ቢመሳሰሉም አንድ አይደሉም

YonasJB

ሙዚቃ እውን ገለልተኛ ነው? ሙዚቃ እንደ አዳማጩ ነው? ዘፈንና መዝሙር ልዩነቱ በቃል ላይ ነው? አማንያን በደጃቸው ሲያልፉ መደብሮች የሚያባርቁትን ሙዚቃ ዝቅ ያድርጉ? በሬጌ ምት የሚዘመሩ መዝሙሮች የቦብ ማርሊን ጠጉር ሥራና የጋንጃ ዕጣን ሱስ እንዳያስይዙ በቤተክርስቲያን ይወገዙ? ሄቦላላ ዝላይ ከአምልኮ ስለሚያዘናጋ በኤም ሲ ሃመር ትዊስትና በጄምስ ብራውን ሸፍል ይተካ?

ወንድም ዮናስ በዩቱብ እና በፌስቡክ በለቀቃቸው አስተያየቶቹ ጠንከር ያለ ትችትና ተቃውሞ ገጥሞታል። ከ500 ዓመት በፊት ሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን እንዳነዋወጠው ጀርመናዊ ሉተር አሻፈረኝ በማለት የተሓድሶ ጥሪ እያሰማ ነው። “[ ]… የሃገሬ የወንጌል አማንያን በትውፊት ያዳበሩትን ይህን እምነት ዝም ብዬ ልቀበል የምችለው [እንዴት ነው]? እንዴት ነው ሙዚቀኛ ስለሆንክ የዘለዓለም እሳት ውስጥ ትገባለህ ብሎ የሚያስተምርን እምነትና አስተሳሰብ ችላ ልል የምችለው? እንዴት ለእኔ ዮናስ ጎርፌ ፕሮፌሽናል ሙዚቀኛ ከዚህ የበለጠ አንገብጋቢ ጉዳይ ሊኖር የሚችለው? እንዴት ነው ጧትና ማታ በዚህ ሃሳብ ሲብሰለሰሉ የሚውሉ ወጣት ሙዚቀኞች ጭንቀታቸውንና ትግላቸውን እያየሁ በዝምታ የአዋቂ አጥፊ የምሆነው? እንዴት ነው በዚህ ፍጹም በተወላገደ አስተሳሰብና አስተምህሮት ልጅ ከወላጆቹ ተቆራርጦ ሲንገላታ እያየሁ ዝም የምለው? እንዴት ነው በዚህ የማይረባ ትውፊት አስተሳሰባችን ተመርዞ ልጆች ከቤተ ክርስቲያን እንትን እንደነካው እንጨት ተገፍተው ሲጣሉ እያየሁ ዝም የምለው? ንገረኝ ወዳጄ.....ንገረኝ!! ህሊናህን ክደህ ቁም ነው የምትልኝ? አንተ ማድረግ ከቻልክ ይሁንልህ............እኔ ግን የመሸበት አድራለሁ እንጂ አላደርገውም!!! በጭራሽ!!! ሉተርም ያለው ይሄንኑ ነው ‘…ኅሊናን ተቃርኖ መሄድ ልክ አይደለም፣ ጤነኛነትም አይደለም። እነሆ በፊታችሁ ቆሜአለሁ ከዚህ ሌላ ምንም ማድረግ አልችልም…’” [ሜይ 19፡9፡33 ዮናስ ጎርፌ ፌስቡክ]።

1/ የክርክሩን አካሄድ መልክ እናስይዝ፦ “እውነት” ብለው ያነገቡትን ወይም የተቀበሉትን መጠየቅ የተጀመረው ዛሬ አይደለም፤ በአገራችን ብቻ አይደለም፤ በቤተክርስቲያን ብቻ አይደለም። አንዳንዱ አስተምህሮ ሲወገዝ ቆይቶ ኋላ መገበያያ ሆኗል። የክርስትናን አጀማመር እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። አስተምህሮ፣ ያለ ቦታው፣ ያለ ወቅቱና የአዳማጩን አቅም ሳይመጥን ሲቀር ውዥንብር ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ፣ በልሣን መጸለይ፤ የጌታ ምጽዓት “ፕሮግራሞች”፤ “ሐዋርያት”፤ ማለቂያ የለውም። ጀርመናዊው ሉተር “ዓለማዊ” ዜማዎችን ለወንጌል ማስተላለፊያ ተጠቅሟል። በአንጻሩ፣ የኢትዮጵያ “ዘመናዊ” ዘፈኖች ከያሬዳዊ ተጽዕኖ ነጻ ወጥተው አያውቁም። ዓለማዊ ባህል እንዳለ ሁሉ ክርስቲያናዊ ባህልም አለ። አንዱ በሌላው ላይ ተጽእኖ ያደርጋል።

2/ ወንድም ዮናስ “ፕሮፌሽናል ሙዚቀኛ” እንደ መሆኑ፣ ብዙዎቻችን “ፕሮፌሽናል” ምላሽ መስጠት አንችልም፤ ያ ማለት መልስ አንሰጥም ማለት አይደለም። ሁለተኛ፣ በ ‘መንፈሳዊ’ እና ‘ዓለማዊ’፣ በ ‘ነፍሳዊ’ እና ‘ሥጋዊ’፣ በ ‘መንፈሳዊ ክርስቲያን’ እና ‘ሥጋዊ ክርስቲያን’ ላይ የተቀራረበ መረዳት ከሌለ መግባባት አንችልም። በአገራችን፣ ‘ለነፍሱ ያደረ’ እና ‘ለሥጋው ያደረ’ የተቃረኑ ግንዛቤዎች ናቸው፤ ከሁለቱ ግንዛቤዎች የሚመረጠው ለነፍስ ማደር ነው። ሦስተኛ፣ ሙዚቃ የድምጽ ብቻ ቅንብር ነው ወይስ የሚያስተላልፈው መልእክት እና የሚያነሳሳው ስሜት አለ? እውን ሙዚቃ ከሞራላዊ ሚዛን የጸዳ ነው? አራተኛ፣ ባህል የጫነብን፣ በወንጌል ብርሃንና በአእምሮ ብስለት ያልተገራ አመለካከት ብዙ አለ፤ ብዙዎቻችን “መንፈሳዊነትን” ስናነሳ አእምሮን እንደሚጨምር ዘንግተን ነው። አምስተኛ፣ ሙዚቃውና ቃላቱ ያልተጠበቀ ተቃራኒ እይታ ሊያስከትሉ ይችላሉ። የሶፊያ ሽባባው “ዘራፍ ለጌታ” ምን ዓይነት መንፈሳዊ ወኔ እንዲቀሰቅስ ታስቦ ነው? ሰንደቅ ዓላማ፣ የተጫነ በቅሎና ጎራዴ ከሰላም ወንጌል ጋር ምን ዓይነት አካሄድ ይኖረዋል? [ማቴ 26፡52፤ ዮሐንስ 18፡11]። የዘሪቱ “ሰይፍህን አንሳ” በ “ዘራፍ ለጌታ” ላይ ምን ተጽዕኖ አድርጓል? ሰይፉ “መንፈሳዊ” ምስል እንደሆነ አንዘነጋም፤ መንፈሳዊ ሰይፍ ግን በዐይን አይታይም። የምስልን ተጽዕኖ ካለመረዳት ወንጌልን ጂሃዳዊ ገጽታ አቀብለነው ይሆን? በመጨረሻ፣ እውነቱንና እውነት መሳዩን የምንለየው እንዴትና በምንድነው?

ከመጨረሻው ነጥብ እንጀምር። የክርስቶስ ተከታዮች እውነቱንና እውነት መሳዩን የሚለዩት ውስጣቸው ባደረው በመንፈስ ቅዱስ ነው። ከቅዱሱ መንፈስ የተነሳ አሁን ቅዱሳን ናቸው። የተቀደሰ ይቀድሳል ማለት ምን ማለት ነው? መንፈስ ቅዱስ የእውነት መንፈስ ሆኖ “ወደ እውነት ሁሉ” ይመራል። ሐዋርያቱ ካስተማሩት ከኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ጋር የሚስማማ ሁሉ እውነት ነው፤ ከኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ጋር የማይስማማ ሁሉ እውነት አይደለም። ታዲያ፣ እውነትም ውሸትም ያልሆነ ግራጫ የለም ወይ እንል ይሆናል። ግራጫ አለ እንጂ፤ በእርግጠኝነት የማናውቃቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፤ አለማወቃችን ግን እውነትና እውነት ያልሆኑ ተለይተው አይታወቁም ማለት አይደለም። “ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ [1 ቆሮ 13:12]።” እርስ በርስ ትዕግስትና ትሕትና እንዲኖረን የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። “ወደ እውነት ሁሉ” ሲል ሙዚቃን ይጨምራል። የምርምርና የዕውቀት ማዕከላትን ይጨምራል። ባጭሩ፣ ኢየሱስን ሳያገናዝብ ወደ እውነተኛ እውነት መጥለቅ አይቻልም።

“ፕሮፌሽናል” መሆን ጠቃሚ ነው። የክርስቶስን መንፈስ ለተቀበሉ እውነቱን ለይቶ ለማወቅ ግን “ፕሮፌሽናል” መሆን አይኖርባቸውም። በሌላ አነጋገር፣ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት የአገራችን ባላገር የጀርመኖችን ክላሲካል ሙዚቃ ምንነት ባይረዳም በመንፈሱ “ይኸ ፍሬ ቢስ ነው፤ አይጠቅምም” ወይም “ይኸ በጀርመን ቃልቻ መንፈስ የተደለቀ ነው” ሊል ይችላል። እርግጥ፣ የሁላችንም የመረዳትና በጌታ የመጠንከር አቅማችን አንድ ነው ማለት አይደለም። እያንዳንዱ በደረሰበት ይመላለስ ያለው ለዚህ ነው። “እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር” [ፊልጵስዩስ 2:3]። ኅሊናው ደካማ የሆነው በአንተ መረዳት እንዳይሰናከል መብትህን ወደ ጎን አድርገህ በፍቅር ተመላለስ ያለው ለዚህ ነው [ሮሜ 14፡ 15፣ 20-21]።

ያልወገነ መደዳ ሐተታ እነሆ፦ በጌታ ሆኖ ጌታ በሠራው ቤት ቤተኛ አለመሆን አይቻልም። አማኙ ቤቱ ነው፤ ራስና አዳኙ የቤቱ ባለቤት ነው። ችግር አይገጥምም ማለት አይደለም። የማስገባትና የማስወጣቱ ሥልጣን ግን ለሰው አልተሰጠም። ለሙግት ሲሉ ሙግት የሚያስነሱ አሉ፤ በአሳብ ዙሪያ ከመነጋገር ይልቅ በመርታትና በመረታት ያመኻኛሉ። አንዱ የተናገረውን በሌላ መልኩ ይደግማሉ። የትም የማያደርስ ውይይትና ሙግት ይወዳሉ፤ ከእነዚህም አንዳንዶች “ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉት” ናቸው። ጎራ ለይቶ መፋለም ኢትዮጵያውያን የምንወደው ስፖርት ነው። እልባት ባያገኝም ተፋልመን በሌላ ዘመን እያነሳን፤ እከሌ፣ ያኔ እንዲህ ሲል የነበረው አይደል? እያልን ጊዜ እናባክናለን። ወዳጅን ደግፈን ባላጋራን አዋርደን ወዳጅነትን እናጠናክራለን። ሌላውን በዕውቀታችን መውገርና አድናቆት ማትረፍ ስውር ፍለጋችን ነው። ስለ በደል መሟገት መልካም ነው፤ ስለ በደል ሁሉ አለመሟገት ግን ግብዝነት ነው። አማንያን ለዓለም ማቀንቀናቸውን የነቀፉ አንዳንዶች፣ ዓለማዊነትን በቤተክርስቲያን ውስጥ እያዩ ምንም ያላሉ ናቸው። ነገሮች የተያያዙ ናቸው፤ ሥራ አጥነት፣ ሐሺሽ፣ የተዛባ ቲዮሎጂ፣ ብልሹ አስተዳደር፣ ስደተኛነት፣ ጎሠኛነት፣ ወዘተ። አንዱ ችግራችን ሊነጣጠሉ ያልተገባቸውን መነጣጠላችን ነው።

