bird2

ከፊቴ መገተሯ ለምን ይሆን?

በእጅ የምትገፋ ሣር ማጨጃዬን፣ ሠሌን አልብሼ ከደጅ ትቼ። የሠሌኑ ጠርዝ ክሩ ተተርትሮ ኖሮ የወፊትን እግር ተብትቦ ጠልፎ ስትንፈራገጥ ደረስሁ። ክንፎቿን ታርገበግባለች፣ ትንጫጫለች። ከአዳኝ ወጥመድ ለማምለጥ ስትቻኮል ጥፍሮቿ የባሰ ተጠላልፈው መውጫ አጥታለች።

ምን ቸግሯት እዚህ ውስጥ ገባች? ሰማዩ የርሷ። ዛፉ የርሷ። ሜዳው የርሷ። ዓለም የርሷ። ጠጋ ብዬ ተመለከትኩ። ማጨጃዬ እጭድ ሣር ተሰግስጎበት፣ ተሸፋፍኖ ስለ ከረመ ከውስጡ ቊጫጭ ፈልቶበት ኖሯል።

ጫጫታዋ አላስቀርብ አለ። እንደ ወዳጄ ሙላቱ ብችልበት በወፍ ቋንቋ እሞክራት ነበር። በእንግሊዝኛ ምን ላርግልሽ አልኳት። እኔ ያጠመድኩ መስሎሽ ከሆነ ተሳስተሻል። ሹል ጥፍሮቿ ተቀስረዋል። አላቅቀኝ፣ አላቅቀኝ፣ ውይ፣ ውይ፣ የምትል መሰለኝ። መቀስ ይዤ መጣሁ ብያት ቤት ገባሁ።

ተመልሼ እንዴት ልቅረባት? ምኗን ልያዛት? ጥፍሯ አስፈራኝ፣ እጅ ዐይኔን ብትቦጠቡጠኝስ? አንዴ ... አንዴ ብቻ ታገሺኝ፣ አልኳት። የራበው መቀሴ ሲያዛጋ አይታ እንዲያውም ባሰባት። አይዞሽ አልጎዳሽም፣ ስትክለፈለፊ በራስሽ ላይ ያመጣሽ አንቺ፣ ምን አርግ ነው የምትዪኝ ... ደግሞስ ምን ምርጫ አለሽ፣ አንቺ ወሬኛ አልኳት። አይተሽ አትራመጂም? ለ ሌ ላ ጊ ዜ ት ም ህ ር ት ይ ሁ ን ሽ ...

ብቻ ደስታ ይሁን ፍርኃት፣ እንደ እንዝርት እየሾረች አላስቀርብ አለች። ጥፍሮቿን እንዳልቆርጥ ተጠንቅቄ፣ መቀሴን አሾልኬ ትብታቡን ከሥሩ በጠስኩላት። ብርርርርርርርርር... እግሮቿ እንደ ታሠሩ በረረች። ታንክዩ እንኳ የለ አልኳት። በርራ ሄዳ ዛፍ ላይ ወጥታ ቁጭ አለች። ቊልቊል ታየኝ ጀመረች። ሠራሁለት የምትልም መሰለኝ!

የእግሯቿ ነጻ አለመውጣት ግን አሳሰበኝ፤ ኅሊናዬ ይወቅሰኝ ጀመር። እኔማ ነጻ ያወጣኋት መስሎኝ፤ ግማሽ ነጻነት ግን ከእስራት አይሻል። “ቀስ ብለህ ብትይዛት እኮ ምንም አታረግህም ነበር” አለኝ ኅሊናዬ አድብቶ። ምክንያቴ ያው ፍርኃት ነበር። ብትቧጭረኝስ? ዐይኔን ብትጠነቊለኝስ? ነጻ ማውጣት መስዋእት እንደሚያስከፍል ዘንግቼ!

ትክ ብዬ አየኋት። በርራ ከፍ ካለው ባላ ላይ አረፈች። በዐይኖቼ ተከታተልኳት። እግሯ ታስሮ መብረር ጣጣው ታየኝ? ለባሰ አደጋ አጋለጥኳት ይሆን አልኩ። እጄ ከኋላዬ ቢታሰር መራመድ አይከለክለኝ ይሆናል፤ እጅ ነጻ ሆኖ እንደ መራመድ ግን ከቶ ሊሆን አይችልም ... ወይም እግሬ ታስሮ ሸከፍ ሸከፍ ማለት፤ ያልተለመደ ስለሆነ ይከብዳል አልኩ ... የማደርገው ሲጠፋኝ፣ እኔና እርሷን ወደ ፈጠረ አምላክ መጸለይ ጀመርኩ። አምላክ ሆይ፣ የተጣበቀባትን ትብታብ አንተው በብልሃትህ ፍታላት ብዬ። ወይ ቀርባ በመንቆሯ የምትፈታላት ጓደኛ ላክላት ብዬ። አምላክ ስለ ወፍ ይገደዋል? ስለ ወፍ ጸሎት ይሰማል?

በነጋታው ከቤት ወጥቼ ወደ መኪናዬ ሳመራ፣ አንዲት ወፍ መጥታ መረማመጃ መንገዴ ላይ አረፈች። ልብ ያልኩት፣ ስጠጋ ባለመብረሯ ነው። ወደ ጎን መንገድ ለቅቃልኝ ቆመች። ትክ ብዬ አየኋት። ይቺ ትናንት ከነትብታቧ ያላቀቅኋት አይደለች? ታዲያ የእስራቷ ገመዷ የት ገባ? ወይ ሌላ ትሆን? መጥታ ከፊቴ መገተሯስ ለምን ይሆን?

ምትኩ አዲሱ

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave