በዚህ ክፍል በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መርኪና የጻፉትን በአጭር በአጭሩ በመጥቀስ እንጨርሳለን።

ዘርና ጎሣ። ጊዜው 1948 ሆኖ ከኖርዌጂያን ሉተራን ሚስዮን ጋር እየሠራሁ በነበርኩበት ወቅት ታንዛንያ የተካሄደውን የሉተራን ዓለም ፌዴሬሽን ጉባዔ ለመካፈል አጋጣሚ አገኘሁ …በረርንና ኬንያ ደረስን … በሚቀጥለው ቀን ጧት በአውቶቡስ ተጓዝን …የአውቶቡሱ አሽከርካሪዎች ሁለት አፍሪካውያን ነበሩ። በአውቶቡሱ ውስጥ አንድ እንግሊዛዊ ከነሚስቱ ተቀምጦ ነበር። ከሦስት ሰዓት ጉዞ በኋላ ለራት ቆምንና ከእንግሊዛዊውና ከሚስቱ ጋር ወደ ምግብ ቤት አመራን። በልተን ስንወጣ ከአውቶቡሱ አሽከርካሪዎች አንዱ፦ “እናንተ አፍሪካውያን ናችሁ። እዚህ ነጮች ብቻ እንዲገቡ በተፈቀደበት ቤት ለምን ገብታችሁ ትበላላችሁ” አለን። እኛም፣ “በአገራችን እንደዚህ ዓይነት ነገር የተከለከለ አይደለም” አልን። እኛ በዚህ አገር ፍጹም እንግዶች ነን። የኬንያ አሽከርካሪዎች የአዳም ልጆች አይደሉም? የውጪ ዜጎችስ የማን ዘር ናቸው? እንደዚህ ዓይነት የዘር መድልዎ ለእኛ እንግዳ ነገር ነበር። እንደዚህ ዓይነቱን ልዩነት እግዚአብሔር ያስወግድ ብለን ጸለይን። [ገጽ 45]

አሜሪካ በነበርንበት ጊዜ [1957] ዳግመኛ የጥቁርና የነጭ ልዩነት ተነሣ። ልጆቻቸው በተመሳሳይ ትምህርት ቤት አይማሩም፤ በጸሎት ቤት ውስጥ በአንድነት አይቀመጡም፤ በአንድ አውቶቡስም አብረው አይሳፈሩም። ይህ የእግዚአብሔርን ቃል የሚጻረርና ማንም የማይክደው ሃቅ ነው። በአሜሪካ በቆየሁበት ጊዜ የተመለከትኩት አንድ ደካማ ነጥብና በአዕምሮዬ ለተፈጠረብኝ ጥያቄ መልስ ያጣሁለት ቢኖር የቆዳ ልዩነት ጉዳይ ነበር። “ዓለማውያኖች ደስ የሚላቸውን ያድርጉ፤ ነገር ግን ክርስቲያኖች ለምን በጌታ ቃል ላይ አይቆሙም? “የክርስቶስን ፈለግ ለምን አይከተሉም? ክርስቶስ ራስ ሲሆን፣ እኛ ብልቶቹ ነን። ልዩነት የለም፤ የአሜሪካ ክርስቲያኖች ይህን ማሰብ ይኖርባቸዋል።” [ገጽ 91-92]

እኛ ክርስቶስን ስናምን በጎሣና በዘር ልዩነት ነበረን። የእግዚአብሔር ቃል በመጀመሪያ አዳምና ሔዋንን ፈጠራቸው፣ ከእነርሱ የሰዎች ዘር ሁሉ እንደ መጣ ቃሉ ይናገራል። ስለዚህ እኛ አማኞች ከሆንን በኋላ በፊት ከማናገኛቸው ሰዎች ጋር አብረን በላን፣ ጠጣን፤ አንድነት አደረግን። ስለዚህ በአሜሪካን አገር ያላችሁ አማኞች አሳባችሁን ለውጣችሁ ጥቁሮችን ብታስተምሩ ጥሩ ነው።” [ገጽ 176]

በአጋንንት ላይ ሥልጣን። ነባር ቤተክርስቲያን እያጠናከርን፣ ለአዳዲስ ቤተክርስቲያናት ቤት ለመሥራት የሚመች ቦታ እንመርጥ ነበር። በየሄድንበት ቦታ ቃሉን እንሰብካለን። ሾሻ ወደሚባለው አካባቢ ስንደርስ፣ በርኩስ መንፈስ የሚሠቃይ ሰው ነበር። ብዙውን ጊዜ ሰይጣን እሳት ውስጥ እንዲሁም ወንዝ እየወሰደውም ይጥለው ነበር። ጎረቤቶቹም በሰንሰለት ማሰሩ ሰልችቷቸው ነበር። በሰይጣን የተያዘው አቶ ሻለሞ የሚባለው ሰው ሲሆን፣ ከእኔ ጋር አቶ አንጁሎ የሚባል ወንጌላዊ ነበርና ሰውየውን አይቶት መጽሐፍ ቅዱስን በራሱ ላይ ጭነን እንጸልይለት፣ ሰይጣኑም ይለቅቀዋል አለኝ። ወደ እርሱ ስንጠጋ፣ ሰውየው እያለቀሰ ወደ ጓዳ ገብቶ ተደበቀ። እኛም ተከትለነው “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ከእርሱ ውጣ” ብለን ጸለይንና፣ ደግመንም፣ “ይህ የእግዚአብሔር ሰው ነው። በክርስቶስ ደምና በቃሉ እናዝሃለን፤ ለቅቀኸው ውጣ” አልን። መጽሐፍ ቅዱሱንም በላዩ ላይ ጭነን እንደገና ጸለይን። የሰይጣን መንፈስም ለቀቀውና ሰውየው ደህና ሆነ። ሦስት ዓመት ሙሉ በሰንሰለት ታስሮ የኖረ ሰው በጌታ ኃይል ፈውስን አገኘ። [ገጽ 57-58]

እምነት፣ ታማኝነትና መስዋእትነት። መባ አሰጣጣቸው ሁልጊዜ የሚያስደንቀኝ ነበር። በወቅቱ ገንዘብ ያልያዙ ሰዎች ቃል ሲገቡ ይመዘገባሉ። ገንዘብ ይዘው የመጡትም ወዲያው ይከፍላሉ። ባለፈው ዓመት ቃል ገብቶ የነበረ ሰው ገንዘቡን ሳይሰጥ ቢሞት ሚስቱ አምጥታ ትከፍላለች። ለምሳሌ፣ የአቶ ሳቃቶ ሚስት በሞተች ጊዜ ቃል ገብታ የነበረችውን ገንዘብ ባለቤቷ ከፍሏል። አማኞች ሥራቸው ገንዘብ ሰጥተው የወንጌላዊውን ወጪ ችለው መላክ ብቻ አይደለም። የለበሱትን ልብስ አውልቀው ለጌታ አገልጋዮች እንዲሰጥላቸው ያበረክቱ ነበር። ሰዓታቸውንም ከእጃቸው እያወለቁ ይሰጡ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጫማቸውን እያወለቁ ይሰጡ ነበር። በሬ፣ ላምና በቅሎ የሚሰጡም ነበሩ። ልጆች ደግሞ ያረቡትን ዶሮ ይሰጡ ነበር። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ብዙዎች ወንጌላዊ ሆነው ለማገልገል ራሳቸውን ይሰጡ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ለጌታ ካላቸው ፍቅር የተነሣ እንጂ ማንም አስገድዷቸው አልነበረም …አቶ ኤካሶም “እኔም አንድ ላም አለችኝ። የላሟን ወተት ግማሽ ለጌታ መስጠት እፈልጋለሁ” አለ። በሚቀጥለው ቀንም ለሁለተኛ ጊዜ ቆሞ፣ “እኔ የላሟን ወተት ከጌታ ጋር መካፈል አልፈልግም። ላሟን እንዳለች ለጌታ ሰጥቻለሁ” አለ …በስብሰባው መጨረሻ ቀን አሁንም አቶ ኤካሶ ተነሥቶ፣ “የወላይታ ቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ቦርድ አባል ከምሆን፣ ወንጌላዊ ሆኜ ለማገልገል ራሴን ሰጥቻለሁ። ጌታ ወደ ላከኝ ቦታ ሁሉ እየሄድኩ ማገልገል የተሻለ ነው። ወንጌላዊ ሆኜ በሕይወቴ ሙሉ ጌታን ለማገልገል ራሴን ሰጥቻለሁ። [ገጽ 59-60፣ 82]  

