ርዕሰ አንቀጽ

ጆሮ ያለው ይስማ!

ከታሪክ በስተ ጀርባ እግዚአብሔር ቆሞአል። ከበስተ ጀርባ ቆሞ ቀናቱን ከነምግባራቸው ያሰማራቸዋል። “ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ያለ እርሱ አልሆነም።” አደራረጉን በሙሉ መረዳት ባይቻልም፣ የጣቱን አሻራ ሳይተው የቀረበት ጊዜ የለም። እግዚአብሔር ታሪክ ፈጣሪ፣ መሪና ተቆጣጣሪ ነው። “ብርሃን ይሁን!” ያለ ዕለት ታሪክ ተጀመረ። “ተፈጽሞአል!” ሲል ፍጻሜ ይሆናል። “እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ [ኢሳ 46፡9-10፤ ዘፍ 1፡2-3፤ ራእይ 21፡5-6]።”

ኢየሱስ አልዓዛርን ከሙታን እንዳስነሳ ሰሙ። “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ አሉ። በዚያችም ዓመት ሊቀ ካህናት የነበረ ቀያፋ የሚሉት ከእነርሱ አንዱ። እናንተ ምንም አታውቁም፤ ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም አላቸው። ይህንም የተናገረ ከራሱ አይደለም፥ ነገር ግን በዚያች ዓመት ሊቀ ካህናት ነበረና ኢየሱስ ስለ ሕዝቡ ሊሞት እንዳለው ትንቢት ተናገረ፤ ስለ ሕዝቡም ሁሉ አይደለም፥ ነገር ግን የተበተኑትን የእግዚአብሔርን ልጆች ደግሞ በአንድነት እንዲሰበስባቸው ነው እንጂ [ዮሐ 11፡46-52]።” ሰዎች የሚሉትን ሲሉ፤ ሳያስተውሉ፣ የጌታን ፈቃድ ይፈጽማሉ።

ኢየሱስን በጲላጦስ የፍርድ ወንበር ፊት አቀረቡት። በደል ባያገኝበትም ጲላጦስ ኢየሱስን ለስቅላት አሳልፎ ሰጠው። “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ጽሕፈት በዕብራይስጥና በሮማይስጥ በግሪክ ቋንቋዎች ጽፎ በመስቀሉ ላይ አኖረው። የአይሁድ ካህናት አለቆች ጲላጦስን። እርሱ። የአይሁድ ንጉስ ነኝ እንዳለ እንጂ የአይሁድ ንጉሥ ብለህ አትጻፍ አሉት። ጲላጦስም። የጻፍሁትን ጽፌአለሁ ብሎ መለሰ [ዮሐ 19፡19-22]።” ኢየሱስን ከመስቀል አውርደው እነ ማርያም እያዩ ቀበሩት። “በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና … ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት። ጲላጦስም። ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው። እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ [ማቴ 27፡ 62-66]።” መቃብሩን በራሳቸው ጠባቆች አስጠበቁ። የኢየሱስ ከሳሾች ሳያስቡ ለትንሣኤው ምስክሮችን አኖሩ። “… ከጠባቆቹ አንዳንድ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩ …አለቆችም ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው። እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ” አሏቸው [ማቴ 28፡11-15]። እንዲያ ይበሉ እንጂ ሁላቸውም የሆነውን አውቀዋል። ተኝተው ሌባ እንደ ሰረቀው እንዴት አወቁ? ኢየሱስ ግን እንደ ተናገረው ተነሥቷል! የኢየሱስን ትንሣኤ ለማፈን ያልተደረገ ሙከራ የለም። እግዚአብሔር ራሱን ያለ ምስክር የተወበትም ጊዜ የለም። እውነቱን ለማጥፋት በሞከሩ መጠን እውነቱ አሸነፈ። እያሸነፈ ምሥራቹ ለኛ ደረሰን። ለሚቀጥለው ትውልድ የማድረስ አደራ ተጥሎብናል።

አንድ ሰው ለሁሉ ይሞት ዘንድ ተገባ። “የአይሁድ ንጉሥ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ” ለሁሉ እንዲታይ በጎልጎታ ተራራ ላይ። በሁሉ እንዲነበብ በዕብራይስጥ በሮማይስጥና በግሪክ ቋንቋዎች ተጻፈ፤ ጽሕፈቱን ሊሽር ማንም አልቻለም። የሮምን ንጉሥ ሥልጣን ሊያስከብር የወጣ ጲላጦስ፣ “የጻፍኩትን ጽፌአለሁ” በማለቱ የነገሥታት ንጉሥ ኢየሱስን አንግሦ ተመለሰ። ከቄሣር ሌላ ንጉሥ አናውቅም ያሉ አይሁድ፣ ከኢየሱስ ሌላ ንጉሥ የለም ተባሉ። ዓለምን ታንቀጠቅጥ የነበረች ሮም ዛሬ መንግሥቷ ወዴት አለ? “በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ …መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቶችም ሁሉ ይገዙለታል ይታዘዙለትማል …መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን …ሁሉ በእርሱ ሆነ፣ ከሆነውም አንዳች ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፣ ጨለማም ከቶ አላሸነፈውም [ኢሳ 46፡10፤ ዳን 7፡27፤ ማቴ 6፡13፣ለ፤ ዮሐ 1፡3-5]።”

ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ። መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም እንደ አይሁድ ባህል ሽቱ ሊቀቡት ማልደው ወደ መቃብሩ መጡ። በመንገድ ሳሉ “ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል?” ይባባሉ ነበር። ድንጋዩ እጅግ ትልቅ ነበርና፤ አሻቅበውም አይተው ድንጋዩ ተንከባሎ እንደ ነበር ተመለከቱ። ከመድረሳቸው አስቀድሞ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ አንከባሎታልና። ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። እርሱ ግን፦ አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ። እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ፤ አላቸው።

የትንሣኤው ኢየሱስ ለማርያም ታዬ። ለደቀመዛሙርቱ በገሊላ ወንዝ ዳርቻ ታዬ፤ ተሰብስበው በነበረበት ክፍል ውስጥ ደጁ ተዘግቶ ሳለ ታዬ። የታሸገ መቃብር እንዳይወጣ ሊያግደው አልቻለም፤ የተዘጋ ደጅ እንዳይገባ ሊያግደው አልቻለም። የተከፈተ ልብ ሊያዘገየው አልቻለም።  በኤማሁስ መንገድ ላይ ታዬ። በደማስቆ መንገድ ላይ ታዬ። በተራራ ላይ ታዬ፤ በሸለቆ ውስጥ ታዬ። ከምድር በታች ተገኘ፤ በሰማየ ሰማያት ተገለጠ። በማለዳ ታዬ፤ በቀትር ታዬ፤ በውድቅት ሌሊት ታዬ። በፍጥሞ ደሴት ላይ ታዬ። በውሃ ላይ፣ በየብስ ላይ፣ በአየር ላይ ታዬ። እያዩት አረገ፤ የምድር ስበት ሊይዘው አልቻለም። በነጳውሎስ ዘመን ታዬ፤ በቅድመ አያቶቻችን ዘመን ታዬ። በኛም ዘመን ታዬ። በእስያ ታዬ፤ በአውሮጳ ታዬ፤ በአፍሪካ ታዬ፤ በኢትዮጵያ ታዬ። ያልታየበት ዘመንና ሥፍራ አልተገኘም። በህልም ታዬ፤ በውን ታዬ። ለብዙዎች ታዬ፤ በብዙዎች ታዬ። ኢየሱስ ተነሥቷል። ኢየሱስ ሕያው ነው። ሁሉ እንደ ተናገረው ሆነ፤ ሁሉ እንደ ተናገረው ይሆናል። ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ ብሏል፤ ሁሉ አዲስ ይሆናል። ተመልሼ እመጣለሁ ብሏል፤ ተመልሶ ይመጣል። መምጣቱም መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ እንዲሁ ይሆናል። የሚያምንብኝ የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ይሻገራል ወደ ፍርድ አይመጣም ብሏል፤ እንደዚሁ ይሆናል። ስለ ኃጢአታችን ስርየት ሞተ፣ ተቀበረም፤ ስለ ጽድቃችን በሦስተኛው ቀን ተነሣ። ሞትን ድል ነሣ። በኃጢአትና በአጋንንት ለታሠሩ ምሕረትን አወጀ። ጆሮ ያለው ይስማ!