ርዕሰ አንቀጽ

አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም

ስንነጋገር እውነትን ለማወቅ የምንሻ እንመስላለን። በተለይ ኢትዮጵያውያን። እንዲያውም ሐቅና ፍትሕ ፈላጊዎች ነን ብለን እንኲራራለን! እውነቱ እንዳሰብነው ሳይሆን ሲቀር ግን እናመኻኛለን፣ እናኮርፋለን፣ ወገን ለይተን እንቆራቆሳለን፣ እንጋደላለን።

እውነትን ለማወቅ እንሻለን? እውነቱ እንዳሰብነው ባይሆን፣ ቢቆጠቊጠን ቢያደማን እንኳ ለማወቅና አስተሳሰባችንን ለማቃናት እንፈቅዳለን? ለዚህ ምላሽ ሳንሰጥ ወደ ሌላ መዛመት ራስን ማታለል፣ ዘመናችንን ማባከን ነው። 

“እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ብሎናል (ዮሐንስ 8፡32)። መረጃ እፊታችን ቀርቦ፣ ላለመረታት የራሳችንን መረጃ እንደረድራለን። እውነቱ ሌላው ጋ ሆኖ እያየን፣ ምን ተደርጎ? ማ መስዬው ነው? ይሞክረኝና ይየው! እንላለን! ቀድሞውንም ቅን አልነበርንማ! ሰላም ያጣነው ለምን ይመስለናል?

እውነት አብሮን ሳይኖር ያስታውቃል፤ ረብሻና ጩኸት እናበዛለን። በቍጥርና በጋጋታ ብዛት እናደናግራለን። እውነት እንደ ጧፍ ነው፣ አንዲት ቀጭን ሆና ብዙውን ድቅድቁን ጭለማ ታበራለች፣ ታባርራለች!

ኢየሱስ ለአይሁድ ብዙ ብዙ መልካም ሥራ አሳያቸው፤ ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ፤ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። “የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ፤ ባደርገው ግን፥ እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ” አላቸው። (ዮሐንስ 10፡30-38)

የዕውሩን ዐይኖች አበራ። “ብዙዎች። ጋኔን አለበት አብዶአልም፤ ስለ ምንስ ትሰሙታላችሁ? አሉ።” (ዮሐንስ 9፤10፡20) ጋኔን ያሳውር እንደ ሆነ እንጂ የታወሩ ዐይኖችን ሲያበራ አልተሰማም! ጥላቻ በልባቸው የቋጠሩ እንዲህ ይታወራሉ! ጥላቻቸውን ካልጣሉ ከእውነት ጋር እንደ ተጣሉ ይኖራሉ።

እጁ የሰለለችን ሰው በሰንበት ፈወሰ። የተፈወሰውን ሰው በዐይናቸው አዩት። ኢየሱስን ይከሱት ዘንድ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት። እርሱ ግን። ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው? እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! መልሱ፣ ሰው ከበግ ይበልጣል ነው! ግልጽ እኮ ነው። ግን እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት። (ማቴዎስ 12፡9-14) የኢየሱስ መልካም ድርጊት በልባቸው የሸሸጉትን ክፋት ገለጠባቸው። እውነትን የሚሹ፣ እውነቱ ሲገኝ አሳባቸውንና ድርጊታቸውን ለመለወጥ መዘጋጀት አለባቸው!

...

ኢየሱስን በስቅላት ከገደሉት በኋላ ቀበሩት። በሦስተኛው ቀን እነሳለሁ ሲል ስለ ነበረ ለምናልባት ብለው መቃብሩን በራሳቸው ወታደሮች አስጠበቁ። በሦስተኛው ቀን በማለዳ፣ ኢየሱስ እንደ ተናገረው ተነሣ! ጠባቆቹም … ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ ... መጥተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩ። የሆነው ምንድነው? የሆነው ጠባቆቹ ተኝተው ሳይሆን፣ እያዩ “የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ።” (ማቴዎስ 28:2-4) የካህናት አለቆች ኢየሱስ እንደ ተናገረው ከሙታን እንደ ተነሳ ተረዱ። እውነት ባይሆንማ ጠባቆቹ ይገደሉ ነበር። ስለዚህ ምን አደረጉ? ከሽማግሎች ጋር ተሰብስበው ተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው። እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ። ይህም በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ፥ እኛ እናስረዳዋለን እናንተም ያለ ሥጋት እንድትሆኑ እናደርጋለን አሉአቸው። እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ሲወራ ይኖራል። (ማቴዎስ 28:1-15) አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም!

ተኝተው ከነበሩ፣ ደቀ መዛሙርት መስረቃቸውን እንዴት አዩ? የሚገርመው፣ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ይነሳል ብለው አልጠበቁም! መነሳቱን ቀድመው ያዩ ሲነግሯቸው እንኳ ወዲያው ለማመን ተቸገሩ! 

...

እውነትን ማጣመም ከእውነት ሕይወት መወገድ ነው። ጠባቆቹ “ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ሲወራ ይኖራል።” እውነትን በገንዘብ፣ በሥልጣን፣ በወገንተኝነት መለወጥ በእግዚአብሔር ፊት ነውር ነው። ከእውነት ጋር አለመስማማት አሳሩ ለራስ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ ይተርፋል። እውነት ነው ብለን የያዝናቸውን እንመርምር። ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ሰው፣ ስለ አገር፣ ስለ ባህል፣ ስለ ቋንቋ፣ ስለ ታሪክ፣ ወዘተ። እውነቱ የቱ ጋ ነው? እውነቱ እኛ ጋ ባይኖርስ?

እውነት አያዳላም። የጋራ እንጂ የአንድ ብሔር ወይም የአንድ አገር አይደለም። እውነት የሰው ሁሉ ነው። እውነት ሰው ነው፣ በሰው አምሳል የተገለጠው፣ ከሙታን የተነሳው፣ ሊፈርድ የሚመለሰው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል።” (ዮሐንስ 14፡6፤ 8፡32)

...

በሕይወታችን፣ በምድራችን ሰላም ቢወርድ እንወዳለን? ሁሉ ተስማምቶ ቢኖር፣ ውዥንብር ባይገዛን፣ መነካከስ ቢረግብ እንወዳለን? እንግዲያውስ እውነቱን ለማወቅና ከእውነት ጋር ለመስማማት እንቊረጥ። እውነትን በመፈላለግ ውስጥ ወደ ስምምነትና ወዳጣነው ሰላም እንደርሳለን! ያም እውነት ኢየሱስ ያስተማረውና የኖረው ሕይወት ነው!

የትንሣኤው ጌታ ይርዳን!