ይድረስ ለኢትዮጵያውያን
ይድረስ ለ"ክርስቶስ ደቀመዝሙር"

 

ሐምሌ 17/2006 "ይድረስ ለኢትዮጵያዊ" በሚል ርዕስ ኢትዮሚድያ ዶት ኮም የለጠፈውን ጽሑፍ አንብበናል። የጽሑፉ ደራሲ "የክርስቶስ ደቀመዝሙር" ነኝ ብሎናል። ጽሑፉ ታሪክን ስነ መለኰትን ፖለቲካን ያካተተና ውስብስብ በመሆኑ በመሠረታዊ አሳቦቹ ላይ በቀር በያንዳንዱ ላይ ምላሽ ለመስጠት ጊዜውም ቦታውም አይፈቅድልንም። ምላሽ መስጠት ያስፈለገው ምናልባት ጽሑፉን የሚያነብቡ የሃይማኖት አስተምህሮ ብዙ ያልገባቸው በሚያነብቡት ክርስቲያናዊ ቋንቋ እንዳይወናበዱ ከመሥጋት ነው። "ደቀመዝሙሩ" ያነሳቸው አሳቦች ምንና ምንድናቸው? 1/ አገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ፦ ጭከና የበዛበት፣ ማስተዋል የጠፋበት፣ ዘረኝነት የነገሠበት፣ ሰይጣን መንግሥትን ከበስተኋላ የሚያንቀሳቅስበት፣ የዘመኑ መጨረሻ የተቃረበበትና ሃሰተኛው መሲሕ ሊገለጥ ፍንጭ ያሳየበት ነው ሲል ሥሎልናል። ሃሰተኛውም መነሻው ከዐረብ ምድር ሳይሆን ከኢትዮጵያ ነው ብሎናል [ገጽ 9]። በዚህ መሠረት 2/ በአገራችን ለተከሰተው ችግር ምንጩ በተለይ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝና ጴንጤ/ፕሮቴስታንት ደጋፊዎቻቸው ናቸው። ስለዚህ፣ 3/ ከፍተኛ ትግል አለብን፤ ትግሉ እንዲሠምር ክርስቲያኑና እስላሙ አንድ መሆናቸውን መረዳት አለባቸው፤ 4/ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የገባላት ተስፋ ስላለ የአገራችንን አስከፊ ሁኔታ ለመቀየርና የክርስቶስን ዳግም ምጽኣት ለማፋጠን እንነሳ የሚል ነው [ገጽ10]።

በ"ደቀመዝሙሩ" እይታ ኢትዮጵያ "ከእስራኤል ይልቅ የእግዚአሔር በኩር ልጅ ነች [ገጽ 1]። ነቢያቱ ሕዝቅኤል፣ ኢዩኤል፣ ኢሳይያስ፣ ወዘተ ስለ እስራኤል የተነበዩት ስለ ኢትዮጵያ ነው [ለምሳሌ ሕዝቅኤል ምዕራፍ34 እና 40 "በግ" ሲል እስራኤልን አይደለም ብሎናል]። እንደዚህ የመሰሉ ግንዛቤዎች ቀርበውልናል። ከዚህ የምንረዳው "ደቀመዝሙሩ" አገሩን በጣም እንደሚወድና፣ ምድሪቱና ሕዝቦቿ ሰላም፣ ፍትኅና ብልጽግና እንዲጎናጸፉ ለማየት በብርቱ እንደሚሻ ነው። ችግሩ ግን ከስሜታዊነት ባለፈ ታሪካዊና ስነ መለኰታዊ መረጃ ማቅረብ አልቻለም። እውነትን ያልተገነዘበ አገር ወዳድነት ወደ ባሰ ጥፋት ያመራል። ምንም የሌለው ሰው፣ ብዙ እንዳለው ቢያስብ፤ ብዙ ያለው ደግሞ ምንም እንደሌለው ቢያስብ፤ የሁለቱም ግንኙነቶች በራሳቸውና በሌላው ዐይን እውነቱን የሚያዛባ ውጤት ማስከተሉ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስ ሲጠቅስ፣ ለምን እንደ ተጻፈ፣ መቸ እንደ ተጻፈ፣ ለማን በምን ሁኔታ ውስጥ እንደ ተጻፈ፣ ቀድሞ ለተጻፈላቸው ምን ትርጉም እንደነበረው፣ ዛሬ ለምናነብበው ምን ትርጉም እንደሚሰጥ በማገናዘብ አይደለም። ሊለው የፈለገውን አሳብ ለማጽናት የነስነሳቸው እንጂ ቀዳሚ ይዘታቸውን በመረዳት አይደለም።

ግልጽ ለማድረግ፣ የባለ ቅኔ ጸጋዬ ገብረመድኅንን "ደንስ ጐበዝ! ደንስ ጀግና" የሚል ሐረግ ያዘለ ግጥም በምሳሌነት እንጥቀስ ["እሳት ወይ አበባ"፣ገጽ 208፣ 1999]። ግጥሙን በሙላት ማንበብ ይቻላል። ችግሩ፣ ሐረጉ ተሰድዶ ለብቻው ሲቆምና አገሩ ገብቶ ከሠፈሩ ልጆች ጋር ሲታይ የሚያሳየው የደምግባት ልዩነት ነው። "ደቀመዝሙሩ"፣ ኑ እንደንስ! የሚል ጥሪ ያቀርብልንና፤ ምክንያቱስ ስንለው፦ ምክንያቱማ፣ ባለ ቅኔው "ደንስ ጐበዝ፣ ደንስ ጀግና" ስላለ ነው ይለንና፣ አስከትሎ መደነስ ጀግና ያደርጋል እንደሚል ይመስላል። ጥቅሱ ቃል በቃል ትክክል ቢሆንም ባለ ቅኔው ከጻፈበት ዓላማ እጅጉን የራቀና ተቃራኒ ትርጉም እንዳዘለ መገንዘብ አያዳግትም። የባለ ቅኔው መሠረተ አሳብ ዳንሱን በ "ሙዚቃው ናዳ" ማጋጋል ሳይሆን፣ ለተግሳጽ ነው። ተግሳጹ፣ የምትደንሰው ዝግ ብለህ ላለማሰብ ከኅሊናህ ለመሸሽ ነው፤ ዝግ ካልክማ ጭንቅላትህ ልትሰማ የማትወደውን አንዳች እውነት ይነግርህና ታርፋታለህ ለማለት ነው። ሁለተኛ ምሳሌ፣ ገጽ 2 ላይ "በዳዊት መዝሙር ቁጥር 87 ላይ ፅዮን "ኢትዮጵያ የአሕዛብ እናት ተብላለችና" ይለናል [ገጽ 2]። መዝሙር 87 የተጻፈው "ኢየሩሳሌምን" ቅድስቲት ከተማ እንደሆነች፣ በተቀደሰ ተራራ ላይ ቆማ በምድርና በሰማይ የምትታይ፣ የከተሞች ሁሉ ክብር፣ የነገሥታት ንጉሥ እግዚአብሔር ስም የሚጠራባት እንደሆነች ለማወደስ ነው። መዝሙሩ ቁጥር 4 እና 5 ላይ እንዲህ ይላል፦ "የሚያውቁኝን ረዓብንና ባቢሎንን አስባቸዋለሁ፤ እነሆ፥ ፍልስጥኤማውያን ጢሮስም የኢትዮጵያም ሕዝብ፥ እነዚህ በዚያ ተወለዱ። ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፥ በውስጥዋም ሰው ተወለደ፤ እርሱ ራሱም ልዑል መሠረታት።" "ኢትዮጵያ" ስለ ተጠቀሰ ብቻ ዘልሎ የሌለ ትርጉም መስጠት ስቶ ማሳት ነው። ለአገር በጐ ማሰብ ወይም ኢትዮጵያ "የአሕዛብ እናት" ብትባል መመኘትና የአባባሉን ይዘት ማጤን ለየብቻ ናቸው።

