ርዕሰ አንቀጽ
መጠየቅ ክልክል ነው?

ልጅ አፍ ከመፍታቱ ጥያቄ ማዥጎድጎድ ይጀምራል። ወፍ ስትበርር እንዴት አትወድቅም? ልጅ ከየት ነው የሚመጣው? ቡና መጠጣት መጥፎ ነው? ቢራቢሮ ለምን ቢራቢሮ ተባለች? ከማን ጋር እያወራሽ ነው? [እየጸለይኩ ነው]፤ እየጸለይኩ ምንድነው? [ለእግዚአብሔር መናገር ነው] እግዚአብሔር የት ነው ያለው? [አንተ ልጅ እንዳትቀሠፍ]፣ እንዳትቀሠፍ ምንድነው? በራዲዮ የሚያወሩ ለምን አይታዩም? ማቆሚያ የለውም። በመጠየቅ ብዛት ከአካባቢው ጋር ይተዋወቃል፤ በእውቀት ያድጋል። ካልተበረታታ ግን የተባለውን ሁሉ አለጥያቄ መቀበል ወይም በሆድ መያዝ ይማራል። ከቤተሰብ ቀጥሎ ትምህርት ቤትና ቤተ ሃይማኖት ይህን የመጠየቅ ፍላጎት ያበረታታሉ ወይም ያከስማሉ።

ከቄስ ትምህርት ቤት እስከ ዘመናዊው፣ የተባለው ሳይለወጥ ማስተላለፍ የኖረ ባሕል ነው። የተማሪ መብዛት፣ የአስተማሪ ጥራትና ቁጥር ማነስ ዛሬ ለጥያቄና ለመልስ ያላመቸ ሁኔታን ፈጥሯል። ጥያቄ የአስተማሪ ብቻ ድርሻ እንደ ሆነ። አስተማሪ ባብዛኛው በጥያቄ ጠልፎ ለመጣል የሚያደባ ፍጥረት መስሏል። ማርክ እንዳያስቀንስ የአስተማሪን ቃል የመጽሐፍን አባባል አለመለወጥ ይመረጣል። ሴቶች ዝምታ ነው የሚያምርባቸው ተብሏል። አለመጠ-የቅ፣ ድብቅነት፣ ዛቻና ኩርኩም በበዛበት፤ ዜጋ መጠየቅ ይፈራል፤ የአጠያየቅን ሥርዓት ሳይማር ያድጋል፤ ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ይህንኑ መልሶ ተግባራዊ ያደርገዋል።

በመረጃ የተደገፈ ጥያቄ መጠየቅና በመረጃ የተደገፈ መልስ መሻት የዘመናዊ ትምህርት አንድ ገጽታ ነው። መቸ? ማን? ለምን? እንዴት? የት? ምን? ጥያቄ መጠየቅ ደግሞ ዋጋ ያስከፍላል፤ የአስተሳሰብና የአኗኗርን አቅጣጫ ያስቀይራል። ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? ከመቶ ሺህ በላይ ሕጻናት እንዴት አዲስ አበባ ጎዳና ላይ ተገኙ? ኢትዮጵያውያን በሳውዲ እንዲህ ሲንገላቱ የቤተክርስቲያን መሪዎች ለምን ድምጽ አላሰሙም? ከወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት መሓል ምዕራባዊ ባህላዊ ክርስትናን እንዴት ማጥራት ይቻላል?

ጥያቄ መጠየቅ ሕልውናን ማስከበርያም ነው፤ ፈጣሪ ከእንስሣ ለይቶ አእምሮ የሰጠን ለዚሁ ነው። አጠያየቅ ማወቅ ግን ያስፈልጋል። ተገቢ የሆነ ጥያቄ አለ፤ ተገቢ ያልሆነ ጥያቄ አለ። ለምሳሌ፣ አቶ አለባቸው አቶ ኩራባቸውን ቢፈነክት። የአቶ አለባቸው ጎረቤት ስም ማነው ብሎ መጠየቅ ከሚያበሳጭ ሌላ ለተከሰተው ሁኔታ ፋይዳ የለውም። የሚጠቅመው ይልቅ፣ አቶ ኩራባቸው እርዳታ አገኘ? ተጎዳ? ፖሊስ ተጠራ? ማለቱ ነው። በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ተማሪዎች ብዙ ጥያቄ ጠይቀዋል። ለምን በዘውድ እንገዛለን? ለምን እንደ በለጸጉት አገሮች የመናገር የመጻፍና የመደራጀት መብት አይኖረንም? ሕዝባዊ መንግሥት ለምን አይኖረንም? ይህ ጥያቄአቸው እንዴትና በማን እውን እንደሚሆን ግን አላሰቡበትም። ሳይቆይ ጥያቄአቸውን በሚቃረን ተግባር ተሠማሩ፤ ውጤቱም መራራ ሆነ። መጠየቅ መልካም ነው፤ ተገቢና በእውነታ የተፈተነ ጥያቄ መጠየቅ ግን የተሻለ ነው፤ አለዚያ አለመጠየቅ ይሻላል። ለዚህም ነው አንዳንዱ አለማወቁ እንዳይታወቅበት ጥያቄ የማይጠይቀው፤ ለዚህ ነው ዝምታው አዋቂ የሚያስመስለው።

በዓመቱ መግቢያ፣ ከወደ አቃቂ ቅዱስ ገብርኤል፣ መስቀል ከሰማይ ወረደ የሚል ዜና ተሰምቶ ነበር [አዲስ አድማስ መጽሔት፣ መስከረም 2006 ቅጅ ይመልከቱ]። ዜናው ጥያቄ የፈጠረባቸው ነበሩ፣ መስቀሉ ከሰማይ ለመውረዱ ይጣራ ማለታቸው ግን ሊያሳስብ ወይም ሊያስፈራ አይገባም ነበር። [ከሕዋው ተወርውረው ምድር ላይ የሚወድቁ ፍንካቾች በየጊዜው ታይተዋልና።] የቤተክርስቲያኑ መጋቢ ሀዲስ ግን "የማይሞከር ነው" ብለው ጠያቂውን ፊት ነሥተዋል። በቀን እስከ ሦስት ሺህ ሰው ለማየት እንደሚጎርፍ ገልጸው ለሕዝብ የሚታየው ጭቃው መንገድ ከተሠራ በኋላ ፓትርያርኩ በተገኙበት ህዳር 11/2006 ነው ብለዋል።

ይህ ዜና እውነት ነው ብለን እንቀበል ወይስ ለማጣራት ጥያቄ እንጠይቅ? ገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ እንደ ሆነስ? በነገራችን ላይ፣ ዘረፋ ከመብዛቱ የተነሳ በታህሳስ ወር አብያተ ክርስቲያናት "ካሽ ሬጂስተር" እንዲያስገቡና በዚያ ብቻ ገንዘብ እንዲሰበስቡ ትእዛዝ ወጥቷል። [እውን ግን "ካሽ ሬጂስተር" ያድናል? ታዲያ ለምን እስካሁን የነጋዴዎችንና የመንግሥት ባለ ሥልጣናትን ዘረፋ ማስቆም አልተቻለም?] ከአቃቂ ገብርኤል የተሰማው ዜና ግራና ቀኙን የማያውቀውን ሕዝብ ማታለልና የእግዚአብሔርን ስም መቀለጃ ማድረግ ነው። ፓትርያርኩስ በተቀጠረው ቀን ተገኝተው ምን ሊሉ ይሆን? ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀል ፎቶ ባሁኑ ሰዓት በአስር በአስር ብር እየተሸጠ ይገኛል። [ከምኔው ፎቶ ተነሳ? ከምኔው ንግድ ተጧጧፈ? ፎቶውን አጥቦ ያባዛው ማነው? የተባዛው ፎቶ ብዛቱ ምን ያህል ነው?] ይህ ሁሉ ግርግር ባጭሩ ቤተክርስቲያን ምን ያህል በዓለማዊ ብልሃት ተዘፍቃ ከአዳኟና ከጌታዋ እንደ ተራራቀች የሚያሳይ ነው። ምነው ጌታ ደርሶ ጅራፉን ባነሳና ቤቱን ከለዋጮችና ከሻጮች ባጸዳ!

እንግዲህ እንዳይጠየቁ ገና ለገና "አትመራመር፤ አትጠይቅ" ብሏል ይላሉ። የቱ ጋ እንደ ተጻፈ ግን ራሳቸውም አያውቁም። እንኳን ሰው እግዚአብሔርም "ጠይቁኝ ... ኑና እንዋቀስ" ብሏል እኮ [ኢሳይያስ 45፡11፤ 1፡18]። መሪ ዕውር ከሆነ፣ ተመሪ ምን ይሁን? የሚሉትን ካሉ በኋላ ለምን? እንዴት? ሲባሉ "ይኸ በእምነት ነው" ይላሉ። እምነት በጭፍን እንደሚሆን ያስመስላሉ። እንዳትቀሠፍ ይኸ ክፍል ምሥጢር ነው እያሉ በፍርሃት ይተበትባሉ። የኢየሱስ ሞትና ትንሣዔ በመረጃ የተደገፈ፤ በታሪክና በተከታዮቹ የሕይወት ልምድ የተመሰከረ ሆኖ እያለ የክርስትናን መሠረት ያንጋድዳሉ።

ጥያቄ መፍራት ከበድንነት አይሻልም። ለመሆኑ ሰባኪው እሑድ የሰበከው ስለ ምንድነው? በቂና አሳማኝ መረጃ አቅርቧል? ከአጠያየቅ ይፈረዳል፣ ከአለባበስ ይቀደዳል። "መንፈስን ሁሉ አትመኑ፣ ... መርምሩ" ተብለናል፤ 1ኛ ዮሐንስ 4፡1።

አገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ በሚጠየቁና በማይጠየቁ ጥያቄዎች ዓይነት ማስረዳት ይቻላል። የራስን አቋም እስካልነካና እስካላናጋ ድረስ ለምን? እንዴት? ብሎ መጠየቅ ይፈቀዳል። አለዚያ መወነጃጀል ይጀምራል። ባሁኑ ወቅት ለተገቢው ጥያቄ ተገቢ መልስ ከመሻት ይልቅ በቡድንና በውሸት አጥር መካለል የተመረጠበት ምክንያቱ ይኸው ነው።

ሌሎች ምሳሌዎችን እንጥቀስ። ገጣሚና ጸሐፌ-ተውኔት ዶ/ር ፍቅሬ ቶለሳ "እኛ ኢትዮጵያውያን ታላቅ ሕዝብ ነን። እራሳችንን ዝቅ ማድረግ አይገባንም" ብሎ ይጀምርና "ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁድ ማስተማር ሳይጀምር ለኢትዮጵያውያን ለሶስት አመት ያክል ከ22 ዓመቱ እስከ 25 አመቱ ድረስ" አስተምሯል ይለናል [ኢትዮሚድያ ድረገጽ ይመልከቱ]። ለዚህ የቀረበው መረጃ የተከፋፈለውን ትውልድ ለማስማማት "ኢትዮጵያውያን ታላቅ ሕዝብ ነን" ከሚል አገር-ወዳድ አስተሳሰብ የመነጨ እንጂ ታሪካዊና ሳይንሳዊ አዎንታ ያገኘ መረጃ አይደለም። እንደዚሁ፣ የፊዚክስ ፕሮፌሰር ዶ/ር መስፍን አረጋ "አማሮምኛ/ሰገላዊ አማርኛ" ብለው በፈጠሩት አዲስ ቋንቋ "እግዚአብሔር" መጠሪያ ቃሉ የተንዛዛ ስለሆነ "አብሔር፣" ክርስቶስ "ወልደሔር፣" ክርስትና [ባዕድና ግሪክኛ ስለሆነ] "ደቀሔርፍናም፣" ቤተክርስቲያን "ቤተሔር፣" ይሁን ብለዋል [ቋጠሮ ዶትኮም፣ ኦገስት 2010]። ማህበረሰብ በረጅም ትግሉና ሂደቱ ያካበተውን ግንዛቤ ሽረው እኚሁ ግለሰብ በዘፈቀደና ባቋራጭ እንዲህ ብዬአለሁ እናንተም እንዲሁ በሉ ይሉናል። የሚያስገርመው ሁለቱም ምሑራን አገር ወዳድ። የስድሳ ስድስቱ አብዮት የወለዳቸው። ከጀርመናዊው ካርል ማርክስ ተቀብለው፣ በሳይንስ ያልተደገፈ ስለሆነ ሃይማኖት አደንዛዥ ዕጽ ነው ሲሉን ከነበሩት መሓል መነበራቸው ነው። እኛስ አገር አይወዱም እንዳንባል ፈርተን ከመጠየቅ እንቆጠብ?

አጠያየቅ ማወቅ አስፈላጊ ነው፣ መረጃ ሲገኝ ደግሞ ቅንና ፈቃደኛ እንደ መሆን ከግል ዓላማ ጋር ስላልገጠመ ብቻ ሰበብ መፍጠር እውነትን ክዶ መንከራተትና መዘባረቅ ነው።

ብዙዎቻችን መጽሐፍ ቅዱስ የምናነብበው ጥያቄ ፍለጋ ሳይሆን መልስ ፍለጋ ብቻ ነው። መልሱ የጠበቅነው ካልሆነ የሚስማማንን እስክናገኝ እናውደለድላለን፤ መልሱ አሁንም ካልጣመን ቃሉ ያላለውን እናሰኘዋለን። ቀድሞውንም እውነትን ፍለጋ አልወጣንማ! ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄም እንዳዘለ ያስተዋልን ስንቶች ነን? እስቲ እነዚህን እንመልከታቸው፦ ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል? [ማቴዎስ 16፡26]። የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን? [ዘፍጥረት 4፡9]። እውነት ምንድነው? [ዮሐንስ 18፡38]። የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ? [ሉቃስ 10፡25]። ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? [መዝሙር 139፡7]። ኢየሱስ፦ ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው ...እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? [ማርቆስ 8፡ 27፣ 29]። "ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለው? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው? ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው?" [2ቆሮንቶስ 6፡14-16]። እነዚህን ጥያቄዎች በጥሞናና በቁም ነገር የሚያሰላስል። ዋጋ ቢያስከፍልም እውነቱን ለማወቅ የሚሻ ማንም፣ አስተሳሰቡና አኗኗሩ እንደ ነበረ አይቀጥልም።

ሌላም ጉዳይ አለ። ሳይንስ ብቻ ነው ጥያቄ መጠየቅና ትክክለኛ መልስ መስጠት የሚችል? እውን ሳይንስና ሃይማኖት ይቃረናሉ? ከሀዲዎቹ የማህበረሰብ ጥናት ሳይንቲስቶች ሮድኒ ስታርክና ዩርገን ሃበርማስ፤ አውሮጳ ከኋላ ተነስታ ቻይናና ዐረቦችን በሳይንስ ምርምርና ውጤት የቀደመችው ክርስትናን በመቀበሏ ነው ብለውናል። ሳይንስ እውን እግዚአብሔርን መካድ ይጠይቃል? ይህን አስተሳሰብ የሚያራምዱ ከታዋቂ ሳይንቲስቶችም እንኳ አማንያን እንደ ነበሩባቸው ወይ አያስተውሉም ወይም አውቀው ይክዳሉ [ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ አለንበት ዘመን ብንጠቅስ፣ አይዛክ ኒዩተን፣ ጋሌሌዎ፣ ፍራንሲስ ኮልንስ፣ ወዘተ ይገኙባቸዋል]። ወይም ሳይንስ በተፈጥሮ ውስጥ ያየውን ከመዘገብና ከማብራራት ውጭ አዲስ ነገር እንደማይፈጥር ዘንግተው ያዘናጋሉ። ይልቅ ሳይንስ ከቁስ አካል ውጭ መመርመሪያ አቅም እንደሌለውና፣ በሳይንስ የማያምን ሳይንቲስት እንደሌለ ማወቅ ከብዙ ስሕተት በጠበቀ ነበር። ሳይንስ እውነቱን ለመረዳት አንደኛው እንጂ ብቸኛ መንገድ አይደለም። ውድነሽ ለተድላ የቼኮላታ ኬክ ሠርታ ብታመጣለት ድርጊቷን ለመረዳት የኬኩን ወርድና ስፋት መለካት፣ መቅመስ ወይም የተቀመመበትን ንጥረ ነገር መመርመር የትም አያደርስም። ተድላ፣ ውድነሽና ሌላው ታዛቢ ነገሩን በትክክል ይረዳሉ። በሌላ አነጋገር ሳይንስ ፍቅርን የሚመረምርበት ዐይን ሆነ ጆሮ የለውም። ከዚህ የተነሳ ፍቅር ብሎ ነገር የለም ይባል? ይልቅ ሳይንስ የእምነትን ምንነት ለመመርመር ትክክለኛ መሳርያ አይደለም ማለት አይቀልም?

ስለ ተኣምር ደግሞ ሁለት ነጥቦችን እናንሳ። አንደኛው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተኣምር ተግባሩ የእግዚአብሔርን ምሕረትና የማዳን ኃይል መግለጥ ነው። "ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ" [ዮሐንስ 11፡45]። የሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር። ለፍጥረቱም ሕግና ሥርዓትን የደነገገ እግዚአብሔር። ምሕረቱን ለማሳየት ሥርዓቱን ላፍታ ቢቀይር ለምን ይገርማል? የማይቻል እንደ ሆነስ ለምን ይታሰባል? ሌላው ጉዳይ፣ ተኣምር ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው ማለት አይደለም። ሰይጣንም የማያውቁትን ለማሳት [አስመስሎ] ተኣምር ያደርጋል ይላልና፤ "ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ፤ ማቴዎስ 24፡24፤" ሰይጣንና ተከታዮቹ ዓላማቸው ማሳት ነው፤ ሰውን ወደ ፈጣሪው ሳይሆን ወደ ፍጡሩ፣ ወደ ተኣምር ሠሪው ሳይሆን ወደ ተኣምሩ በመጠቆም ማሳት ነው።

ከሰማይ ወረደ የተባለው መስቀል በእግዚአብሔር ቃል ሲመረመር ከፈጠራ ወሬ አያልፍም። የተሰበሰበውም ገንዘብ አግባብ አይደለም።