ኮሮናቫይረስ የዘር ፖለቲካ ቫይረስ ለማጥፋት ተልኮ ይሆን?

ethnic

ኮሮናቫይረስ ዓለምን ከጥግ ጥግ አጨናንቋል። ሕዝቦችና ጠቢባን ተጨንቀዋል፤ የሰው ብልሃትና ትምክሕት ከንቱ ሆኗል! በግንኙነቶቻችን ላይ ያልነበረ ለውጥ እየታየ ነው። እግዚአብሔር ምን እያለ ይሆን? አንዳች ቊምነገር እንማር ይሆን?

እጅ አትጨባበጡ፤ ሁለት ሜትር ተራራቊ፤ (ሁለት ሜትር ወደ ታች ሳይሆን ወደ ጎን ነው!) ከቤት አትውጡ፤ እጅ ታጠቡ፤ አፍ ሸፍኑ። ውሃ በጠፋበት እጅ መታጠብ ወይስ መጠጣት ይቅደም? የኮሮና ወይስ የረሓብ ሳል ይብስ? የእለት ጒርስ፣ ጎጆና ጎተራ ላጡ ደጅ አትውጡ ፋይዳው ምንድነው? በጠባብ ክፍል ለታጎሩ፣ መጸዳጃ ላጡስ? መሪዎች በሥልጣን ከመገዳደል፣ ፈቅ ያላለውን የሕዝቡን ኑሮ ለማቃናት ከእንግዲህ ቆርጠው ይነሱ ይሆን? ኮሮና፣ ከዘረኛነት አዙሪት ያላቅቀን ይሆን?

ከሁለት ሜትር ርቀት አብሮ መብላት አይታሰብም! ፓርላማ ተበትኗል። መለስ በሞቱ ሰሞን ፓርላማ ለሦስት ወር ከተበተነ ወዲህ ይኸ ሁለተኛው ነው። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ምግብ ቤቶች፤ ናይት ክለቦች፤ ሺሻ ጫት መሸታ ቤቶች፤ ስታዲየም፤ የሕዝብ መጓጓዣዎች፤ ባጭሩ ለየብቻህ (በየደጃፍህ) ተብሏል። ሰላማዊ ሰልፍ የማይታሰብበት ዘመን መጣ! ተደጋግፎ እንጂ ለብቻው መቆም የማይሆንለት ሕዝብ አማራጩ ምንድነው? የተፋፈጉ በተልካሻ ምክንያት ወህኒ ያጣበቡ ዜጎችስ ዕጣ?

ለነሐሴ የተቀጠረው አገራዊ ምርጫ ላይካሄድ ይችላል ተብሏል። መንግሥት ይጽና ይፍረስ የሚያውቅ የለም። ኮሮናቫይረስ የሚባል በዐይን የማይታይ፤ በነፍጥ ሆነ በአስማት የማይበገር፤ ዘርና ሥልጣን፣ የፖለቲካ ዘውግ የማያውቅ ጠላት መጥቶብናል። ጒሮሮ ሲከረክር እሱ ይሆን? በቫይረሱ ይለከፍ አይለከፍ፣ ባለተራ ማን እንደሆነ ማወቅ አይቻል። ላስተዋለ ግን፣ ሰዓቱ የንስሃ ሰዓት ነው። ዘር የምትቆጥሪ ማንሽም ከማንሽ አትሻይም እየተባልን እንደሆነ ገብቶናል?

ጊዜው ርኅሩኅ አስተዋይ መሪ የሚጠይቅ ጊዜ ነው። አብዛኛው ሕዝብ በቅንነቱ የሚያስታውሰው መሪ ማን ይሆን? የዐቢይ አስተዳደር ቅንነቱን ሳያስመሰክር አጋጣሚው ያመልጠው ይሆን? ወቅታዊ መግለጫዎችን በመስጠት ተኣማኒነትን ይቀዳጃል ወይስ የሕዝብን እልቂት በምሥጢር ይዞ የለመድነውን ግፍ ይፈጽምብናል? ያ አካሄድ ለኃይለሥላሴ፣ ለደርግ፣ ለህወሓት/ኢሕአዴግም አልበጀ፤ እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ ነዋ!

ኮሮናቫይረስ በጎ እና በጎ ያልሆኑ ውጤቶችን ማስከተሉ አይቀርም። በሰፋፊ አዳራሾች የሚደረጉ ስብሰባዎች መቋረጥ ራሳቸውን በሾሙ ነቢያት ላይ ሲደገፍ የኖረን ምእመን፣ በሥጋ ለባሽ ላይ መደገፍ እንደማያዋጣ፣ እንደሚከዳ ያስገነዝባል እንበል። ወይም ከእውቀት ማነስ፣ ለዝናና ለረብ ሲሉ ሕዝቡን ለአደጋ ያጋልጣሉ እንበል። መንግሥት ዝም ብሎ ያያቸዋል ወይስ የሕዝብን ጤና በህግ ያስከብራል?

የዘር ፖለቲካ ሊበትነው ያልተቻለውን ሕዝብ፣ ኮሮናቫይረስ አንድ ያደርገው ይሆን? የኮሮና አማራ የለውም፤ የኮሮና ትግሬ እና ኦሮሞ የለውም! የዘር ፖለቲካን ውዳቂነት በገሃድ እያየን ነው። ኢዜማ፣ ብልጽግና፣ ወዘተ፣ ሕዝብን ለሥልጣን መወጣጫነት ሳይሆን ለማገልገል አዲስ አገራዊ ራእይ ይጎናጸፉ ይሆን? ፈጣን ልማት ለተጋረጠብን ፈተና ምን ያህል አዘጋጅቶናል? ያለ ዜጋ ተሳትፎ፣ ያለ ዲሞክራሲ፣ ያለ ህግ የበላይነት፣ ልማት ለጥቂቶች መፈንጫ እንደ ተመቸ አይተናል።

የሕዝቦች ጤና ቀውስ ፍጥነቱ እየጨመረ ነው፦ ኤይድስ (ከ1973 ዓ.ም. እስከ ዛሬ)፤ ስዋይን ፍሉ (2001 እስከ 2002 ዓ.ም.)፤ ኢቦላ (2008 እስከ 2010 ዓ.ም.)፤ ዚካ ቫይረስ (ከ2007 ዓ.ም. እስከ ዛሬ)፤ ሳርስ፣ መርስ፣ ኮሮና። ቀጥሎ ምን ያመጣ ይሆን? ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚንከባከቡን፣ ሐኪሞች ነርሶች እና ወታደራዊ ክፍሎች ይኑሩልን። ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተሻለ አደረጃጀት ይቀዳጅ ይሆን? ሚኒስቴር መ/ቤቶች በተለማማጆች ሳይሆን ቅንና ብቃት ባላቸው ዜጎች መመራት ይጀምሩ ይሆን?

የአገር ጸጥታ አስጊ ሁኔታ ላይ ነው። ሕዝብ የሚበላው ሲያጣ፣ ሥራ አጡ በዝቶ፣ ሥራ ያለው ከሥራ ገበታው ተፈናቅሎ፣ ውጤቱ አስከፊ አይሆንም ማለት የሰውን ባህርይ መዘንጋት ነው። በኮማንድ ፖስት ተደራጅቶ ሕዝብ ላይ ጥይት ሲያርከፈክፍ የነበረ ጦር ሠራዊት ለሕዝብ ደራሽ የሚሆንበት፣ ከአብራኩ በወጣው ሕዝብ ፊት የጎደፈ ገጽታውን የሚያድስበት አጋጣሚ መጥቶለታል። ነፍጥ ላነሱ ደግሞ ትጥቅ የሚያስፈታ ኮሮና መጥቶባቸዋል!

ህወሓት/ኢሕአዴግ ከቻይና ተውሶ ኢንደስትሪያል ፓርክ አደራጅቷል። ፓርኩ ያስፈለገው ለ “ፈጣን ልማት” ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ሥልጣን ላለማጋራት፤ የዜጋን ተሳትፎ ለመግታት ጭምር ነው። የመለስ ዜናዊ አገዛዝ፣ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ከሁለት ሺህ ሦስት መቶ በላይ ሕዝባዊ ድርጅቶችን አግዶ የሚፈልጋቸውን ብቻ አስቀርቷል። ፓርኩ እርግጥ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖች ሥራ ፈጥሮላቸዋል እንበል። ሥራ ይፍጠር እንጂ ከዓለም አቀፍ የሠራተኞች መብት ጥበቃ አኳያ (በክፍያና በጤና እንክብካቤ) ብዙ በደል እየታየ ነው። የዐቢይ አስተዳደር በግል አምራቾችና በሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ ህወሓት/ኢሕአዴግ ያደረገውን ዕቀባ ከእንግዲህ ያነሳ ይሆን?

ወንጌላውያን ምን ቢያደርጉ ነው በሕዝብ ዘንድ መታመንን የሚቀዳጁት? ከመጣው መንግሥት ጋር መዋል ምነው አማራቸው? የመንግሥት እጅ ሳይገባበት ወንጌል ብቻውን እንዴት ሊያስማማቸው አልቻለም?

ማሕበረሰብን ያያያዘ ልማድና ሥርዓት ወላልቆ ሰው እራቊቱን በጌታ ፀባኦት ፊት እንደሚቆም ለየብቻው ቆሟል። ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል እንል ነበር፤ ቡና ለብቻ አይጠጣም እንል ነበር፤ ቀባሪ አታሳጣኝ እንል ነበር። እነሆ፣ ኤይድስ እንኳ ያልነፈገውን አብሮነት ኮሮና ነጥቆናል፤ አንዳንዶቻችን ያለ አስታማሚ ያለ ቀባሪ ምድርን ለቅቀናት ልንሄድ ነው። የባልንጀራን ውድነት፣ የሰውን ክቡርነት እስክናውቅ ድረስ ለየብቻ እንበላለን እንጠጣለን እንሞታለን።

ሁሉን ተወት አድርገን፣ ዜጋ ለዜጋ እንተሳሰብ! ይህን መዓት እንዲያሻግረን እግዚኦ መሓረነ ክርስቶስ እንበል።

አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ። ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥ ከኃጢአቴም አንጻኝ፤ እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና። አንተን ብቻ በደልሁ፥ በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥ | አቤቱ፥ በቍጣህ አትቅሠፈኝ፥ በመዓትህም አትገሥጸኝ። ድውይ ነኝና አቤቱ፥ ማረኝ፤ አጥንቶቼ ታውከዋልና ፈውሰኝ። ነፍሴም እጅግ ታወከች፤ አንተም አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ነው? አቤቱ፥ ተመለስ ነፍሴንም አድናት፥ ስለ ቸርነትህም አድነኝ። | ዓይኖቼን ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ? | ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም | እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም። እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል። | ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት፤ | እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል። | ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል። | ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም። | ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፤ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም። | እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፥ | ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ ይመግባቸው ዘንድ፤ | ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና፤ | ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና፤| አቤቱ፥ ምሕረትህ በላያችን ትሁን፥ በአንተ እንደ ታመንን። | በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል፤ ያከማቻል የሚሰበስብለትንም አያውቅም። | አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው? እግዚአብሔር አይደለምን? ትዕግሥቴም ከአንተ ዘንድ ነው። መዝሙረ ዳዊት 51። 6። 121። 33። 39።

ምትኩ አዲሱ

መጋቢት 16/2012 ዓ.ም.

photo credit: Petterik Wiggera