doorknock

ምን ልርዳዎ?

ምትኩ አዲሱ

ወደ አንድ መንደር መጣ። ከፊት ለፊቱ የሚታየውን ቤት ሄዶ አንኳኳ። ደጋግሞ አንኳኳ፤ የሰውም የውሻም ድምጽ አልተሰማም። አልከፈቱለትም። አለፍ ብሎ ሌላ ደጅ አንኳኳ። ማ ልበል? አሉ። ማ ልበል? ብለው ወሬአቸውን ቀጠሉ እንጂ ተነሥተው አልከፈቱለትም። ወረድ ብሎ አንኳኳ። ሲከፍቱለት ተገትሮ ቆሟል። ቊመናውን ከላይ እስከ ታች ገላምጠው ተመለከቱ። ምን ልርዳዎ? አለ። ከት ብለው ሳቊ፤ ምን ልርዳዎ ትላለህ? መረዳት ያለብህ አንተ! ብለው ደጃቸውን ፊቱ ላይ ደ     ረገሙት፤

መንገድ ተሻግሮ አንኳኳ። ሲከፍቱለት፦ ምን ልርዳዎ? አለ። ምን ምን ልርዳዎ ትላለህ? መረዳት ያለብህስ አንተ! አሉና ወደ ጓዳ ተመልሰው ትርፍራፊ ይዘውለት መጡ። እንካ! ራስክን አልቻልክ፣ ያለአቅምክ ትንጠራራለህ! አሉት። ምንም አልመለሰም። እዚያው እንደቆመ ደግሞ፦ ምን ልርዳዎ? አለ። የማ ቀልደኛ ነው እቴ? አሉና ደጃቸውን ጥርቅም አርገው ዘጉ።

ራቅ ብሎ ዳርቻ ላይ ካለ ቤት ሄዶ አንኳኳ። ሲከፍቱ፦ ምን ልርዳዎ? አለ። ምን ልርዳዎ? እውነትክን ነው? ምን ልርዳዎ አልክ? አሉት። አይ አምላኬ! ምን ልርዳዎ? የሚል አመጣህልኝ፤ ተመስጌን! ግባ አሉት።

© ምትኩ አዲሱ፣ 2013 ዓ.ም.