ጒግል ብሎ አዋቂ

የጒግል ጥቅሙ ብዙ ነው። ለብዙዎቻችን ብቸኛ የመረጃ ምንጭ መሆኑ ግን አሳሳቢ ነው። በአገራዊ ጒዳይ ላይ ለመወያያ ሞባይላቸውን እንደ አቡነ ዘበሰማያት የሚደጋግሙ በዝተዋል። ለእንደዚህ ዓይነቶች እንቅፋት ተጋርጦባቸዋል። እነዚሁ በአብዛኛው፣ ስለሚወያዩበት ጒዳይ መሠረታዊና ሁለገብ እውቀት የላቸውም፤ የእውቀት አድማሳቸው መጥበብ የመረጃ ምንጮችን ተኣማኒነት ለማመሳከር እንዳይችሉ አግዷቸዋል። ላሰቡት ዓላማ ካልሆነ መረጃ አይሹም፤ መረጃ የሚሹት ሌላውን ለማንበርከክ፣ ወዳጅን ለማገዝ፣ አዋቂ ለመምሰል ነው።

ልጆች ሳለን አበበ ቢቂላ ቶኪዮ ጃፓን ማራቶን አሸነፈ ማለትን ሰማን። ከአብሮ አደጌ ጋር እንደ ተገናኘን ስለዚሁ ማውራት ጀመርን። ማራቶን የሚል ቃል ስንሰማ የመጀመሪያችን ነበር፤ ስለ አበበ ቢቂላም ሰምተን አናውቅም። ቤታችን ለአውሮፕላን ማረፊያ የቀረበ ነበርና ያን እለት ከዚያ ሄደን መሮጥ ጀመርን። አበበ ያሸነፈው እንዴት ፈጣን ቢሆን ነው ብዬ ሳስብ፣ ጓዴ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ (ዲሲ 3) መሬት እንደነካ አበበ ቢሮጥ ይቀድመዋል የሚል አሳብ አመጣ። አባባሉን ለማመን ጊዜ አልፈጀብኝም። እርግጥ አሁን ሳስበው ያስቀኛል። ያኔ ግን የእውቀቴ አድማስ ጠባብ ነበር። የማራቶንን (42 ኪ.ሜ.) ርቀት ለመገመት አልበቃሁም ነበር። የጓደኛዬን አለማወቅ የሚከላከል የመረጃ ጒልበት አልነበረኝም፤ አባባሉ ግን በሰዓቱ ጥሞኝ ነበር። ማራቶንና ጦርነት ለየቅል ቢሆኑም፣ ጣልያንን አድዋ ላይ ድል እንደመታን፣ አበበ ጃፓን ላይ ፈረንጁን ጒድ ማድረጉን ፈልጌው ነበር።

bikilaEALአገር ወዳዱ “መምህር ታዬ” የቆየ ታሪካችንን ሲያብራሩ የሰሙ ብዙዎች አወድሰዋቸዋል። የኢትዮጵያውንን መጋመድ ለማስረዳት የራሳቸውን ቤተሰብ ታሪክ በምሳሌነት አቅርበዋል። ምሳሌው፣ የአገር መሪዎቻችን ሥልጣን ላይ ለመቆየት የተጠቀሙት ከፋፋይ አጋዳይ ስልት የመከነበትን ምክንያት የሚያጎላ ነው። የመምህሩ ትምህርት ካነጣጠረባቸው አንደኛው የጀዋር (አኖሌ ጡት ቆረጣ)ትርክት” ላይ ነው። (ለመማማሪያ እንጂ ጀዋርን ለመደገፍ አይደለም፤ ሆኖም ጀዋርም እንደ እስክንድር፣ እንደ ብርቱካን፣ እንደ ታማኝ አሳቡን ለመሠንዘር መብት የለውም ማለት አይደለም።)

