ጸሎት እና ስፖርት

celebrategoal

የዓለም እግር ኳስ ጨዋታ። ሰው ኃይማኖተኛ መሆኑ። የጸሎቱ አበዛዝ። የጸሎተኛው ዓይነት። ከተጫዋች እስከ ተመልካች። ከአፍሪካዊ እስከ አውሮጳዊ እስከ እስያዊ፣ ከወጣት እስከ አዛውንት። ያማትባል፣ ያማተበበትን ጣት ይስማል። ይሰግዳል። እጆቹን ወደ ሰማይ ያነሳል፤ በእጆቹ የቤተክርስቲያን ጉልላት ይሠራል።። መሬት ይስማል። ይንበረከካል። ያጎነብሳል። ዐይኑን ይጨፍናል። መሬት ላይ በቁመቱ ይዘረጋል። እንግዲህ ምን ቀረ? መቁጠርያ ይዟል፣ መስቀል አንግቷል።

 

ጭንቅ ሁኔታ ሲፈጠር ጸጥታው ያደነቁራል፤ ስታዲየሙ ቤተመቅደስ እስኪመስል። በፍጹም ቅጣት ምት ሰዓት እጅ ለእጅ ይያያዛሉ፤ ይንበረከካሉ። ይቁነጠነጣሉ። እንባ ይራጫሉ። ከምጡ እስኪገላግል ...። ይህን መመልከት ሰው ምንኛ ጎስቋላ ነው ያሰኛል።

 

የተጨዋቾቹ ቁመና - ሰው በራሱ ብርታትና ቅልጥፍና ብቻ መኖር የሚችል ይመስላል። በሃያና በሠላሳ ዓመት ዕድሜ ክልል የተለገሠው ችሎታ የማያልፍ ይመስላል፤ የማይቻል ምንም የለም ያሰኛል። ሆኖም ነገሮች በፍጥነት ይለዋወጣሉ። በሕይወት ሂደት አንድ ቦታ መርጋት አደጋና ሞት ነው። እንቅስቃሴ ለድልና ለተስፋ ያቃርባል። የብራዚሉ ለግላጋ ኔይማር እንደ ተወንጫፊ ኮከብ ደምቆ ወጥቶ ነበር፤ ሳይታሰብ ወገቡን ተቀጨ። ከሜዳ በቃሬዛ ሲያወጡት የኮሎምቢያም እንኳ ባይጨመርበት የብራዚል ሕዝብ ጸሎት አጅቦት ነው። ሁሉ ነገር እጅ በእጅ ነው። የማያልፍ ጎልማሳነት በውበቱና በኃይሉ ግፊት አሁን እፊታችን ይታያል። ሳይታሰብ ይነጠቃል።

 

ሰው ያለ ጸሎት መኖር አይችልም። ያለ አምላክ መኖር አይሆንለትም። ከጅምሩ ያኖረው አምላክ ስለሆነ ከርሱ ኅልውና ሊፋታ አይችልም። አይሞክርም ማለት አይደለም። እንዲህ በመሰሉ ሁኔታዎች ግን እንዳልተቻለው በራሱ ይመሰክራል። ሳይዘጋጅበት የሚሆነው ያ ለሰው እውነተኛ ቀለሙ ነው። ቀውጢዋ ሰዓት ስታበቃና በፈነዳ ደስታ ማዕበል ተገፍቶ ሲንሳፈፍ ቶሎ ብሎ የደስታ እጆቹን ወደ ሰማይ ያነሳል። እንባ ይራጫል። የዋይታ እንባ አለ፣ የሆታ እንባ አለ። ሰው ከእንባ የተቀመመ ፍጥረት ነው። ግንባሩንና ከንፈሩን ወደ መሬት ያቀርባል። ላፍታ የሚሆነው ይጠፋዋል። መጥኖለት ነው እንጂ መከራ የማይገድለውን ሰው፣ የደስታ ብዛት ይገድለዋል።

 

በደስታው ሰዓት አምላክ የሌለው ሰው ማንን ያመስግን? ሰውን ብቻ? ራሱን ብቻ? ሰውን ብቻ ከሆነ ደስታው ትርጉም የለሽ ደስታ ይሆንበታል።

 

የሚታየው ጸሎት ሁሉ እውነተኛ ጸሎት ሊሆን አይችልም። በዘልማድ ሊሆን ይችላል። ለጥሩ ነገር ልማድ ጥሩ ነው። ካለመጸለይ መጸለይ ይሻላልና። ከሚጸልዩ መካከል ሕይወታቸውና ድርጊታቸው ለየቅል የሆነ አይጠፉም። ቁምነገሩ ግን ድርጊቱ ከፍ ወዳለ አምላክ መጠቆሙና ከምድራዊው ባለፈ ሰማያዊውን ማሳሰቡ ነው። እርግጥ ጸሎት ግለሰቡ በልቡናው ለአምላኩ የሚያቀርበው ነው። ጸሎትም ለታይታ መሆን የለበትም። እርግጠኛ ነኝ ከተጫዋችና ከተመልካች ለጸሎት ብሎ ወደ ስታዲየም የመጣ የለም። ሁሉም የመጣው ቡድኑን ለመደገፍና ለመዝናናት ነው። ስፖርቱ በሕይወቱ ትልቅ ሥፍራ ስላለው ነው። ማንም ሳይወጥነው መደረጉ ግን ጸሎቱ ለታይታ እንዳልሆነ ያስረዳል።

 

ከየትኛውም ወገን ይምጣ ጸሎት የሚቀርበው ጸሎትን ለሚሰማ አምላክ ነው። ችግር የሚፈጥረው አምላክን ከራስ ቡድን ጋር ለማሠለፍ ሲሞክር ነው። ባገኘው ድል ተሸናፊውን ለማንኳሰስ ሲሞክር ነው። ጸሎት አቅራቢው ብዙ ነው፣ ጸሎት ሰሚው ግን አንድ ነው። ሰው የራሱን ጸሎት መመለስ አይቻለውም። የሚመለስ ጸሎት አለ፤ የማይመለስም አለ። ያልተመለሰው ስላልተሰማ አይደለም። ባልተጠበቀ መንገድ የሚመለስ አለ፤ ዘግይቶ የሚመለስ አለ። የመልሱን ዓይነት የሚወስነው ጸሎት አቅራቢው አይደለም። የጸሎትን መልስ በራሱ ፈቃድ ማስደረግ ጥንቆላ እንጂ እውነተኛ ጸሎት ሊሆን አይችልም። ለሥጋ ለባሽ ሰው ጸሎቱን ማቅረቡ ይበቃዋል፤ የሚገኝበትን ሁኔታ ከአምላክ ጋር ማገናዘቡ፣ የአምላክን ኅልውና መጥራቱ ይበቃዋል። ችሎታ ለሰጠው ክብር መስጠቱ ይበጀዋል።

 

በተሟላ የአእምሮና የአካል ጥንካሬ ውስጥ ተገኝቶ አምላክን ሲማጸን ማየት ድንገተኛ ደስታን ይፈጥራል። ደስታ የሚፈነቅለው ድንገት ሲሆን ነው፤ የተዘጋጁበት ደስታ እውነተኛ ደስታ ሊሆን አይችልም። ለማንኛውም፣ በእሑዱ የዋንጫ ሽሚያ አርጀንቲና እንዲያሸንፍ እንጸልይ። ጀርመንስ? የሚለኝ አይጠፋምና፣ ፍጻሜውን እግዚአብሔር ያውቃል ማለት ሳይሻል አይቀርም። 

 

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave