ስሜን በእንግሊዝ

አገራችን ከገባችበት ችግር ለመውጣት፣ የራስን ስም አስተካክሎ መጻፍ፣ የሌሎችን አስተካክሎ መጥራት፣ ያለ ስም ስም አለመስጠት ጥሩ ጅማሬ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ራሳችንን ማክበር ሳናውቅበት፣ ሌላው ያክብረን ማለት ከሌለ ደመና ዝናብ እንደ መጠበቅ ነው!

ስሜን በእንግሊዝ የምጽፈው M-i-t-i-k-u ብዬ ነው፤ የአባቴን ደግሞ A-d-i-s-u ብዬ። አገር ቤትና በዓለም ዙሪያ የተበተኑ ሞክሼዎቼ ስማቸውን Mitikku Meteku Metiku Addisu Addissu Adissu ይላሉ። ምክንያታቸውን እነርሱ ያቅርቡ ብዬ ልለፍ?

ስሜን ስቀርጽ ለፈረንጁ ቀላሉን ድምጸት በማሰብ ነበር፤ ለምሳሌ፣ “d” ከጅማሬው በነጠላ ሲነበብ “ዲ” እንጂ “ድ” አይሆንም፤ “i” “d” ን ሲከተል ያጠብቀው እንደሆን እንጂ አያላላውም። አሁን የቸገረኝ፣ ስሜ ያለ ፈቃዴ ሁለተኛ “ዲ” መጫኑ ነው። ለምሳሌ፣ “የሚሌኒየም እንቊጣጣሽ” የተሰኘ ጽሑፌን የ “ሳይበር ኢትዮጵያ” አታሚ ሁለት “ዲ” አሸክሞ አትሞታል። ተመራማሪው ዳታ ዲአ A Sombre Lesson in Political Leadershipን ሲጠቅስ፣ “by Mitiku Adisu” በግልጽ ተመልክቶ፣ ስሜን ድርብ “ዲ” አርጎ አርሞታል! ይህን ባህል ተደጋግሞ ሳይ፤ ጥያቄ ፈጠረብኝ።

ፈረንጆች ለቋንቋችን ባእድ ናቸውና፣ የፊደል ጭማሪ ወይም ግድፈት የተለያዩ ሰዎች ስም እንጂ የአንድ ሰው አይመስላቸውም። ኢንተርኔት ነጋዴዎች ያን ተቀብለው ይከንፋሉ፤ ከምንጩ ለማጣራት ብዙ ሰው በማይፈቅድበት ዘመን የስህተት ድግግሞሽ ይፈጥራሉ። ባጭሩ፣ ሳላውቅ ሳልፈቅድ ንብረቴ በንጥቂያ ለሌላ ተሰጠ ማለት ነው!

ነገርን ጨምሮ ወይ ቀንሶ ማየት የሚያበዛ ሰው አለ። አንዳንዱ የራሱን ስህተት ሳያርም፣ የሌላውን አለማወቅ ለማረም ይቻኮላል። ያለባለቤቱ ፈቃድ ህግ ያግደኛል እንኳ አይል! ከመሬት ተነሥቶ ስምህ በአንድ “ዲ” አይጠብቅም ይላል። “ዲ”ን ሳልደርብ፣ በነጠላ አደባባይ የወጣሁ ያስመስልብኛል! ለምን ትርፍ ፊደል ጫናችሁብኝ ስላልኩ ያኮረፉ ገጥመውኛል፤ “ዲ” ሆነ “ዲዲ” ምን ለውጥ ያመጣና ነው ብለውኛል!

እስቲ ከአገር መሪዎች ከፊል ምሳሌ ላቅርብ፤ [ደማቅ ፊደላት ባለቤቶቹ የሚጠቀሙበት ነው፤ ደብዛዛው ሌሎች። እርግጥ ነው ለኢትዮጵያውያን ለውጥ የለውም፤ Birtukan Mideksa, Birtukan Midekssa, Birtucan, Birtukan Midaksa, Bertukan Midekssa ቢደረደር አንድዬዋ ብርቱካን ሚደቅሳ እንደ ሆነች አይሳሳተንም! ስህተቱ ግን እንግሊዝኛን በቋንቋችን ሥርዓት ሥር ማስተዳደር እንደማይቻል ካለመገንዘብ የመጣ ነው! ስህተቱ ሌላውን እንደ ሌላነቱ እንደ መቀበል፣ በድፍረትና በግዳጅ በእኛ ቀለበት ውስጥ ለማስገባት መቻኮላችን ነው!]፦

Abiy Ahmed, Abey Ahmad, Abbiy Ahmed | Sahle-Work Zewde, Sahlework, Sahle Werk Zwide, Sahlewerq | Berhanu Nega, Berehanue Nega, Birhanu Negga | Tsegaye Gabre-Medhin, Tsegaye Gebremedhin, Tsegaye Gebre Medhin | Tilahun Gessesse, Telahun Gesese, Tilahun Gessese, Tlahun Gessese, Xilahun Gessessee | Mengistu Worku, Mengistu Werku, Mengestu Werqu

ላይታረም፣ ሁሉም በመሰለው በዩቱብ በፌስቡክ መጻፍና መለጠፉ መረን ለመውጣት ምክንያት ሆኗል። የትምህርት ጥራት መውደቅ የጀመረው ገና ከመጠሪያ ስም ነው! ስሙን አስተካክሎ ካላወቀ ሌላው አስተካክሎ እንዲያውቅለት መጠበቅ ሞኝነት ነው። ዕድሜ ልኩን ስሜ አይደለም ሲል ይኖራታል፤ ወይም ያለ ስሙ “ወይ!” ይላል። በተጽእኖ ብዛት ማንነቱን እንዲክድ ይደረጋል!

ስም የማንነት መገለጫ ነው። ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ምድራችን በማንነት አንድ እግር ቆማ አለች። በአጽንዖት የተያዘው “ጥያቄ” እንጂ መፍትሔ አይደለም፤ ጥያቄ ተዛብቶ መልስ ይስተካከል ማለት ግን ሥራ መፍታት ነው። ግልጽ እንሁን፤ በዓለማችን ሳይቀባበል፣ ራስን አግልሎ መኖር እንደማያዘልቅ ሳይረዳ መፍትሔ አይገኝም! እንስሳም እንኳ አብሮነትን በደመ ነፍስ አውቆታል። ሁለተኛ፣ ሳይደራደር፣ በቀጭን ትእዛዝ ብቻ መፍትሔ አይመጣም።

ችግራችን ነገሮችን ሚዛናዊና ሁለገብ በሆነ መልካቸው አለማየት ነው። መፍትሔው ደግሞ ስምና ምግባርን አስተካክሎ ማወቅ ነው! ድሮ የጎጃም ንጉሥ፣ የትግራይ፣ የሸዋ፣ የጂማ፣ የወላይታ ንጉሥ፣ ወዘተ እንል ነበር። ከዚያ፣ የወለጋ ጠቅላይ ገዥ፣ የኤርትራ፣ የሐረር ገዥ፣ ወዘተ አልን። ከዚያ፣ የሸዋ አስተዳዳሪ ፣ የባሌ፣ የከፋ፣ ወዘተ። ወደ ኋላ ተመልሰን የክልል ፕሬዚደንት አመጣን። ዛሬ በፖለቲካ ፕሬዚደንት ብዛት አገራችንን የሚተካከል የለም! ሌላውን ሁሉ ሳንጨምር፣ ዘጠኝ የክልል ፕሬዚደንት፣ አንድ የአገር ፕሬዚደንት (ወይም ጠቅላይ ፕሬዚደንት?)። የኦሮምያ ፕሬዚደንት፣ የትግራይ ፕሬዚደንት፣ የአፋር ፕሬዚደንት፣ ወዘተ። ለውጭ እንግዳና፣ በክልል ተወልዶ በክልል ላደገ፣ አንድ ሳይሆን አስር አገር ቢመስለው አይደንቅም። “እንደራሴ” “አስተዳዳሪ” እና “ጠቅላይ ገዥ” ምን ጒድ ተገኘበት? በነገራችን ላይ፣ ብሔራዊ ባንክ ዛሬም “ገዥ” አለው!

ሌላው በሚያየን ዐይን ራሳችንን አለማየት ለመታረም አለመፍቀድ ነው። አጥርቶ አለመስማት በጭፍን እንደ መራመድ ነው። ያልገባንን አለመጠየቅ ትሑት አለመሆን ነው። ለመታረም አለመፍቀድ በድንቊርና መቅረት ነው። ድንቊርናው ለጎረቤት ጭምር የሚተርፍ ነው። የታሪክን ስህተት መደጋገም ነው።

ሌላውን ንቆ በማንነቱ ሲኲራራ፣ ሰው ራሱን ያዋርዳል። ለራሱ ክብር ያጣን ያክብረኝ ማለት ቂልነት ነው። እንደ ኢትዮጵያዊ አንገተ ደንዳና ያለ አይመስለኝም፤ እምቢተኛነትን እና አዙሮ አለማየትን፣ ጀግንነትና ብሔራዊ ወኔ አሰኝቷል። የበሽታውን ዓይነት ስላሳሳተ በጣእር ተይዞ አለ፤ ደንዳናነቱ መድኃኒቱን አርክሶ ፈውሱን አዘግይቶበታል።

ሁለት ስም፣ ሁለት ማንነት መፍጠር ነው፤ ግራ ተጋብቶ ግራ ማጋባት ነው። የዛሬ ዘመን ዳኛ ደፍሮ ስምህ ሁለት ስለሆነ ለምስክር አትበቃም ይለኛል? አንድ “ዲ” ሆነ ሁለት፣ ያው “ዲ” ነው ብሎ ያልፈኛል? በዚህ በሽብር ዘመን፣ ድርብ ስም አውሮፕላን ያሳፍረኛል? ሥራ ያስቀጥረኛል? ለትልቅ ኃላፊነት ያበቃኛል?

ቀላል የመሰለ ነገር ይኸውላችሁ፣ ውጤቱ እንደዚህ ውስብስብ ነው! የተጋረጠብንን ችግር ለመፍታት፣ የሌላውን ስም አስተካክሎ መጻፍ ይቀድማል!!