እውነተኛ የዘር ምንጭ?

ዶ/ር ፍቅሬ በ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” መጽሐፉ አዲስ እሳት ለኵሶልናል። እሳቱ ባጭሩ፣ ሁሉም የሚስማማውን ታሪክ ይጻፍ የሚል ነው። ቍጥራቸውና ማንነታቸው ያልታወቀ አወዳሾቹ፣ “ሐቀኛ የኦሮሞ ልጅ የኢትዮጵያ ልጅ” “የመከራ ቀን ደራሽ” “የመከራ ቀን ልጅ” “የታሪክና የፍቅር አባት” “የኢትዮጵያ መድን” “የህዝብ እርቅ አባት” “አስታራቂ” “የኢትዮጵያ ቤዛ” “ነብይ” ብለውታል። ሙገሳው የለመደበት “ካብ ካብ፣ ጣል ጣል” ባህላችን ነው ብለን እንለፈው።

አንዳንድ “ምሑራን” ጭሱ አፍኗቸው መስኮት ለመክፈት ሯሯጣሉአንዳንዶች የጎሳ ክልል መደብዘዝ የሥልጣን ወንበር እንዳያሳጣቸው ሠግተው። ሌሎች በአገር ወዳድነት። አንዳንዶችም ያልተፈጠረ ንጹሕ ጎሳ በስውር የሚያውጁ ናቸው። ከኢትዮጵያ መንደር ውጭ ማሰብ የተሳናቸው፤ በምድር ዙሪያ የሕዝቦች አሠፋፈር፣ መፍለስና መተካካት፤ መገፋፋትና ባህል መወራረስ የከረመ እውነት መሆኑ አልዋጥ ያላቸው ናቸው። ሕዝብ ነሳሳልን እሳቱ ይሻለናል ያሉ አሉእሳቱን በፈለጉት ሰዓት ማዳፈን የሚችሉ መስሎአቸዋልበእሳት መጫወት የታሪክ ዐመድ እንደሚያስታቅፍ ያልገባቸው ናቸው።

ፍቅሬቶሎሳ1ጎሠኛ ክልል ያቆረፈደው እንደ እሳት እራት ወላፈኑን ከብቦ “ከከፋፋይ ታሪክ የሚያቀራርበን ልብ ወለድ” ይሻለናል እያለ ነው። ከሚመርር እውነት “ልብ ወለድ” ይመረጥ? ሁሉም ራሱን እያወደሰ ሌላውን እያንኳሰሰ እውነቱን ላለመጋፈጥ ሽሽት ይዟል። “ከፋፋይ ታሪክ” = ኦሮምያ በአማራ፣ ደቡብ በትግራይ ጉዳይ አያገባውም መባሉ ነው። “ከፋፋይ”፣ እኔ ካልኩት ውጭ ሌላው ሁሉ ስሕተት ነው ነው። “ከፋፋይ፣” እኔ ብቻ ተበዳይ ነኝ ነው። እያንዳንዱ ራሱንና ሌላውን አጕድሎ ስለ መዘነ መፍትሔውም የሳተ ሆነ። እነሆ፣ “ከከፋፋይ ታሪክ የሚያቀራርብ ልብ ወለድ” ተመረጠ። የሠርቶ አደሩ የበላይነት ተመረጠ፤ የጎሳ ፌደራሊዝም ተመረጠ፤ ቅድስት ኢትዮጵያ ተመረጠ። በተነቃነቀ ጥርስ ቆሎ እንደ መቆርጠም ሆነ። በሌላ አነጋገር፣ ከሁለት ጎባጣ አናሳውን አምጣ። ቀና ጠፍቶ ጎባጣ መምረጥ ግን የታሪክ ኃፍረት መሆን ነው። በሃምሳ ዓመት ጉዞአችን ሩቅ አሳቢ የአስተሳሰብ ለውጥ ወይም እድገት አለማሳየታችን ለምን ይመስለናል? ዙፋን ለመገልበጥ የጎሳ ፖለቲካ የለኮሱ ያልበሰሉ ያልተሞከሩ ወጣት ምሑራን፣ የአገር መሪነትን ሲይዙ የተዳፈነውን እሳት እንደ ቆሰቆሱ አንርሳ።

ዶ/ር ፍቅሬ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” ጎጃም ነው ይለናል። ከአባይ ማዶ ገዳም ተገኘ በሚለን ነድ መሠረት ሁለቱ ጎሳዎች አባትና በአያት አንድ ናቸውአዳምና ሄዋን የተፈጠሩት ጎጃም፣ ዳሞትና ጣና አካባቢ ነው። ሲነሽጠው ሁላችንንም አሳፍሮ ወስዶ ቅድስቲቱ ከተማ ያራግፈናል። “ኤደንን ከሚያጠጡ አራት ወንዞች ውስጥ አባይ የምንለው ነው ኤፌሶን የሚባለው። በኦፌር ወርቅ ዙሪያ የሚዞር መሆኑ ተፅፏል። በኔ ድምዳሜ፣ የኤፌሶን ወንዝ የአሁኑ ዋቢ ሸበሌ ነው። ጤግሮስና ኤፈራጥስ ደግሞ ጊዮን ራሱ ጥንት ሜዲትራኒያን ባህር ይገባ ነበር። ድሮ ሜድትራኒያን ‘ኪቲ’ ይባል ነበር። ጥንት ጊዮን ወንዝ ሜድትራኒያን ሲደርስ ተራራ ስለነበር ተጋጭቶ ይመለስ ነበር። ከዚያ ነው መሬት ተነቃንቆ፣ ቦታው ተቆራርጦ አሁን ወዳለበት ኢራቅ የሄደው እንጂ አካባቢው እዚሁ ነበር።” በሌላ አነጋገር፣ መጽሐፈ ዘፍጥረት [ብሉይ] አፈታሪክ ስለሆነ ምሑራዊና ሳይንሳዊ መስፈርቶችን አፍርሶ ሁሉም የሻውን አፈታሪክ መቀፍቀፍ ይችላል ነው። አሁን እዚህ መዘርዘር የማያሻንን ድምፀቶችን በማመሳሰልና በማያያዝ “ማራ” አማራ ነው ይለናል። ልኩ ለጠፋበት፣ ሁሉ ልክ ሲሆንራስን መካብና ሌላውን ማንኳሰስ፣ ዘረኛነትና የአብሮነት ጠንቅ ነው። ዶ/ር ፍቅሬና አወዳሾቹ የሚቃወሙትን “ከፋፋይ” ታሪክ በሌላ መልኩ እየደገሙት እንደ ሆነ አላስተዋሉም። ይልቅ ከጥንት በተቀበልነው “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” [ዘፍጥረት 1:27] በሚለው የፈጣሪ ቃል ብንጸና ይኸ ሁሉ አሣር ባልገጠመን!  

ዶ/ር ፍቅሬ የሚያደርገውን የማያውቅ እንዳይመስለን። ገጣሚና ጸሐፌ-ተውኔት እንደ መሆኑ፤ ይበልጡኑ አብዮተኛ ትውልድና አገር ወዳድ። ፈጠራ ሙያው ሆኖ ሥነ-ሐተታ አማልክትን ልብና ቀልብ የመስረቅ ምሥጢር የተገነዘበ የሊተራቱር ሊቅ ነው። ጆሴፍ ካምበልን ያስታውሰናል። ካምበል፣ አፈ-ታሪክ፣ ልብ ለማሸፈት፣ ሰው ምኞቱን ተንተርሶ እንዲያልም ፍቱን መሳሪያ እንደ ሆነ የታሪክ ጭብጥ ባይኖረውም የማሳመን ኃይሉ እሙን ነው ብሎናል። ጥቁር አሜሪካዊውን ሞሌፊ አሳንቴን ያስታውሰናል። ሞሌፊ [ነጭ] ግሪኮች [ከጥቁር] ግብጽ አፍሪካ ሠርቀው እንጂ በሥልጣኔ አይቀድሙንም ይላል። የነጮችን የታሪክ አጻጻፍ ግድፈት ሲያጎላ ሳያስበው ራሱ በተበተበው ገመድ ተጠልፎ ወድቋል። ዶ/ር ፍቅሬም ሲሰብከን “ኢትዮጵያ የሚለው ከግሪክ ቃል  የመጣ ነው የሚለው ውሸት ነው። ይሄን አጣርቻለሁ። [ሄሮዶቱስ ለመኖሩ አጣርቶ ይሆን?] በነሱ መዝገበ ቃላት ውስጥ ይሄ ቃል የለም። ‘ፊቱ የተቃጠለ’ የሚለው ቃል በግሪክ ቋንቋ ኢትዮጵያ የሚለውን ሳይሆን ሌላ ትርጉም ነው የሚኖረው። ግሪኮቹ ከኛው ሰምተው ነው መልሠው ኢትዮጵያ ያሉን። እኛ ከነሱ በፊት ነበርን እንጂ እነሱ ከኛ በፊት አልነበሩም፤ ስማችንን ሊያወጡልን አይችሉም” ይለናል። ለመሳቅ እንኳ የሚቸግር አካሄድና ድምዳሜ ነው።

ፒተር መንዝ በ “ሂስትሪ ኤንድ ምት[ስ]”፣ ማህበረሰብ “ታሪክ ከተጻፈ በኋላም” እንኳ አዲስ የምኞት ታሪክና ያልተኖረበት ዓለም ይፈጥራል ይለናል። ወደ ፈጠራ ዓለም በመንጋጋት ሃብታምና ደኃ አንድ መሆናቸው፣ ሰውን ማጥመድ በምኞቱ በኩል መሆኑን ያስረዳል። የስድሳ ስድስቱ አብዮትና የሰማንያ ሦስቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በመሠረታቸው የምኞት ጉዞዎች ናቸው።

ዶ/ር ፍቅሬ የምርምር ውጤቶችን ወደ ጎን አድርጎ ሁሉን “ሀ” ብሎ መመርመር ይሻልታሪካዊ መረጃዎች አለመሟላታቸው ግድ አይሰጠውም። መጽሐፉን “እውነተኛ ታሪክ” ብሎ የሰየመው የሳሳውን መረጃ ለማለባበስና ሌላው ሁሉ ውሸት ነው ለማሰኘት ነው። በኤስያን አፌርስ መጽሔት [ጥር 2002 ዓ.ም] ተጠይቆ፣ የመጽሐፍ ቅዱስና ቊራን አምላክ አንድ፤ ነቢያቱ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ኢየሱስ፣ መሐመድ የጸለዩት ለአንድ አምላክ ነው ብሎናል። ሁሉ ኃይማኖት አንድ ይሁን ለሚሉ የዶ/ር ፍቅሬ ምላሽ ጥያቄ አይፈጥር ይሆናል። በኢየሱስና በመሐመድ ማንነትና ትምህርት ላይ ግን ይህን መሳይ ስህተት መፈጸም ከሞራላዊና ምሑራዊ ስነ ምግባር መጕደል ነው። በዚህ ሳያበቃ፣ ኢየሱስ ከ22 እስከ 25 ዓመቱ ድረስ በኢትዮጵያ ኖሯል ይለናልየግፍና የዓመጽ መቀፍቀፊያም እንደ ሆነች ተዘንግቶ፣ ምድራችን ቅድስት፣ ህዝቦቿም የእግዚአብሔር ምርጦች ናቸው ለሚሉ ምኞተ ብዙኃን፣ ምኞታቸው እንደ ያዘላቸው እንጂ መሠረተ ቢስ ስብከት መሆኑ ግድ አይሰጣቸውም።

ዶ/ር ፍቅሬ እንዴት እንዲህ ሊሳካለት ቻለ? ዋናው ምክንያት ማኅበራዊና ስነ ልቦናዊ ክፍተት መኖሩ ነው። አገር በቋንቋ መካለሉ፣ የትምህርት ጥራት መውደቁ፤ የዜጎች ተሳትፎ መመንመኑ። ትውልድ የቅርብ ዓመታት ታሪኩን እንኳ አጥርቶ አለማወቁና ከዘመኑ ጋር ለማነጻጸር አለመብቃቱ። ክፍተቱ በከፊል ሆን ተብሎ፣ በከፊል ተቆርቋሪ በመጥፋቱ የተከሰተ ነው። አርስጣጣሊስ በአንደኛው ትዝብቱ፣ ክፍተት በተገኘበት በተገኘው ይሞ-ላ-ል ብሏል። ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል ነው ነገሩ። ሌላው ምክንያት፣ ብዙኃኑ በገዛ አገሩ ሙሉ ተሳትፎ እንዳይኖረው መደረጉ፤ የኦሮሞና አማራ ሕዝብ ቊጥር 70 ሚሊዮን ያክል መድረሱ [በ100 ሚሊዮን ሕዝብ ብዛት ሲሰላ]። ሕዝብ ብሶቱን ማንሸራሸርያ ማግኘቱ። መንግሥት መጽሐፉን ማገዱ። የምሑራን ስንፍናና አድር ባይነት፤ ስንፍናቸው ለስምብቻ ምሑራን መድረክ ማቀዳጀቱ። ስለ አገራችንና ስለ ሕዝቦቿ በትምህርት ቤት፣ በመንግሥት አፈቀላጤዎች፣ በክልል ፖለቲከኞችና ውጭ አገር በተበተነው ተቀናቃኝ የተዘራው እንክርዳድ የእውነትን ረኃብ ለማስታገስ አለመቻሉ። የሥጋና የመንፈስ ራብ መመሳሰሉ ለዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ መግነን ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።

ማህበራዊ ድንቍርናና ውዥንብር መበርከቱቤተ ክርስቲያን መስቀል ከሰማይ ወረደ ብላ ቀኝና ግራውን የማያውቅ ምእመን ስትበዘብዝ። የናይጄሪያ ጠበል ሕዝብ ላይ ረጭቶ ፍራንክ ሲለቅም። ሥርዓተ አልበኛ ነብያት ምኞቱን እንዲነግሩት ለሚሻ ሁሉ ቀምመው ትንቢት ሲነሰንሱ። ለማበጣበጥ የተፈጠሩ ጥያቄዎች እንደ ጎን ውጋት በየሁኔታው መቆስቆሳቸው፦ አማራ ማለት አማርኛ ተናጋሪው ነው? አማራ የሚባል ጎሳ አለ? ሁሉ ጎሳ እኵል ነው? “እኵል” ማለት ምን ማለት ነው? ትግሬ ከጤግሮስ ኢራቅ ተገኘ? እውን [ገዳ] ዲሞክራሲ ነው? ከግሪኮች ዲሞክራሲ ይቀድማል? ኦሮሞ መጤ ነው? ሌላው ከየት መጣ? ወዘተ።

ፖል ካርትሌጅና ዳያን ክላይን፣ የጥንት ግሪካውያን ዲሞክራሲ፣ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምዕራቡ ዓለም ከተከሰተው በብዙ መልኩ የተጻረረ ነው ብለውናል። ሁሉም የየራሱን እውነት ይዞ የሌላውን ያንቋሽሻል። ሌላውን ሳያከበር ልከበር ይላል። የቋንቋ ፖሊሲ ለምን በእንጥልጥል ተተወ? ሁለት “ሕጋዊ” ፓትርያርክ ለምን አስፈለገ? ዛቻ፦ የትግራይ ሪፐብሊክ ዛቻ። የኦሮሞ ሪፐብሊክ ዛቻ። እነዚህ ክፍተቶች ለዶ/ር ፍቅሬ እሳት መለኮሻ ጉልቻ ፈጥረውለታል። ትውልዱ የተነገረው ታሪክ ውሸት መሆኑን ሲያውቅ በደርግ፣ በኃይለሥላሴና በዚህ ዘመን ካሳየው ዐመጽ ውጭ ምን እንዲያደርግ ይጠበቃል? ወይስ ጊዜው ሲደርስ በአፈ-ሙዝ ማዳፈን ይቻላል? ስንቱን እናንሳ። ባጭሩ፣ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንበል። ሌባው ግን ሁሌ ሌላኛው ነው።

መፍትሔውስ ምንድነው? መፍትሔው፦ ብርሃን የበራላቸው ማታለል ያቁሙ። ለግራና ለቀኝ የማይል እውነት ያስተም። ብርሃንን ከእንቅብ በታች ማኖር ብርሃንን መቀማት፣ ለጨለማ መንበርከክ እንደ ሆነ ይወቁ። ያልተማሩ ይማሩ። አርነት የሚሹ ከእውነት አይሽሹ።                 

ምትኩ አዲሱ

ታህሳስ 19/2009 ዓ.ም. [12/28/2016] edited 1/2/17

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave