የ ተ ራ ብ ን  እ ኛ  ያ ስ ራ ብ ን   እ ኛ

ምትኩ አዲሱ

begena lady

ከእለታት አንድ ቀን የአካል ክፍሎች አደሙ፤ በሆድ ላይ አደሙ። እኛ በደከምንበት ምንም ሳይሠራ ሆድ ለምን ቊጭ ብሎ ይበላል ብለው አደሙ፤ ዝግ ስብሰባ ጠሩ።

እጅ ተናገረ፦ ያረስኩ እኔ፣ ያረምኩ እኔ፣ የወቃሁ እኔ፣ ያበሰልኩ እኔ ... ዐይን አቋረጠውና በምንህ አይተህ? አለ። መብሰሉን በምን አውቀህ? አሉ፣ አፍንጫና ምላስ። በየት ገብተህ? አለ፣ አፍ። ይኸ ሁሉ ሳያንስ ከገበታ ላይ ቆርሼ አፍ ጋ የማቀርብ እኔው መሆኔ ቆጨኝ፣ አለና እጅ፣ “ጒዳቴ! ጒዳቴ!” ብሎ እየየውን ለቀቀው።

እሺ፣ ቆርሰህስ አነሳህ፤ አንስተህ እኔ ባልፈቅድልህ በየት በኩል ትገባ ነበር? በጆሮ ነው ባይን አለ ጥርስ፤ ደግሞ እኔው ሆኜ እንጂ አልፈጭም ብልስ አለ። ጆሮ ከጎን ቆሞ ይሰማል፤ ሁላችሁም ቀደም ቀደም ባትሉ ምናለ? ሆድ ሲያስገመግም ሰምቼ ዝም ብል ሁልሽም ሥራ ሥራ የምትዪ ወሬኛ ሁላ! አለ።

ማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ አሉ? አለ እግር። አንዴ ስንበረከክ፣ እንደ ወላድ፣ ወገብና ጭንቅላት አዝዬ ቀና ስል፣ አንዴ የኋሊት፣ አንዴ ወደ ጎን አንዴ ወደ ላይ ስንጠራራ የኔ መንገላታት አይብስም? አለ። እሺ፣ ይኸስ ሆነ፣ አሁን ምን ይሻላል ትላላችሁ? አለ ዐይናፋሩ ምላስ፣ ከጓዳ ውስጥ ብቅ ብሎ።

ሆድ ሠርቶ መብላት እንዲለምድ አስገዳጅ እርምጃ እንውሰድ ተባባሉ። ከዛሬ ጀምሮ፣ ጆሮ ወሬ ስትሰማ አታሰማ፣ ዝም በል። እጅ ከወገብ አትለፍ፣ ኮሮናን ለመከላከል ብቻ ጭንብል እሠር፣ ተጣጠብ። እግር ተጣጥፈህ አረፍ በል። ዐይን ፀልይ፣ አትቀላውጥ። ጥርስ ጒድህ እንዳይገለጥ ተከናነብ። ምላስ ደጅ ደጅ አትበል። በዚህ ተስማሙ።

ይኸ ሁሉ ሲሆን ሆድ አሳብ ገብቶት አንዱንም ነገር አልሰማም። ይህን ሁሉ ዘመን አብረው ሲኖሩ ያድሙብኛል ብሎ ጭራሽ አልጠረጠረማ! ዝግ ስብሰባ ያካሄዱት ሰኞ ግንቦት ሃያ ነበር። ሮብ ‘ለት እግር ተዝለፈለፍኩ አለ፤ እጅ ከወገብ አልፌ ወርጄ ቊርጭምጭሚት ጋ ልደርስ ምንም አልቀረኝም፣ ወየሁ! አለ። ጆሮ፣ “ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች” እንዲል፣ ብዙ ጩኸት እሰማለሁ፣ ለምን ይሆን አለ። “በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል” ብሏልና ጥርሶች ተንቀጫቀጩ፣ ከንፈር የማይሸፍነው ዓይነት መንቀጫቀጭ ተንቀጫቀጩ፤ በእንቅጭቅጭ መሓል ሦስት ጥርሶች ተሸራርፈው ወደቁ። ዐይኖች ተረሳረሱ። ምላስም እንኳ ደርቄአለሁ፣ መናገር ተሳነኝ አለ። ሆድ ሆድ ነውና፤ የሆነውን ሁሉ በሆድ ይዞ አደረ።

ነገር እንዳሰቡት አልሆነም። ሁሉም ተማረሩ፤ ያልተማረረ አንድም ታጣ። በሦስተኛው ቀን ከደረሰባቸው ጒዳት እንደተማሩ፤ ሆድ ሥራውን ባይሠራ ኖሮ በጠፋን ነበር አሉ። ታዲያ ምን እናድርግ ተባባሉ። የበግ ጠቦት እንረድ አሉ፤ የበግ ጠቦት አረዱ። ተማርረዋልና ሥጋውን በመራራ ቅጠል ጠበሱ፤ ጠብሰው በሉ። በልተው ሲጨርሱ እጅና እግር ዐይን ተጋግዘው ገበታውን አነሱ።

ይኼኔ ጣት አቀብሉኝ አለ። ምን እናቀብልህ አሉት። በገና ልደርድር አለ፤ በገና አቀበሉት፦

የተራብን እኛ፣ ያስራብንም እኛ፤

የተጣላን እኛ፣ ያጣላን እኛ ...

የተራራቅን እኛ፣ የተራረቅን እኛ ...

ተው ስማኝ አገሬ፣ ኧረ ስማኝ አገሬ ...

ከዚያኔ ወዲህ ያ ዓይነት አድማ ሆነ ዝግ ስብሰባ አልተደገመም። እርግጥ ሆድ አንዳንዴ፣ ምነው ዘገያችሁ? አንዳንዴ፣ ምነው አሳነሳችሁ? ሌላ ጊዜ፣ ምነው አበዛችሁ? ማለቱ አልቀረም። ዐመል ነው ብለው ሁሉንም እንደ ዐመሉ ያዙት እንጂ አላደሙም።

 © 2020 by Mitiku Adisu | ከ አፈ-ታሪክ ከእንደገና፣ 2012 ዓ.ም. | Pic: Courtesy of Yerom Dedjene

ጭራቆቻችን