ቴክኖሎጂም እንደ አዋሽ

አዋሽ

ዛሬ ቴክኖሎጂ ያልነካው የዓለም ጥግ የሕይወት ጥግ የለም። ማን ከማን ጋር እንዴትና መቸ እንደሚነጋገር ወሳኙ ቴክኖሎጂ ሆኗል። ወይም ቴክኖሎጂውን የሚዘውሩ ግለሰቦችና ኃይላት እንበል። እነዚሁ ኃይላት በተገኘ ዕድል ነጻ መውጣታችንን ያበስሩናል። ሁሉም ነገር በቊጥጥራችን ሥር እንደሆነልን ይነግሩናል። ዓላማቸው ሰዎችን ማቀራረብ ነው ይሉናል። አላቀራረቡንም አንልም።

እውነተኛው ዓላማቸው ግን ተጽእኖ ማሳደርና ሃብት መፍጠር ነው። ዋነኛው ሃብታቸው ክርስትና የተነሳንበትን ቀን ማወቃቸው፣ ከእነማን ጋር ስናወራ እንዳመሸን ማወቃቸው ነው። ተጽእኖ ማለት፣ ሌላኛውን ሰውና ማኅበረሰብን በራስ አምሳል መፍጠር ማለት ነው። በአለባበስ፣ በሰላምታ አሰጣጥ፣ በአምልኮ፣ ወዘተ፣ ከቀን ቀን ፈረንጁን እየመሰልን የመጣው ለምን ይመስለናል?

ሃብት ለመፍጠር ምሥጢሩ ተጠቃሚውን አዲስ ልማድ፣ አዲስ ቋንቋ ማስተማር፣ ሱስ ማስያዝ ነው። መንጠቆ የዋጠ አሣ ምርጫው ምንድነው? በቀን ስንቴ ነው ሞባይላችንን አይፓዳችንን ላፕቶፓችንን ዴስክቶፓችንን የምንማጸነው? የምንገላምጠው? የተማጽኖአችን ብዛት የጸሎት መጽሐፋችንን ከእጅ አስጥሎናል። በሌላ አነጋገር፣ መንግሥታችን አንዳንዴ ኢንተርኔት መዝጋቱን ጨርሶ ጠቀሜታ እንደሌለው ማየት የለብንም! ለመሆኑ፣ ኢንተርኔት ሲዘጋ የሚያጯጩኸን ሱስ ነው ወይስ መብት?

ቴክኖሎጂ እንደ አዋሽ ነው። ያበላል፣ ይበላል። ለሕይወት የሚሆን ውሃ ተሞልቷል። ቊሻሻ ተሞልቷል፤ ሕይወት እና ሞት ጎን ለጎን ይዟል። “የጽዮን ግርማዋ የሱስ ክርስቶስ ነው” የምትለዋን መዝሙር በዩቱብ ለመስማት፣ ለአስራ አምስት ሴኮንድ ያረቄ ማስታወቂያ መመልከት ግድ ነው፤ ቅልጥ ያለ ዳንኪራ የጦር መሳሪያ ቊማር፣ እዚህ መጥቀስ የማያሻን ውሸት ጩኸት ቅጥ ያጣ ውፍረት። ሲደጋገም ሱስ እንደሚሆን ባለቤቱ ያውቃታል! ለጠማው የጨው ውሃ ድፍርስ ውሃ አቅርቡለት።

ነጻ ትወጣለህ ብሎ እስራት! ያለ ቴክኖሎጂ፣ መኖር ዋጋ እንደሌለው እንደማይቻል መስሏል። በምቾትና በቅልጥፍና ስም ሰውን ከሰው መነጣጠል፤ ብቻ ማስቀረት፣ ለብቻ ማስወራት። ያለ ቴክኖሎጂ፣ ሰው ወትሮ የሚግባባባቸው መንገዶች ታጠሩ፣ ያለ ቴክኖሎጂ አማራጮች እንደሌሉ መሰሉ። ቤተክርስቲያን ለሃያ አራት ሰዓት የቴክኖሎጂ ጾም ብታውጅ የሚሰማት ታገኝ ይሆን? የቴክኖሎጂ መቋረጥ፣ ስደት ያልቻለውን ስንት አገልግሎት ስንት ቤተክርስቲያን ያዘጋ ይሆን? እግዚአብሔርም እንኳ ያለ ቴክኖሎጂ መናገር አቊሟል እንባል ይሆን?

ቴክኖሎጂ፣ “አሁን፣ አሁን” ይላል። ወንጌል፣ “በተስፋ በትእግስት በኅብረት በጸሎት በጸጥታ በመጽናት ሙሉ ሰው በመሆን” ይላል። ቴክኖሎጂ፣ “እጅ እጅ” “ዐይን ዐይን” “ማንነት ልዩነት” ይላል። ወንጌል፣ “እግርና ጆሮ ከአካል ተነጥሎ ሞት ነው” ይላል። ቴክኖሎጂ፣ “ፍጥነት፣ ፍጥነት” “ንጥል ግንጥል” ይላል። ወንጌል፣ “ተጎራባችነት ተያያዥነት” ይላል። ምርጫችን የቱ ነው? ወይስ ምርጫ የለንም?

ምትኩ አዲሱ

ዕለተ ጥምቀት 2012 ዓ.ም.

ቀላሉን መንገድ | የማለዳ ድባብ | ከየት ተገኘሽ ሳልል | ቋንቋን በቋንቋ | ስደተኛውና አምላኩ | ሞት እና ፕሮፌሰር | የድመትና ያይጥ ፍቅር | የልማት መሠረቱ መታመን ነው | ጒግል እንደ አዋቂ | ቆመህ እያየህ | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | ትዝብቶች ከ “አባቴ ያቺን ሰዓት” | ይድረስ ለቴዲ አፍሮ | ችግሩ አልተፈታ | በፎቶ ኢትዮጵያና እንግሊዝ | ጸሎትና ስፖርት | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ልቤ ከብዷል ዛሬ | ቸር ወሬ አሰማኝ | መንበርና እርካብ | ጒዞዬ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | Land of the Shy, Home of the Brave