መጠይግምገማ

“እንዴትክሌታው አሰብከው?”

የዚህ ጽሑፍ መነሻ ኢትዮቱብ ያስተላለፈው የ “ከአሜን ባሻገር” ምረቃ ነው። በዕውቀቱ ሥዩምን ያነጋገረው የቪኦኤው ጋዜጠኛ አሉላ ከበደ ነው። የአሉላ አቀራረብ ጥሩ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ደራሲያንና መሪዎችም እንዲሁ ቢያደርግ በአሳብ ዙሪያ መነጋገርና አንባቢነትን ለማዳበር ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።  

መጽሐፍን በሽፋኑ አትዳኝ ቢልም፣ ያለ ዓላማና ያለ ትርጕም አይደለምና፣ ከሽፋኑ እንጀምር። ሽፋኑ ላይ ብስክሌታ ጉብ ብሎበታል። “ር” ፊደል የባንዲራችንን ከረባት አንጠልጥላለች።

ብስክሌታጥያቄ፣ “እንዴት ብስክሌታውን አሰብከው?” መልስ፣ [የታሪክን] ሂደት በተሻለ መንገድ የሚገልጽ ሆኖ ስላገኘሁት።

እኛም እንጠይቅ፦ ኮርቻው ለምን ተቀማጭ የለውም? ታሪክ የሚንቀሳቀሰው በራሱ ተነሳሽነት ነው ለማለት ነው? የጎማዎቹስ ዐይኖች ለምን በሳንቲም ተለበጡ? ከደርግ የወረስነው አንበሳ ቁጣው እስከ ዛሬ እንዴት አልበረደም?

በዕውቀቱ የምኒልክን ሳንቲም ከኋላ ጎማ ላይ አድርጎት እንደ ነበርና፣ የሚመራን ያለፈ ታሪካችን መሆኑን ስገነዘብ  ወደ ፊተኛው አዛወርኩት ብሎናል። ሳንቲሞቹን እስቲ እንመርምር። ከቁጡው አንበሳ [2002 ዓ.ም.] ጀርባ ፍትኅ እና “አንድ ብር” ተሸሽጓል፤ ‘ከፍትኅ?’ ‘ከገንዘብ?’ የቱን መርጠናል? ከምኒልክ [1889 ዓ.ም.] ጀርባ፦ “ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ፤ አንድ ብር” ይላል። ዘውድ የደፋ አንበሳ መስቀልና ባንዲራ አንግቧል። “የይሁዳ አንበሳ” [ኢየሱስ ክርስቶስ] እውን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበር? አንበሳውስ እንዴት በሦስት እግር መቆም ቻለ?

ሳንቲሞቹ በጀርባቸው ያዘሉትን ጉድ ማወቃችን አረፋ እየደፈቀ በጭፍን ለሚጋልብ አመለካከት ምን እርምት ይሰጥ ይሆን? ለመሆኑ ለምን ሳንቲም ተመረጠ?

ደግሞ ስለ አዲሱ ትውልድ እናውራ። [አዲስ ስንል ለንግግር እንዲያመች እንጂ የትውልድ አሮጌ የለውም፤ ሁሉም በዘመኑ አዲስ ነው። ሦስትና አራት ትውልድ አንድነት መጓዙ፤ በትዝታዎቹና በቅርሶቹ መያያዙ ሂደቱ ነው።] ይህን ስንል፣ ትውልድን የለያየ “የታሪክ አጋጣሚ” የለም ማለት አይደለም። የለያየው አንደኛው፣ በሥፍራና በጊዜ ሳንቲም2ያልተገደበ የቴክኖሎጂ ግኝት ነው። ሁለተኛው የንግድ ቅልጥፍና  ነው[በዕውቀቱ ለምሳሌ፣ “ስድሳ፣ ሰባ መጽሐፍ ገዝታችሁ ለጓደኞቻችሁ ስጡ” ሲለን]። የብስክሌታው ዐይኖች ስለ ንግድ ምን ፍንጭ ይጠቁሙናል? የይስማእከ ወርቁ “ዴርቶጋዳ” ከ200ሺህ ቅጅ በላይ በመሸጥ በአገራችን ህትመት ሪኮርድ አስመዝግቧል። ይስማእከ ዛሬ የራሱ ማተሚያ ቤትአለው። ፈር ቀዳጅና ደፋር ትውልድ ራሱ ብድግ ብሎ ፈቃዱን ይፈጽማል እንጂ  እስኪደረግለት አይጠብቅም። ይኸ አንድ ተስፋ ነው። እንደ ዳኛቸው ወርቁ [1986 ሞተ]  “አደፍርስ”ን[1970 ታተመ] በቮክስዋገን ጭኖ በየማዕዘኑ ተገትሮ ገዥ ማፋለግ ቀረ። ተነባቢ መጽሐፍ አሳትሞ ዕዳ መግባት ቀረ። ጣጣውን ፈርቶ አለማሳተም ቀረ። የበዕውቀቱ “መግባትና መውጣት” [2002] በሰባት ህትመት 50 ሺ ኮፒ ተሽጧል። ትውልዱ አንባቢ አይደለም፤ አማርኛ ወድቋል የተባለው ውሸት ኖሯል! ስላላጣራን ብቻ፣ ስንቱን ውሸት፣ ኑሮ ብለን እየኖርን ይሆን? 

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ የሚጀምረው በቴዎድሮስ ሆኖ ሳለ ለምን ተረማምዶ ምኒልክን መረጠ? በዕውቀቱ ቴዎድሮስ ክርስቲያን ነኝ ማለታቸውን አይወድላቸውም። ዮሐንስ ቦሩ ሜዳ ላይ የቤተክርስቲያንን ቀኖና ለማወያየት ተሰይመው ንግግራቸው ያልጣማቸውን ሊቃናት ምላስ ማስቆረጣቸውን፣ የመናገር ነጻነት ተወልዶ የተገደለበት ቀን  ነው ሲል አልፎአቸዋል። ዘመናዊ እንሁን ካልን ኃይለሥላሴን ምን ይወጣላቸዋል? ደርግስ እንዴት ይረሳል? ደርግ እግዚአብሔርን መካዱና በብስክሌታው ሁለት ዐይኖች ልክ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ” ማለቱ በዕውቀቱን እንዴት ሳይስማማው ቀረ? ብሔር ብሔረሰቦችን ጎማው ላይ መጫንስ? የትኞቹን ከፊት፤ የትኞቹን ከኋላ ማድረግ ስላቃተ ይሆን? ያለ መሪ ብስክሌታው የት ሊደርስ? መሪ በደቦ እንዴት ይሆናል? የኮርቻ ላይ ሽሚያ ጎማ ቢያፈነዳስ?

ከብስክሌታው ይልቅ መርከብ ይሻል ነበር ይሆን? የመርከብ ጕዞ ትርጓሜው ግልጥ ነው፦ ለራስሽ ስትዪ አትስማሚና እንደተሰደዱ ወገኖቻችን ሁልሽም አብረሽ ትሰጥሚያታለሽ ነው! ቴዎድሮስ ደርሰው ባያጨናግፉ ኖሮ ዘመነ መሳፍንት ትልቅ መቻቻል የታየበት ዘመን ነው ይለናል በዕውቀቱ። ታዲያ ለምን የሚቆራቆሱ መሳፍንትን ፊት ጎማ ላይ አልጫናቸውም? ክልላዊ መንግሥትስ ምን የባሰ በደል ተገኘበት?

ሳንቲም1ከጎማው ላይ የደራሲው ፎቶ አለመለጠፉ፣ ከኮርቻው ላይ ተፈናጥጦ መቀመጡን ላፍታም አይሠውርብንም!

ኃይማኖት ከተነሳ፣ የምኒልክ ኃይማኖተኛነት ቢበረታ እንጂ ከቴዎድሮስና ከዮሐንስ በአንዳች አያንስም። ምኒልክ አድዋ ሲዘምቱ እንደ ቀዳሚዎቻቸው ታቦት አጅቧቸው ነው። ጎራዴአቸው ላይ “የምኒልክ ተስፋው እግዚአብሔር ነው” የሚል ተጽፎበታል። ኢያሱና ዘውዲቱ ለምን ታለፉ? የዚህን ምሥጢር ለማወቅ ስጥር፣ ፍቺውን ዐይነ ሳንቲም ጎማ ላይ አገኘሁት፦ ለማሻሻጥ ከጊዮርጊሱ ፈረሰኛ፣ ከምኒልክ የተሻለ አይገኝም! መለስ የሞቱ ሰሞን ለቀስተኛ በነቂስ እንዲወጣ የታወሱትና የተሞገሱት ምኒልክ ነበሩ። ታሪከኛው ሪፖርተር ጋዜጣ፣ ምኒልክ መሞታቸውን ሕዝብ ያወቀው ከዓመታት በኋላ እንደ ነበርና፤ መለስ ሦስት ወር ወሬአቸው ጠፋና ለምን ይገርማል ሲል ወርፎን ነበር። በፖለቲካ አሻሻጭነት ምኒልክን የሚተካከላቸው የለም ያልኩትን ለማረጋገጥ፣ አንባቢ በጎማው ልክ መሪዎችን በዐይነ ኅሊናው እያቀያየረ ይሞክራቸው [“ሳልሳዊ ቴዎድሮስ” መንግሥቱ ኃይለማርያም ምናልባት ሁለተኛ ይወጡ ይሆናል]። ባጭሩ፣ በሞቱትና በሕይወት ባሉት የኢትዮጵያ መሪዎች መሓል ዛሬ ምሽት ነጻ ምርጫ ቢካሄድ ምኒልክ ሰብስበው ዳግመኛ ከመቃብር ይገዙ ነበር። ክርክር የሚዳዳቸው ሁሉ፣ ብዕራቸውን ከማሾላቸው በፊት የምኒልክን የአድዋ ጦርነት ክተት አዋጅ በጽሞና ያንብቡ፤ ማንበብ ብቻ ሳይሆን በንግድ አስተዳደርና በፖለቲካ አመራር ላይ የተሠማሩ ሁሉ በጥንቃቄ ያጥኑት፤   

እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፋፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም ... ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ ለሚስትህ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልተውህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም...”[1887 ዓ.ም.]

ምኒልክ ስለ እግዚአብሔር የተናገሩትን ልብ እንበል፦ እግዚአብሔር ቸር ነው። የሚያኖር እግዚአብሔር ነው። አገር ለመምራት የሚያስችል፣ ድል የሚሰጥ፣ ከጦርነት የሚያሳርፍ እግዚአብሔር ነው። ንጉሥ ሰው ብቻ እንደሆኑ፣ ሟች እንደሆኑ፣ ሕይወታቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደሆነ አስተውለዋል። እግዚአብሔርን ያከበረ እግዚአብሔር እንደማያሳፍረው አስተውለዋል። ተስፋቸው በእግዚአብሔር እንጂ በዙፋናቸው፣ በጦር ኃይላቸው፣ በብልሃታቸው፣ በሃብታቸው እንዳልሆነ ተረድተዋል። ሕዝብን መበደል እግዚአብሔርን መበደል እንደሆነ ተረድተዋል። ሕዝብን አለመበደል፣ በርኅራኄና በአክብሮት ማነጋገር የሕዝብ ድጋፍ እንደሚያስገኝ ተረድተዋል። ንጉሥ ሕዝቡን ቸግሮኛልና ድረስልኝ “እርዳኝ” ሲሉት እንመለከታለን። ንጉሥ ሕዝቡን ችግርህ ችግሬ ነው እያለው ነው። ንጉሥ የሕዝብና የአገርን ጉዳይ እንደ ራሱ ጉዳይ ያያል። የአገር ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ እንደሆነ፣ አታስፈልግም የሚባል አንድም ዜጋ እንደሌለ፣ ሁሉም በአቅሙ ለጋራ ጥቅም የሚያበረክተው እንዳለ፣ የሁሉም ተሳትፎ ሳይኖር ድል እንደማይኖር  ንጉሥ አውቀዋል። የአሜሪካኖች ፕሬዚደንት ኬኔዲ በ1953 ዓ.ም.፣ “አገሬ ምን ታርግልኝ አትበል፤ ይልቅ ላገሬ ምን ላርግላት በል” ካሉት ንግግር ንጉሥ በሠላሳ አራት ዓመት ቀድመዋል። ንጉሥ ቤተሰብና ትውልድ፣ ሃይማኖት እና ሕገ ደንብ ለአገር ኅልውና ቁልፍ እንደሆነ አውቀዋል። ሕግ ለሚወሳልቱ ምህረት እንደማያደርግ። ወስላታ በቃሉ የማይገኘው ነው፤ እምነት የማይጣልበት አታላዩ ነው፤ ሥራ ፈትቱ ነው። እንዲህ ዓይነቱን መቅጣት ፍትኃዊ ነው፤ በንጉሥ ዘንድ ፍትህ በአማላጅና በመማለጃ አይታጠፍም። ምኒልክ በሁሉም መስክ ተዋጥቶላቸዋል ወይም እንከን የለሽ ነበሩ ለማለት አይደለም። እንከን የሌለበት ስንት ይገኝና ነው? ከአዋጁ አንጻር ግን ብልህ መሪ እንደነበሩ ማስተዋል አይቸግርም።

ከስድሳ ስድስቱ አብዮት ጀምሮ የመሪዎቻችን አንደበት ለእግዚአብሔር የተከፈተበት ሰዓት በጣት ይቆጠራል። ሊቀመንበር መንግሥቱ ሥልጣን ሲይዙና ከሥልጣን ሊሰናበቱ ዓመት ያህል ሲቀራቸው። መለስ ከመሞታቸው ዓመት በፊት ፓትርያርክ ጳውሎስ በአደባባይ መስቀል ሲያሳልመዋቸው። ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠ/ሚንስትር የሆኑ ሰሞን ከቤተሰባቸው ጋር የእግዚአብሔርን ስም እንደሚጠሩ ነግረውን።

በዕውቀቱና ትውልዱ ትልቅ ሥራ እየሠሩ ነው። በብዙ ሺዎች የሚቆጠር አንባቢ ፈጥረዋል፤ ወይም አሳድገዋል። “በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፤ በስሜ ስለሚደረገው ውልና ውሳኔ ማወቅና መሳተፍ መብቴ ነው። አያገባህም፣ አትሳተፍ መባልን መስማት አልሻም። አገር ማልማት ለመንግሥት ግዴታውና ለእኔም መብቴ እንጂ እንደ ተመጽዋች እንደ ውለታ ሊቆጠርብኝ አይገባም። የምችለውን በማድረግ ግዴታዬን እወጣለሁ። መስዋእት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ” የሚል መልእክት እያስተላለፉ ነው። የቀደሙት በከፈሉት መሥዋዕት ላይ መገንባት ይህንን ይመስላል። ጋሬጣ የለም ማለት አይደለም። አንደኛው ጋሬጣ፣ ዐይነተኛነት መንምኖ፣ ጥራዝ ነጠቅነት መበራከቱ፤ የአገሬው ተንቆ የባዕዱ መሠልጠኑ ነው። ዐይነተኛነት፣ የማይደጋገም የማይኮራረጅ ሰብዓዊነትና ማህበራዊነትን የሚያጎለብትና የሚጠይቅ ሥራ መሥራት ነው። ሌላኛው ጋሬጣ፣ አድናቂ እንጂ የሰከነ ሃያሲ መመናመኑ ነው። 

በአሉላ ከበደ አስተናጋጅነት ከቀረቡት ጥያቄዎች ደግሞ ጥቂቶቹን እንመልከት፤

ጥያቄ 1/ የፖለቲካ አጀንዳ ሳይኖር ደራሲ መጻፍ ይችላል? ከጠቃቀስናቸው ጉዳዮች በመነሳት መልሱ “አይችልም” ነው። ዐይን ያወጣ ፕሮፓጋንዳ አይሆን ይሆናል፤ ዞሮ ዞሮ ግን በኪነጥበብም ተሳብቦ ደራሲ የሚጥላቸውና የሚያነሳቸው አሳቦች የሉም ማለት አይቻልም።

ጥያቄ 2/ ይህን መጽሐፍ ለምን ጻፍክ?

መልስ፦ እንደ ቀኖና የማይጣሱ፣ የማይደፈሩ አሳቦችን “አሜን፣ አሜን” ብለን የተቀበልናቸውን፣ በአብሮ መኖራችን ላይ ጠንቅ የሆኑብንን የታሪክ ሸክሞች ለማቃለል ነው። በኃይማኖት “አሜን፣ አሜን” ነው። ኃይማኖት ኑፋቄን አይታገስም፤ ወይ ያገልላል ወይ ይገድላል። ያለጥያቄ የተቀበልናቸውን ፈትሼ የግሌን ድምዳሜዎች የሚያንጸባርቁ ጽሑፎች ለማሰባሰብ ነው ብሏል። በዕውቀቱ ያልገለጸው፣ መንግሥታት የሚያራምዱት አሐዳዊ አስተሳሰብም ይህንኑ መምሰሉን ነው። አዲስ ትምህርት፣ በነባሩ ኑፋቄ መባሉ የኖረ ጉዳይ ነው። የስድሳ ስድስቱ አብዮት ነባሩን ፈትሾ የተካው አዲስ ሥርዓት ከምን ደረሰ? አሁን የሚገዛው መንግሥት ሲጀምር ምን ነበር? ሰንብቶ ምን ሆነ? ከደርግ ምን ያህሉን ወረሰ? ሌላው ጉዳይ፣ ነባሩ መሠረቱን ሲለቅ ወደ መሠረቱ ለመመለስ ተሃድሶን መጥራት የኖረ ሐቅ ነው። ይህ በኃይማኖት ብቻ አይወሰንም። “አሜን” ብለን የተቀበልናቸውን ሲያማ በዕውቀቱ የራሱን አስተያየት እየሠነዘረ ነው፤ “እግዚአብሔር የለም!” አሜን በሉ! ሲለን፣ ይህንማ ከካርል ማርክስ ተምረን አልበጀንም እንለዋለን። ዘመነ መሳፍንትን ሲናፍቅ፣ በጤና ነው ወይ? እንለዋለን። ከልዩነታችን ይልቅ ጠንካራና የኖሩ የጋራ እሴቶች አሉን ሲለን እንመርቀዋለን! እንኳን አማራ ከኦሮሞ ቀርቶ፤ ትግሬ ከኪኩዩ ጋር፣ ከምባታ ከፈረንሳይ ጋር ከማይጋሩት የሚጋሩት ይመዝናል። በስተፍጻሜ ጥያቄው ማን በልቶ ማን ጦም ይደር ነው። ማን ጎጆ ቀልሶ ማን ደጅ ይደር? ማን ተሽሎ ማ ተጥሎ ነው።

ጥያቄ 3 ከአድማጭ/ በታሪክ አተረጓጎም ላይ፣ “ሐበሾች” የሚለውን ከፈረንሳይኛ ወደ አማርኛ ስትተረጉም “አማራ” ማለቱ ነው ስትል ትርጓሜህ ጥራቱ ምን ያህል ነው? ሌሎች ባለሙያዎችን አማክረሃል?

መልስ፦ ለመነጋገርያ ሳይሆን ሰነዱን ለማጥናት ያህል ቋንቋውን አጥንቼአለሁ። ከዚያ በመነሳትና በጊዜው የነበረውን አረዳድና ልማድ ሳልዘነጋ ተርጉሜአለሁ ብሏል። በዕውቀቱ የሰጠው መልስ ሌሎች ያልታሰቡ ችግሮችን ያስነሳል። በመጀመሪያ፣ ጠያቂው በደራሲው ብቃት እንዳልተማመነ ያስታውቃል። ለዚህ መፍትሔው፣ ደራሲው ከእርሱ የላቁ ሥልጣናትን እንዳማከረ መግለጹ ነበር። ለነገሩ፣ “ሐበሾች” ሲል “አማራ” ማለቱን ለማጣራት በውጭ ቋንቋ የተጻፈ ሰነድ ጋ መሄድ አያሻም። ሁለተኛ፣ በዕውቀቱ “ሐበሻ” የሚለውን ሲተረጉም በዘመኑ አረዳድ መመዘን እንደነበረበት ሁሉ፣ አፄ ቴዎድሮስን ሲመዝን ግን ሚዛኑን ወደ ጎን አድርጎት እንመለከታለን። በሌላ አነጋገር፣ እዚያ የቋጠረው እዚህ ተበትኖበታል። ደግነቱ፣ በዕውቀቱ የምርምርን አድካሚነት ተረድቶ፣ ወደ ደራሲነት ጥሪው ለመጠቃለል ቆርጧል። የአገራችንን ታሪክ አተረጓጎም በሚመለከት፣ የሚካሄደውን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጠቅሷል። ከዚያ በመነሳት “ነገሥታት አምላኪ” ተብለው የተፈረጁትን ተክለጻዲቅ መኩሪያና ደብተራዎችን ማድነቅ ጀምሬአለሁ ብሎናል። ከአቋሙ ጋር ስላልተጣጣመ ብቻ ሳይጠቅስ የዘነጋው ግን ደብተራዎችና ቀደምት ታሪክ ጸሐፊዎች የእግዚአብሔር ፍርኃት የሚገዛቸው እንደነበሩ ነው። ቃልና አደራ መጠበቅ በስፋት ይታወቅ ነበር እንጂ እንደ ዛሬ ብርቅ አልነበረም። 

ጥያቄ 4/ አንተ ደራሲ ነህ? ኮሚክ ነህ? ገጣሚ ነህ? የቱ ጋ ነህ?

መልስ፦ ደራሲ ነኝ። አሉላ ጥሩ ጠይቋል፤ በዕውቀቱም ጥሩ መልሷል። ጉልበቱን ቆጥቦ ዋነኛ ጥሪው ላይ ማተኮር ይኖርበታል። ሥራዎቹ የሚገመገሙት በአንድ ሰሞን ሳይሆን በሕይወት ዘመኑ ልክ መሆኑን መዘንጋት የለበትም። ሙያዊ ጥንካሬ ሳይኖረው በአመለካከቶች ላይ አስተያየት መስጠቱ ጠቀሜታ የለውም ባይባልም፣ ብዙ ውስብስብ ጉዳዮችን ባንድ ጊዜ ለመፍታት መሞከሩ ከአቅሙ በላይ ነውና፤ እያደር ተኣማኒነቱን ያመነምንበታል። ብርቱና ደካማ ጎኑን ቶሎ መለየት የሚኖርበት ለዚህ ነው። ለምሳሌ፣ ጳውሎስን “የክርስትና ዋና መስራች የሆነ ሐዋርያ” ብሎታል። ጳውሎስም እንኳ ይህንን ሊል አልደፈረም። ይኸ አጥርቶ ታሪኩን ያለማንበብ ውጤት ነው፣ ስቶ ማሳት ነው። “ጳውሎስ ጳውሎስ ከመሆኑ በፊት ሳዖል ነበር፤ ሳዖል የይሁዲነት/ዕብራዊ ስሙ ነው፣ ጳውሎስ ደግሞ የክርስትና ስሙ ነው” ብሎናል። ታሪኩ ግን እንደዚያ አይደለም። ጳውሎስ የሮማዊ ስሙ ነው፣ ሳዖል የዕብራዊ። የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 9:4 ላይ የተገለጠለት ኢየሱስ የተጣራው “ሳዖል፣ ሳዖል” ብሎ ነው። በዘመኑ ሁለት ስም መጠቀም የተለመደ ነው። ለምሳሌ፣ ማርቆስ ወንጌላዊው ዮሐንስም ይሰኛል [የሐዋርያት ሥራ 12:12]፤ ማርቆስ ሮማዊ ስሙ ሲሆን፣ ዮሐንስ ዕብራዊ ስሙ ነው። ጣቢታ ስሟ በግሪክ ዶርቃ ነው [የሐዋ ሥ 9፡36]። የጥንቃቄ ጉድለት እንደ ቀላል ስሕተት ሊታለፍ አይገባም። ምሳሌው የተፈለገው በኃይለ ጊዮርጊስና በባልቻ ተገን ስለ ክርስትናና ስለ ስም አወጣጥ አንድ ድምዳሜ ለማቀዳጀት ስለሆነ። መነሻውን ስቶ፣ መደምደሚያው ትክክል ሊሆን አይችልም። “ቅምቀማና ቅድስና አይጋጩም” ሲለን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቅድስናና ስለ “ቅምቀማ” በሚያስተምረው ላይ በቂ ጥናት እንዳላካሄደ ይገልጥበታል። አንድ አምላክ ማመን፣ ብዙ አማልክት እንደሆነላቸው፣ ለአስተሳሰብና ለኢኮኖሚ እድገት አያበቃም ይለናል፣ ወዘተ። ይኸም ግምት ነው። አሉላ በትክክል እንደጠየቀው፣ ምርምሩና ድምዳሜው ቀድሞ የወጠነውን እንዲደግፍለት ሳያስበው ያሰበ ይመስላል።

አስበንባቸው ተግባራዊ በምናደርጋቸው ጉዳዮች ውስጥ ያልታሰቡ በጎና በጎ ያልሆኑ ውጤቶች ይከሰታሉ። ብስክሌታው የታሪክ ሂደት ተምሳሌት ነው ተብለናል። የራሱን ታሪክ አስተካክሎ ለማያውቅ ግን፣ ብስክሌታ መጋለብ እንደማይችል ሰው የትም ሳይደርስ ተፈንግሎ ይቀራታል። ዛሬ የቸገረው ሁሉም ጎማው ላይ የየራሱን ግጣም አስገብቶና አንድ ኮርቻ ተፈናጥጦ ወደ ፈቀደው ለመጓዝ መፈለጉ ነው። ጣጣው ይታየን። በዕውቀቱ ያላቀደው መፍትሔም በጎማው ውስጥ ተሰውሯል። መፍትሔው፣ ታሪክ ካዛባ ቂመኛ እልኸኛ ፖለቲካ ይልቅ እግዚአብሔርን ወደ መፍራት መመለስና በፍትኃዊ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ማተኮር ነው። ሳንቲሞቹ ይህን ብቻ ካስታወሱን ትልቅ ነገር ነው፤ ምንዛሪም ከኪሳችን አናጣም።

ከአድማስ ባሻገር [ይቅርታ] ከአሜን ባሻገር ሽፋኑ ሲገለጥ ምን ይላል? ሌላ ጊዜ እንመለስበት ይሆናል። ከዚያ በፊት ደራሲው “ክብር እስከ መቃብር”ን ያስነብበን ይሆን?

ምትኩ አዲሱ

የማለዳ ድባብ

የስደተኛው ማስታወሻ