ሙዚቃስ ከሞራል ሚዛን የጸዳ ነው? የጸዳ ነው የሚሉ አሉ። ለመሆኑ፣ ሚዛኑ በተዛባ ዓለም ገለልተኛ መሆን እንዴት ይቻላል? ነገር ሲጋጋል ሁሉም የራሱን ዳኝነት ሚዛናዊ ነው ለማሰኘት ይሯሯጣል፤ እውነቱ ያለው እኔ ጋ ነው ይላል፤ በአድራጎቱ ሌላውን ይኮንናል። ሰውና ባህል የነካው ግን አሻራ ሳይጥል አይቀርም። ፖለቲካ ውስጥ አንገባም በማለታቸው ከፖለቲካ ነጻ እንደሆኑ እንደሚያስቡት ዓይነት መሆኑ ነው። “ነፍስ የሌለበት ነገር እንኳ ዋሽንትም ክራርም ቢሆን ድምፅ ሲሰጥ የድምፁን ልዩነት ባይገልጥ በዋሽንት የሚነፋው ወይስ በክራር የሚመታው መዝሙር እንዴት ይታወቃል? ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? 1 ቆሮንቶስ 14:7-8።” ድምጽ [በዚህ መሠረት ልሣን] ትርጕም ሊሰጥ ይገባል። ክራር ለመዝሙር፤ መለከት ለክተት አዋጅ። ከበሮ ሲደልቅ መናፍስትን ለመጥራት ወይም ደስታን ለመግለጥ ሊውል ይችላል። ሙዚቃ በጓንታናሞ እስረኞች ላይ ሲያባርቅ የስብዕናቸውን አጥር ለመስበር አልሞ ነው ፤ ዋሽንት ነፊው ናፍቆትን ሲጠራ ቃል ሳይወጣው ነው። ከአውሮጳ ክላሲካል ሙዚቀኞች መሓል ከግብጽና ከኖርዲክ አማልክት፣ ከሂንዱ፣ ከፍሪሜሰንስ እና ከናዚ ዘረኛ ፀረ-ክርስትና ምሥጢራት ጋር የተነካኩ እንዳሉባቸው አንርሳ። በምን መንፈስ ምን አሉ? ብሎ መጠየቅ ግድ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ “የጽዮን ቈነጃጅት ኰርተዋልና፥ አንገታቸውንም እያሰገጉ በዓይናቸውም እያጣቀሱ፥ ፈንጠርም እያሉ፥ በእግራቸውም እያቃጨሉ ይሄዳሉና” ይላል [3፡16]። ቃል ሳይወጣ ብዙ ንግግር አለ። በጎ አምላካዊ ንግግር ደግሞ አለ። ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች። ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም። ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ [መዝ19፡1-4]።

ሙዚቃ መሠረቱ ዐይን ከሚያየው ያለፈ “አምልኮአዊ/መንፈሳዊ” ገጽታ እንዳለው ባንዘነጋ። ሰው በሙዚቃ ተገን የመጠቁ መገኘቶችን ወይም አብሮነቱን ይቀሰቅሳል። ሰው ከአምልኮ መጽዳት አይቻለውም። ባዕድ አምልኮ አለ፤ አምልኮተ ፈጣሪ አለ፤ የፍጡር አምልኮም አለ። ከአስራ ስምንተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ ምዕራባዊ አስተሳሰብ የአምላክን ሥፍራ ለሰው ሰጠ፣ ሰው ራሱን አምላክ ነው አሰኘ። ሰውን ያማከለ ሰላምና ወሰን የለሽ የእውቀት አድማስ ዘረጋ። የድንቊርናን ደጅ ለመክፈት ቁልፉ ሳይንሳዊ እውቀት ብቻ ነው አለ። እምነትን ከሳይንስ እውቀት ነጠለ። ሙዚቃ፣ ሊተራቱር፣ ኪነጥበብ ለነፍስ ጨለማ ብርሃን ነው አለ። ሰው መነሻውና መድረሻው ምድራዊ ነው አለ። የሳይንስ ግኝት በገነነ መጠን ምጡቅ አምልኮአዊነት ጠውልጎ ይደርቃል፤ ሰውም ከጨቅላነት ተላቅቆ ትልቅና ሁሉን ቻይ ወደ መሆን ይሻገራል። ጦርነት ይሻራል። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት [በፈረንጅ 1914-18] “ጦርነትን ሁሉ የሚሽር ጦርነት” ተብሎ እንደ ነበር አንርሳ። የሰው ልጅ የራሱንና የአካባቢውን ተፈጥሮ ወደ ፈቀደው የመምራት እውቀት ይቀዳጃል አለ። ይህ አስተሳሰብ በፍልስፍና በፖለቲካ፣ በኪነ ጥበባት ዘርፎች ተሠራጨ። ዮናስ መነሻ ያደረገው የአውሮጳዉያን አስተምህሮ፣ የአንባቢውም ተሞክሮ ነው ማለት አይደለም። ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ይዋሃዳል ማለትም አይደለም። በሌላ በኩል፣ ዮናስ ያሠለጠናቸው አንዳንዶች ምሩቃን በዓለማዊ ተግባር መሠማራታቸውን ያማረሩ አሉ። ወቀሳው ተገቢ አይደለም። ለጎዳና ተዳዳሪ አንድ ብር ብሰጥ፤ ሄዶ ሲጃራ ቢያቦንበት ጥፋተኛ ልባል ነው? ነፍስ ያወቀ ሁሉ ለራሱ መወሰን ይኖርበታል፤ ተጠያቂው ግለሰቡ እንጂ በሌላ መሳበብ የለበትም።

በዙሪያችን የምናየውን መካድ፣ አንገታችንን አሸዋ ውስጥ ቀብረን እንደ መተንፈስ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ክርክር ለሁሉም ወጥ የሆነ ደንብ መደንገግ ቀላል አይሆንም። ዘፈን በጆሮዬ አይግባ ማለት የምንገኝበትን ዓለም እውነታ መካድ ነው። በአፍ አለማንጎራጎር በልብ ማንጎራጎርን ሊያስቀር አይችልም። ጣዕመ ዜማ አለ። መካድ አንችልም። ውብ ቅኔ አለ። የከበደ ሚካኤል ቅኔ፤ የጸጋዬ ገብረመድኅን፤ ወዘተ፤ “አሜን፣ ሃሌሉያ” ካላሰኘ ውድቅ ነው እንዳንል እንጠንቀቅ። እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ ስለ ፈጠረው ብቻ እርሱነቱ፣ የእውነት የውበትና የበጎነት ሽርፍራፊ፣ በሰው ባህልና እንቅስቃሴ ውስጥ አይከሰትም ማለት አይደለም።

ወንጌላውያን የሆንን የተቀበልነውን እውነት ተግተን ስላላሰብንበት ስናፋልስ እንዳንገኝ። ስለ ፍትኅ ስናወራ ለይተን ነው። የተረዳነውን እውነት በ “መንፈሳዊ” አልባሳት ሥር መሸሸግ አውቀንበታል። ስሕተትን ስንቃወም ወዳጅ እንዳያሳጣን መርጠን ነው። የማንፈጽመውን ህግ ለሌላው እንደነግጋለን። ሹም ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ማግኘት ቸግሯል። በመንፈስና በአእምሮ አብሮ የማደግን አስፈላጊነት መዘንጋት ትልቁ ስሕተት ነው [ኤፌሶን 4: 13፣ 23፤ 1:8]። በኢትዮፕያንቸርች የተለያዩ አስተያየቶች ይደርሱናል። ካስገረመን አንዱ አንባቢ፣ “ጌታ ይባርካችሁ፤ ትልቅ ሥራ እየሠራችሁ ነው” ካለን በኋላ፣ በሳምንቱ ያው ሰው [ሌላ ጽሑፍ አንብቦ ይመስላል] “አሁን እናንተ ክርስቲያን ነን ትላላችሁ?” ብሎ ወርዶብናል። ያልተስማማው ጽሑፍ የትኛው እንደሆነና ምላሽ እንዲጽፍ ብናሳስበውም ፈቃደኛ አልሆነም። ስለሚያስተምሩት ትምህርት ምላሽ እንዲሰጡ መጠየቃቸው አንዳንዶችን አስተማሪዎች ጭራሽ ያበሳጫቸዋል። “ቤት ያጣው ቤተኛ” የሚጠቅመውን ወስዶ ለመማማር የሚፈቅድ ልቡናን ከሁላችን ይጠይቃል ማለት ነው።

3/ እስካሁን ባነሳናቸው ጉዳዮች ላይ እስቲ የእግዚአብሔርን ቃል እናብራባቸው፦

ዓለምና ሞላዋ የእኔ ነው ይላል እግዚአብሔር [መዝሙር 50:12]። ምድርና ሞላዋ ለእግዚአብሔር ናት፤ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ሁሉ [መዝሙር 24:1]። ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ [ማርቆስ 16:15]። ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ፣ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም [ዮሐ 17:15]። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም [ዮሐ 17:16]። ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአል [ቆላስይስ 3:3]። ሁሉ የእናንተ ነው፥ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው [1 ቆሮ 3:23]፤ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ [1ቆሮ 12:27]።

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ [1ቆሮ 3:16-17]። መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤ [1ቆሮ 6፡13]። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ … እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። … ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ እንደ ሰው ሥርዓትና ትምህርት። አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ ለሚሉት ትእዛዛት በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ትገዛላችሁ? እነዚህ ሁሉ በመደረግ ሊጠፉ ተወስነዋልና [ቆላስይስ 2:8, 16-17, 21-22]።

ነፍስን ከሚዋጋ ከሥጋዊ ምኞት ራቁ… [1 ጴጥሮስ 2፡11]። መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ [ኤፌ 5:18-20]። እኔ ሕያው ነኝ፣ ይላል ጌታ፤ ጉልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካ፥ መላስም ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግናል ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን። የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና ... እንደዚህ አድርጎ ለክርስቶስ የሚገዛ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኛልና፣ በሰውም ዘንድ የተመሰገነ ነው። እንግዲያስ ሰላም የሚቆምበትን እርስ በርሳችንም የምንታነጽበትን እንከተል [ሮሜ 14፡11-12፣ 18-19]። 

በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ ሁሉ ግን አይጠቅምም። ሁሉ ተፈቅዶልኛል፥ በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም። መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤ እግዚአብሔርም ጌታንም አስነሣ እኛንም በኃይሉ ያስነሣናል። ሥጋችሁ የክርስቶስ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ የጋለሞታ ብልቶች ላድርጋቸውን? አይገባም። ወይስ ከጋለሞታ ጋር የሚተባበር አንድ ሥጋ እንዲሆን አታውቁምን? ሁለቱ አንድ ሥጋ ይሆናሉ ተብሎአልና። ከጌታ ጋር የሚተባበር ግን አንድ መንፈስ ነው። ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል። ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ [1ቆሮ 6:11-20]። በቀረውስ፣ ወንድሞች ሆይ፣ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ [ፊልጵስዩስ 4፡8]

4/ ደግሞ እንጠይቅ። ይኸ የምንሰማው፣ የምናየውና የምናነበው ያንጻል? ወደ ክርስቶስ ያጠጋጋል? ለበጎ ሥራ ሁሉ ያዘጋጃል? ለመንፈስ ቅዱስ ይመቻል? የመንፈስ ቅዱስ ደስታ አለበት? ከቅዱሳን ጋር ህብረት ለማድረግ ይጠቅማል? ለጌታ ስም ክብርን ያመጣል? ከዓለማዊነት ይለያል? የመንፈስን ወይስ የሥጋን ፈቃድ ያነሳሳል? ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን ያወድሳል? ወደ ጸሎት ይመራል? ከጌታ ቃል ጋር ይጻረራል ወይስ ይስማማል? እያንዳንዱ በግሉ የሚመልሰው ነው፤ በቅዱሳን ማኅበር የሚመክርበት ነው። ጌታ በመረጠው መንገድ ሲያስተምረው ለመስማትና ለመታዘዝ መፍቀድ የያንዳንዱ ፈንታ ነው። እግዚአብሔር መንገዱን የሚገልጠው ለመታዘዝ ለቆረጡ ነው።

መደምደሚያ

ቤተክርስቲያን የተጋረጡባት ዋነኛ ጉዳዮች ምንድናቸው? አንዳንዶቻችን ስንጠይቅና ስናጠያይቅ የኖርነው ጥያቄ ነው። ሰኔ 2007 የተሐድሶ ጥሪ በሚል የተዘጋጀ ሰነድ ቤተክርስቲያን የተጋረጠባትን በሦስት መልክ 1/ የሕይወት ጥራት 2/ የአስተምህሮ ጥራት እና 3/ የአመራር ጥራት ብሎ አስፍሮታል። አገራችን የተጋረጡባት ጉዳዮችስ? የአገር መሪዎች ለሙስናና ለብልሹ አስተዳደር መፍትሔ እንዳጡለት እየነገሩንና እያየን ነው። በዚህ ረገድ የቤተክርስቲያን [የአማንያን] ተሳትፎ ምን ሊሆን ይገባል? ጥቂቶች [በቤተክርስቲያን ውስጥ ጭምር] ከደሃው አፍ እየነጠቁ ሲንደላቀቁ፣ ልጆቻቸው ሲቀማጠሉ ብዙኃኑ መውጫ በሌለው የድህነት አዙሪት መያዙ ምንም አይደለም? እግዚአብሔር ያደለው ስለሆነ ነው? “ትንቢት” እስኪፈጸም ነው? አገራችን በሰማይ ስለሆነ ለሚጠፋ ምድር መጨነቅ ስለማያሻ ነው? የፖለቲካ እድፍ እንዳይነካን ከዳር ቆሞ መጸለይ ስለሚሻል ነው? “ፖዘቲቭ” መሆን ስለሚቀል ነው? ጥሪአችን ነፍሳትን ወደ መንግሥተ ሰማይ ማግባት ስለሆነ፣ ወፎችን የሚመግብ አምላክ ለደሃው ያስብላቸው እንበል? ወደ እነዚህ ጉዳዮች እንሻገር።                            

 ምትኩ አዲሱ

photo credit: Yonas Gorfe, Book Signing [May 5, 2016]; James Brown, NPR.ORG [April 2016]