ይህ የምሰማብህ ምንድር ነው?

ደግሞም ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ መጋቢ የነበረው አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ በእርሱ ዘንድ። ይህ ሰው ያለህን ይበትናል ብለው ከሰሱት። ጠርቶም። ይህ የምሰማብህ ምንድር ነው? ወደ ፊት ለእኔ መጋቢ ልትሆን አትችልምና የመጋቢነትህን ሂሳብ አስረክበኝ አለው። መጋቢውም በልቡ። ጌታዬ መጋቢነቱን ከእኔ ይወስዳልና ምን ላድርግ? ለመቈፈር ኃይል የለኝም፥ መለመንም አፍራለሁ። ከመጋቢነቱ ብሻር በቤታቸው እንዲቀበሉኝ የማደርገውን አውቃለሁ አለ።

የጌታውንም ባለ ዕዳዎች እያንዳንዳቸውን ጠርቶ የፊተኛውን።

ለጌታዬ ምን ያህል ዕዳ አለብህ? አለው።

እርሱም፦ መቶ ማድጋ ዘይት አለ።

ደብዳቤህን እንካ ፈጥነህም ተቀምጠህ አምሳ ብለህ ጻፍ አለው።

በኋላም ሌላውን። አንተስ ስንት ዕዳ አለብህ? አለው።

እርሱም፦ መቶ ጫን ስንዴ አለ።

ደብዳቤህን እንካ ሰማንያ ብለህም ጻፍ አለው።

ጌታውም ዓመፀኛውን መጋቢ በልባምነት ስላደረገ አመሰገነው የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸውና። እኔም እላችኋለሁ፥ የዓመፃ ገንዘብ ሲያልቅ በዘላለም ቤቶች እንዲቀበሉአችሁ፥ በእርሱ ወዳጆችን ለራሳችሁ አድርጉ። ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፥ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው። እንግዲያስ በዓመፃ ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ እውነተኛውን ገንዘብ ማን አደራ ይሰጣችኋል? በሌላ ሰው ገንዘብ ካልታመናችሁ፥ የእናንተን ማን ይሰጣችኋል? ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ገንዘብንም የሚወዱ ፈሪሳውያን ይህን ሁሉ ሰምተው ያፌዙበት ነበር። እንዲህም አላቸው፦ ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኵሰት ነውና። [የሉቃስ ወንጌል 16: 1-15] 

እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን። [ሮሜ 14፡12]