ገንዘብና አገልግሎት። ወደ ዳሞት ፍላሳ ማኅበር ኮርስ ለመጀመር በምንሄድበት ጊዜ ከአቶ አታሎ ቤተክርስቲያን አንድ ሰው፣ “የት ትሄዳላችሁ?” ብሎ ጠየቀን። እኛም “ኮርስ ልናስተምር ነው የመጣነው” ብለን መለስን። ሰውዬውም፣ “በሶዶ ዓመታዊ ጉባዔ የሰጠነው ገንዘብ ተልኳል። አሁን ወደ እኛ መንደር ብትመጡ፣ ሌላ ገንዘብ ዳግመኛ የሚሰጣችሁ የለም” አለን። እኛም መልሰን “እኛ ገንዘብ ለመጠየቅ አልመጣንም፣ የመጣነው የእግዚአብሔርን ቃል ልናስተምር ነው፤ አንተም መጥተህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ” አልነው …ስብሰባው ለሦስት ቀን ቀጠለ። አንዲት እኔ የማላውቃት ሴት ሁልጊዜም ስብሰባ ላይ የምትገኝ ስትሆን፣ ከፊት ለፊት ተቀምጣለች። እርሷም በወገቧ ያለውን መቀነቷን ፈታችና ገንዘብ አውጥታ ሰጠች። ቀጥላም የአንገት ልብሷን/ነጠላዋን፣ በቀጣዩም ጊዜ ሻሽዋን ሰጠች። በመጨረሻም፣ የፈረስ መጋለቢያ ሱሪዋን ሰጠች። “ገንዘብ የሚሰጥ የለም” ይል የነበረው ሰው በየቀኑ በበቅሎው ላይ እየተቀመጠ ይመጣና ስብሰባውን ይካፈል ነበር። በቅሎውንም ከደጅ ሣር በሚበላበት ቦታ ያስረዋል። በኮርሱ መጨረሻ ቀን ተነሥቶ ቆመና “አስቀድሜ የምትሰበሰቡት ገንዘብ ለመውሰድ ነው። ማንም ግን የሚሰጣቸው የለም ብዬ ነበር። አሁን የእግዚአብሔር መንፈስ በቅሎዬን እንድሰጥ አሳስቦኛል። ከጌታ መንፈስ ጋር መከራከር አልችልምና በቅሎዬን ሰጥቻለሁ” አለና አምጥቶ ሰጠ። እኛም ጌታን አመሰግን።[ገጽ 79-80]

የሴቶች ጉዳይ። ሴቶች ቸል ይባላሉ ወይ? በቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ክትትል ሚስ በርግስተን ከወላይታ ወረዳ አብያተ ክርስቲያናት ልጃገረዶችን መርጠው መጽሐፍ ቅዱስና እጅ ሥራ ብዙውን ጊዜ ሹራብ ሥራ እንዲማሩ ተደረገ። ሴቶች ወገባቸውን የሚያስሩበትንና ለልጆቻቸውም ደግሞ ሹራብ ይሠራሉ። ሥልጠና አግኝተው የሚሄዱ ልጃገረዶች በተራቸው ሄደው በቤተክርስቲያን የሚገኙትን ሴቶች መጽሐፍ ቅዱስንና የሹራብ ሥራን ያስተምራሉ። [ገጽ 68]

ቤተክርስቲያንና መንግሥት። በ1953 ዓ.ም. አንድ ጊዜ በአካባቢያችን የብዙ ሕዝብ መታሠር ነበር። ክርስቲያኖቹም መልሰው፣ “መንግሥት ሃይማኖት የግል አገር የጋራ መሆኑን በሕገ መንግሥቱ ደንግጓል። እንዴት እንደ ከብት እየነዳችሁን በእስር ቤት ታጉሩናላችሁ?” አሉ …[አዲስ አበባ ሄደን] ማመልከቻ ለማቅረብ ወሰንን። የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘን ከስድስት ኪሎ ወደ ታላቁ ቤተመንግሥት አመራን። ሁላችንም አቤት እያልን እንጮህና እናለቅስ ነበር። ንጉሡም ጩኸታችንንና ለቅሶአችንን ሰምተው ወደ እርሳቸው እንዲያቀርቡን ወታደሮቻቸውን አዘዙ። [ገጽ 132]

ቤተክርስቲያንና ልማት። የወንጌል ሥራና የዕድገት/የልማት ሥራ ጎን ለጎን የሚሄዱ ናቸው። በአውራጃችን ውስጥ መሃይምነትን ለማጥፋት 738 ቤተክርስቲያናት ትምህርት ቤቶችን አዘጋጅተው አስተምረዋል። ዶክተሮች፣ አስተዳዳሪዎች፣ አስተማሪዎች፣ የሕግ ባለ ሙያዎች እና ሌሎች በርካታ ምሁራን ከእነዚያ ቤተክርስቲያን መሥርታ ካስተማረቻቸው ትምህርት ቤቶች የፈለቁ ናቸው። ለወላይታ በዘመናዊ ትምህርት መራመድ በሩን የከፈተችው ቤተክርስቲያን ነች። [ገጽ 123]                             March 2009