ውጫሌ እንዳይደገም

trumpnile

ኢትዮጵያና ፋሺስት ጣልያን ሚያዚያ 25/1881 ዓ.ም. ውጫሌ ላይ ውል ተፈራርመው ነበር። ውሉ በአማርኛ እና በጣልያንኛ ቅጅ ነበረው። “የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከኣውሮፓ ነገሥታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በጣልያን መንግስት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል” የሚለውን (አንቀጽ 17)ን ጣልያኖች፣ እኛ ሳናውቅ ከሌሎች አገራት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ አትችሉም የሚል ትርጒም ሰጥተውት ነበር። ያም ለአድዋ ጦርነት መንስኤ ሆነ።

ቋንቋ ለአንድ አመራር ቊልፍ ነው። የውጭ ቋንቋ መማር ለአገር ደህንነት እና ለዲፕሎማሲ መሠረት እንደ ሆነ አፄ ሚኒሊክ በጽኑ ያሰቡበት ከዚያ ወዲህ ነው። በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ከፍተኛ የዲፕሎማቲክ፣ በተለይ የአውሮጳዊ ባህል እውቀትና ልምድ ዳበረ። እነ ክቡር አቶ አክሊሉ ሀ/ወልድ፣ አቶ ከተማ ይፍሩ፣ ዶ/ር ምናሴ ኃይሌ የመሳሰሉ መሪዎች ከአገር አልፈው የአህጒር አኲሪ ነበሩ። በህወሓት/ኢሕአዴግ ዘመን በኃላፊነት ላይ ለመመደብ ብቃት ሳይሆን ዘር በመደረጉና የትምህርት ጥራት በመውደቁ በስንት ድካም የዳበረ ቅርስ ባከነ።

አገራችን የኃይል ማመንጫ ግድብ መሥራቷን አስመልክቶ ከግብጽ ጋር ክርክር ይዛለች። የግብጽ ሥጋት፣ የሚገደበው ውኃ ይደርሰኝ ከነበረው መጠን አንሶ ችግር ላይ እወድቃለሁ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ጒዳይ በሳይንሳዊ ጥናትና በድርድር የሚወሰን ቢሆንም ግብጽ ውሉን ለማዘግየት እንጂ ተጋርታ ለመቀበል አልፈቀደችም። ይልቅ የኢትዮጵያን አለመረጋጋት እንደ ቋሚ ፖሊሲ መተግበሯን ቀጥላበታለች። እንዲያውም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ፕሬዚደንት ትረምፕን አማላጅነት ጠርታለች። ትረምፕ የኛን የግብጾችንና የሱዳኖችን መሪዎች ዋሽንግተን ጠርተው በተደጋጋሚ አነጋግረዋል፤ በዓለም ባንክ በኲል ማግባቢያ ብድር ሰጥተዋል። ከቻይና ጋር ቊርኝታችንን እንድናላላ በውጭ ጒዳይ ሚንስትራቸው በኩል ልከውብናል። መሪዎቻችን ግን የምናጣራው አለ ብለው የመጨረሻውን ስብሰባ አልተሳተፉም። ውሉም ሳይፈረም ቀርቷል። ትረምፕ ውሉ ሳይፈረም ግድቡን ውኃ መሙላት እንዳይጀመር ብለዋል። ግብጽ እርምጃ እወስዳለሁ ብላ ዝታለች። የትረምፕ ገለልተኛ አደራዳሪ አለመሆንና ለአፍሪካውያን ያላቸው ንቀት የአደባባይ ምሥጢር ነው። (ከላይ ፎቶውን ይመልከቱ)

የአገራችን ሁኔታ አሳሳቢ ነው። በዚህ ወቅት ቆራጥ ብልሃት እንጂ “ዘራፍ! ዘራፍ!” አይጠቅምም። ግልጽ እናድርግ። የቋንቋና የዲፕሎማሲ ብቃት ማነስን በወኔ መተካት የትም አያደርስም! አንደኛው ብልሃት በሌሎችም አገሮች እንደሚደረገው በአስተርጓሚ መጠቀም ነው! ሁለተኛው ከውስጥ መጠናከር ነው!

ከጅምሩ ዋሽንግተንን ደጅ ያስጠናን ከግብጽ ጋር ስምምነት ላይ ባለመደረሱና ግብጽ ለአሜሪካ አቤት ማለቷ ነው። የአሜሪካ መንግሥት አደራዳሪ በሆነባቸው ጒዳዮች ሁሉ ከተደራዳሪዎቹ ይልቅ ራሱን እንደ ጠቀመ የተሰወረ አይደለም። የትረምፕ አስተዳደር በእስራኤልና በፍልስጤማውያን መሓል ፍልስጤማውያንን አግልሎ ውል መፈራረሙ። በአፍጋኒስታን፣ የአፍጋኒስታንን መንግሥት ሳያሳትፍ ከታሊባን ጋር መፈራረሙ። በኢራቅም፣ በሊቢያም የቅርብ ጊዜ ዜና ነው። አሜሪካ ጣልቃ መግባቷ ለሚያስከትለው እልቂት ትረምፕ ደንታ እንደሌላቸው ግልጽ አድርገዋል። ለኢትዮጵያ የተለየ ጥንቃቄ ወይም እንክብካቤ ይደረጋል ብሎ መጠበቅ የመንግሥታትን የጂኦፖለቲክ ስልት አለመረዳት ነው። የ “የኢትዮጵያ ወዳጅ” የኤሚሬቶች አልጋ ወራሽ ሞሓመድ ቢን ዜይድ እንኳ በቀደም በዓባይ ጒዳይ የግብጽ ደጋፊ ሆነው ተገኙ።

የአሜሪካ ግብ ዘርፈ ብዙ ነው። አንደኛው፣ በግብጽ በኲል ፍልስጤም ላይ ጫና በመፍጠር እስራኤልን መጥቀም ነው። እስራኤልን መጥቀም የአሜሪካና የእስራኤልን ንግድና ደህንነት መጥቀም ነው። ሌላኛው፣ የአሜሪካን ታላቅነት ማሳየት ነው፤ የማኖር እኔ፣ የምጥል እኔ ቅኝት።

ለህዳሴ ግድብ ሕዝብ ያዋጣው ገንዘብ በሜቴክና በህወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎች መመዝበሩና ግድቡ የሚጠናቀቅበት የጊዜ ገደብ መዛነፉ ያስከተለው የገንዘብ ችግር መሪዎቻችን ወደ አሜሪካ ለማቅናታቸው ምክንያት እንደሆነ አንርሳ።

በነሐሴ ብሔራዊ ምርጫ ይካሄዳል። ከውስጥና ከውጭ ያልተረጋጋ ሁኔታ ይታያል። የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የግብጽን ፕሮፓጋንዳ ለመቋቋም የሚበቃ የቋንቋ ጥራትና ግብረ ኃይል እንደሌለው፣ በእንግሊዝኛ የሚታተሙ ጋዜጦችና ቲቪ ፕሮግራሞችን ጥራት መመልከት በቂ ነው። መንግሥት ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ማቅረብ እንኳ አልቻለም። ከዚህ የተነሳ እኲይ ዓላማ ያላቸው በክፍተቱ ውዥንብር እየነዙ ይገኛሉ። ግብጽ በዐረብ ማሕበር፣ በአውሮጳ ማሕበር፣ በኤዥያ ራሷን እንደ ተጠቂና ፍትህ ፈላጊ አድርጋ አቅርባለች። ምን ማድረግ ይቻላል?

በዚሁ ድረገጽ ላይ ፌብርዌሪ 10/2020 እና ኖቬምበር 6/2019 የለጠፍናቸውን ጽሑፎች እንድገማቸው፦

[ፌብርዌሪ 10/2020]፦ “ዐቢይ ጁላይ 27/2018 ኋይት ሃውስ ተገኝተው ከአቻቸው ከትረምፕ ጋር ሳይሆን ከትረምፕ ምክትል ፔንስ ጋር መወያየታቸው፣ ትረምፕ የነጋዴ እንጂ የወንጌል አማኝ አንደበት ስላልተካናቸው፣ ዐቢይና ፔንስ ወንጌል አማኝ መሆናቸውን ከእሳቤ በማስገባት ነው። ነጋዴ የሚያዋጣውን ብቻ ያያል፤ በቃሉ ላይታመን ይችላል። ፖለቲከኛም እንደዚሁ ነው! የፔንስ ፖለቲከኛነት እንጂ ወንጌል አማኝነት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደማይገባ ዐቢይ ይታጣቸዋል አንልም… ከእስራኤሉ ጠ/ሚ ናታንያሁ ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች የትንቢት ፍጻሜ ማፋጠኛ እንደሆኑ መታሰብ የለባቸውም። እርግጥ ነው እግዚአብሔር በፖለቲካም ውስጥ ይሠራል። ናታንያሁ ሆኑ ፔንስ የማታ ማታ ዓላማቸው የፓርቲአቸውን እና የአገራቸውን ጥቅም ማስከበር ነው!”

[ኖቬምበር 6/2019]፦ “ቤተ መንግሥቱንና ቁልፍ ተቋማትን ከአሞጋሾችና ከአወዳሾች ማጽዳት፤ በተለይ ደግሞ የሕዝብ ግንኙነቱን ክፍል። በየመስኩ ችሎታ ላላቸው ዜጎች ኃላፊነትን ማጋራት ይኖርባቸዋል፤ ለምሳሌ፣ የህዳሴ ኃይል ማመንጫውን እንዲያሸማግሉ የውጭ ኃይላትን ጣልቃ ማስገባት ለትውልድ ፀፀት እንዳይሆን መጠንቀቅ፣ ከናስር ግብጽ (ዓለም ባንክ ከደገሰላቸው አንጻር)፣ ከዩክሬን፣ ከሶርያ፣ ከኢራቅ ተሞክሮዎች መማር ይጠቅማል።”

ውጭ አገር የፈሰሰውን ዜጋ እውቀት፣ የባህልና የልምድ ሃብት በየቆንስላ ጽ/ቤቶች በኲል በተለይ በፕሮፓጋንዳው ጦርነት እንዲሠለፍ አለማመቻቸት ከበደልም በደል ነው። ይቺን ጠባብ ሰዓት እስክንሻገር፣ ከዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አመራር ጋር አለመቆም ትርፉ ለትውልድ ፀፀትና ውርደት ነው! ውጫሌ ትዝ ይበለን! ለአገራችን እንጸልይ!!!

ምትኩ አዲሱ

መጋቢት 1/2012 ዓ.ም.

photo credit: globalconstructionreview.com

ቋንቋን በቋንቋ | የማለዳ ድባብ | የድመትና ያይጥ ፍቅር | ለመቶ ሚሊዮን የአገሬ ሕዝብ | መጠየቅ ክልክል ነው? | የሺህ ጋብቻ ወይስ ቅዱስ ጋብቻ? | መሬት መሬት ሲያይ | ፓትርያርክ በዕጣ | ባንተ በኲል ስትቦረቡር | No Deal on the Nile | Lent as a Way of Life