መጻሕፍትን ስንታዘብ፣ ራሳችንን እንታዘባለን

100pagebks

መጻሕፍት = የእውቀት ኮሮጆ። ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ፣ የቋጠሩትን በደረሱበት ይዘራሉ። መጻሕፍት = ሐውልት። ዘመን ይሻገራሉ። እውቀት = በሕይወት ጒዞ ላይ አማራጭ ጠቋሚ...

በኢትዮጵያውያን ዘንድ መጽሐፍ ዳጎስ ሲል ይመረጣል፤ ከግቡነቱ ይልቅ ጠጠር ማለቱ መለፋለፉ ይፈለጋል። በዚህ ዘመን የፊደላት ቊመናና የገጾች ቅያስ ዘርዛራ ሲደረጉ ይስተዋላል። የመጽሐፍ ዳጎስ ማለት ግን ወፈርፈር እንዳለ ገላ የጤና ላይሆን ይችላል። ቃላተኛነትም ያፋፋል፤ ጎበዝ አርታኢ አለመኖር ያዝረከርካል፤ ቶሎ መበልጸግና ዝና ስውር ዓላማ ይሆናል፤ ሁለት መቶ ገጽ ሊሆን የተገባው መጽሐፍ ወደ አራት መቶ ይተረተራል፤ ሃምሳ ብር በመቶ ሃምሳ ይመነዘራል!

በአገራችን ባህል የእውቀት አንድ ተግባሩ ጠላትን መውጊያና ማንበርከኪያ ነው። “እከሌ እኮ አዋቂ ነው!” ትሑት ሳይኾን ራስን ማተለቂያ ነው። ባዕድና ወገንን መለያያ፤ ወገንን መጥቀሚያ፣ ባዕድን ማድሚያ። ባጭሩ፣ እውቀት የጦር መሣሪያ ነው! እውነትን ማወቅና ጥበብን በነፍስ መፈላለግ ከቶውንም አልታሰበ! የሚጠራጠሩ በመገናኛ ብዙሃን የሚጫጫሩትን ይመልከቱ! ትልቊ የድግሪ አገልግል ሲፈተሽ፣ ረሃብ የሚያስታግስ፣ ዐይን የሚገልጥ ፍርፋሪ እንኳ የለበት!

ዳጎስ ያለ ሁሉ ፍሬ ከርሲኪ ነው ማለት አይሁንብን። “ፍቅር እስከ መቃብር” (ሀዲስ ዓለማየሁ) የናጠጠ የ 555 ገጾች ማኅበራዊና ታሪካዊ (አብዮታዊ) ድግስ ነው (መጀመሪያ በ1958 ዓ.ም.፣ እስከ ዛሬ 19 ጊዜ ታትሟል!)። እንደ “መሬት ላራሹ!” ያሉ ዓይነተኛ ለውጦችን አስገኝቷል። “ፍቅር እስከ መቃብር” ሦስት ትውልድ ተሻግሮ ገና አልነጠፈም፤ ሰብዓዊነታችንን እያገነነ። የትረካና የቋንቋን ውበት እያስመሰከረ ነው። ሀዲስን የገዛቸው የሊተራቱር ፍቅር፣ የአገር ፍቅር እንጂ ንዋይ አልነበረም!

በአንጻሩ፣ ፈር ቀዳጁ ሰሎሞን ዴሬሳ ከመቶ ባነሱ የ “ልጅነት” ገጾች፣ ያልታየንና ያልኖርነውን ስላች መንገድ ጠቊሞናል (በተለይ ከአቤ ጒበኛ የደረሰበትን ውረፋ ባንዘነጋ!)። ለውጥ የሚያስገኝ መሠጠት፣ ይዘትና ግቡነት እንጂ ዳጎስ ማለትና አለማለት አይደለም! ለውጥ፣ መከባበርና በአሳብ ዙሪያ መነጋገርን፣ ከድግግሞሽና ከከንቱ ውዳሴ ሱስ መላቀቅን ግድ ይላል። ከመቶ ባነሱ ገጾች ዘመን ተሻጋሪ፣ ለውጥ አብሳሪ መጽሐፍ የሚጽፉ በምድራችን ይነሱ ይሆን?

ከመቶ ባነሰ ገጽ ተጽፈው ዓለምን ያነዋወጡ መጻሕፍት ጥቂት አይደሉም፤ የኮሚዩኒስት ማኒፌስቶ (በካርል ማርክስ፣ 1840 ዓ.ም.)፤ ዘ ፕሪንስ (በኒኮሎ ማክያቬሊ፣ 1503 ዓ.ም.)፤ ባለ-1 ገጽ፣ ዘጠና አምስት ነጥቦች መነሻ ሙግት (በቄስ ማርቲን ሉተር፣ 1509 ዓ.ም.)፤ ዘ ዴዝ ኦፍ ኢቫን ኢልዪች (ቶልስቶይ፣ 1798 ዓ.ም.)፤ ኦፍ ማይስ ኤንድ ሜን (ስታይንቤክ፣ 1929 ዓ.ም.)፤ አኒማል ፋርም (በጆርጅ ኦርወል፣ 1937 ዓ.ም.)፤ እስከ ዛሬ የዘለቁ ማኅበራዊ ነውጦችን አስከትለዋል። የሚገርመው፣ ሁሉም ጸሐፊያን ማለት ይቻላል፣ አውሮጳውያን መሆናቸው ነው!

መጻሕፍትን ስንገልጥ። ራሳችን እንገለጣለን...

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር