ርዕሰ አንቀጽ
በቤተክርስቲያን ስም

ማርስ ሂል በአሜሪካ የሚገኝ የ11 አብያተክርስቲያናት ስብስብ መጠሪያ ነው። የማርስ ሂል መሥራች ማርክ ድሪስኮል ሁሉን ጠቅልዬ ልዘዝ በማለቱና የስህተት ትምህርት በማስተማሩ ባለፈው ዓመት ሥልጣኑን እንዲለቅቅ ተገዷል። ማርስ ሂል በአገራችን ከ21 እስከ 67 ለሚደርሱ አገልጋዮች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ እንደማያቋርጥ አስታውቋል። አንዳንዶች ግን በገንዘብ አሰባሰብ ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ለምሳሌ በሕንድና በኢትዮጵያ ስም ከተሰበሰበው10ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 9ሚሊዮን 9መቶ ሺህ ያህሉ እዚያው አሜሪካ ቀርቷል። በ2006 ዓ.ም. ሪፖርት መሠረት፣ 5 "ማርስ ሂል አብያተክርስቲያናት" በአገራችን ተተክለዋል ወይም ሊተከሉ ነው፤ 5 ተከታታይ ትምህርቶች ተሰጥተዋል፤ ለ67 ወንጌላውያን የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል [መጠኑ አይታወቅም]።

ወንጌል እናሠራጫለን የሚሉ ሁሉም [አገር በቀሎችን ጨምሮ] ቅኖች ናቸው ማለት እውነታን መካድ ነው። እንዳመቻቸው በአምሳላቸው አብያተክርስቲያናትን ማቋቋማቸው ወንጌል አማንያንን አዥጎርጉሮአቸዋል። በዚህ ዘመን በተለይ መነሻቸው ሰሜን አሜሪካና ምዕራብ አፍሪካ የሆነ ጥቂቶች ያይደሉ ድርጅቶች የወንጌልን ሥራ ገንዘብ ለመሰብሰቢያ፣ ከታክስ ነጻ ፈቃድ ለማግኛና ተጓዳኝ ንግድና የግል ኑሮ ማካሄጃ አድርገውታል። ውጭ አገር ለምንኖር፣ እነዚህን መሳይ ተቋማት ዓመታዊ ዕቅድ፣ ገቢና ወጪአቸውን ይፋ ለማድረግ ስለሚገደዱ እንቅስቃሴአቸውን መከታተል ቀላል ነው። እስቲ በዚህ ዓይነት ከሚንቀሳቀሱት መሓል የሦስቱን ብቻ በከፊል እንጥቀስ፦
1/ በአፍሪካ አህጉር በዓመት ወደ 20ሺ የሚጠጋ መሪ አሠለጥናለሁ ብሎ ገንዘብ የሚሰበስብ ድርጅት አለ። ከ10 ዓመት በፊት ይኸው ድርጅት በአንድ ሥፍራ ገንዘብ ለማሰባሰብ ስለአገራችን የሚያወሳ ቪዲዮ አዘጋጅቶ ነበር። ዳሩ ግን ሊታይ የታቀደው ቪዲዮ ተሠርዞ በምትኩ አንድ የዚምባብዌ ሰው በአንድ ዓመት 10ሺ ቤተክርስቲያኖች ተከልን የሚል ሪፖርት አቅርቧል! የፕሮግራም ለውጥ የተደረገው ኢትዮጵያዊ በስብሰባው መሓል እንደሚገኝ አዘጋጆቹ ስለ ሰሙና ቪዲዮው ውስጥ ዐይን ያወጣ ቅጥፈት እንዳለበት ኋላ ለመረዳት ችለናል።
2/በኮሎራዶ ግዛት የሚገኝ አንድ ድርጅት 2ሺ2መቶ አብያተክርስቲያናት ተክያለሁ/እተክላለሁ፤ አንድ ቤተክርስቲያን ለመትከል 1,850 ዶላር ብቻ ያስፈልጋል፣ ይርዱ የሚል ሪፖርት አሠራጭቶ ገንዘብ ሲያሰባስብ ነበር።
3/በደቡቡ የአገራችን ክፍል የሚንቀሳቀስ አንድ ድርጅት ደግሞ ዓመታዊ የገንዘብ ሪፖርቱ ሥርዓት እንደጎደለው አሳስበን ምላሽ ሊሰጠን አልፈለገም። ብዙ ሳይቆይ የድርጅቱ መሪ በሌላ በባሰ አስጸያፊ ተግባር ተከስሶ ባሁኑ ሰዓት በአሜሪካ ዩታህ ግዛት እስር ቤት ይገኛል።

በጎ ሥራ ቢታይባቸውም ግልጽነት የጎደላቸው አገልግሎቶችን ዝም ብሎ ማለፍ በደኃና በወንጌል ስም የሚነግዱትን ሃይ አለማለት መሰለ። እርዳታ ሰጭውን ማፋጠጥ ደግሞ ተጠቃሚውን ከመጉዳትና ያችኑ ትንሿን ጥረት ከማጨናገፍ በቀር ምንም አይጨምርም የሚሉ አሉ። ተጠቃሚው በስሙ ከሚካሄደው ማጭበርበር ይልቅ በአገራችን አቅም የሚያገኘው ትልቅ ጥቅም አሳስቶታል። ምን ማድረግ ይሻላል ይላሉ? አጭር፣ አጥጋቢና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልስ ካለዎ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ይላኩልን።