እንኳን ደስ አለን፣ እግዚአብሔር ይርዳን!

abiyNobel

Niklas Elmehed. © Nobel Media

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የአውሮጳ 2019 የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሆነዋል። ይህም በአንድ መልኩ ለኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ ያጯቸው ግለሰቦች የተቀናበረ ጥረት ውጤት ነው። ኮሚቴው ዶ/ር ዐቢይን የመረጠበትን ምክንያት፣ “ሰላምና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ለማስፈን፣ ይልቅ ደግሞ ከኤርትራ ጋር የነበረውን የድንበር ግጭት ለመፍታት ስለ ወሰዱት እርምጃ” ሲል ገልጾታል።

በሰላም ኖቤል ተሸላሚነት ዶ/ር ዐቢይ ከአፍሪካ ዘጠነኛው ሰው መሆናቸው ነው። ለምሳሌ፣ ኮሎኔል ሳዳት በ1978 ከእስራኤል ጋር ስለ ተፈራረሙት የሰላም ውል (ከእስራኤሉ መናኽም ቤግን ጋር ሽልማቱን ተጋርተዋል)። (ሳዳት ከሦስት ዓመት በኋላ ስምምነቱ ባስቆጣቸው በጀማ ኢስላሚያ ቡድን ተገድለዋል።) የኬንያዋ ዋንጋሪ ማታይ በ2004 (ችግኝ በመትከልና በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው)። ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ዶ/ር ዴኒስ ሙክዌጌ በ2018 በሴቶች ሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው። ወዘተ።

ከ1901 ጀምሮ በፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዚኦሎጂ ወይም ህክምና ሳይስንስ፣ ሊተራቱር፣ ሰላም፣ እና የኢኮኖሚ ሳይንስ ኖቤል ሽልማቶች ተሰጥተዋል። ኖቤል፣ ለሰው ልጆች ጠቀሜታ የሚውሉ ጥረቶችን በማበረታታት ቀዳሚው ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው። ሽልማቱ ገንዘብ፣ ሜዳልያ፣ እና ዲፕሎማ ያካትታል፤ የዚህ ዓመቱ የገንዘብ ሽልማት $986 ሺህ ዶላር (ሃያ ዘጠኝ ሚሊዮን፣ አንድ መቶ ሃያ አራት ሺህ፣ አራት መቶ ሰባት ብር፣ ከሰባ ሦስት ሳንቲም) ነው።

የሽልማቱ አሰጣጥ ተቃውሞና ቅሬታ አያስከትልም ማለት አይደለም። ለምሳሌ፣ በ1973 የአሜሪካው ውጭ ጒዳይ ሚ/ር ኪሲንጀር እና የሰሜን ቪየትናሙ ለ ዶክ ቶ ሽልማቱን እንዲጋሩ ተደርጓል (ለ ዶክ ቶ ሽልማቱን አልቀበልም ብለዋል)። ተቃውሞው፣ አሜሪካ ጠብ ጫሪና አውዳሚ ሆና፣ ጦርነቱም ሳይቆም፣ ኪሲንጀርን እንደ ሰላም አምጪ መሸለም በግፍ ላይ ግፍ ነው የሚል ነበር፤ ግፉን በመቃወም የኖቤል ኮሚቴው ሁለት አባላት ወዲያው ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቅቀዋል።

ኖቤል ኮሚቴ ፖለቲካዊ ዓላማ የሌለው ነጻ ድርጅት አይደለም። ለምሳሌ፣ በ2009 ሥልጣን በያዙ በ11ኛው ቀን፣ ለአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የተሰጠው ሽልማት፣ ከእርሳቸው ቀድመው የነበሩት ጆርጅ ቡሽ የቀሰቀሱትን ኢፍትሓዊና አውዳሚ የኢራቅ ጦርነት እንዲያስቆሙ፣ የግፍና የሰቆቃ ማእከል የነበረውን ጓንታናሞን እንዲዘጉ ለማበረታታት ጭምር ነበር። አንደበተ ርቱዑ ኦባማ “ተስፋ” “ሰላም” “እኲልነት” “ፍትኅ” “ፍቅር” ሲሉ ነበረና። በስምንት ዓመት አመራራቸው የታየው ግን የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን አሁን ለሚታየው ዐይን ያወጣ የሰውን ልጅ አዋራጅ ሥርዓት መንገድ ከፍቷል።

ባራክ፣ ዶ/ር ዐቢይ ከሚያደንቋቸው መሪዎች ቀዳሚና ለኖቤል ኮሚቴ ካጯቸው መሓል ናቸው።

ውድ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፦ የባራክን ስሕተት እንዳይደግሙ፣ ግለ ታሪክዎም እንዳይጎድፍ፣ አሻግራለሁ ያሉት የኢትዮጵያ ሕዝብ የከፋ ዘመን ከፊቱ እንዳይጠብቀው፣ ቀና ከሆኑ ልምድ ካካበቱ ከጎሠኛነት ከተላቀቁ ዜጎች ጋር በመመካከር አስቀጣይ እርምጃ እንዲወስዱ፣ ሥልጣን ላይ ሙጭጭ የማለት አሳብ እንደሌለዎት በገለጹት መሠረት እንዲጸኑ፣ እና እንዲከናወንልዎ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳዎ! ኖቤሉ፣ ሽልማት ብቻ አለመሆኑ የሚዘነጋዎ አይመስለንም። ሽልማቱ ጒቦ ነው፤ ቀፎ ነው። አውሮጳና አሜሪካ በአፍሪካና በአፍሪቃ ቀንድ በተለይም በአገራችን ያላቸውን ስትራቴጂያዊ እቅድ ማስፈጸሚያ ነው። የጠ/ሚንስትርነቱን ሥልጣን እንደ ጨበጡ ቶሎ ከአሜሪካ አምባሳደር ጋር በአዲስ አበባ፣ ኋላ ከአሜሪካው (ፕሮቴስታንት) ም/ፕሬዚደንት ፔንስ ጋር በዋሽንግተን፣ ከዓለም ባንክ ለጋርድ ጋር፣ ከእስራኤል ኔታንያሁ (የአሜሪካ ዐይን በመካከለኛ ምሥራቅ) ጋር መገናኘትዎ ይህን ጠቋሚ ነው። የአገራችንና የሕዝቦቿን መብትና ጥቅም ማስጠበቅ፣ ከባእዳን ቡድኖች ጥቅም ጋር ማስታረቅ ትልቅ ፈተና አለበት። ብቻዎን መሆንዎ፣ አገራችን ከተጋረጠባት ውጣ ውረድ አንጻር፣ በብዙ መልኩ አፋፍ ላይ አድርሶናል። ከእንግዲህ በዙሪያዎ የሰበሰቧቸውን አማካሪዎች ብቃትና ቅንነት በጥንቃቄ መመርመርና ለተተኪ ድርጅቶች ማመቻቸት የግድ ይኖርብዎታል።  

እንኳን ደስ አለዎት!

ለመቶ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