ሐ ተ ታ ና  ግ ም ገ ማ

ኑ፣ ሥራውን እዩ፤ በተመስገን ሳህለ [ወንጌላዊ ኬዳሞ ሜቻቶ እንደተረኩለት]፤ አሳታሚ፦ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ/ክ፣ 2008 ዓ.ም.፤ አ/አበባ፤ 408 ገጾች

ስለ መታሰቢያ አንዳንድ ነገሮች። የመጽሐፉ ጠቀሜታ። የአዘጋጁ ድርሻ። ኹለንተናዊ እና ዘመን ተርጓሚ ትዝብቶች። ቀጥተኛ ወንጌል። መሪነትና ጾታ። 2ኛ እትም እርምቶች። “መጽሐፍ ቅዱስ አይከለክልም።” ሁሉ እንደ ነበረ ነው።

ስለ መታሰቢያ አንዳንድ ነገሮች። ታሪክ የመጻፍ ባህል በአገራችን እየዳበረ መጥቷል። በአንጻሩ፣ የጥንቱ ቀርቶ የቅርብ ጊዜ ታሪክ እየደበዘዘ፣ ሁሉም የየራሱን ያልተመረመረ ምኞትና ምሬት ታሪክ ነው እያሰኘ የሚገኝበት ዘመን ላይ ነን። ወቅቱን ጠብቆ ልኩን ለመናገር፣ ልኩን አጥርቶ ማወቅና ቆራጥ መሆንን ይጠይቃል። የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በተመለከተ ወንድዬ ዓሊ፣ ጌታቸው በለጠ፣ ስሜ ታደሰ፣ ሌሎችም ያደረጉት አስተዋጽዖ ቀላል አይደለም። አሁን ደግሞ ተመስገን ሳህለ። ባለፈው እትማችን፣ ሰዎች ለምን ታሪካቸውን አደባባይ ያወጣሉ? ብለን የጠቀስነውን እዚህ መልከቱ።

በቀድሞ ዘመን የነገሥታትና የሰማእታትን ገድል እንጂ ግለ ታሪክን በጽሑፍ ማስፈር አልተለመደም። የቀለም ትምህርት አለመስፋፋት አንደኛው ምክንያት ነው፤ ሌላኛው፣ ራስን ማተለቅ መምሰሉ ነው። ከዚህ የተነሳ ብዙ ታሪክ ሳይዘገብ ባክኖ ቀረ፤ አንዳንዱም በአፍ ሲነገር ሲቀጠልና ሲቀነስ “እውነት እንደ ነጋሪው” ነው አሰኘ፤ ትውልድ አደኸየ። የነ ቾ፣ የነ ቼ፣ የነ ኒ፣ የነ ቲቢን ብቻ ታሪክ ስናስተናግድ የራሳችንን ችላ አልን። ይህም ‘የውጭው ይሻላል’ የሚል አሉታዊ ተጽዕኖ አሳደረ።

ነገሥታት ዝናቸውን ለማግነን፣ ሕዝባቸውንም ለመግዛት፣ ታሪካቸውን አሰማምረው ያጽፋሉ። ተቀናቃኝ አይታገሡም። በአማልክት ልክ የሚያገኗቸውን ይሾማሉ፣ ይሸልማሉ። ለእምነት ሰዎች ግን መታሰቢያቸው በሰው ልብ ውስጥ መቅረታቸው ነው፤ ለዚያውም ከሞቱ በኋላ ነው፤ ከሁሉ ይልቅ ግን ተስፋቸው ስማቸው በሰማይ መዝገብ ውስጥ መጻፉ ነው። ለዚያም ብዙዎች አይታደሉም። አቡነ ጳውሎስ በሕይወት እያሉ በ400 ሺህ ብር ከመዳብና ከብረት ቅልቅል [ከነሐስ] ለራሳቸው ሐውልት ማስተከላቸው ያነሣሣው ትዝብት ዛሬም አልረገበም። እርግጥ ነው፣ ዜና እረፍት በአደባባይ ይነገራል። ገላ፣ ግሬደር ወጥቶበት እስኪያፈራርሰው ባፈር፣ በሙጃና በእብነ በረድ ይከደናል። ሟች በሕይወት ሳለ መልካምነቱ ባይጎላም፣ የሞተ በክፋት አይነሳምና፣ ደግ ደጉ ተነግሮለት ነፍሱን በገነት አኑርልን ብሎ ይቋጭለታል። እነሆ፣ ከዘመን በኋላ የፓርቲ አባላትም እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሰማእታት ተሰኙ፤ ቆምንለት፣ ሞትንለት፣ ከሚሉት ሕዝብ ተነጥለው፣ ባጌጠ በተከለለ መካነ መቃብር ተጋደሙ።

ዛሬ፣ በቍም ስለ ራስ ማውራትና ማስወራት፣ መረጃ ተዛብቶ እንኳ የማያሳፍርና የሚፈለግ ሆኗል። በቤተ ክርስቲያንስ? በወንጌላውያንስ ዘንድ? ራስን ማግነን የለም? ኑ፣ ሥራዬን እዩ፤ ዝናዬን ስሙ፦ “ሐዋርያ ነኝ”፣ “ነቢዪት ነኝ”፣ “የእግዚአብሔር ሰው ነኝ” ማለት እየተለመደ መጥቷል። ከስግደት ያላነሰ የሚያስተናግዱ ተነስተዋል። ሰው በሚያቆላምጡት አፍ ይመዘናልና ብዙዎች ተመዝነው ቀለሉ። ለመሆኑ ይኸ ባእድ ባህል እንዴት በአንድ ትውልድ እንዲህ ሊንሠራፋ ቻለ? ወይስ አድብቶ ምቹ ቀን ሲጠብቅ ኖሯል?

ግለ ታሪክ መጻፍ ፋይዳ የለውም ማለት ያስቸግራል። በተለይ አዲሱ ትውልድ ቅርሱን ለይቶ አለማወቁና የቀደሙትን መዋእል ተግቶ አለማንበቡ፣ ስሕተታቸውን እንዲደግም አድርጎታል። ‘ስነ መለኮት ምን ያደርግልናል፣ መንፈስ ቅዱስ ያስተምረናል’ የሚለው አለማስተዋል ያለእረፍት ከትውልድ ትውልድ ተሸጋግሯል። የምእራባውያንና የአገሬው ባህላዊ ክርስትና፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊና ሐዋርያዊ መስሎት ተወናብዷል።

ወንጌል አገልጋዮች መስዋእት ከፍለው የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን አስረክበውናል። ሕያው እግዚአብሔር ጠርቶአቸውና አጽንቶአቸው በእጃቸው ባከናወነው ላይ ተጨምረን የመንግሥቱን ሥራ እንድናራምድ እንጂ ወደ ኋላ እንድንመልስ አይጠበቅብንም። የቀደሙን የዘሩትን ያጨድን፣ እኛው ዘርተን እንዳጨድን ብንቆጥር እንበድላለን [ዮሐንስ 4:37-38]። የእግዚአብሔርን ኃይል ሥራ ማውራት፣ ምስጋናውንም ማሰማት ጥሪአችን ነው [መዝሙር 106:2]። እግዚአብሔር ምን የትና እንዴት ሠራ? ለካንስ እንዲህም አለ? ብሎ ዝናውን ማግነን እና ቀጣዩን ትውልድ ማነሳሳት ግድ ነው። በጌታ አገልግሎት ዘመናቸውን ያስረጁ ሁሉ የሠራውን መተረክ የሚኖርባቸው ዛሬ ነው፣ ለዚህ ነው።  

kedamofotoየመጽሐፉ ጠቀሜታ። ወደ ወንጌላዊ ኬዳሞ ሜቻቶ [ኬዳሞ] ታሪክ እንመለስ። ኬዳሞ ጌታን ካመኑ ከ1942 ጀምሮ እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ ለ66 ዓመታት የክርስቶስን ቤተክርስቲያን አገልግለዋል፤ እያገለገሉም ነው። የዚህ መጽሐፍ ጠቀሜታ ምንድነው? ጠቀሜታ ስንል ለተለያዩ ሰዎች የተለያየ እንደሚሆን አንርሳ። ባጭሩ፣ ይህ መጽሐፍ የመረጃ ማእድን ነው፣ ጌታ የሠራው ጥቂት፣ የመትረፍረፍ ኃይል አለውና። የኬዳሞ ታሪክ፣

ሀ/ የኢትዮጵያን የፖለቲካ፣ የኃይማኖትና የባህል ታሪክ ለሚያጠኑ የዐይን ምስክር መረጃ ይዟል። አምልኮ ሰይጣን፣ ለፀሐይና ለጨረቃ ስግደት፣ በዓመት ለሁለት ሳምንት ቀን ቀን መጾም፣ ወንዝ ወርዶ መታጠብና ጥፍር መቆረጥ የ“ፈንዳኖ” እምነት [ገጽ 30]። መናናቅ፤ ባሪያ ግዥና ሽያጭ፤ የኬዳሞ ወላጆች በገንዘብ የተገዙ ወንድና ሴት ባሪያዎች ነበሯቸው [ገጽ 31]፤ ይህም በሰሜን፣ በምእራብ በምሥራቅ በመሓል ኢትዮጵያ፤ በሩስያ፣ በጀርመን፣ በስካንድኔቪያ፣ በደቡብና በሰሜን አሜሪካ የነበረና ያለ ልማድ ነው። ክርስቲያን ዜና ማዳመጥና በማህበራዊ ጕዳዮች መሳተፍ ይችላል? ለሚለው ጥያቄ [ገጽ 161-165]። ፋሽስት ጣልያን በአውሮፕላን ቦምብ ሲያርከፈክፍ ቤታቸውን ጥለው ሲሸሹ [ገጽ 32]። ልጅነትና አስተዳደግ ምን ይመስል ነበር? [ገጽ 33-35]። በዱራሜ፣ በሃላባና አካባቢ የእስልምና መስፋፋት፣ “ሙስሊሞች ... ለየሰው እንደ ሹመት የሼኪነት ማእረግ ይሰጡ ስለነበር እምነቱ እንደ ሰደድ እሳት ይስፋፋ ነበር” [ገጽ 117]። በቋንቋ፣ በባህል፣ በኃይማኖት ያልተሳሰረ የኢትዮጵያ ሕዝብ የለም፤ ኢትዮጵያ የአራት ቤተሰብ ቋንቋዎችና የገበሬ ምድር ነች፤ የሃዲያዋ [ንግሥት] እሌኒ የ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ ሚስት ነበረች [ገጽ 29]። ሥልጣን ለማራዘም በጋብቻ መተሳሰር በምድር ዙሪያ የኖረ ስልት ነው። ለ/ የኬዳሞ ታሪክ ከመርኪና መጃ፣ ከአማኑኤል አብርሃም፣ ከኦነሲሞስ ነሲብ፣ አስቴር ጋኖ፣ ከጕዲና ቱምሳና ሌሎች መሪዎች ጋር አንድነት መሪነትን ለማስተማርያ፣ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮና ወንጌል ስርጭትን፣ በተለይ ስለ አገር በቀል አደረጃጀትና የትምህርተ እምነት [ዶክትሪን] አስፈላጊነትን ለማጠናከሪያ ሊውል ይችላል። መ/ ወንጌል በተሰበከበት ሁሉ ስር-ነቀል መንፈሳዊና ማህበራዊ ለውጥ ይከተላል። ሁሌም የቸገረው የሰው ልብ ነው። የሰውን ልብ እንዴት መለወጥ ይቻላል? አካባቢያዊ ለውጥ አይጠቅምም ባይባልም፣ ውጫዊ ለውጥ የልብ/የአስተሳሰብ ለውጥ እንደሚያስገኘው ዘላቂነት የለውም። የምናምነው አምላክ ለነፍስ ብቻ አይደለም፣ ለሥጋም ይገደዋል። ሕዝቡን ከግብጽ ባርነት ነጻ አውጥቶ ወደ ተስፋዪቱ ምድር ያገባ አምላክ ነው። ደቡባዊ ኢትዮጵያ ከሰባ ዓመት በፊት የነበረበትንና ዛሬ የሚገኝበትን በጎ ሁናቴ ከክርስቶስ ወንጌል ኃይል ሥራ ለይቶ ማየት አይቻልም። ከወንጌላዊ ኬዳሞ የአገልግሎት ሕይወት የምንማረውን በአንድ ሐረግ መጠቅለል ቢቻል፣ “ማመካኘት አይፈቀድም” [ወይም በግልባጩ፣ “ከኃላፊነት አልሸሽም”] የሚል ይመስለናል። ፊደል ከቆጠረው የአገራችን ሕዝብ ከመቶ አንድ እጅ ይህንን መመሪያው ቢያደርግ ምድራችን ከፍተኛ ለውጥ እንደምትቀዳጅ ጥርጥር የለንም።

የአዘጋጁ ድርሻ። ተመስገን ሳህለ በጣም ተነባቢና ጥራት ያለው መጽሐፍ አቅርቦልናል። እግዚአብሔር ይባርከው። ተራኪው ምንም ሳያስቀሩ ሕይወታቸውን ግልጽልጽ ማድረጋቸው ታሪካቸውን ተሸጋጋሪ አድርጎታል። በሌሎች ቋንቋዎች ቢተረጎም የታሪኩ ለዛና ኃይል አብሮት ይዛመታል፤ በጴንጤቆስጤ ቀን “እያንዳንዱ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ነበር” እንዲል [የሐዋ ሥራ 2:6]። ኬዳሞ አውሮጳና ሰሜን አሜሪካ ተጕዘው ለፈረንጁ ማህበር ባስተርጓሚ ሲሰብኩ፣ ፈረንጅ ወገኖቻችን ያለቅሱና እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር [ገጽ 234-235]

የአዘጋጁ/አርታኢው ድርሻና ኃላፊነት እስከ ምን ድረስ ነው? ይህንን በሁለት መልኩ እንመልከት። አንደኛ፣ ወንድም ተመስገን “እንደተረኩልኝ” እንጂ “በታሪኩ ውስጥ የቀረቡ መረጃዎች በጥልቅ ምርምር የተገኙ ውጤቶች” አይደሉም በማለቱ እጁ እንደሌለበት ሊያሳምነን ሞክሯል [ገጽ20]። ሆኖም፣ ምእራፎቹን ሲከፍት በእንጥልጥል የተተው አሳቦችን አሰባስቦ በአንዳንዱ ላይ የራሱን ድምዳሜ አክሎበታል። ለምሳሌ፣ የኬዳሞ ልጅ የሞተው “በሚማርበት ትምህርት ቤት አንድ ዕቃ ጠፍቶ የወሰደው ሰው ሳይገኝ” መቅረቱና “አንዲት ምዕራባዊት የትምህርት ቤቱ ባልደረባ በጥርጣሬ ስለ ዕቃው የሚያውቀው ነገር እንዳለ አጥብቃ ዳዊትን” መጠየቋ ህመም ላይ ጥሎት ነው ይላል [ገጽ 171-2]። ቀጥሎ፣ “የወንጌላዊ ልጅ እንደመሆኑ ዕቃ ቢጠፋ አንስቶ ከመስጠት ውጪ ለራሱ መውሰድን ያልለመደው ልጅ በነገሩ ክፉኛ ተጨነቀ” [ገጽ 172]። ይኸ የኋለኛው የአዘጋጁ ማብራሪያ ነው፤አስፈላጊነቱ ግልጽ አይደለም። አንድ የጥበብ ሰው ቅርርብ መፍጠሩ ተገቢ ነው ቢባልም፣ ስሜቱ በተደራሲው እንዳይወሰድ ርቀት መፍጠር ይኖርበታል [ገጽ 18]። እንደዚሁ፣ በኬዳሞና በመጋቢ ዮሐንስ ባሳና መካከል የነበረው የአመለካከት ልዩነት “በአገልግሎቱ ዙሪያ ካሉ አንዳንድ መሰናክሎች” ብቻ ተብሎ ታልፏል [ገጽ 305-309]። የቃለ ሕይወት ጽ/ቤት አመራር ስለ ጉዳዩ መቸና ምን እንደሚያውቅ፣ ምን እርምጃ እንደወሰደ ወይም ለምን እንዳልወሰደ አልተገለጸም። ከኬዳሞና ከዮሐንስ ባሳና ሌላ የሌሎች ሁለት “ብሔራዊ ወንጌላውያን” አሳብ አልተብራራም። ሁለተኛ፣ አዘጋጁ ሳያስበው ልንሰማው ከሚያስፈልገን በላይ መድረኩን ተጋርቶ ስለ ራሱ ነግሮን ይሆን? “የመጀመሪያው በኔ የተጻፈ ሙሉ መጽሐፌ የወንጌላዊ ኬዳሞ ግለ ታሪክ መሆኑ ሌሎች ጸሐፍት የሚቀኑበት ጸሐፊ እንዳደረገኝ ይሰማኛል ... በወንጌላዊ ኬዳሞ የመመስገንን ዕድል በማግኘቴ በጣም ተደሰትኩ” ወዘተ [ገጽ 10፣15-18]። ስለ ቄስ በሊና ሣርካ፣ ሀብታሙ ኪታባ፤ ስለ ገርቦሌ ሂርጳ፣ ደረጀ በቀለ የጻፉትን ማነጻጸር ይጠቅማል።

ኹለንተናዊ ዘመን ተርጓሚ ትዝብቶች። ሀ/ ወንጌል ጉዞው በሻሾጎ፣ በአዲስ አበባ፣ በተሰደዱ ወገኖቻችን መካከል ነው። በኬንያ፣ በአውሮጳና በሰሜን አሜሪካ ጭምር ነው። ለ/ ኬዳሞ በውጣ ውረዱ ውስጥ በወንጌላዊነት ጥሪአቸው ጸንተው እናያለን። “የማገለግለው ስለሚከፈለኝ [ዋጋ] ሳይሆን፣ ስለተከፈለልኝ ታላቅ ዋጋ ነው” [ገጽ 357]። ዛሬ ስንቶች አገልጋዮች ይህን ለማለት ይደፍራሉ? ይኸ በየመድረኩ የምንሰማው ማቃጨልና ግርግር ምንድነው? በአንድ መልኩ፣ ወንጌላዊ ያልሆነ ወንጌል አገልጋይ የለም። ኢየሱስ ወንጌላዊና እረኛ ነበረ [ሉቃስ 4:16-22፣ 42-44፤ ዮሐንስ 10]። ወንጌላዊና እረኛ መባል የሚወድድ ግን እየጠፋ ነው፤ ወንጌላዊ፣ ፓስተር ሆኗል፤ ፓስተር፣ ሐዋርያ። ፓስተር፣ እረኛ ከመባል ይመረጣል። እረኛ የተናቀ ገጠሬና ኃላፊነትን ስለሚያጎላ፤ ፓስተር የሠለጠነ ቢሮና ከተሜነትን። “ሐዋርያ” በነጴጥሮስና ጳውሎስ ልክ አለመሆኑና ብዙ ጥያቄ ማስነሳቱ፣ በ “አፖስል”፣ በ “የእግዚአብሔር ሰው” “ማን ኦፍ ጎድ” ተሸፋፍኗል። መጠሪያ በአስተሳሰብና በግንኙነቶች ላይ ትልቅ ተጽእኖ አለው። ሰማንያ አምስት በመቶ የአገራችን ሕዝብ ገበሬ መሆኑ፣ “እረኛ”ን ከ “ፓስተር” ይልቅ ለአገሬው አስተሳሰብና ኑሮ ቅርብ ያደርገዋል። ትርጓሜአቸው አንድ ነው ቢባልም፣ ስንቶች ፓስተሮች እረኛ መባል ይፈቅዳሉ?[ኤፌሶን 4፡11] ሐ/ የኬዳሞ አገልግሎት ትረካ “ትለመልማለህ!” በሚል የድል መፈክር ተገባድዷል [ገጽ 330]። የጌታ የሆኑትና ጌታን በታማኝነት ያገለገሉት ሁሉ ምእራፋቸው የሚዘጋው በመሸነፍ ሳይሆን በድል ነው። ቢገደሉ ደማቸው የሚያብብ ነው። “ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፥ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር” ብሎአል [የሐዋ ሥራ 28:30-31]። ያገለገለው ጌታ የትንሳኤ ጌታ ነውና ጳውሎስን እስር ቤት ሊያስረው አልቻለም፤ እርጅና ሊገዳደረው፣ ሞትም እንኳ ሊያስቆመው አልቻለም። መ/ ለቤተ ክርስቲያን መገዛት፣ ለክርስቶስ መገዛት ነው፤ ለቤተ ክርስቲያን አለመገዛት፣ ለክርስቶስ አለመገዛት ነውእልኸኛና ትእግስት አስጨራሽ [“የሻሾጎ ወይፈን” “ኦኢስ”] ለመንፈስ ቅዱስ ሲገዛ ለእግዚአብሔር ዓላማ ተመቸ። ጌታ ዛሬም ለደካሞች ኃይልን ይጨምራል፤ ኃይለኞችን ዓላማውን እንዲፈጽሙ ይገራቸዋል። ሠ/ መማር፣ ማንበብ፣ ማጥናት፣ መጻፍ፣ መምራት፤ የኬዳሞ ሕይወት። ስንቶች አገልጋዮች ሳያቋርጡ መንፈሳቸውንና አእምሮአቸውን በቃሉ ይመግባሉ? ይጽፋሉ? የብዙዎች አገልግሎት ኃላፊነትና ዲሲፕሊን የማይጠይቅ፣ ተጠሪነት የማይታይበት “መንፈሳዊነት” እየሆነ ነው። ረ/ ትክክለኛ ጥሪ የተቀበለ፣ ዓላማው ራሱን ማኖርና መገልገል ሳይሆን የሚያገለግላቸውን ኑሮ በቃሉ ማነጽና ለቤቱ ሥራ ቍምነገር ማብቃት ነው። የቃሉ መረዳትና ሥልጣን ሳይኖር በግል ልምምድ ብቻ ደቀ መዝሙር ማፍራት ድካም ነው። ሰ/ ወንጌል በተሰበከበት ሁሉ ሰዎች ከጨለማ ወደ ብርሃን ይሻገራሉ። ኑሮአቸው ይለመልማል። ለሰባት ቀን ሰባት ኮርማ ማረድ፣ ከአጋንንት ማእድ መብላትና መጠጣት ሥራ የመፍታት ኪሳራ። በጠላትነት ከመተያየት ነጻ ማውጣት፣ ትምህርት ቤቶች ማቋቋም። ሰው ሠራሽ ለውጥ፣ ከባላባት ቀንበር ነጻ ሲያወጣ፣ የሚያቃቅር፣ የፍርኃትና ያለመተማመን፣ የደም መፋሰስ ቀንበር ሰው ላይ ጭኖ ነው። ሰው ሠራሽ ለውጥ፣ እኩልነትና ነጻነት ሲያውጅ፣ በስግብግብነት፣ በፍርኃትና በከረመ ቂም ለባብጦ፣ አቃርኖና አበላልጦ ነው። ከገዛ አገሩ የሚሸሸው፣ የሕዝቡ ኑሮ መውደቅና የሚሰማው ምሬት ይህን ያመለክታል። አሁንም ዘላቂና ሥር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ የክርስቶስ ወንጌል ብቻ ነው።

ሸ/ ወጣቱ እረኛ ኬዳሞ ሻሾጎ ላይ “እኔን የፈጠርኸኝ አምላክ ሆይ ይህ ዝናብ እንዲመለስ አድርግ ... ሰው ከየት መጣ? ...” ይላል። ወጣት ገርቦሌ ሂርጳ [እዚህ ይጠቍሙ] በ450 ኪሎ ሜትር ርቀት ሻምቡ ወለጋ ላይ ከብት እያገደ የኬዳሞን ዓይነት ጥያቄ ይጠይቃል [በቋጥኝ ላይ የበቀለች ዋርካ፣ 2003 ዓ.ም]። እግዚአብሔር ለእረኞች ቅርብ ነው [ሉቃስ 2:8-20]። ኬዳሞና ገርቦሌ ማንበብ መጻፍ የማይችሉ ነበሩ፤ ሰው ሊያቅደው በማይችለው መንገድ ግን ወንጌልን ሰምተው ወንጌል ሰባኪዎች ሆኑ። ወንጌል ይዘው እስከ ዓለም ዳርቻ ዘመቱ። ቀ/ አገልጋይ ቃሉን ከመስበክ ውጭ አማራጭ የለውም፤ ራሱን ሲሰብክ እንዳይገኝ መጠንቀቅ አለበት። ሁሌ ዝግጁ መሆን አለበት። ኬዳሞ “ጥቅሶችን ስንማር 700 ያህል ጥቅሶች በቃላችን አጥንተን መጽሐፍ ቅዱስ ባንይዝ እንኳን ወንጌልን እንደሚገባ መመስከር እንድንችል ብቍ አድርጎናል” ብለዋል [ገጽ 59]። ሰባት ወይም አሥራ ሰባት ጥቅስ እንዳላሉ ልብ እንበል። ቤተ ክርስቲያን ምእመንን በቃሉ ለማስታጠቅ ምን ጥረት አድርጋለች ወይስ ዘመኑ አእምሮ አልባ ሆኖ፣ ለእንዲህ ዓይነቱ ጊዜ የለውም? ቍልፍ የሆኑ ወንጌላዊ አስተምህሮ ጥቅሶችን [ዮሐንስ 1:1-5፤ 12፤ 3:16-21፤ 5:24፤ ሮሜ 3:24-25፤ 8:1፣ ወዘተ] በቃል ማጥናት ቢጀመር ስንቶች በሕይወታቸው ይታደሳሉ? ስንቶች ከስህተት ትምህርት ይጠበቃሉ? በአንድ እሑድ ወይም በአንድ ኮንፈረንስ ምን ያህሉ ሰዓት ለቃሉ ንባብ፣ ጥናትና ትምህርት ይውላል? በ/ “በዚያ [የመከራ] ዘመን ክርስቲያኖች በጣም ይተሳሰቡ ነበር” [ገጽ 168]፤ “እንደ አንድ ሰው ነበርን” [ገጽ 250]። በ “ነጻነት”ስ ዘመን? የወቅቱ ፖለቲካና የቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ራሱን የቻለ ጥናት ይጠይቃል! ተ/ “በላከችው የዲቪ ቅጽ አማካኝነት ... መላው ቤተሰብ አሜሪካ በክብር ለመኖር የሚያስችለው የዲቪ ሎተሪ እድለኛ አሸናፊ ሆነ” [ገጽ 301]። “አሜሪካ በክብር ያኖራል” የሚለው ፈሊጥ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ሆኖ በአገሩ ተስፋ የቆረጠ ትውልድ ድምጽ ነው። በአንጻሩ፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ ያለፈውን ትውልድ ስሜት እንዲህ ገልጸውታል፣

ኑሮ ከፋኝ ብሎ ሲፈልስ ወጣቱ / ኑሮ ከፋኝ ብሎ ሲፈልስ አዛውንቱ

አገር ከፋኝ ብሎ ሲሰደድ ምሑሩ / ሰው መኖር ሲያቅተው በትውልድ አገሩ

“ልሂድ!” “ልውጣ!” ሲሆን የሰው ንግግሩ / “አንተ እንኳን አትሄድም። ባታስበው!” ብሎ
ያገር ፍቅር ደዌ ይዞኛል ቸክሎ!

 

ቀጥተኛ ወንጌል። ኬዳሞም ቀጥተኛ ናቸው። ጳውሎስ “እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም” ይላል [1ኛ ቆሮንቶስ 2:4-5]። “ለቀኝና ለግራ በሚሆን በጽድቅ የጦር ዕቃ” እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን [2ኛ ቆሮንቶስ 6:7]። ዛሬ የቸገረው በቀጥታ የሚናገሩ አገልጋዮች ቍጥር መመናመን ነው። በዓለማዊ ልማድ፣ ሁሉን ማስደሰት ሲሹ፣ ሰሚውን ላይጠቅሙ ከእውነተኛው ወንጌል ተፈናቅለው አፈናቀሉ። ይኸ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የሚታይ ችግር ሆኗል። “እንግዲህ ይህን ሳስብ ያን ጊዜ ቅሌትን አሳየሁን? ወይስ በእኔ ዘንድ አዎን አዎን አይደለም አይደለም ማለት እንዲሆን ያን የማስበው በዓለማዊ ልማድ ነውን? እግዚአብሔር ግን የታመነ ነው፥ ለእናንተም የሚነገረው ቃላችን አዎንና አይደለም አይሆንም። በእኛ ማለት በእኔና በስልዋኖስ በጢሞቴዎስም በመካከላችሁ የተሰበከ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ አዎንና አይደለም አልነበረም፥ ነገር ግን በእርሱ አዎን ሆኖአል። እግዚአብሔር ለሰጠው የተስፋ ቃል ሁሉ አዎን ማለት በእርሱ ነውና፥ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ስለ ክብሩ በእኛ የሚነገረው አሜን በእርሱ ደግሞ ነው” [2ኛ ቆሮንቶስ 1:17-20]። ኬዳሞ በአገር ቤትና በውጭ አገር ሲያገለግሉ የታዘቡት ቀጥተኛ ትምህርት ማስተማር ሰውን ቅር እንዳያሰኝ [ገቢ እንዳያስቀር] ችላ መባሉን ነው። ምእመን ያፈቀደውን ለብሶ ቢመጣ "እግዚአብሔር ከልቤ እንጂ ከልብሴ ምን አለው? ደግሞስ አንተን ማ ፈራጅ አደረገህ?" በሚል ፈሊጥ ዝም ይባላል? "... ስለ ቅድስና በአጽንዖት እስበክ ነበር። ይህንን በማድረጌም በየ ቤተ ክርስቲያኑ ያሉ አንዳንድ መጋቢያን [ ] በቀጣዩ ፕሮግራም ሰው ይቀራል ብለው እንደ ሰጉ ይነግሩኝ ነበር። ነገር ግን የግሳጼ መልእክት እያቀረብኩ እንኳ ሕዝቡ ከመሸሽ ይልቅ ጭራሽ ተጠራርቶ በብዛት ይመጣ ነበር ... ከአገልግሎቴ በኋላም መሪዎቹ፣ እኛ እንዲህ ዓይነት ስብከት ብንሰብክ ሰው ትቶን ይሄዳል ብለን እንሰጋለን" አሉ [ገጽ 235፣ 313]። ይኸ ስለ አገልጋዮች ሕይወት፣ ስለ ትምህርታቸውና ስለ ምእመን ጤና ምን ይነግረናል? አጥርቶ በቀጥታ የሚናገር ስለጠፋ ወይም ስለተገፋ “ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤ አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥ በዘይትም አልለዘበም” [ኢሳ1:6]።

መሪነትና ጾታ። ኬዳሞ ሴቶችን በመሪነት ሥፍራ አይቀበሉም [ገጽ 303-4]። ብዙ ዓይነት አመራር ስላለ፣ መሪ ስንል ምን ማለታችን ነው? ሴቶች የጸሎት ፕሮግራም ማስተባበር እንጂ መምራት የለባቸውም ማለት ትርጉሙ ምንድነው? በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ጥቂትም ቢሆኑ ሴቶች በመሪነት ተጠቅሰዋል [ዲቦራ = መሳፍንት ም.5፤ ጵርስቅላና አቂላ፣ ፌበን [ሮሜ 16:1-3]። በየ ቤተ ክርስቲያኑ የሚታየው ምእመን በአብዛኛው ሴት መሆኑ፣ ሴቶች በአመራር ላይ እንዲገኙ ግድ አይልም? የእግዚአብሔር ሥራ በጸጋ እስከ ሆነ ድረስ ጸጋ የተሰጣቸውን ለይቶ ማሠልጠንና ኃላፊነት ማጋራት አይገባም? ሴቶች፣ ወንድና ሴት ሕጻናትን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስተምሩ መደረጉና ወጣቶቹ ሲያዳድጉ ግን ሴቶችን እንጂ ወንዶችን እንዳያስተምሩ መከልከሉ ትርጕሙ ምንድነው? ይህን የምንለው “መብትና ነጻነት” ወይም “ዘመን ተለውጧል” በሚሉት ስሜት ሳይሆን ከምናየው በመነሳት መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠውን ምሪት በማሰብ እንጂ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን በመነጣጠልና በማቃረን አይደለም። እህቶች ጸጋም እንኳ እየታየባቸው፣ ሥልጠናም ሳያንሳቸው ከውሳኔ አካባቢ ተገልለው በስልክ ተቀባይነት፣ በታይፒስትና በሻይ አቅራቢነት መወሰናቸው ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ጕዳት ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ የዋነኛ ኮሚቴ አባላትን ስም ዝርዝር ማየት ለዚህ ለተዛባ አመለካከት በቂ ማስረጃ ነው። ኬዳሞን የገደዳቸው “የዋና ጽሕፈት ቤት ግቢ [ ] በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቃለ ሕይወት ጋር ግንኙነት የሚፈጥሩ አካላት ሁሉ የሚመጡበት መሆኑ” ነበር [ገጽ 303-304]። ደግነቱ በወቅቱ የነበሩ መሪዎች አሳቡን አልተቀበሉትም።

ለሁለተኛው እትም እርምቶች። ሀ/ “ባተሌ” አጠቃቀሙ ልክ ነው? [ገጽ 299]። ለ/ የኬዳሞ እድሜ በቀጥታ አልተጠቀሰም፤ አባታቸው ጥቅምት 1/1939 ዓ.ም ሲሞቱ የ11 ዓመት ልጅ ነበሩ [ገጽ 39-40]፤ ይህም የትውልድ ዘመናቸውን 1928 ዓ.ም፣ እድሜአቸውን ዛሬ [በ 2009] 81 ያደርገዋል። በ1994 የመልቀቂያ ደብዳቤ ሲያስገቡ 75 ዓመት እድሜ ላይ ነበሩ [ገጽ 305]፤ ዛሬ 90 ያደርሳቸዋል። ገጽ 345 ላይ እድሜአቸው 87፣ ገጽ 357 ላይ ደግሞ 88 ተብሎአል።

“መጽሐፍ ቅዱስ አይከለክልም” ማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይፈቅዳል ማለት ላይሆን ይችላል። ኬዳሞ ሁለተኛ ሚስታቸው ወ/ሮ ታደለች ከሞቱ በኋላ በ80 ዓመት እድሜአቸው ሦስተኛ ሚስት አግብተዋል። ይህን እዚህ የምናነሳው ለትምህርታችን እንዲሆን በመጽሐፋቸው ውስጥ ስለሠፈረ ብቻ ነው [ገጽ 330-340]። የጕዳዩን ቅደም ተከተል እንመልከት፦ የኬዳሞ ሴቶች ልጆች ከቤት ወጥተዋል፤ ወ/ሮ ታደለች ሲሞቱ “ጓዳውን የሚያስተዳድር ትክክለኛ ሰው” አልነበረም። “ከትውልድ አገራቸው ትልልቅ ሰዎች” መጥተው “ሠራተኛ የሚሰጥህን እየተመገብህ መኖር አይመችህም፤ አገልግሎትህን መቀጠል እንድትችል ትዳር መመሥረት አለብህ” አሏቸው። በነገሩ ላይ ለመጸለይ፣ ከቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ከልጆቻቸው ጋር ለመመካከር ወሰኑ። ለሚያገቧት ስድስት መመዘኛ ነጥቦችን አውጥተው ለሦስት ወራት ጸለዩበት። እግዚአብሔር “በመጽሐፍ ቅዱስ በዲፕሎማ የተመረቀች ቀጭን ጠይም ሴት” አሳያቸው፤ ይህን ባዩ በሁለተኛው ቀን ሰኞ ወደ ሆሳዕና መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ለማስተማር ተጓዙ፤ ለትምህርት ቤቱ ዳይሬክተርና የአስተዳደር ኃላፊ አሳባቸውን አካፈሉ። ማክሰኞ ወደ ቦቢቾ ሄዱ፤ እየጸለዩ ሳለ ያቺው “ጠይም ሴት አልጋዬ ላይ ካጠገቤ ተቀምጣ አየኋት፤” የነገሯቸው ሰዎች ግን ያቺን ሴት ሊያገኟት አልቻሉም። ሐሙስ አዲስ አበባ ተመልሰው ለሚቀርቧቸው ሁለት ሴቶች ጉዳዩን አማከሩ፤ አንደኛዋ “ይህችማ ቦሌ ያለችው አልማዝ ናት” አለች። ከአልማዝ ጋር ቢስማሙም ከልጆቻቸው ጋር ሊጣሉ ሲሆን አሳቡን ተውት። አሁንም በህልም “አንዲት ቀይ፣ ረዥም፣ መልከ መልካም ሴትና አንዲት ጠይም፣ ቀጭን ሴት” ሰዎች ሲያመጡላቸው አዩ፤ ቦቢቾ ሄጄ በህልም ያየኋት “ጠይሟ” [ከበቡሽ መኮሮ] እግዚአብሔር የሰጠኝ እርሷን ነው ብለው ወሰኑ። ከበቡሽ ሳትወልድ ባል ሞቶባታል፤ እድሜዋ “አርባ ሊሆን ይችላል”፤ ኬዳሞ ከሃምሳ በላይ እድሜ ነበር የጠበቁት። አንድ “አስተዋይ” የኬዳሞ ዘመድ ወደ ኬዳሞ መጥቶ “እድሜዋ ከ50 ዓመት በላይ የሆነ የኛ አገር ሴት መች ትዳር ትፈልጋለች?” ብሎ የረሱትን አስታወሳቸው። ሆሳዕና ከተማ “ከሠላሳ ምስክሮች በላይ” በተገኙበት በመካኒሳ ቃለ ሕይወት መጋቢ አላምረው የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ፈጸሙ። 

ኬዳሞ ሦስተኛ ለማግባት ማሰባቸው “በወንጌላዊው የቅርብ ሰዎች፣ በትውልድ አገራቸው ሰዎች፣ በጌጃ አጋሮቻቸው፣ አገልጋይ መሪዎችና ቤተሰቦች፣ በመካኒሳ አጥቢያ ቤተ/ክ ሽማግሌዎች፣ በቃለ ሕይወት ቤተ/ክ ልዩ ልዩ አካላት እና መሪዎች” ዘንድ “ጥያቄና ሙግት” አስነሳ። ጥያቄና ሙግት የተነሳው “ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይልቅ የአዲስ አበባ ባህል” መመዘኛ ስለተደረገ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል? [ገጽ 337-338] መጽሐፍ ቅዱስ አይከለክልም ማለት ይፈቅዳል ማለት ነው? ኬዳሞ ቀጥለው እያንዳንዳቸውን በግል ለማሳመን ጣሩ፤ “ሽማግሌዎችም ላቀረብኩት የጋብቻ ጥያቄ እሽ ብሎ መወሰን ከበዳቸው ... ለመጨረሻ ጊዜ ከሽማግሌዎች ጋር ቀርቤ ስነጋገር ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር የሚከለክለኝ ምንም ነገር እንደሌለ ስላመኑ ጠንከር አድርጌ ተናገርኳቸው፤ ‘ለካስ እናንተ መጽሐፍ ቅዱስን የማታውቁ እና የማትታዘዙ ዓለማውያን ሽማግሌዎች ናችሁ። የምትታዘዙት እና የምትመሩት መጽሐፍ ቅዱስን በመከተል ሳይሆን በዓለም ባህል እና ልማድ ነው። እኔንም የምትከለክሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ታዝዛችሁ ሳይሆን በባህል እና ልማድ ተይዛችሁ ነው’ አልኳቸው፤ በመጨረሻም በተደጋጋሚ ሲማከሩ ቆይተው ተስማሙ እና ጋብቻውን ፈቀዱልኝ። በቤተ ክርስቲያን አማካኝነትም ቃል ኪዳኑ እንዲካሄድ ተስማማን።” ከቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችና ከኬዳሞ አቀራረብ ምን እንማራለን?

ሁሉ እንደ ነበረ ነው። ብዙ ለውጥ ቢመጣም፣ ብዙም ለውጥ የለም። ምን ይደንቃል? ዘመንና አድራሻ ይለዋወጣል። የሰው ማንነት ግን እንደ ነበረ ይቀጥላል። አንዱ በሌላው ላይ ለመሠልጠን ይጥራል፤ ነጭ በጥቍር ላይ፣ ጥቂቶች በብዙኃን ላይ፣ በቅኝ አገዛዝ፣ በባሪያ ፍንገላ። ጅብ መቀለብ፣ ዛር፣ አምልኮ ሰይጣን፣ ዛፍ ቅቤ መቀባት ጥንቆላ በኢትዮጵያ በምድር ዙሪያ። በሃዲያ የተነሳው እስላማዊ እንቅስቃሴ በአርባ ዓመቱ፣ በ1984 ዓ.ም.፣ 2 ሺህ የሚያህሉ ወጣቶች ሳውዲ ለሁለት ዓመት ሠልጥነው ኢማም ሆነው ተመለሱ። መስጊድ መሥራት ተፋፋመ፤ ሴቶች ፊታቸውን ሸፋፈኑ። ‘የኔ ብሄር፣ ያንተ ብሄር’ ዛሬም አለ። የያኔው “መሬት ላራሹ!” ዛሬም ምላሽ አላገኘም። "ሰዎች ከነ ዘር ማንዘራቸው ሲኖሩበት በነበረ ምድራቸው እንደ አዲስ እንግዳ መቀበሪያ [አጡ] ... የባለቤታቸውን የእንጀራ አባት መሬት ለመውሰድ አንዱ ጉልበተኛ የኔ ነው ብሎ ከሰሳቸው። በዘመኑ ፍርድ የሚሰጠው ጉቦ እየተበላ ስለነበር ለሰውዬው ተፈረደለት" [ገጽ 162-163]። ሃያ ገንቦ ጠላና አምስት ኮርማ ለባእዳን አምላኮች መሠዋት ቢቀር፣ ለዘመኑ አገልጋዮች፣ ዶላርና ብር በመሠዋት ተተክቷል። የስሕተት ትምህርት አስተማሪዎችና በቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ደንቃራ የሆኑ ሰዎች ዛሬም አሉ፤ ወዘተ።

ሁሉ ደግሞ እንደ ነበረ አይቀጥልም። የአገራችን አንጋፋ ትውልድ በዐይናችን ፊት እያለፈ ነው። አማኑኤል አብርሃም፣ መርኪና መጃ፣ ዘውዴ ገብረሥላሴ፣ ሪቻርድ ፓንክረስት፣ አባተ መኵሪያ፣ ወዘተ። የሕይወት ታሪካቸው ቢቀር፣ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱ ግለሰቦች [አቶ ብርሃኑ ደረሰ፣ አቶ ሺፈራው ወልደሚካኤል፣ ሌሎችም፣ ቄስ ኢተፋ፣ መጋቢ መርዕድ ለማ፣ ወዘተ] ከአስተዳደር፣ ከህገ መንግሥት፣ ከስነ መለኮት፣ ከጾታ-አልባ አመራር፣ ከወቅታዊ ፖለቲካ፣ ከወንጌል ስርጭት፣ ስለ እምነት ከመሰደድ አንጻር፣ ከአገር ከመሰደድና ከወንጌል አገልግሎት አንጻር፣ ከፍትኃዊ ልማት አንጻር፣ ከሚሲዮናዊ ድርጅቶች ጋር ባለው ግንኙነት፣ ከታሪክ፣ ከሚሲዮናዊና ባእድ ባህል፣ ወዘተ፣ አንጻር አንዳንድ ምእራፍ አስተዋጽኦ ቢያደርጉ አንድ ጠቃሚ የመረጃ መድበል ይወጣዋል። በጌታ ያፈራናቸው ሳይበተኑ ማሸጋገር የማያቋርጥ ትጋት ይጠይቃል።

ትናንት የሠራ እግዚአብሔር ዛሬም ይሠራል፤ አልተለወጠም፣ ኃይሉም አልነጠፈም። ኑ፣ እግዚአብሔር በኬዳሞ የሠራውን ሥራ አንብቡና የሥራውን ባለቤት አመስግኑ!

ምትኩ አዲሱ

መጋቢት 25/2009 ዓ.ም. [published 4/3/2017; edited 4/14/17]

በተጨማሪ ያንብቡ