ርዕሰ አንቀጽ

የያዝነውና የሚመጣው

የያዝነው ዓመት እንደ ልማዱ ሊያልቅ ነው። እኛም እንደ ልማዳችን “ይኸ ዓመት እንዴት ይሮጣል? … ከምኔው አለቀ” እያልን ነው። ዓመት ባመት አሮጌው ግርጌ ቆመን ይህንኑ ሳንደጋግም የቀረንበት ጊዜ የለም።  

ዘመኑ ይሮጣል። ሳናስበው ይጠራቀምና አምስት ይሆናል፤ አስር ይሆናል። ልጅነት እየራቀ፣ ትዝታ እየጨመረ፣ አቅም እያነሰ፣ መርሣትና መረሣትም እየጎላ ይሄዳል። ጅምሩ እያደገ ይከተላል። ጊዜው ወዴት ይሄዳል? ዘመኑ ወዴት ይገሰግሳል? ብዙ ሰው ይህን አይጠይቅም። የሚቀጥለው እርምጃ ይቀጥል አይቀጥል የሚያውቅ የለም። ምን ማድረግ ይቻላልና ነው የምጠይቀው ይላል። ይሩጥበት፤ ማቆም ወይም ማዘግየት ይቻልና ነው? ማዘግየት ቢቻል እንኳ፣ ማፍጠን የሚፈልግ ስለማይጠፋ ትርምስ ሊሆን ነው። ታዲያ እየገፈታተረ ወዴት ሊያደርስ ነው?

በጊዜ አዙሪት ተይዞ ቁርሱን ምን እንደ በላ የማያውቅ ሞልቷል። አንዳንዱ ቀኑ ሰኞ ይሁን እሑድ ተማቶበታል። ሳንገናኝ ዓመት ሆነን እኮ! ይላል፤ ስድስት ወር ሳይሞላ። ይባስ ብሎ፣ የፈረንጆች አዲስ ዓመት ጥር፤ የኛ መስከረም መሆኑ ቀናቱን አሳክሮአቸዋል።

EtNewYear09የቀናቱ፣ የወራቱና የዓመታቱ መቅለብለብ አንድ ሁኔታ ላይ ማድረሱ አይቀርም። ያቺን ነው እንግዲህ ሰው ማሰብ የሚፈራው። መፍትሔው ግን ያቺኑ በማሰብ ውስጥ ነው። ዛሬን እንሞታለን፤ ዕለት ዕለት እንሞታለን፤ ነገን በተስፋ እንኖራለን። ተስፋው የሚያኖር ተስፋ ካልሆነ ግን ምን ተስፋ ነው? ተስፋ የቆምንበትና የምንረማመድበት ወዴት እንደሚወስድ በማወቅ ውስጥ ነው። የመንገዱን አስተማማኝነት በመገንዘብ ውስጥ ነው። መንገዱ እውነተኛ መንገድ መሆኑን በመለየት ውስጥ ነው፤ ሞትን ማሻገር ይችል እንደ ሆነ፣ ለሕይወት ዋስትና ይሰጥ እንደ ሆነ በመታመን ውስጥ ነው። ወንጌል ይህን ዋስትና በክርስቶስ ውስጥና በዳግም ምጽዓቱ ጠቅልሎታል። ከአንደኛው ቀን ወደሚቀጥለው ለመሻገር፣ ከአንደኛው ወርና ዓመት ወደ ሌላኛው፣ ወደ ፍጻሜው ወርና ዓመት ለማሻገር ድልድዩ እርሱ ሆኗል። ከሞት ወደ ሕይወት ለመሻገር፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሚያረጅና ከሚያልፍ ዘመን ወደማያልፍ ወደ ዘላለሙ ለመተላለፍ ድልድዩ ኢየሱስ ነው። እርሱን ማወቅ ጅማሬና ፍጻሜን ማወቅ ነው። መተላለፊያ ማግኘት ነው። “በእርሱ ሕያዋን ነንና፣ እንንቀሳቀሳለን፣ እንኖርማለን።” አልገዛ ያለው ቀን፣ ቀኑን ለሚገዛ ስንገዛ፣ ይገዛልናል። 

ቀኑ አልያዝ ሲል ሌላ ምን ማድረግ እንችላለን? ወይስ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል እንበል? የለም፤ ከቁጥጥር ውጭ አልሆነም። ወጣ ብለን የዐደይ አበባ፣ የመስከረም አበባ እንልቀም። እንደተገኘንበት ምድር የሚስማማንን አበባ እንሸምት። ይኸ በእጃችን የያዝነው አበባ መዐዛው የሚያውደው፣ ፊት የሚያበራው፣ መንፈስ የሚያረካው፣ ለአፍታ ነው። ከተቀጠረለት ሰዓትና ቀን በኋላ አበባ ነውና ይረግፋል። ይረሳል። የሚረግፈው ግን የተወሰነለትንና የተበጀለትን ተግባር ፈጽሞ ነው። ምሥጢሩ ይኸ ነው።

ወዳጅነት ዛሬ ነው። ነገ አይደለም። ቡና አብሮ መጠጣት ዛሬ ነው። ኋላ አይደለም። ወደ ጌታ ፊትን ማዞር ዛሬ ነው። መጸለይ ዛሬ ነው። ሲመች ሲያረጅ አይደለም። ሲመችማ ቁምነገሩን ማ ያስታውሳል? እርጅና ቀጠሮውን ይጠብቅ እንደሆነስ ማ ያውቃል?

ዛሬ የሆነው ነው ምናልባት ለነገ የሚተርፈው። “ለሰው፣” ይላል መጽሐፈ መክብብ፣ “ለሰው ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም፤ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተሰጠ አየሁ …መልካምና የተዋበ ነገር፣ ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ እድል ፈንታው ነውና …ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማነው?”

ባጭሩ፣ ጥቃቅኑን የዕለቱን ዘንግቶ የወርና የዓመቱን ማጣጣም አይቻልም። ትላልቁንና የሩቁን ከማሰብ ጋር ጥቃቅኑና የዕለቱ ከተዘነጋ፣ በሚዛን ካልተያዘ፣ መሪ ለቆ እንደ መነዳት ይሆናል። የሩቁን አቀርባለሁ ስንል በእጅ ያለውን መጣል፣ ቀርቦ ያለውን ማራቅ እንዳይሆን ማስተዋል ይጠቅማል። የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች እንዳይተረትብን። የብብቱ፣ በእጅ አለን የምንለው፣ መብላትና መጠጣት፣ ሠርቶ ደክሞ ውሎ የደከሙበትን ፍሬ መጠቀም፣ ለሌላው መትረፍ ነው። በዚያም ውስጥ የእግዚአብሔርን እጅ ማሰብ ነው። ሁሉ ከእርሱ፣ በእርሱ ሆኗል፤ ለእርሱ ምስጋናና ክብር ይሁን። መብላትና መጠጣት ደግሞ አረፍ ብሎ ነው። በቁም እንደ ወራሪ፣ እንደ ወፍ፣ እንደ ፍየል፣ እየነጠቁ፣ እየለቀሙና እየቀነጠቡ አይደለም። ሁሉም እንደ አቅሙ አምላኩን አመስግኖ ሲቆርስ ነው። ከዚህ ይልቅ ምን ይመረጣል? ሰው አቅሙ ትንሽ፣ ዐይኑ ትልቅ፣ ዘመኑ አጭርና በአብዛኛው መንገላታት የበዛበት ነው። ቢያንስ ቢያንስ በዓመቱ ጅማሬ ያልሞላላቸውን ማሰብና ለአፍታ ማሳረፍ ተገቢ ነው።

ቀናቱ እየበረረ አልጨበጥ ሲል ሌላኛው መድኃኒቱ፣ በዝማሬ መረብ ማጥመድ ነው።

እንግዲህ ጌታ ሆይ፣ እንዳስተውል አርገኝ

በቀረልኝ ዘመኔ ፈቃድህን እንዳደርግ አስተምረኝ [አስተምረኝ]

ፈቃድህ ድንቅ ነው የፈጸምከው በኔ

ለዛሬም ለነገም ባንተ ላይ ነው ዐይኔ

የምሄድበትን መንገዴን አሳየኝ

በቀረልኝ ዘመን ፈቃድህን አስታውቀኝ [ፈቃድህን አስታውቀኝ]

እንግዲህ ጌታ ሆይ፣ እንዳስተውል አርገኝ

በቀረልኝ ዘመኔ ፈቃድህን እንዳደርግ አስተምረኝ [አስተምረኝ] – [በተስፋዬ ጋቢሶ፣ ቁ.6/4]

እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰን። ዓመቱ የእግዚአብሔርን ምሕረት፣ ተስፋና ጥበቃ የምናይበት፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ለሕዝብ የሚራሩና ሕዝብና ምድሪቱን የሚያሳርፉ አስተዋይ መሪዎች የሚነሱበት ዘመን ይሁንልን።

ምትኩ አዲሱ / ከ “ዘንድሮስ አልዋሽም” 2002 ዓ.ም. / ገጽ 57-60