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ በሥጋ በተመላለሰባቸው 33 ዓመታት የት ነበር? ምን ያደርግ ነበር? ወይስ ይህ የሥላሴ ሁለተኛ አካልም ፖዝ ተደርጎ ነበር? እንደ ፖዝ ትምህርት እግዚአብሔር ወልድ 33 ዓመታት ከመለኮትነት ፖዝ የተደረገ ይመስላል። ይህ የክርስቶስ ሐዋርያ ዮሐንስ ያስጠነቀቀን ስሕተት ነው። ገና በዮሐንስ ዘመንም ይህ ችግር ነበረ። ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ። ይላል። ኢየሱስ ክርስቶስ፥ እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ እንደ መጣ፥ አምላክ ሥጋ ለብሶ ሰው እንደሆነ የማይታመን መንፈስ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው። ፖዝ የሚነግረን ኢየሱስ ግን በሥጋ የመጣው ክርስቶስ እግዚአብሔር ወልድ ሳይሆን ሥጋ ወይም ሰው ብቻ የሆነ ኢየሱስ ነው። የተሰቀለው ኢየሱስ ሰው የሆነው ኢየሱስ ብቻ ነው።  የሐዋ ሥራ 2፥ቁ.22 እና 36 በማያያዝ ፖዝ ኢየሱስ ከትንሣኤ በኋላ ደግሞ ጌታና ክርስቶስ የተደረገው መሆኑን ሊያስረዳ ጥረት አድርጎአል። ይህ ሰው ዐውድ ስለሚባለው ነገር ፈጽሞ ግራ የገባው፥ ወይም ጨርሶ የማያውቅ፥ ወይም ሆን ብሎ ለማሳት ታጥቆ የተነሣ መሆኑን የሚያሳይ አጠቃቀስ ነው። የሐዋ ሥራ 2 22 “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤” ይላል። 'ሰው ነበረ' የሚለው ሐረግ ላይ ነው ያተኮረው። ቁጥር 36 ላይ ደግሞ፥እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” ይላል።

ከትንሣኤው በኋላ ጌታና ክርስቶስ ተደረገ። በሐዋ ሥራ ም. 2 ጴጥሮስ እየሰበከ ያለው ከአይሁድ ሦስት ታላላቅ በዓላት በዓለ ኀምሳ የተባለውን አንዱን ለማክበር ለመጡ፥ ምናልባት ፋሲካን አክብረው በዓለ ኀምሳንም ለመድገም እዚያው ለሰነበቱ አይሁድ ነው። ይህ ለክርስቲያኖች የቀረበ ስብከት አይደለም። በዚያን ወቅት ደቀ መዛሙርት ቁጥራቸው 120 ያህል ብቻ ሲሆን በዚህ ቀን ያልዳኑት ቀርተው የዳኑትና የተጠመቁት ብቻ እንኳ ሦስት ሺህ ነፍስ ነበሩ። እንግዲህ ይህ ስብከት ላልዳኑ አይሁድ የሰሰበከ ነው። "በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት" ብሎ በቀጥታ ነው የተናገረባቸውና፥ ምናልባት አብዛኞቹ ከኀምሳ ቀናት በፊት በነበረው ፋሲካ ቀን የተደረገውን ያዩና የተሣተፉ ናቸው።  እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ያውቁና ይረዱ የነበረው እንደ ሰው ብቻ ነበር። ስለዚህ፥ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ ይላል እንጂ ለእናንተ የተገለጠ አምላክ ነበረ፤ ሊል አይችልም። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ያዩት የነበረው እንደ ተራ ሰው ብቻ ነበርና። ኋላ ግን ጴጥሮስ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ብቻ ሳይሆን ጌታና ክርስቶስ መሆኑን በመግለጥ፥ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ (. 38) ብሎ በስሙ እንዲጠመቁ ነበር ያዘዛቸው። ቀድሞ ጌታ ሰብከው ደቀ መዛሙርት ሲያደርጉ በአብ፥ በወልድ፥ እና በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ነበር የነገራቸው። ጴጥሮስ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ ያዘዛቸውና የኃጢአታቸው ስርየት በስሙ ከመጠቃቸው ጋር የተቆራኘው ያልተቀበሉት ጌታ፥ ሰው ብቻ የመሰላቸውና ሰው ብቻ ያሉት ጌታ፥ እርሱ እግዚአብሔር ወልድ መሆኑን አምነው ቀድሞ የካዱትን አሁን ይቀበሉ ዘንድ ነው። ቢያውቁት ኖሮ ባልሰቀሉትም ነበራ! የጌታ ሐዋርያ ጳውሎስ 1ቆሮ. 28 ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም በር፤ አለ። የክብርን ጌታ ነው የሰቀሉት። በመስቀል ላይ የተሰቀለው ጌታ ሰውየው ብቻ ኢየሱስ ሳይሆን የክብር ጌታ የሆነው ኢየሱስ ነው። ያላወቁትም እውነት ነበር። ሰውየው ኢየሱስ ብቻ ነበር የመሰላቸው እንጂ የክብር ጌታ መሆኑን አላወቁም፤ ቢያውቁ ኖሮ ባልሰቀሉትም ነበር። 

ጌታ ኢየሱስን አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉና ይሞክሩ የነበረው፥ ኋላም በእርግጥ የገደሉት በመካከላቸው የኖረና ያስተማረ ሰው ብቻ ወይም ሰውየው የሆነ አስተማሪ ስለነበረ አይደለም። ለምሳሌ፥ ዮሐ. 518 እንግዲህ ሰንበትን ስለ ሻረ ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ደግሞ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካክሎ፦ እግዚአብሔር አባቴ ነው ስላለ፥ ስለዚህ አይሁድ ሊገድሉት አብዝተው ይፈልጉት ነበር። ይላል። በዚህ ጥቅስ ኢየሱስ ሁለት ነገሮች ማድረጉን እናስተውል። መጀመሪያ ሰንበትን ሻረ፤ ይህን ያደረገው የሰንበት ጌታ ስለሆነ ነው። ለአይሁድ ሰንበትን መሻር የሚያስገድል ኃጢአት ነው፤ ዘጸ. 3114 ዘኁ. 153236 ሁለተኛ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካከለ። መለኮትነቱን እዙፋኑ ላይ  አስቀምጦ ብቻ ቢሆን የመጣው ይህ ማስተካከል ሊኖር አይችልም ነበር። ይህ መስተካከል ከትንሣኤው በኋላ የተነገረ ሳይሆን ከመስቀሉ በፊት የተገለጠ ነው። መለኮታዊ ሥልጣኑን ፈቅዶ አለመጠቀሙ፥ "ሰው ብቻ ነበር" አያሰኘውም። ለአይሁድ ኢየሱስ ማን መሆኑን መናገሩ ከቶም አልተድበሰበሰባቸውም። ሰው ብቻ ነኝ ያለ ሰው አይደለም እንዲሰቀል ያስደረጉት። ጌታ ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት ሲመረመር ሊቀ ካህናቱ ማንነቱን በጠየቀው፥ በተለይም የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ እርሱ መሆኑን በግልጥ በጠየቀው ጊዜ፥ ኢየሱስም፦ እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ ብሎ ተናገረ፤ ማር. 14 62 ሊቀ ካህናቱ የቡሩክ ልጅ ያለው የሚጠብቁትን መሢሕ ሲሆን ጌታ ኢየሱስ የሰው ልጅ ያለውም እርሱን ነው። ጌታ ራሱን፥ 'የሰው ልጅ' እያለ ይጠራ ነበር። ሰው ብቻ ስለሆነ አይደለም ራሱን የሰው ልጅ እያለ ይጠራ የነበረው። ይህ በደመና የሚመጣ የሰው ልጅ ለአይሁድ እንግዳ ቃል አይደለም። አይሁድ ይህ የሰው ልጅ ማን መሆኑን አሳምረው፥ አብጠርጥረው ያውቃሉ።  የሰው ልጅ የተሰኘው ሐረግ ለሰዎችም (ለምሳሌ ሕዝቅኤል ብዙ ተጠርቶበታል) ቢያገለግልም እዚህ ጥያቄ ላይ የቀረበው የሰው ልጅ ከዚህ በፊት የተነገረ ነገር ያለው የሰው ልጅ ነው። በዳን. 713 በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት። ይላል። ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀድዶ ሌላ ምስክር አለማስፈለጉን መናገሩ የምናልባትና የግምት መረዳት አልነበረም። እዚህ ጌታ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላች   ያለውና እዚያ በዳንኤል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ የተባለው አንድ መሆናቸውን የአይሁድ አለቆች አሳምረው ያውቃሉ።

ለነዚህ የአይሁድ አለቆችና ካህናት መልስ ይሰጥ የነበረው ኢየሱስ ሰውየው ኢየሱስ ብቻ አልነበረም። በመስቀል ላይ የተሰቃየውና የሞተው ጌታ 'ሰው ብቻ' የሆነው ኢየሱስ አልነበረም። እርግጥ ነው መለኮት እንደማይሞት የታወቀ ነው። 'ሰው ብቻ' ግን፥ ቢበዛ የራሱ ቤዛ ነው የሚሆን እንጂ ስለሌላው ቤዛ ሊሆን አይችልም። ስለ ሌላ ቤዛ የሚሆነው፥ የዓለምን ሁሉ ኃጢአት የሚያስወግደው ሰው፥ 'ሰው ብቻ' አልነበረም። ይህ ሰው ከሰው ብቻነት ከአዳምነት ያለፈ ነው። አምላክ መለኮቱ ሳይሰረዝ ሰው፥ ቃልም ቃልነቱ ሳይጠፋ ሥጋ የሆነው ለዚህ ነው። ተራ ሰው የኔን የአንዱን ሰው ኃጢአት ብቻ እንኳ መሸከም አይችልም። ይህ ሰው ተራ ሰው ሳይሆን አምላክ ሰው (በስነ መለኮት ቋንቋ ቴአንትሮፖስ) ነው። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የተደረጉት ትልልቅ ጉባኤዎች በኢየሱስ ማንነት ላይ የተከራከሩና ያረጋገጡ ጉባኤዎች ነበሩ። በኬልቄዶን 325 . . የተደረገው በአርዮስ ትምህርት ላይ፤ 381 . . በቁስጥንጥንያ የተደረገው በአርዮስ፥ በአቡልናርዮስ፥ እና በሰባልዮስ ትምህርት ላይ፤ 431 . . በኤፌሶን የተደረገው በንስጥሮስ፥ በጰላግዮስ እና በእመአምላክነት ጉዳይ ላይ፤ በኬልቄዶን 451 የተደረገው በአውጣኪ እና በኢየሱስ መለኮትና ስብዕና ላይ (ይህ 4ኛው ጉባኤ አውጣኪና የአንድ ባሕርይ ትምህርቱ በአገራችን ተዋሕዶ የሚባለው የተወገዘበት ትምህርት ነው) እንዲህ እያልኩ ቀጣዮቹን ጉባኤዎችም መዘርዘር ይቻላል። ነጥቤ፥ እነዚህ ጉባኤዎች ስለተቀመጡና ተነጋግረው እምነታቸውን ስለገለጡ ወይም ስሕተትን ስላወገዙ ብቻ ትክክል ናቸው ማለት ሳይሆን የተነጋገሩባቸው የቃሉ እውነቶችና ያወገዟቸው የተሳሳቱ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው ወይ ማለት አግባብ መሆኑና እነዚህ ስሕተቶች እንዳልኖሩ መቁጠር ስሕተት መሆኑን ነው።  የኒቅያ ጉባኤ የተቀመጠው አርዮስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር የተለየ ማንነት ስላለው ነው ብሎ ያስተማረው ትምህርት ስለናኘ ነበር። ዘመናዊዎቹ አርዮሳውያን የይሖዋ ተከታዮች ይህንን ነው የሚያስተምሩት። ንስጥሮስ የተባለው ኢየሱስ ሰው ብቻ ሆኖ ነገር ግን በአምላክ ቃል (ሎጎስ) ይደገፍና ኃይል ያገኝ ነበር ይላል። አውጣኪ የተባለው ክርስቶስ ሰውም አምላክም ያይደለ ሦስተኛ ሌላ (በሮማይስጥ tertium quid) ነው ብሎ ነበር። ይህን ተከትሎ ሞኖፊሳይቶች (አንድ ባሕርይዎች) መለኮታዊው ባሕርይ ሰብዓዊውን ሰልቅጦታል የሚል ትምህርት ገነነ። እንዲህ እያሉ የክርስቶስን መለኮትና ስብዕና በተመለከተ የተፈጠሩትን ስሕተቶች ሁሉ ለመዘርዘር ብዙ ናቸው። ሰውየው ኢየሱስ ለፖዝ የተገለጠ አዲስ ስሕተት አይደለም። 

በአገራችንም እንኳ በኛ ቆጠራ 1870 . . በቦሩ ሜዳ የተደረገው ጉባኤ በክርስቶስ ማንነት ላይ ነበረ። ቀድሞ ቅባት፥ ካራ፥ ተዋሕዶ፥ እና የጸጋ ልጅ የተባሉ በክርስቶስ ማንነት ላይ የነበሩ የቆዩ የተለያዩ ትምህርቶች ነበሩ። ወደነዚህ ሁሉ በዝርዝር መግባት ራሱን የቻለ ሥራ ነው። ግን የቀደሙትም ሆኑ የአገራችን ጉባኤዎች እዚህ ሰየጠነ፥ ሰው ብቻ ነው፥ ፖዝ የሚያደርግ ሰው ሾመ በተባለው ኢየሱስ ላይ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። የፖዝ አቋም ኢየሱስ ከጽንሰቱ እስከ ትንሣኤው ሰይጣንነትንም ጨምሮ፥ ሰው ብቻ ነው እንጂ ምንም መለኮትነት የለውም የሚል ነው። ፖዝ ጌታ ኢየሱስ ስግደት ሲቀበል ለነገሥታት እንደሚቀርብ ያለ ስግደት ብቻ ነው የተቀበለው እንጂ ለአምላክ የሚቀርብ አምልኮ አልተቀበለም ይላል። እርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኛቸው ስግደቶች ሁሉ የአምልኮ አይደሉም። አንዳንዱ ስግደት የአክብሮትና የሰላምታ ስግደት ሊሆን ይችላል። ግን አንዳንዱ የአምልኮ ስግደት ነው። ገና ሕጻን ሳለ የሰገል ሰዎች አልሰገዱለትም? (ማቴ. 22-11) ሰግደውለታል። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስን ሰላም ሊሉት አይደለም የመጡት። ይህ ስግደት የሰላምታ ስግደት አይደለም። እዚህ ጥቅስ ውስጥ ያለው ስግደትና በሌሎች ቦታዎች፥ ለምሳሌ፥ ማቴ. 49-10 ሰይጣን ጌታን እንዲሰግድለት የጠየቀው ቃል ተመሳሳይ ነው። ሰይጣን ጌታን፥ 'ሰላም በለኝና ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ' እንዳላለው መቼም ግልጽ ነው። በግልጽ ጌታም ለእግዚአብሔር ብቻ እንደሚሰገድ የተጻፈውን ጠቅሶ እዚያው ተናግሮአል። ይህ ቃል አምልኮ ነው። በማቴ. 1432 የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው የሰገዱለት ከማንነቱ ጋር የተቆራኘ አምልኮ ነው። የአምልኮ ስግደት ደግሞ ለአምላክ ብቻ የሚሰጥ ነው። ጌታ ይቅርታ ሲያደርግና ኃጢአት ሲያስተሰርይ ማንም ሰው የሚያደርገውን ዓይነት ስርየት ብቻ ነው ያደረገው እንጂ ከአምላክ በቀር ማንም ሊያደርግ የማይችለውን ስርየት አላደረገም ይለናል ፖዝ። ተአምራት ሲያደርግም ተራ ሰው የሚያደርገውን ተአምር ብቻ ነው ያደረገው ነው የሚለን። የሚደንቅ ድፍረት ነው! ፖዝ በኢየሱስ አገልግሎት ልክ የሆነ ተአምራት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ስግደት መቀበልና ስርየት መስጠትም እንደሚችል ነው የተናገረው። መጥተው እግሩ ስር የሚወድቁ ሰዎችን፥ 'እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ነው የምላቸው' ይላል። ከጌታ የተበደረው ቋንቋ ነው። ቶሎ ካልመለሰው ብዙ የሚወልድበት ብድር ነው።

ጌታ ክርስቶስ ኃጢአትን ሲያስተሰርይ ወይም ይቅር ሲል፥ ጻፎችና ፈሪሳውያንም፦ ይህ የሚሳደብ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው ያስቡ ጀመር። ተብሎ ተጽፎአል፤ ሉቃ. 521 መረዳታቸው ግልጽ ነው። ጌታም መረዳታችው ስሕተት ቢሆን ኖሮ ባረመ ነበር፤ ነገር ግን የጌታ መልስ ግልጽ ሆኖ፥ ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአት ሊያስተሰርይ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ብሎ፥ ሽባውን፦ አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፥ አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ አለው። ነበር፤ . 24 ኢየሱስ እንደ ሰውነቱ ሥልጣኑን ሁሉ ባይገልጥም እዚህ የሰው ልጅ ሥልጣንና የእግዚአብሔር ሥልጣን ተስተካክለው ነው የታዩት። በጌታ ሕይወት ስብዕናውንና መለኮትነቱን ተጣምረው የምናይባቸው ቦታዎች በርካታ ናቸው፤ ለምሣሌ፥ አልዓዛርን ከማስነሣቱ በፊት እንደ ሰውነቱ አነባ፤ ግን እንደ አምላክነቱ ከሙታን ጠርቶ አስነሣው፤ ዮሐ. 11 በታንኳዋ ውስጥ እንደ ሰውነቱ ደክሞት ተኛ፤ ተነሥቶ ግን እንደ አምላክነቱ ባሕሩንና ማዕበሉን ዝምና ጸጥ እንዲሉ ተናገራቸው፤ ማር. 4

የእግዚአብሔርና የሰው በክርስቶስ አንድ መሆን ታላቅ ድንቅ ነገር ነው። ሙሉ በሙሉ ባይገባን ሊያስገርም አይገባም። ስላልገባንም የሆነውን ኹነት ልንክድ የተገባ አይደለም። ወይም እስከገባን እስከ ዝቅተኛው ደረጃ ልናወርደው ለመሞከር እኛ ራሳችን የተገባን አይደለንም።  በቃለ መጠይቁ መካከል ስለ ኢየሱስ ሰው ብቻ ስላለመሆኑ መለኮት ከመሆኑ ጋር ስለመታጀብ ተነሥቶ ሲጠየቅ፥ "ኢየሱስ ክርስቶስ ሊወግሩት ሲሉ በመሃላቸው አልፎ ሄደ ሲል እኮ ዝም ብሎ አልፎ ሄደ እኮ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ በመሃላቸው አልፎ ሲሄድ መለኮታዊ መሰወር አለ፤ ጠፋባቸው።" ካለ በኋላ፥ ኢየሱስ ስለመሰወሩ በመናገሩና ያንን መሰወር 'መለኮታዊ መሰወር' በማለቱ (አምልጦት መሆን አለበት) በጋዜጠኛዋ ታዲያ መለኮታዊ ማንነቱን አያሳይ እንደሆነ ሲጠየቅ፥ "ይሰወራል የሚለው ቃል እኮ የመለኮት መለኪያ አይደለም ብዬ ነግሬሻለሁ። መሰወር የሚለው ቃል፥  ጠንቋይስ ይሰወር የለ እንዴ አንቺ? ምን፥ ከባድ ነው መሰወር? ተሰውረው ይሄዳሉ እኮ? ይበርራሉ በአየር ላይ።" ብሎ ነበር።  ኢየሱስ ምንም መለኮታዊነትን አለመግለጡን፥ እንዲያውም ከዓለማችን ጠንቋዮች የተለየ ሥራ አለመሥራቱን፥ ሰው ብቻ መሆኑን ለማረጋገጥ የተደረገ የተነወረና አሳፋሪ ሙከራ ነው። አሳፋሪ ያልኩት፥ 'መለኮታዊ መሰወር' ብሎ ተሳስቶ ከተናገረ በኋላ መልሶ የተፋውን መዋጥ በመገደዱ ነው። ስነ መለኮቱ ገና ተቀርጾ ያላለቀ ስለሆነ ይሆናል እያመለጠውና እየተሳሳተ ኋላ የሚያርመውን ነገር የሚናገረው። በዚሁ በመጨረሻ ወደተነሣው ወደ ታጃቢው ኢየሱስ እንለፍ። 

4/ ታጃቢው ኢየሱስ። ኢየሱስ በአጃቢዎች እየተከበበ ይመላለስ ነበር!” ፖዝ አንድ ስፍራ ላይ ሊናገር እንደሞከረው ይህ የመታጀብ ጉዳይ እርሱ ያስደረገው ሳይሆን ሌሎች ያደረጉት ነገር መሆኑን በአጭሩ ገልጦ አላስፈላጊ ዝባዝንኬነቱን ተናግሮ ሊያልፍ ሲችል እየሞገተ ትክክል መሆኑን መናገሩና ታጅቦ መሄዱን ለማጽደቅ ወይም ትክክል መሆኑን ለማሳየት ምሳሌ አድርጎ ኢየሱስን በመጥቀሱ ነው ልናገርበት የምፈልገው። በአጃቢ መሄዱን ሲገልጥና ትክክልነቱን ሲያስረግጥ፥  መጀመሪያ በጋርድ የሄድኩት እኔ ነኝ። ሁሉ ነገር ስፍራ አለው፤ እስታንዳርድ አለው፤ ደረጃ አለው፤ አሠራር አለው። . . . በጋርድ መሄድ ምንድነው ፐርፐዙ? ዓላማው ምንድነው? ደግሞስ ሲቀጥል፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይ? ጌታ ኢየሱስ ጋ ሰዎች ሕጻናት ልጆች ይዘው መጡ ይላል። ደቀ መዛሙርቱ ከለከሏቸው ይላል። ጌታ ኢየሱስ አትከልክሏቸው አለ ይላል። በሌላ አማርኛ ጌታ ኢየሱስጋ ማንም ሰው ከመድረሱ በፊት ደቀ መዛሙርቱ ይከለክሉ ነበር ማለት ነው። . . . ሉቃስ የሚለው ፊልም ላይ አይተሻል? ጅራፍ ይዞ ገርፎ አስወጣቸው፤ ከዚያ በኋላ ሰዎች ተበጣበጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ከለሉት። ፊልሙ ላይ ያየሁትን ነው ምነግርሽ። . . . ሪያሊቲው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፤”

ፖዝ ፊልምን እንደ ምስክር መጥቀሱ እጅግ በጣሙን ቢያሳፍርም (የትምህርቱ ምንጭ ፊልምና የቴሌቪዥን ሰባኪዎች ይሆኑ?) ስለ ፕሮቶኮልም ተናግሮአል። በስነ ሥርዓት እና የመስተንግዶ አገልግሎት ላይ ማንም ጥያቄ የሚያነሣ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። ነገር ግን ጋዜጠኛዋም በግልጽ ያነሣችው የአስተናጋጆችን አገልግሎት ሳይሆን የዘብ አጀብ (security detail) ተግባር ነው። ፖዝ ኢየሱስ ታጅቦ ይሄድ እንደነበር ዋና ማስረጃ አድርጎ ያቀረበው ሐዋርያቱ ሕጻናትን መከልከላቸውን ነው። ይህን ክፍል ሳያነብብ ሲጠቅስ ልክ እንደተጻፈ አስመስሎ ነው የተናገረው። 'ደቀ መዛሙርቱ ከለከሏቸው' ብሎ ነው የተናገረው። ይህ ያዘመሙ ዘመነኛ 'ሐዋርያት' ከቅዱስ ቃሉ ጋር ያላቸውን ግንኙነትና የአጠቃቀስ ዘይቤ የሚያሳየን እውነት ነው። ያልተጻፈ ቃል እንደተጻፈ ተደርጎ ሲነገር ቃሉን ያላነበቡ ተመልካቾች ወይም አድማጮችም እውነትም የተጻፈ ይመስላቸዋል። እዚህ ሐዋርያቱ የከለከሏቸው ሊመስላቸው ይችላል።  ይህ ታሪክ በሦስቱ ወንጌላት (ማቴ. 19 ማር. 10 እና ሉቃ 18) ተጽፎአል። ፖዝ የሚያስተዋውቀንን ኢየሱስ ማንነት ለማጨፍገግ ከመስመር ለመውጣት ደስተኛ ስለሚሆንና ቃሉን የራሱን ፍላጎት መፈጸሚያ ለማድረግ ከአሳቾች እንደ አንዱ ስለሚጠቅስ ነው ይህን ቃል መጥቀስ ያስፈለገኝ። በሦስቱም ወንጌላት እነዚህ ክፍሎች ሕጻናትን እንዲዳስሳቸው ወደ እርሱ ማምጣታቸውን፥ ሕጻናቱም ኢየሱስ ዘንድ መድረሳቸውን እንጂ ለማምጣት ከአጋፋሪዎች ጋር ግብግብ መግጠማቸውን አይናገሩም። ማቴዎስ፤ በዚያን ጊዜ እጁን እንዲጭንባቸውና እንዲጸልይ ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ገሠጹአቸው። ማርቆስ፤ እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ያመጡአቸውን ገሠጹአቸው። ሉቃስ፤ እንዲዳስሳቸውም ሕፃናትን ደግሞ ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም አይተው ገሠጹአቸው። በሦስቱም ወንጌላት ሕጻናቱ ወደ ኢየሱስ መጥተዋል። ወደ ኢየሱስ ደርሰዋል። ካመጡ በኋላ ነው ደቀ መዛሙርቱ ያመጧቸውን ሰዎች የገሠጹት እንጂ ሳያመጡ ከሩቅ አላገዷቸውም። ኢየሱስን እንደ ክብር ዘብ ሆነው አልከለሉትም። ቢሆንማ ኖሮ ያመጧቸው ተግሣጽ ለመቀበል ወይም ኢየሱስም ሕጻናቱን ለመባረክ ዕድሉ ባልኖረም ነበር። ዛሬ በአጃቢ የሚሄዱ ሐዋርያትና ነቢያት ተብዬዎች መኖራቸው አያስደንቅም።

መጀመሪያ በጋርድ የሄድኩት እኔ ነኝ፤ . . . በቢልቦርድ መጀመሪያ የወጣሁት እኔ ነኝ . . ." ማለቱ ለማንነቱ የሚሰጠውን ስፍራ ይገልጠዋል እንጂ ፖዝ የመጀመሪያው ታጃቢ አልነበረም፤ የመጨረሻውም አይሆንም። እነዚህ ሰዎች እኮ የሚኮርጁት ኢየሱስንና የመጀመሪያዎቹን ሐዋርያት ሳይሆን ርእሳነ ብሔሮችን፥ ቱባ የክልልና የግዛት ባለ ሥልጣናትንና የትልልቅ ኮርፖሬሽን ዲሬክተሮችን ነው። ይህ የሚያሳየን ከአለባበስ እስከ አኗኗር ድረስ ሞዴሎቻቸው ዓለማውያን መሆናቸውን፥ ከመደዴው ክርስቲያን ተርታ የወጡ ጥዩፎች መሆናቸውን ነው። በዚህ ዘመን የዓለምን መንግሥታትና ክብራቸው አይተው የወደቁና የሰገዱ 'ሐዋርያት' ተብዬዎች በዝተዋል። አሳጃቢዎችና አጃቢዎች እስካሉ ድረስ ታጃቢዎች ደግሞ ይኖራሉ። ለምጽፈው ነገር ማየት ስለኖረብኝ አንድ ሁለቱን ሐዋርያና ነቢይ የተባሉ ታጃቢ ሹሞች እየቀፈፈኝ አይቻለሁ። ሁለቱም ጅንኑዎችና ኩራታቸው አናታቸውን በርቅሶ የወጣ ይመስላሉ። አረማመዱንም ጭምር አስቀድሞ የተለማመዱት ይመስላሉ። ማየቱ ራሱ አሳፋሪ ነው። እነዚህን ትተን ወደ ኢየሱስና ወደ ደጎቹ ሐዋርያት እንመለስ። ኢየሱስ በአጋፋሪዎችና አንጋቾች የሚታጀብ ቢሆን ኖሮ ያቺ 12 ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች ደካማ ሴት ልብሱን ትዳስስ ነበር? ጌታ የዳሰሰው ማን እንደሆነ ሲጠይቅ ደቀ መዛሙርቱ የመለሱት መልስ፥ ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ፦ ማን ዳሰሰኝ ትላለህን ? ነበር። ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ! ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላው እንዲጋርዳቸው ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው ያኖሩ ነበር፤ የሐዋ ሥራ. 5 ጴጥሮስ በአንጋቾች አልታጀበም። ከጳውሎስ ከአካሉ ጨርቅ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፤ የሐዋ ሥራ. 19 'ከአካሉ' የሚለው ከለበሰው ልብስ፥ ከላዩ እየተቆረጠ መሆኑን የሚያሳይ አገላለጥ ነው። ከላዩ በካራ እየቆረጡ ሲወስዱ አጃቢ ከልካይ አልነበረም። እንኳን ሌላ እርሱም ራሱ የተከላከለ አይመስልም። አጃቢ፥ አጋፋሪ፥ ከልካይ፥ ተከላካይ የለም። ይህ ከተርታው ክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር እንደ ወንድሞች መደባለቃቸው ውበታቸውም ነበር።

ከላይ እንዳልኩት ይህ የአጀብ ግርግርና የትኩረት ጥማት እንጂ አስተምህሮታዊ ጉዳይ ስላልሆነ ትልቅ ችግር መሆን የለበትም። ሐዋርያ ፖዝ እና ዘበናይ ሐዋርያት በአጀብ ቢሄዱ፥ ግምጃ ይነጠፍልን፥ ሳር ይነስነስልን፥ ቄጠማ ይጎዝጎዝልን፥ ማንም አይንካን፥ ከላይ ፀሐይ፥ ከጎን የሰው ዓይን አይውጋን፤ ጋርዱን፥ ከልሉን፥ ክደኑን፥ ሸፍኑን ቢሉ አያስደንቅም። የሚያስደንቀው እና ይልቁንም የሚያሳፍረው ግን ኢየሱስንና የኢየሱስን ሐዋርያት የዚህ ስንፍናቸው ምስክር አድርገው ሲጠሩ ነው። ኢየሱስ ታጃቢ አልነበረም። የክርስቶስ ሐዋርያትም የኢየሱስ አጃቢዎች አልነበሩም። እንዲያውም በቀውጢዋ ሰዓት ጥለውት ነበር የሸሹት። ጌታ ብዙ ጭፍራ የመላእክት ሠራዊት እንዲከላከሉለት ማድረግ እየቻለም አላደረገም። ጌታ አማኑኤል ነበረ፤ እግዚአብሔር ከሰው ጋር። ጸጋና እውነትን ተመልቶ በሰዎች ያደረ ጌታ ነበረ። ኢየሱስ፥ 'ወደ እኔ ' ብሎ የጋበዘ ጋባዥ ነበረ። ሲል ብረት ለበስ ታጣቂዎች አቁሞ አልነበረም። ኢየሱስ ታጃቢ አልነበረም። 

መደምደሚያ። መሆንና ማድረግ። የሐዋርያ ፖዝ ስሕተት ዋና አደጋ ኢየሱስ ሰው ብቻ ሆኖ ስለተመላለሰ እርሱ የሆነውን እንሆናለን ወይም ያደረገውን እናደርጋለን የሚል ነው። የሆነውን መሆን እንደማንችል በግልጽ የታወቀ ነው። እኛ በእግዚአብሔር ጸጋና መንፈስ ዳግም ተወለድን እንጂ በባህርያችን ኃጢአተኞች ሆነን የተወለድን ሰዎች ብቻ ነን እንጂ መለኮት አይደለንም። ከመንፈስ ቅዱስ በውስጣችን መኖር የተነሣ የመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች ተደረግን እንጂ ምንም መለኮትነት የሌለብን ሌጣ ሰዎች ብቻ ነን፤ ያውም ኃጢአተኞች። እዚህ ላይ መስመር መሰመር አለበት። ኢየሱስ አምላክነቱን ሳይጥል ሰው እንደመሆኑ እኛ ሰውነታችንን ይዘን ወይም ጥለን መለኮት እንሆናለን ማለት የሐሰት ትምህርት ነው። ይህ ትምህርት ግን አዲስ አይደለም፤ ዛሬም በቃል-እምነት ትምህርቶች ዙሪያ የሚደመጥ ነው። በአገራችንም፥ 'መንፈስ ነን' ከሚሉቱ ጀምሮ፥ 'አንሞትም፥ እርሱ እንደሆነው ነን፥ እንዳደረገው እናደርጋለን' እስከሚሉቱ የሚታይ ስሕተትም ነው። ወደ ኢየሱስ ማንነት ስንመጣ ኢየሱስ በምድር ሲመላለስ እንደ ሰው ብቻ ተመላለሰ፤ ይቅርታ ያደረገው እኛም የምናደርገውን ነው፤ ተአምራቱም እኛም የምናደርጋቸው ናቸው . . . የምንል ከሆነ ሌሎቹንም በመለኮቱ ብቻ በምድር ያደረጋቸውን ነገሮች በመሆንና በማድረግ ልናሳይ ልንገደድ ነው። በመጀመሪያ ራሳችንን፥ 'አምላክ ነን' ብለን መቀበል አለብን። ጌታ ኢየሱስ አምላክ የሆነውን ማንነቱ አውልቆ አንድ ስፍራ ደብቆ አስቀምጦ በሰውነቱ ስብዕና ብቻ አልተመላለሰም። አማልክት ነን የሚል ትምህርት አዲስ አይደለም፤ ደግሞም የብዙ ሃይማኖቶች ትምህርትም ነው።

በክርስትናም ጥቂት ጥቅሶችን ከዐውዳቸው፥ ከአካላቸው ነቅለው ሰዎችን አማልክት ሊያደርጉ የሚያስተምሩ ሰዎች አሉ። ጌታ ግን በሚያገለግልበትና በሚያስተምርበት ጊዜ ማንነቱን አልደበቀም። አይሁድ ሲከስሱትና እንዲሰቀል ሲያደርጉት ሰው ብቻ መሆኑን ተናግሮ ከመሰቀል በተረፈም ነበር። አይሁድ ሊወግሩት የሞከሩት፥ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን የቀደደው ስር ነቀል ትምህርት ያስተማረ ሰው ብቻ ስለሆነ አይደለም። እንደ ኢየሱስ ነን ካልን አምልኮን ለመቀበል ሥልጣን አለን ማለት ነው፤ ኢየሱስ ይህን ከትንሣኤው በኋላ ብቻ ሳይሆን በፊትም ተቀብሎ ነበርና፤ ማቴ. 1432-33 ዕብ. 16 የዘላለም ሕይወትን ማደል ይቻለናል ማለት ነው፤ ዮሐ. 1027-28 በሥልጣናችን ኃጢአትን ማስተስረይ ይቻለናል፤ ማር. 25-11 የፈሰሰው ደም የፍጹም ሰው ብቻ ደም ነው ልንል ነው፤ ሐዋ. 2028 እንደ እግዚአብሔር ቃል ሥልጣን ያለው ቃል መናገር እንችላለን ማለት ነው፤ ማቴ. 52729 እንዲህ እያልን መዘርዘርና መቀጠል እንችላለን።  ፖዝ ከንግግሩ እንደምንረዳው እነዚህን ነገሮች መሆንና ማድረግ እንደሚችል ያስብ ይሆናል። ይቅርታ ማድረግን ኃጢአትን ከማስተስረይ ጋር አመሳቅሎ ማመሳሰል ራስን ወደ አምላክ ሥልጣንና ማንነት ማስጠጋት ነው። ተአምራት ማድረግስ? የሆነውን አለመሆናችን በብዙዎች በአክብሮት እንደሚታሰብ፥ የሚያደርገውን እናደርጋለን የሚለውን ግን ጠንቀቅ ብለን እንድናየው ያስፈልጋል። በጌታ ስም ተአምራት እንደሚደረጉ የታወቀ ነው። ግን ተአምራት ሁሉ ሲደረጉ በጌታ ብቻ እንደተደረጉ ካሰብን የማንወጣበት፥ ከወጣንም ተጋግጠን የምንወጣበት ወጥመድ ውስጥ እንገባለን።

ሰይጣንም ተአምራትን ሊሠራ ይችላል፤ የሚያምኑትን እንኳ እስኪያስት ድረስ መሥራት ይችላል። ዛሬ አፍ የሚያስከፍቱና የሚያስጨበጭቡ፥ ግን መንፈሳዊ ሕይወትን ከመሬት ግማሽ ክንድ እንኳ ከፍ የማያደርጉ ምልክቶች እየሰማንና ውሸታም ተአምራትን እያየን ነን። 'ጌታ በምድር ሲመላለስ ያደረጋቸውን ተአምራት እናደርጋለን፤ ማድረጋችንም እንደ እርሱ የመሆናችን አስተማማኝ ማረጋገጫ ነው' ከተባለና ምልክቶቹ ሁሉ ቢደረጉ ምልክቶቹ የዚያ ሰው ኢየሱስን በትክክል መምሰል ዋና አረጋጋጭ ሊሆን ነው ማለት ነው። ስሕተት! 'የተአምራቱ ምንጭ ማን ነው?' ነው ጥያቄው። ዛሬ እየሆነ ያለው ነገር ቤተ ክርስቲያን በተባለ ቦታ የሚደረጉ ድንቆች ሁሉ ወይም በኢየሱስ ስም የተደረጉ ነገሮች ሁሉ በጌታ የተደረጉ ተአምራት ናቸው ብሎ በየዋኅነት የመቀበል ስሕተት ነው። ይህ ተአምራትን ማፈንፈን በአሳቹ ጠላት ፉርጎ ውስጥ በጅምላ ለመነዳት መሳፈር ነው። ለመጋለብም ጀርባን መስጠት ነው። ተአምራት ሲደረጉ እንዲያው አፍ ከፍቶ በመደነቅ ፈንታ መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄዎች አሉ። ጥቂቶቹ፤ 1. ተአምራቱ ምን ፈየዱ? ውጤታቸው ምን ሆነ? የአያትህ ስም፥ ወይም ቀን የበላሽው ምሳ፥ ወይም ኪስህ ውስጥ ያለው ጫት፥ ወይም ፍሪጅሽ ውስጥ ያለው መድኃኒት መነገሩ ጥንቆላ እንጂ ተአምር አይደለም። ተአምራት የተፈጥሮ ሕጎች በገሃድ ሲጣሱ ነው።  ሰማይ ሲዘጋና ሲከፈት፥ ውኃ ወደ ወይን ሲቀየር፥ የሞተ ሲነሣ፥ ሁለት ዓሣና አምስት እንጀራ ወደ 15 ሺህ ሰው አጥግቦ ሲተርፍ ነው። የተፈጥሮ ሕግጋት ተለጉመው ተይዘው እግዚአብሔር የከበረበትና የሰዎች ሕይወት የተሠራበት ተአምር ተደረገ ወይስ የምልክቶች ርችት ተተኮሰ?  2. ተአምራቱን አድራጊው ሰው ትምህርቱና ሕይወቱ ክርስቶስን ይመስላል? ክርስቶስ ምን ይመስል ነበር? ጌታ ምን ይመስል እንደነበር አራቱ ወንጌላት ይናገራሉ።

ደግሞስ፥ ኑሮአቸውና ምስክርነታቸው የቀደሙትን ሐዋርያት ይመስል ነበር? የቀደሙት ሐዋርያት ትምህርትና ኑሮ ምን ይመስል እንደነበር ከሐዋርያት ሥራና ከመልእክቶቻቸው እናነብባለን። ያንን የማይመስል ከሆነ የክርስቶስ ሳይሆኑ የራሳቸው ሰዎች የመሆናቸው ዋና አመልካች ነው። እንግዲህ ተአምራት በሚደረጉባቸው ቦታዎችና ጊዜዎች ከሆንን ከተአምራቱ ይበልጥ ማየት ያለብን ሰዎቹ ናቸው። ሰዎቹ በኑሮና በሕይወት ያልተገለጡና ምስጢራውያን ከሆኑ፥ ትምህርታቸው የደፈረሰና ያልጠራ ከሆነ ልንጠረጥር ይገባናል። 3. ምልክቶችን ሁሉ ከእግዚአብሔር ናቸው ብለን መቀበል ስሕተት ነው። ሰይጣንም ምልክቶችን ሊያደርግ እንደሚችል መታወቅ ሊቅነትን የሚጠይቅ ጉዳይ መሆን የለበትም። ማቴ. 722-23 በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። ይላል። በዚህ የምናየው በስሙ ትንቢት የተናገሩ፥ አጋንንት ያወጡ፥ ተአምራት ያደረጉ፥ ተአምራት ብቻ ሳይሆን ብዙ ተአምራት ያደረጉ፥ ግን ከቶ ያልታወቁ የነበሩ ሰዎችን ነው።

ልብ እንበል፤ እነዚህ ነገሮች የተደረጉት በጌታ ስም ነው። ነገሮቹ በእርግጥ ተደርገዋል። በሰይጣን ሳይሆን በጌታ ነው የተደረጉት። ነገሮቹ የተደረጉት ከአድራጊዎቹ ማንነት የተነሣ ሳይሆን፥ እነርሱ ማንም ካለመሆናቸውና ከጌታ ማን መሆን የተነሣ ነው። እነዚህን ከላይ የጠቀስኳቸውን ሦስት ነጥቦች እንደ መደምደሚያ ላነሣ የወደድኩት ጌታ የሆነውን ሆኖና ያደረገውን አድርጎ ማንነትን ማሳየት የጠቅላላው ጽሑፍ ዘለላ አሳብ ስለሆነ ነው። ዛሬ ክርስቲያኖች ምልክታሞች፥ ምልክት አፈንፋኞች እንዲሆኑ ዘመቻ እየተደረገ ያለ ይመስላል። ምክንያቱም ስለ ክርስቶስ ማንነት ከሚያውቁት ይልቅ የሚደረጉት ትዕይንቶች የሚሰበስቡት አፍ ከፋች አድናቂ ሕዝብ ቁጥር እጅግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስና መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮቶች የከበረ ስፍራ በሰው ሠራሽና በአጋንንታዊ ትምህርቶች እንዳይለወጡ ትጉሃን የቃሉ ተማሪዎች ልንሆን ይገባናል። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፤ ማቴ. 1239 መፍቀሬ ምልክት ወድንቅ ወተአምራት ከመሆን እግዚአብሔር ይጠብቀን። እግዚአብሔር ከስሕተት ትምህርቶችና አስተማሪዎች፥ ከአጋንንታዊ አሠራሮች፥ ከአሳች ትምህርት ዐውሎ ነፋሶች እና ከክፉ ሠራተኞች ይጠብቀን። አሜን።