ፌስቡክ እንደ ሽብር ፈጣሪ?

corraFB

ፌስቡክ ሰዎችን ለማገናኘት የተፈጠረ ቴክኖሎጂ እንደ ሆነ ሰምተናል። በአንድ መልኩ ይህ ትክክል ነው። በተለይም የህዝብን ድምጽ የሚያፍኑትን ለመቋቋም። ቴክኖሎጂው እንደ በረት አጥሮ ፈር እንደሚያስዝ ግን እምብዛም አይወሳም። ሰዎችን ያገናኛቸው ያው መስመር፣ ሰዎችን በብቸኛነት ወጥመድ ውስጥ አስገብቶ እንመለከታለን። ወጥመድ፣ ሱስ ሲሆን ማለት ነው። ሱስ፣ ግለኛነትን፣ ራስ ወዳድነትን፣ ቊጡነትን መቆስቆስ ነው። ራስ ወዳድነት፣ ለመታየት መጎምጀት ነው፦ ይኸን ያህል ተከታይ አለኝ፤ ተወዳጅ፣ ታዋቂ ነኝ ማለት። ፌስቡክ ዞሮ ዞሮ የንግድ እንጂ የበጎ አድራጎት ድርጅት እንዳልሆነ አንዘንጋ!

ፌስቡክ ነገሩ አደባባይ፣ አኳኋኑ ስውር ነው፤ ስም ቀይሮ አደጋ ለመጣል ያመቻል። ተጠሪነትን ላለመቀበል ያመቻቻል። ደግሞ ማህበራዊ እርከን ያበጃል። እዚያ እርከን ላይ ለመድረስ ሌላውም ባዋጣው መንገድ ሁሉ ይጥራል። አብዛኛው ሰው በቅርብ አለመተዋወቁ፣ አጀቡንና ወዳጅነቱን ዝናብ እንደሌለው ደመና አድርጎታል።

ታዲያ ፌስቡክን ከሽብር ፈጣሪ ጋር ምን ያገናኘዋል? ሽብር ፈጣሪ፣ ማህበረሰብ የሚተዳደርበትን ህግና ባህል ወደ ጎን አርጎ የራሱን ፈር ይቀድዳል፤ ተጠሪነትን ይሽራል፣ ውዥንብር ይነዛል። በዚህ መልኩ፣ ፌስቡክ አዲስ ባህል፣ አዲስ ግንኙነቶች፣ አዲስ ቋንቋ (አዲስ አስተሳሰብ) በማዋለዱ ያልነበረ ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ ነው። ፒው የምርምር ማዕከል፣ የፌስቡክ/ሶሻል ሚድያ ጥቅሙና ጉዳቱ መሳ ለመሳ መሆኑን ቅርብ ጊዜ ዘግቧል

ቴክኖሎጂ በቋንቋ ላይ ተጽእኖ ማምጣቱ አይደንቅም። ችግሩ፣ ከባህሉ አንጻር ተግቶ በኃላፊነት ፈር የሚያስይዝ አካል አለመኖሩ ነው፤ ማህበራዊ ተቋማትና መሪዎች የቋንቋ ለውጦችን በማስተናገድና በመምራት እንደሚገባ አለመሳተፋቸው ነው። ግለሰቦች በመሰላቸው ቃላትን መፍጠራቸው፣ ማዕከላዊነት በሌለበት ቃላቱ መደበኛ ሆነው መራባታቸው ነው። ነገር ከተዛነፈ በኋላ ማቃናት፣ ከጅምሩ እንደማቃናት አይቀልም!

የሚገርመው፣ የተማረው ክፍል ይህን ችግር በማባባስ መሠማራቱን አለማስተዋሉ ነው፤ በአደባባይ የሚገለገልባቸው ቃላት፣ ሠፊውን ህዝብ ካለመወከል አልፈው ውዥንብር እየፈጠሩ ነው። ጊዜ ካገኙ፣ የፖለቲካና የትምህርት ተቋማት መሪዎችና የወንጌል ሰባኪዎች የሚጠቀሙትን ቋንቋ ያጢኑ!

ፌስቡክ በአማርኛ መናገር ከጀመረ ወዲህ፣ አፍ የፈታበት እንግሊዝኛና የእንግሊዞች ልማድ ሠርጎ አገራችን መግባቱ፣ በብልሃት ክሩን ካላስለቀቁ በስተቀር፣ ውሎ አድሮ እንደ ፈንጂ የባሰ ጕዳት ማስከተሉ አይቀርም።

ለምሳሌ፦ “ላይክ(ስ)” (Likes) የሚለው “ይውደዱ፣ መውደዶች” ተሰኝቷል፤ በእንግሊዝኛ “ላይክ” እና “ላቭ” ትርጒማቸው ለየቅል ነው፤ “ላቭ”ወዳጅነቱ የጠለቀ ነው። በአማርኛ ግን መውደድ፣ ማፍቀር ነው። “ይውደዱ፣” ያልተገባን ቃል ላልተገባ ግንኙነት መጠቀም ነው፤ እግዚአብሔርን እወዳለሁ፣ አገሬን እወዳለሁ፣ ሚስቴን እወዳለሁ ከሚለው ጋር እንዴት ይጣጣማል? “ጎሽ!” አማራጭ አይሆንም? በባህላችን “ውደዱኝ” ግር ይላል እኮ!!

“የታሪክ አርካይቭዎ” = ለምን “ማህደር” “መዝገብ ቤት” "ጓዳ" አይሆንም? | “ኮቴ” = ለምን “አድራሻ” አይሆንም? | Timeline = የጊዜ መስመር ተሰኝቷል፤ “ዘመን” አይሻልም? | Cookies = ኲኪዎች ተሰኝቷል፤ ኲኪ በአማርኛ ጆሮ ግንድ ማለት ነው!! | “ግላዊነት - ስለ ፌስቡክና ስለ አንተ ደህንነት ተማር” ምን ለማለት ነው? | “ጓደኞችን ይጥቀሱ” = “ጓደኞች ያፍሩ” ወይም “ጓደኞች ያብጁ” አይሆንም? | What is on your mind? “አሁን ምን እያሰቡ ነው?” ተሰኝቷል፤ “አሳብዎን እዚህ ይጻፉ” ማለት አይበቃም?

የምንጋራቸው ቃላት ለማህበራዊ ጤንነታችን መሠረት ናቸው። በጊዜ ማረም ሲቻል፣ ለሚቀጥለው ትውልድ የተዘባረቀ ትርጒም ማውረስ በደል ነው። ወንጌል ሰባኪ የአድማጩን አቅም አለመመጠኑ፣ የወንጌልን እውነት በማክሸፉ በእግዚአብሔር ዘንድ ተጠያቂ ነው። ሁለት ችግሮች ጎልተው ይታያሉ፤ አንደኛው፣ የተማረው ክፍል ጥቂት ሆኖ ሠፊው ህዝብ ወዳለበት እንደ መሄድ፣ የራሱን ክልል አበጅቶ፣ ኃላፊነቱን ዘንግቶ መገኘቱ ነው። ሁለተኛው፣ በቴክኖሎጂው የሠለጠኑ የተባበረ ግንባር ፈጥረው ይህን አረም ለማረም አለመትጋታቸው ነው። ማህበራዊ ቅንነት ካለ አሁንም ጊዜው አላለፈም!