የሚያኖር ተስፋ

masqalEditሰውን የሚያኖር ተስፋ ነው፤ ሰው ያለ ተስፋ አይሰነብትም።

ተስፋ ግን በሚያሻግር በእግዚአብሔር ላይ ካልሆነ ምን ዋጋ አለው? የዛሬ ዓመት የነበርንበትን እናስብ። ዘንድሮ የደረስንበትን እናስብ። ምን የተስፋ ጭላንጭል ታየን?

አምና በዚህ ሰዓት ብዙ ደም ሲፈሥሥ፣ ዜጋ ሲታፈሥ ነበር። መጨረሻው፣ እንኳን ለዜጋ ለአገር መሪም አልታይ ብሎ ነበር። ባልታሰበ አኳኋን ባልተጠበቀ መንገድ የተስፋ ደጅ ተበርግዶ ተከፈተ። መሪዎች እንደ ዜጋ ተመልካች የሆኑበት በር ተከፈተ! ከዳር ዳር አገር በእፎይታ ድምጽ ፈነዳ! ሰው ሁሉ ይኸስ ከእግዚአብሔር ነው አለ! በፍጥነት ነገሮች መታጠፍ ጀመሩ።

ዐመጽ ሲሠለጥን ሕዝብ ያለቅሳል፣ ምድር ትናወጣለች፤ ጽድቅ ሲገለጥ ግን ሕዝብ ደስ ይለዋል! መላ ጠፍቶ ታሽገው የኖሩ ፋይሎች ተከፈቱ። በእስር የማቀቁ ዜጎች፣ የታገቱ አንደበቶች ተፈቱ። በሽብርተኛነት ባዕድ ምድር የተጋዙና የተዘጋባቸው ለአገራቸው ለነጻነት በቁ። በዘርና በኃይማኖት የተነጣጠለው እንደገና ተቀራረበ። ከዚህ ወዲያ ተኣምር ምንድነው?

መንግሥት የእግዚአብሔር ናት። የሚያነሳና የሚጥል እግዚአብሔር ነው። ይህን እውነት የዘነጉ፣ ራሳቸውን ያገነኑ፣ በእግዚአብሔር እጅ ላይ ከመውደቅ አያመልጡም።

“[ንጉሥ ናቡከደነፆር] ከአሥራ ሁለት ወር በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ይመላለስ ነበር። ንጉሡም። ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን? ብሎ ተናገረ። ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ ወደቀና። ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ። መንግሥት ከአንተ ዘንድ አለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፤ ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው” (ትንቢተ ዳንኤል 4:28-32)

በእግዚአብሔር እጅ ላይ የወደቀን የሚያስጥል ኃይል የለም። ንስሃ ብቻ ያስጥላል። እግዚአብሔር ምሕረቱ ብዙ ነዋ! ምሕረቱን የተቀበሉ ደግሞ በተራቸው ምሕረት እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል።

የተስፋ ጎህ ሲቀድ፣ የሚያጨልም ኃይል አብሮ ብቅ ይላል። ጽድቅና ጭለማ እነሆ ጎራ ለይተዋል። በጸሎትና በንጹሐን ደምና እንባ የተዘራው ዘር እንዳያብብና እንዳያፈራ እሾህ ብቅ ብሏል። ጭለማው ከጅምሩ ሐዋሳን፣ ቤንሻንጉልን፣ ኦጋዴንን ጋረደ። አዲሳባ ላይ አጠላ። የሐሰተኛ ነቢያት የመተተኞች የቃልቾች ረድፍ በጫጫታ ነደደ። ፍልሚያው ቀላል አይሆንም። እግዚአብሔርን መታመን፣ አጥብቆ መጸለይና የጭለማን ሥራ መግለጥ ግድ ነው። ሌላ ረድፍ ጦርነት ከፍቶ የሚያዋጋ፣ የወሬ እሾህ የሚያራባውን፣ መንጥሮ ከኋላ ለሚመጡ ጥርጊያ መክፈት ግድ ነው። እሾህን ማጥራት ደግሞ ብልሃት ይጠይቃል። ብልሃቱ፣ እሾህን በእሾህ፣ እሾህን በእውነት እሳት ማምከን ነው።

እግዚአብሔር የሚሠራው ለሥራ ባስነሳቸው ሰዎች እጅ ነው። በትረ መንግሥት ያስጨበጣቸው፣ ቅጣት የተበየነባቸውን ሊቀጡ፣ ምሕረት የተገባቸውን ሊምሩ ግድ ነው። ባለሥልጣን በከንቱ ሰይፍ አይታጠቅም፤ ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው። የያዘው ሰይፍ ሁለት አፍ እንዳለው ግን ምን ጊዜም መርሳት የለበትም! የታዘዘውን ያልፈጸመ እለት ወዮለት!

በእግዚአብሔር እንጂ በሰው ተስፋ ማድረግ አያዘልቅም። እግዚአብሔርን የሚታገሉ ፍጻሜአቸውን ያፈጥናሉ። እግዚአብሔር ተሸንፎ አያውቅም፤ የጀመረውን ሳይፈጽም አይተውም። በአዲሱ ዓመት ይኸ ተስፋ ይሁነን!

የአዲስ ተስፋ ችቦ በምድራችን ይጋይ!

ዐብይን በባራክ   ያከበሩኝን አከብራለሁ   መስከረም፣ መስከረም   የያዝነውና የሚመጣው