ርዕሰ አንቀጽ

እንዲጠራ እሳት ይለኩስበታል

በእምነት የቀደሙን የደረሰባቸውን ተቃውሞ እንዴት ተቋቋሙ? ጓዝ ንብረታቸውን ተዘርፈው ማምለኪያዎቻቸው ፈራርሰው በግርፋት፣ በእስራትና በሞት ተበታትነው እንዴት አንሠራሩ? እንዴትስ ለቀጣዩ ትውልድ የድል ዜና አበሰሩ? ተመሳሳይ ሁኔታ ዛሬ ቢከሰት አዲሱ ትውልድ ምን ያህል ዝግጁ ነው? በዚህ ዘመን ብዙ የሚያምሩ የማምለኪያ ሕንጻዎች ታንጸዋል። የማይታሰቡ የነበሩ ብዙ የአገልግሎት ዘርፎች ተጀምረዋል። ማምለኪያ ቦታዎች ቢዘጉ ወይም ቢወሰዱ፣ ባንክ ውስጥ ያለ ገንዘብ ወይም “ሚኒስትሪ” ቢታገድ፣ መሪዎች በሐሰት ተወንጅለው እስር ቤት ቢወረወሩ፣ አምልኮና የቤተክርስቲያን አሠራር ሕገወጥ ነው ቢባል፣ ወንድም ወንድሙን አሳልፎ ቢሰጥ፣ የወንጌልን መሠረት በሚንድና ንጽሕናን በሚቀናቀን ጉዳይ ላይ ስምምነት ቢጠፋ መጽናናትና መጽናት እንዴት ይቻላል?

ድንገተኛ ለውጥ የማይመጣ ከመሰለን የወንጌልን አስተምህሮ እንደሚገባ አላጤንም፣ የታሪክን ሒደት አላገናዘብንም ማለት ነው። ፈንጠር ብለን ለየብቻ ድንኳኖቻችንን ተክለን ከሆነ የተዘለልን እንዳይመስለን። በሌላው ላይ የደረሰው ለኔም አይቀርልኝም ባንል ከጅምሩ ተታልለናል። ባለመያያዛችን ለጥቃት ተጋልጠናል፤ ክርስትና ማኅበራዊና ተጠሪነትን የሚጠይቅ መሆኑን ዘንግተናል። አንድ ሁኔታ ድንገተኛ የሚሆንብን ከተጠራንበት ጥሪ ውጭ በሌላ ብዙ ነገር ልባችን ሲያዝና ሲከብድ ነው። ልምምድ ያቆመ ስፖርተኛ ብድግ ብሎ ለመሮጥ ክብደቱ ወደ ኋላ እንደሚጎትተውና ስፖርቱ የሚጠይቀውን ማሟላት እንደሚሳነው ማለት ነው። በአእምሮአችሁ የተዘጋጃችሁ ሁኑ የተባልነው አንዱም ለዚሁ ነው።

እርግጥ እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልም። ሕዝቡን አይጥልም ማለት ግን ላለመዘጋጀት ወይም በሚታየው ላይ ልብን ለመጣል ሰበብ ሊሆነን አይገባም። ዘመኑን ዋጁ የተባልነው ቀኖቹ ክፉዎች ስለሆኑ ነው፤ ንቁ የተባልነው የሚያባብሉ እንቅልፍ የሚያስወስዱ ብዙ ሁኔታዎች ስላሉ ነው። ሁለት አስተማማኝ ነገሮች የእግዚአብሔር ታማኝነትና የዓለም አስተማማኝ አለመሆን ናቸው። ዐይኖቻችን ያረፉባቸውን ብንነጠቅ የሚቀርልን ምንድነው? የሚቀርልን እግዚአብሔር በመንፈሱ በውስጣችን ያረገልን እምነት፣ ተስፋና ፍቅር ናቸው። እግዚአብሔር ምን ጊዜም የታመነ፣ ተስፋ ሰጭ አምላክ ነው። “የሚታየው የጊዜው ነውና፥ የማይታየው ግን የዘላለም ነው … በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን።”

እምነት ደግሞ በእሳት ይፈተናል። ግልጽ አቋም መውሰድ ወይስ ተመሳስሎ መኖር? የማያቋርጥ ምርጫ ይቀርብልናል። የመስቀሉን መንገድ ለመጓዝ የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል፤ ጸጋው ይረዳናል። የቱን መምረጥ ተለማመድን? መቸም ቢሆን ያልተለማመድነውን መሆን አንችልም። ይኸ ትውልድ የቀደመውን ይጠይቅ፤ ይጸልይ። ያኛውም መከራና ድሉን ለዚኛው ይንገር፤ አብዝቶ ይጸልይ። እርሱ ብቻ አምላክ እንደ ሆነ ለማስታወቅ፣ ከእርሱ ሌላ ሕዝቡ የተደገፈበትን፣ ልቡን የጣለበትን እግዚአብሔር ዘወር ያደርገዋል። እምነቱ እንዲጠራ፣ ምስክርነቱ እንዲበራ እሳት ይለኩስበታል። ሰዓቱ ደርሶ ይሆን?