"ደቀመዝሙሩ" እስላምና ክርስትና ቁርዓንና መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ናቸው ማለት ቃጥቶታል። ዓላማው ግልጽ ነው፤ እስላምና ክርስቲያኑ አንድ ቢሆኑ "የዲያብሎስና በክርስቲያን ስም የተሰለፉን አገልጋዮቹም አብረው የሚወገዱ ናቸው። የሃይማኖት ልዩነትም አብሮ ይወገዳል፣ ፍትኅ ይሰፍናል፣ መዋደድ ይመጣል፣ ጥላቻ ይወገዳል፣ ፍቅር በመካከላችን ይነግሳል" [ገጽ2-3] ካለ በኋላ የነገረንን ወዲያው ዘንግቶ፣ "ሰዎች በአንድ ሃይማኖት ካልተዋቀሩ በአንድ አገር ውስጥ ሰላምና እድገት አይመጣም በማለት መንግሥት እውቅና የሰጠውን የክርስቲያንና እስላም ጥምረት [ክርስኢስላም] "በማር የተለወሰ ማር ነው" ይለናል [ገጽ 7]። የስድሳ ስድስቱ አብዮትና የሰማንያ ሦስቱ ዲሞክራሲያዊ አብዮት የገቡልን ተስፋና በተግባር ያላሳዩት ይህንኑ ይመስላል። በሶቪየት ኅብረት ሰባ አምስት ዓመት ተስፋ ሰጥቶ የነሳ ሥርዓት ፈርሃ እግዚአብሔር በሌለበት ተሞክሮ ሦስት ትውልድ ፈጅቶ ዛሬ ማስታወሱ የሚዘግንን ቅዠትና መሳቂያ ሆኗል። በሌላ አነጋገር፣ "ደቀመዝሙሩ" ተስፋ የሌለበትን ተስፋ እየሰጠ ነው።

ቀጥሎ፣ መሐመድ የወንጌልን መልእክት የተቀበለው ከአይሁድ ነው። ወደ አገራችን ሸሽተው የመጡትም የመሐመድ ተከታዮች "የደኅንነት ወንጌል በነቢዩ አንደበት የሰሙና ያመኑ ናቸው" ይለናል [ገጽ5]። ይኸ አስገራሚ ትምህርት ነው፤ የክርስቶስ ደቀመዝሙር መሆኑን እስከነአንካቴው ጥርጥር ላይ የሚጥል ነው። በቁርዓንና በወንጌል ውስጥ ተመሳሳይ ቃላት መገኘታቸው ያመሳስላቸዋል ወይም አንድ ያደርጋቸዋል ማለት ትልቅ ስሕተት ነው። ከላይ እንደ ጠቀስነው የአንድ ጸሐፊ መነሻ አሳብ አተረጓጐሙን ይገዛዋል። እውነተኛ የክርስቶስ ደቀመዛሙርት ከመሐመድ አስተምህሮ ጋር ምንም ግንኙነት ሊኖራቸው አይችልም፣ አይገባምም። ይኸንን ከራሳችን በመነሳት የምንለው ሳይሆን ክርስቶስና ሐዋርያቱ ያስተማሩት ነው፤ የክርስቶስን ትምህርትና ጌትነት ያመኑ እርሱንም የሚከተሉ ሁለት ጌታ ሊኖራቸው አይችልም [ማቴዎስ 6:24፤ 2ቆሮንቶስ 6:14-16]። በሌላ አነጋገር፣ እስላም ወገኖቻችን ናቸው፤ አገራችን የጋራችን ነች። ክርስቶስንና መሐመድን፣ መጽሐፍ ቅዱስንና ቁርዓንን ግን በእምነት ደረጃ አንጋራም። ይኸ አክራሪነት ሳይሆን የእምነቱ ዓይነት ነው። ለእስልምና መመሪያው ቁርዓን ነው፤ የክርስትና መሠረቱ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስታወቁት፣ ሰው ሆኖ የተገለጠው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስና የመሐመድ ሕይወትና ትምህርት የሚቃረኑ እንጂ የሚዋሃዱ አይደሉም። የማይስማማውን ለማስማማት የሚሯሯጡ ያልገባቸው ወይም ሌላ ተልእኮ ያላቸው ብቻ ናቸው።