መምህር ታዬ ተኣማኒነታቸውን ለማጠናከር ኦሮሞነታቸውን መግለጥ ነበረባቸው። ከትግራይ ወይም ከሌላ ቢሆኑ፣ በኦሮሞ ላይ ጥላቻ አላቸው እንዳይባሉ። መምህሩ የጃዋር አባት የመናዊ መሆናቸውን በፎቶ አስደግፈው አጋልጠዋል። (በፎቶው ላይ የጀዋር አባት ጀምቢያ ጎራዴ ታጥቀዋል፤ ጎራዴው በባህላቸው ከረባት እንደ ማሠር ቢሆንም መስለቢያ አስመስለውታል! ነገር ከከፋ ጀምቢያ ለመሳሪያነት አይውልም ማለት አይደለም፤ ከረባትም ለመታነቂያ ይውላል እኮ!)። ሁለት ነገር እንታዘብ። ትዝብት አንድ፤ ጀዋር ከአባቱ ቀድሞ አልተፈጠረምና ላለመወለድ ምርጫ አልነበረውም። መምህር ታዬ፣ ጀዋር ላይ ጠነከሩበት እንጂ መወለድ በምርጫ አይደለም ብለውን ነበር። የጀዋር አባት የመናዊነት ያስፈለገው ባእድ (እስላም) ለማሰኘት (በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር) እና በሽብርተኛነት ለመፈረጅ እንዲያመች ነው። ጠላት ከሆነ ለመጥላት፣ ለማግለል፣ ለመግደል ይቀላላ! ደርግ እና ህወሓት/ኢሕአዴግ፣ ያልፈለጓቸውን ለማስወገድ “ሽብር ፈጣሪ” እንዳሉ ሁሉ። እውነቱ ግን የቱ ነው? አባቱ የመናዊ ቢሆኑም፣ ጀዋር ኢትዮጵያዊ ነው። ትዝብት ሁለት፤ መምህሩ የታሪክ ምሑር ናቸውና፤ እውነተኛ ታሪክ ደግሞ ዘመድ አይመርጥምና፣ አፈሙዛቸውን ደጋፊዎቻቸው ላይ ያዞሩ እለት አወዳሾቻቸው እንደሚያወግዟቸው እሙን ነው። ስለ ዶ/ር ነጋሦ፣ ስለ አቶ ለማ መገርሣ፣ ስለ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ስለ ወ/ሮ መዐዛ አሸናፊ፣ ስለ አቶ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ሲባል የነበረውን አሁን እየተባለ ካለው ጋር ያስተያዩ!

አዲሳባን፣ ፊንፊኔ፣ ሸገርም ይሏታል። ህወሓት/ኢሕአዴግ፣ አዲሳባን በኦሮምያ ውስጥ ከልሎ ማንነቷን በእንጥልጥል በመተው፣ በ “ልማት” ስም መሬት ተቀራምቶና አቀራምቶ ሕዝብ አፈናቅሏል። ምግባሩ ሕዝባዊ ዐመጽ በማቀጣጠሉ፣ ህወሓት ሳያስበው ወደ ፖለቲካ ምድረበዳ ተግዟል። ዶ/ር ዐቢይ ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ ሁሉም በየፊናው ስለ አዲሳባ ያቀረበው የታሪክ መረጃ ምንኛ መደማመጥ እንደ ተመናመነ፣ ምሑራን ለስሜታቸው፣ ለሆዳቸውና ለአንጃቸው እንጂ ለእውነት ተገዥ እንዳልሆኑ አይተናል። እውነቱ ምንድነው? እውነቱ አዲሳባ የኢትዮጵያና የአፍሪካ መናገሻ ነች። አዲሳባ፣ ፊንፊኔ ወይም ሸገር የተባለችው ዛሬ አይደለም፤ ፊንፊኔና ሸገር እንዳንላት የሚከለክለን የለም። አገራዊ፣ አህጒራዊና ዓለም አቀፋዊ ከተማ ነችና ስሟን እንለውጥ ማለት ግን ስንት ዘመን የተገነባን ማውደም ነው፤ የልጆች ጨዋታ ነው። የስድሳ ስድስቱ አብዮትና የሰማንያ ሦስቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ያወደሙትን መች አቃንተን ጨረስን!

በአሳብ ዙሪያ መነጋገር ያለመቻል ባህል ከስድሳ ስድስቱ አብዮት ወዲህ ማህበራዊ ውርደትን አበራክቷል። ይህም የአሳብ ድህነት አንደኛው ምልክት ነው። ውርደት ካለበት ክብርና ማህበራዊ እውቀት አይዳብርም። ከገባንበት አዙሪት እንዴት እንውጣ? መረጃን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም ትርፉ ጠባሳ ብቻ እንደሆነ አይተናል። ስለ ዶ/ር ዐቢይ፣ ስለ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፣ ስለ እስክንድር፣ ወዘተ፣ ተቃዋሚዎቻቸው የሚሉትን ማነጻጸር ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለው። አንዳንዶች፣ አንድን አሳብ በወሬ እንጂ በቅጡ ሳይረዱ ይከራከራሉ። አሳቦችን ተረድቶ ተገቢውን ምላሽ በአክብሮት ለመስጠት ትሕትና፣ ጊዜ፣ ብቃትና ትጋት ይጠይቃል። ይህ ስለሌለ፣ በተገኘ የመረጃ ቅዝምዝም አጥንት መስበር የዘመኑ ጊዜ ማሳለፊያ ጨዋታ ሆኗል። ይህ ሃምሳ ዓመት ያረገ የጭለማና የሤራ ባህል እስካልተለወጠ ከገባንበት ማጥ አንወጣም!

“ጀዋር”ን “መምህር ታዬ”ን “እስክንድር”ን በእንግሊዝኛ ጒግል አደረግሁ። ውጤቱ የሚገርምና ግራ የሚያጋባ ነው። ለሁሉም እንደ ዐመሉና እንደ ዓላማው የሚስማማው ምላሽ ተለጥፎለታል። የአስተሳሰቦችን፣ የአስተምህሮዎችን ሂደት አጥርቶ አለማወቅ እውነቱን አድበስብሶታል። ደግሞ “Ethiopia birds”ን ጒግል አደረግሁ። “ኢትዮጵያ (በፈረንጆች አቆጣጠር) እስከ 1974 ድረስ አቢሲንያ” ትባል ነበር አለኝ። በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን የተወለዱ ይህን እንደ አምላክ ቃል ቢቀበሉ አይድነቀን! የአገራችን ልበ ጠባብ መሪዎች ትምህርት ቤቶችን ለአጭር ዓላማቸው በማዋላቸው ወጣቱን ትውልድ ውዥንብር ለቅቀውበት እያስዘረፉት ነው። ቴክኖሎጂ ውዥንብሩን አባብሶታል። መሠረታዊና ሁለገብ እውቀት ሳይኖር እውነቱን ማመሳከር እንዴት ይቻላል? ብዙዎቻችን የጊዜውን ፖለቲካ እንጂ የነገውን አላየን፤ ተባብረን የቆፈርነው ጒድጓድ ሣር ተጎዝጉዞበት እንደሚጠብቀን ዘንግተናል። መፍትሔው ምንድነው ይላሉ?

ለምሳሌ፣ “ዶ/ር እከሌ” የጻፈውን ጠቅሶ የተከራከረ ግለሰብ አለ። “ዶ/ሩ” መረጃውን ሳያጣራ ተከራካሪውን ለመርቺያ ጨማምሮበት እንደ ሆነ ግን ያወቀ አይመስልም። በሌላ አነጋገር፣ ጒግል ላይ ስለ ተገኘ ወይም “ዶ/ር” ስለ ጻፈው ትክክል ነው ማለት አይደለም! ባጠቃላይ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አማራ፣ ወዘተ ተወያዮች የሚጠቅሱት የራሳቸውን “ምሑር” ነው፤ የዘንድሮ እውቀት ክልል በክልል ሆኗል! እነዚሁ ሲመቻቸው ብቻ፣ ሚዛናዊ እንዲባሉ፣ ከሌላው ወገን የሚደግፋቸውን ይጠቅሳሉ! የእውቀት ቅንቅን የክት ልብሳችንን አንክቶት ጒስቊልናችንን የማንደብቅበት ደረጃ ላይ ደርሰናል!

አደባባይ ወጥቶ ገንቢ ውይይት ለመወያየት ቢያንስ ሦስት ነገሮች ያስፈልጋሉ። አንደኛ፣ ትክክለኛ መረጃ የተጠማ አእምሮና ልቡና፤ እውነቱን ተናግሮ የመሸበት የሚያድር ሰውነት። ሁለተኛ፣ ለመማር የሚፈቅድ ጥንቊቅና ትሑት ልብ፤ ሲሳሳት ሰበብ ከመፍጠር ይልቅ ተሳስቻለሁ ብሎ ከስሕተቱ የሚማር፤ ሌሎችም ጋ እውነቱ ሊኖር ይችላል ብሎ የሚያስብ፤ እውነት ብቻ አርነት እንደሚያወጣ፣ ውሸት እስረኛ እንደሚያደርግ የሚገነዘብ። ሦስተኛ፣ የሰው ዘመኑ አጭር እንደ ሆነ የተረዳ፣ በጋራ ለጋራ የሚሠራ፣ ይህም ከአክራሪነት በተሻለ ፍጥነት ለብዙሓኑ የሚብቃቃ በጎ ውጤት እንደሚያስገኝ የሚገነዘብ።

በጒግል ላይ ብቻ መደገፍ፣ ለወገኔ ብቻ ማለት፣ የሚሠበር ተሠንጥሮ የሚወጋ ምርኲዝ እንደ መደገፍ ነው።

ምትኩ አዲሱ

ጥር 6/2012 ዓ.ም.

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave