ርዕሰ አንቀጽ
እውነት ወይስ ውሸት?

ውሸት ቢደጋገም ያው ውሸት ነው። ሲደጋገም ተጽእኖ አያሳድርም ማለት አይደለም። መንግሥታት ሕዝባቸውን፣ ነጋዴ ገበያተኛውን፣ ወዘተ፣ በመደጋገም ብዛት ለማሳመን ይጥራሉ። እውነቱን ለይቶ ማወቅ ትጋትና ንቃት የሚጠይቀው ለዚህ ነው።

መደጋገም እንደሚንጠባጠብ ውኃ ነው። የሚንጠባጠብ ውኃ አለት ያፈርሳል። አለቱ የሚፈርሰው በመጀመሪያው ጠብታ ላይሆን ይችላል፤ በሁለተኛው ላይሆን ይችላል። ሲደጋገም ግን ድንጋይ ለውኃ መንገድ ይለቅለታል። ውኃም በተከፈተለት ቀዳዳ ገብቶ አለቱን ከመሠረቱ ያናጋዋል።

ውሸት ስንሰማ ምን እናደርጋለን? ውሸት መሆኑን እንዴት እንለያለን? እውነትን ለማወቅ ለሚሻ ይህ የማያቋርጥ ጥያቄ ነው። በዚህ ላይ ነጭና ጥቁር ውሸት አለ። ጥቁር ውሸት ዐይን ያወጣ ዓይነቱ ነው፤ ነጩ ከእውነቱ የሚያስቀረው ነው። ቢያጋንኗቸው ቢያሰማምሩአቸው ነጩም ጥቁሩም ያው ውሸት ናቸው።

ውሸት ኃይሉ የሚበረታው እውነቱን በማያውቁ ወይም ለማወቅ በማይጥሩ ላይ ነው፤ ደግሞ እውነቱን እያወቁ ችላ በሚሉና ውሸትን በሚለማመዱ ላይ ነው። ምን አገባኝ በሚሉ ላይ ነው። እነዚህም ከእውነት ጋር ስላልቆሙ ውሸትን ለመቋቋም ኃይል አይኖራቸውም። የውሸት ማዕበል ያንሳፍፋቸዋል፤ ጠርጎ ይዞአቸው ይሄዳል። የስነምግባር ወገብ በላላ መጠን እውነትን ከውሸት ለመለየት እያዳገተ ይመጣል። ኑሮም እያደር የውሸት ኑሮ ይሆናል።

እውነት ነው ብለን የያዝነው ስንት ውሸት ይኖር ይሆን? እያንዳንዱ ሰው ራሱን ይመርምር። እውነት፤ ነገርን ማጣራትና ማመዛዘንን፣ ለእውነትና በእውነት መኖርን ይጠይቃል። ውሸትን ተግቶ መቋቋምና መግለጥን ይጠይቃል። ውሸትን መደጋገም ከእውነት እንደሚያዘናጋ ሁሉ፤ እውነትን መደጋገም እውነት እንዳይረሳና እንዳይበረዝ ይረዳል። ወሬ አቀባዩ ማነው? ለምን ይህን አለ? ለምን አሁን? ሌላ ምን መረጃ አለ? አቋሜ ምን ሊሆን ይገባል? ብሎ መጠየቅ ግድ ነው። መስዋእት መክፈል ግድ ነው።

እስቲ በጋዜጣ፣ በራዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በስልክ፣ በኢሜይል፣ በፌስቡክ ሲደጋገሙ የምንሰማቸውን ጉዳዮች እንቃኛቸው [አንባቢው የራሱን ዝርዝር ይጨምርበት]።

እውነት ወይስ ውሸት?
1/ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ነው
2/ የክርስቲያኖችና የሙስሊሞች አምላክ የስም ልዩነት እንጂ አንድ ናቸው
3/ ዲሞክራሲ ለምዕራባውያን አገሮች እንጂ ለኢትዮጵያ ጊዜው አይደለም
4/ ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ የሚጎርፉት አገራቸው ውስጥ ተፍጨርጭረው ለመኖር ስላልፈለጉ ነው
5/ ኢየሱስ ሰው ይምሰል እንጂ፣ አምላክ ነው
6/ ኢየሱስ ከፍጥረት ሁሉ ቀድሞ የተፈጠረ አምላክ ነው
7/ ኢየሱስ ከፊል ሰው፣ ከፊል አምላክ ነው
8/ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን አብ ተብሎ ይታወቃል፤ በሐዲስ ኪዳን ወልድ፣ ከጴንጤቆስጤ ቀን በኋላ መንፈስ ቅዱስ ተብሎ ይታወቃል
9/ ኢትዮጵያ ምድሯ የተቀደሰ ሕዝቦቿም ለእግዚአብሔር እንደ እስራኤል ሕዝብ ናቸው
10/ የነቢይ ቡሺሪ ሳሙና ገላን ማንጻት ብቻ ሳይሆን ለሚያምኑ መንፈሳቸውን ይቀድሳል
11/ ክርስቲያኖች በድህነት የሚኖሩት ምነት ስለጎደላቸው ነው
12/ አገራችን በፈጣን ልማት ግስጋሴ ከአፍሪካ ቀዳሚ ነች

ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ... እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፣ ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበብሩ፣ ይልቁን ግለጡት እንጂ [ኤፌሶን 5፡6-13]። እውነትን የምታውቁ ስለሆናችሁ፣ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ [1ኛ ዮሐንስ 2፡21]።