እንዳያሰለቸን ስነ መለኰቱን ወደ ጐን ትተን ወደ "ደቀመዝሙሩ" ዋነኛ ወቀሳ እንመለስ። "ደቀመዝሙሩ" አገራችን ለገባችበት ዝቅጠት ተጠያቂው ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና ጴንጤዎች/ፕሮቴስታንቶች ናቸው ብሎናል [ገጽ 1,3,4,5,8]። ይኸ እጅግ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን መሠረተ ቢስ ውንጀላ ነው። "የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ፖለቲከኛ እንዳይባሉ ... ከጣይቱና ከምኒልክ ልጆች ጋር ድምፃቸው እንዳይሰማ አድርገዋል" [ገጽ1]። ብዙ ሳይቆይ መነሻ አሳቡን መሸሸግ ስላልቻለ እንዲህ ይለናል [ገጽ 2-3] "ፕሮቴስታንቱ በህወሓት-ኢሕአዴግ እና ተባባሪዎቹ ላይ ካልተነሳ የኢትዮጵያ ጠላት መሆኑን የሚያመለክት ነው ... ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ "በሁለት አሳብ ያለ በመሆኑ አወዳደቁ የከፋ እንደሚሆን አልጠራጠርም ...የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮችም 'መለስን ያበቀለች ምድር ሌላ መለስን አትሰጥም ማለት እንዴት ይቻላል?' በሚል መፈክር የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሹመት የጸሎት መልስ እንደሆነ ታምኖበት በጴንጤ አማኞች ዘንድ ሃሌሉያ አሰኝቶአል።" ሃሌሉያ ያሉ የሉም ማለት አይቻልም። ያ ግን የግለሰቦቹ ጉዳይ እንጂ ወንጌል አማንያንን በጅምላ የሚኰንን ሊሆን ይገባል? ይህንን ያሉ ፕሮቴስታንት ያልሆኑ ሰዎች እንደሆኑስ ብሎ እንኳ እንዴት አይጠረጥርም? በግለሰብ ደረጃ እንደ ማንም ዜጋ የቀድሞውን ሆነ የአሁኑን ጠ/ሚኒስትር የሚያደንቁ ቢገኙ ለምን ጥያቄ ያስነሳል? "ደቀመዝሙሩ" የራሱ አቋም እንዳለው ሁሉ ሌላውም እንዳይኖረው ለምን ይታሰባል? ወይስ የተለየ አቋም ለመያዝ ፈቃድ ያስፈልጋል? ቀጥሎ፣ "ኃይለማርያም ደሳለኝን አስነስቶ እየቀጣን ነው ... [የኃይለማርያም] ተግባሩ ከቀደሙት መሪዎች እጅግ የከፋ ነው፣" [ገጽ3]። በመጨረሻ፣ "አቶ ኃይለማርያም በፀረ ክርስቶስ መንፈስ የሚንቀሳቀስ መሆኑ አንዱ ማስረጃ፦ ሟች መለስ ዜናዊን 'ዘላለማዊ ክብር ለጠ/ሚኒስትራችን' ማለቱ ብቻም ሳይሆን '[መለስ] ክርስቲያን አልነበሩም ማለት አይቻልም። ፈርሃ እግዚአብሔር ነበሩ ... ቅን መሪ ስለ ነበሩ የብዙ ሺህ ቅዱሳን ጸሎት ደግሞ ስለ ደገፋቸው በሞገስ ሊመሩ ችለዋል'" ሲል ይደመድማል።

ለመሪዎች መጸለይን በተመለከተ የተጻፈውን እንመልከት። ኢየሱስና ሐዋርያቱ አንድ ጌታ ብቻ በሰማይ እንዳለ፣ በምድርም እንደሚገዛ አስተምረዋል። በክርስቶስ ላመነ ከክርስቶስ ሌላ ጌታ ሊኖረው አይችልም። ሥልጣናትን በተመለከተ ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 13 እንዲህ ይላል፦ 1 ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። 2 ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ። 3 ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤ 4 ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። 5 ስለዚህ ስለ ቍጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለ ሕሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው። 6 ስለዚህ ደግሞ ትገብራላችሁና፤ በዚህ ነገር የሚተጉ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸውና። 7 ለሁሉ የሚገባውን አስረክቡ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን፥ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ። በ1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡1-4 ደግሞ እንዲህ ተጽፏል፦ እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። 3-4 ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።"

"ደቀመዝሙሩ" እንዲህ ብሏል፣ "ማንም ሰው በራሱ ብቃት ቀኒቱን ሊያገኝ የሚችል የለምና። ሥልጣንም ቢሆን ከላይ ከአርያም ካልተሰጠ፣ ሰው በገዛ ኃይሉና በወገናዊነቱ ሊያገኘው አይቻለውም" [ገጽ1]። አባባሉ ትክክል ነው፤ ግን ይቀረዋል። ስለዚህ ከላይ የጠቀስናቸውን ሁለት ክፍሎች ጨምረን መዘርዘር ጠቃሚ ነው፤ 1/ የሚሾምና የሚሽር እግዚአብሔር ነው [በራሴ ሥልጣን ላይ ወጣሁ የሚል ሁሉ ራሱን ያታልላል ማለት ነው]፤ 2/ እግዚአብሔር አንዱን ሲሾም፣ ሌላውንም ሲሽር የሰው ምክር አይሻም፤ 3/ የተሾሙ ሁሉ ለእግዚአብሔር መልስ ከመስጠት አያመልጡም፤ 4/ የተሾሙት ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት የፍትኅ ሰይፍ በእጃቸው ተሰጥቶአቸዋል፤ መልካም የሚያደርጉትን ሊያስፋራሩበት ግን አይደለም፤ 5/ መንግሥት በሥርዓት እንዲተዳደር የዜግነትን ግዴታ መወጣት ይገባል [እግዚአብሔር የሥርዓት እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና]፤ 6/ እግዚአብሔር ደግሞ ማንነቱን ለሰዎች ከመግለጽ አይታክትም፤ ሰዎች ብርሃን ስላልበራላቸው ሳይሆን፣ በርቶላቸው በክፋታቸው ሲጸኑ ያኔ እግዚአብሔር ይሽራቸዋል፤ የሚሽረው በሰው ሰዓትና ብልሃት አይደለም [ዳንኤል ም.2-3] 7/ አማንያን ለተሾሙት እንዲጸልዩ፣ በሁሉ ላይ ሥልጣን ባለው በእግዚአብሔር ፊት ልመናቸውን እንዲያቀርቡ ታዝዘዋል፤ 7/ መሪዎች ሰዎች ስለሆኑ ቅን የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ በጸሎት ደግፏቸው ተብለዋል። አመጽ ቢያደርጉስ? ያንንም በእነርሱ ላይ ጌታ ለሆነው ለአምላካችሁ አስታውቁ ተብለዋል [የሐዋርያት ሥራ 4፡23-31]። ቤተክርስቲያን ለአፄ ኃይለሥላሴ፣ ለደርግና አሁን ላሉት መሪዎች እንድትጸልይ እግዚአብሔር ፈቃዱ ነው። ሌላ የምንዘነጋው ሁለት ጉዳይ፣ ተመሪውም እንደ መሪው ስሕተት የሚሠራ ፍጥረት መሆኑንና፣ በደልን ከመሪ ጋር ጽድቅን ደግሞ ከተመሪ ጋር እንደሆነ ማሰብ ከእውነቱ የራቀ መሆኑን። ጸሎት የሚደረገው ጽድቅ እንዲጸና እንጂ አመጽ እንዲበረታ አለመሆኑን፣ ብዙውን ጊዜ ነቀፋ የሚያበዙ ራሳቸው የማይጸልዩና ስለ ጸሎት ያልገባቸው መሆናቸውን ነው።

ቤተክርስቲያን ከወንጌል እውነት ጋር እንጂ ከጊዜአዊ ሥልጣናት ጋር መወገን የለባትም። አማንያን ግን በግለሰብ ደረጃ በአገር ጉዳይ [በፖለቲካው ሳይቀር] ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል። እያንዳንዱ ግን እንደ ተቀበለው ጥሪና ጸጋ ይሳተፋል እንጂ ለሁሉ ወጥ የሆነ ሕግ መደንገግ አይቻልም። አንድ የደርግ ባለ ሥልጣን አንደኛውን ወንጌል አማኝ፦ መጽሐፍ ቅዱስ እኰ የአድሃሪያን መጽሐፍ ነው፣ "ለባለሥልጣን ተገዙ" ይላል፤ አገራችንን ወደ ኋላ ያስቀረው አንዱም ይኸው ነው ብሎ ቢወርፋቸው። አማኙ ተቀብለው፣ "ታዲያ አሁን ለናንተ እንገዛ ወይስ አንገዛ?" ብለው እንደመለሱለት ትዝ ይለናል።

craig landscape

ሁለት ጉዳዮችን አንስተን እንጨርስ። አንደኛ፤ ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሃይማኖተኛነታቸው ይታወቁ እንጂ በዚህ ጉዳይ ቤተክርስቲያንን ሆነ ማንንም አይወክሉም። አቶ ኃይለማርያም ከ "ኦንሊ ጂዘዝ" መውጣታቸው እዚህ መዘርዘር የማያስፈልገን የራሱ የሆነ ስነ መለኰታዊ እይታ አለው። አንደኛው ስሕተት ወንጌል አማንያንን በኦርቶዶክስ፣ በካቶሊክና በእስልምና ዘርፎች አወቃቀር ዐይን ጨፍልቆ ማየት ላይ ነው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ቄስ ቶለሳ ጉዲና ከአንድ ኦሮቶዶክሳዊ ካህን ጋር ዋሽንግተን ዲሲ ባደረጉት ውይይት፣ እንዲህ እና እንዲህ አሉ ተብሎ ምድረ ወንጌል አማኝ ሲወነጀልበት ነበር። ዶ/ር ቶለሳ የተረዱትንና የመሰላቸውን መልስ ስለ ሰጡ ለምን ይደንቃል? ኃላፊነቱ የራሳቸው ብቻ ነው። ማንም አልወከላቸውም፤ ወክሎአቸውም ከሆነ ያንን መግለጽ ይችሉ ነበር።

"ደቀመዝሙሩ" እውነቱን የሳተው እዚህ ላይ ነው። ከኃይለማርያም የቀደሙት የፖለቲካ መሪዎች በእግዚአብሔር ያለማመናቸው ያላስከተለውን መዘዝ፣ ኃይለማርያም "አማኝ ነኝ" ብለው እንዴት እንዲህና እንዲህ ያደርጋሉ ብሎ መወንጀል አግባብ አይደለም። [እርግጥ ስለ እምነታቸው ለ "ምዕራፍ መጽሔት" ጥር 2003 በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የዋህነታቸው ይስተዋላል። እንደ አገር መሪ የግል አስተያየታቸውን የት፣ መቸና እንዴት መናገር እንዳለባቸው እንዳልተገነዘቡ ያስታውቃል።] ግልጽ እንሁን። 1/ ኃይለማርያም የፖለቲካ ሰው ናቸው። ለዚህም በመጀመሪያ፣ ሰንደቅ መጽሔት ካቀረበላቸው ጥያቄ መሓል ለአንዱ የሰጡትን መልስ እንመልከት።
ጥያቄ፦ ለምሳሌ አቶ መለስ አማኝ ወይም ክርስቲያን አልነበሩምና እሳቸው እግዚአብሄር ጋይድ ሆኖ [መርቶአቸው] አያውቅም ማለት ይቻላል?

ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም፦ "እሳቸው ክርስቲያን አልነበሩም ማለት አይቻልም። የእምነታቸው ጉዳይ የግል ስለሆነ እሱን ከፈጣሪና ከእሳቸው ጋር ያለውን ግንኙነት ደጅ ብናደርግ ይሻላል፤ በግሌ ግን እንደማምነው እሳቸው ፈሪሐ እግዚአብሄር ነበሩ በዚያ ላይ ቅን መሪ ስለነበሩና የኃይማኖት ነጻነት ካለገደብ በመፍቀዳቸው የብዙ መቶ ሺ ቅዱሳን ፀሎት ደግሞ ስለደገፋቸው በሞገስ ሊመሩ ችለዋል" ብለዋል። የኃይለማርያም ምላሽ ድርብ አሉታዊ እንደሆነ እናስተውል፤ መለስ ክርስቲያን ስለ መነበራቸው እርግጠኛ አይመስሉም። በአንጻሩ፣ መለስ በሕይወት እያሉ በእግዚአብሔር ያምኑ እንደሆነ በእንግሊዝ ጋዜጠኛ ተጠይቀው እንደማያምኑ፣ ለእንዲህ ዐይነቱ ስፍራ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ሁለተኛ፤ ኃይለማርያም፣ ሁሉ በርሳቸው ፈቃድ የሚመራ ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭ መሪ አይደሉም፤ ሌላ አመለካከት ያላቸው መሪዎችም አብረዋቸው እንዳሉ አንዘንጋ። በተጨማሪ፣ የግል አቋማቸውን ወደ ጎን አድርገው የመንግሥታቸውን ፖሊሲ የመደገፍ ግዴታ አለባቸው። የሌላ ፓርቲ አባል ቢሆኑ ኖሮ በአደባባይ የአቋም ልዩነት እንዳላቸው መግለጽ በቻሉ ነበር። ባጭሩ፣ ለሚናገሩትና ለሚወስኑት ኃላፊነቱ "የጴንጤ/ፕሮቴስታንት" ሳይሆን የግላቸው ነው። ኃይለማርያም በአገር አመራር ላይ እያሉ በሚወስዱት ውሳኔ ለእግዚአብሔር መልስ ይሰጡበታል፤ ለአገሪቱም ሕግ መልስ የሚሰጡበት ሁኔታ አይፈጠርም ማለት አይቻልም፤ የሚያስፈጽሙት ሕግ በርሳቸውና ከርሳቸው ጋር ባሉትም ላይ ሊሠራ ይገባልና። እንደ እግዚአብሔር ቃል አማንያን ሊጸልዩላቸው ግዴታ አለባቸው። በተረፈ፣ ኃይለማርያም በመኖሪያ ቤታቸው በትርፍ ጊዜአቸው ከቤተሰባቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር ቢጸልዩና ቢዘምሩ ለምን ይደንቃል? ሌላው ከሃዲ ነኝ፣ እስላም ነኝ እንደሚለው ሁሉ ክርስቲያን ነኝ ማለታቸው ለምን ይደንቃል? እግዚአብሔር በታሪክ ውስጥ ያልታሰቡ ሰዎችን ባልተጠበቀ መንገድ ረቂቅ ዓላማውን እንደሚያሠራቸው አንዘንጋ። ብዙ ጊዜ መሪም ተመሪም እያየ የሚዘነጋው እውነት አለ። ያም ለሁሉ ነገር ፍጻሜ እንዳለው ነው። ሰው ከእግዚአብሔር ፍርኃት ሲርቅ፣ ማንም የሚያየው አይመስለውም፣ እግዚአብሔር በሌላው ላይ እንጂ በኔ ላይ ይፈርዳል ብሎ አይገምትም፤ ሥልጣን ላይ ያወጣውን ፈጥኖ ይረሳል። በሌላው ላይ የፈረደ፣ ራሱ በአደባባይ ሲፈረድበት እያየን ነው። ይህን እውነት ችላ ማለት ራስን ማታለል ነው። የማያልፍ የሚመስለው ሥልጣን እንደ ድንገት ያልፍና ለማምለጥ እንኳ ፋታ አይሰጥም። ጠ/ሚ ኃይለማርያምን ያነሳነው ጉዳያቸው ወንጌል አማንያንን ለይቶ ለመውቀሻ በመዋሉ ነው። እንጂ አንጃ ፖለቲካ ለማራመድ አይደለም። ኃይለማርያም እንደ ማንም ይሳሳታሉ፤ የፖለቲካ ጨዋታ ይጫወታሉ። "የክርስቶስ ደቀመዝሙር" ነኝ ያለን ጸሐፊ የክርስቶስን ፈለግ ለይቶ ያወቀ አይመስልም። የማይቀላቀሉትን እየቀላቀለ ያደክመናል። ኃይለማርያምን ከመነሻው እንደ ማንኛውም ፖለቲከኛ ቢመለከት ኖሮ ይህን የመሰለ ስሕተት ባልፈጸመ ነበር።

የ "ደቀመዝሙሩ" የፖለቲካ አመለካከት ለምን ይህን መሰለ ማለት አስፈላጊ አይደለም። ማንም የመሰለውን አመለካከት ሊይዝ ይችላልና፤ ከማንም ፈቃድ ማግኘት አይኖርበትም። ስሕተቱን ከተቀበለ ይታረማል። ከመሰሎቹ ጋር ያብርና ያመነበትን ዓላማ ያራምዳል። መደምደሚያ ላይ እንዲህ ተብለናል፣ "ወገኔ ኢትዮጵያዊ ይህን መልእክት ስጽፍ የራሴን እምነት እንድትከተል ወይም ያለኝን እውቀት ላሳይህ አይደለም። አምላክ በሰጠህ ማስተዋል እውነትን አንብበህ፣ በዐይንህም አይተህ፣ በጆሮህም ሰምተህ ከአጥፊዎች እንድትርቅ ነው" [ገጽ10]። እኛም አሜን ብለናል። ሆኖም፣ "ደቀመዝሙሩ" አስተባብራለሁ እያለ ሕዝበ ክርስቲያኑን የባሰ እየነጣጠለ እንዳይሆን። ወንጌላውያንን ለዓላማው ለማነሳሳት ፈልጎ ከሌሎች የእምነት ክፍሎች ጋር እያቃቃረ እንዳይሆን። እሳት ማንደድ፣ የነደደውን እንደ ማጥፋት አይከብድምና።

በተጨማሪ እዚህ ይጫኑ። ላላነበቡ ያስተላልፉ።