rural eth

አ ን ዳ ን ዴ  ህ ይ ወ ት  በ እ ር ግ ጥ ም  'በ ግ ራ  ጎ ን '  ት ነ ሣ ለ ች  መ ሰ ል!

ሲ ሞ ን  ሄ ሊ ሶ

የሥራ ጉብኝት እያደረግን ሳለ አንድ አርሶ አደር ቤት ደረስን። የጠየቅነውን ጠይቀን የመለሱልንን ያህል ፅፈን፥ አመስግነን፥ ልንመለስ ስንል "እቤት ሳትገቡ በመጣ እግራችሁ አትመለሱም" ብለው የግድ አሉን። በብዙ ዝብዝብ እዚያው የቆምንበት እጃችንን አስታጥበው ወፍራም፥ ትኩስ የገብስ እንጀራ በማር አጥግበው አቀረቡልንና ያላቸውን በማጋራታቸው የተሰማቸውን ደስታ በመላ አካላታቸው እየተመለከትን በላን። አመስግነን ስንነሣ ቀረት ብዬ በጥልቁ አየኋቸው። ምናልባት የዚያን ቀን እራታቸውን ነው የሰጡን። ምንም ሳያስቀሩ። እናም በእርግጥ እጅግ ደስ ብሏቸዋል። በምድረ ኢትዮጵያ በዞርኩባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ይህ የዕለት ተዕለት ክስተት ነው። ከዳር፥ እስከ ዳር። ህዝባችን የዋህና የፍቅር ህዝብ ነው።

የትግራይና ትግራዋይ ግን ይለያል ብል ማጋነን አይሆንም። በዚያ ለኑሮ በሚከብድ መልክዓ ምድር እጅና እግሩን ሰውቶ ያገኘውን የዕለት ጉርሱን ሳይቀር ለወገኑ ሰጥቶ፥ ራሱ ጦሙን አድሮ እንግዳ እቤቱ አርፎ ሲመለስ ፈጣሪን የሚያመሰግን ህዝብ ነው። ቀደም ሲል የተረክሁላችሁ አጋጣሚ ያገናኘን ሰው የሚኖሩበት የነጃሺ መስጊድ አካባቢ ዛሬ ፈርሶ ፈራርሶ እንዳለ ደርሼ ባላይም ዓይነ ህሊናዬ ይመለከተዋል።

ዛሬ ዕለተ ጥምቀት ነው። የፌሽታ፥ የደስታ። ሙሉ ደስታና በዓል ለማድረግ ግን አቅም ማግኘቱ ይከብዳል። በእጅግ ብዙ የሃገራችን ክፍሎች ያሉ ህዝብ የሥጋትና ጭንቀት ሌሊትና ቀን እያሳለፉ ስላለ። ከሁሉ የባሰው ችግር በጦርነት ቀጣና ያሉ ህዝቦቻችን የሚያሳልፉት ጊዜ ነው። በሰላም ውሎ የማደር ሥጋት እየናጣቸው የሚኖሩ ብዙ ናቸው። ከሠላም እጦት ጋር እህልና ውሃ፥ መብራትና ስልክ፥ መድሃኒትም በአንዳንድ ሥፍራ መጠለያም ጭምር የማጣት ድርብ ሸክም የተጫነበት የትግራይና ትግራዋዩን አበሣ ስንቃኝ ግን ልባችን ይደማል። ለትግራይ ህዝብ ህይወት "በግራ ጎኗ የተነሣችበት" ምስጢር አይገባኝም። ትግራይ ደርሼ በተመለስኩበት ጊዜ ሁሉ የግዴታ ስለማየው የህዝባችን መልካምነት ባወራሁበት ጊዜ ሁሉ አንድም ወይም ሁለት ለማመን የሚቸገር አላጣም። “ብለህ ነው? ምናልባት ጥሩ ሰው አጋጥሞህ እንዳይሆን።”

አዎን ጥሩ ሰው አጋጥሞኛል። ችግሬ ግን ያጋጠሙኝ ሰዎች ሁሉ በሚባል ደረጃ ጥሩ መሆናቸው ነው። የትግራይ ፖለቲካ ደም አስለቅሶን ደም ያቃባ ሆኖ እንጂ የትግራይ ህዝብ ፍቅር መግቦ የማይጠግብ ለመሆኑ ምሥክር አያሻውም። ሰሞኑን በኦፊሴል ግብዓተ መሬቱ የታወጀው ህዋሃት በትግራይ የተከለው ህፀፅ ሃገሪቱን በሙሉ የለበለበ ክፉ የሰደድ እሳት ነበር። የህዋሃት-ትህነግ የጥላቻ ፖለቲካ በተለይም ወንድሞቻቸውን ኤርትራውያንንና አማራውን አጥብቆ በመጥላት ላይ የተመሠረተ ነበር። ከዚህም ጋራ “ሁሉም ትግራዋይ ህዋሃት ነው” የሚለው እኲይ ስብከታቸው “ሁሉም ትግራዋይ አማራውንና ኤርትራውያንን ይጠላል" በሚል እስኪተረጎም ድረስ እጅግ ደክመዋል። የማይ ካድራው ጭፍጨፋ እርሱንም ተከትሎ በመተከል አማራውና አገው ላይ የደረሰው በደል የዚህ ጥላቻን የመዝራት የትህነግና መሰሎቹ ፖለቲካ ቁንጮው ነው።

ይህ ህፀፅ በአፃፋው በመግደልና ህግ በማስከበር ብቻ የሚመከት አይሆንም። እጅግ የበደሉ፥ ሕግንም የጣሱ የእጃቸውን እንዲያገኙ ከማድረግ ጋራ ህዝብ ለህዝብ እንቅስቃሴ በማድረግ እውነተኛው ትግራዋይ ማንነቱ ጎልቶ እንዲወጣ፥ ይህ የፍቅር ህዝብ የጥላቻን ፖለቲካ ታሪክ ገልብጦ ወንድምነቱን ዳግም የሚያበሥርበት መንገድ መፈለግ የውዴታ ግዴታችን ነው። ለወገኖቼ ግልፅና ቀጥተኛ መልእክት አለኝ፦

ኢትዮጵያ ውስጥና በተለይም ትግራይ ያላችሁ ኤርትራውያን ወንድሞቻችን ሆይ፤ ከዕርቀ ሠላሙ በኋላ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ዘልቃችሁ በመግባት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወዳችሁ፥ የሚያከብራችሁ መሆኑን በተጨባጭ አይታችኋል። ትህነግ በመከላከያ ሃይላችን ላይ ጥቃት ባደረሰ ጊዜ ራቁቱን የሸሸውን ጦር አልብሳችሁ መላካችሁን ስንሰማ የበለጠ ነፍስ አልቀረልንም። እንወዳችኋለን። ታዲያ ትግራዋዩም የዚህ ህዝብ አካል ነው። ትህነግ በኤርትራ ካደረሰችው በደል የተነሣ እንደ ማንኛውም ሰው ትግራዋዩንና ትህነግን በአንድ ዓይን አይታችሁ ከሆነ ዛሬ ይህን ጭምብል አውልቁት። ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲትሉ እንደ ወንድም ተቀበሉት። ትግራይ ውስጥ ትህነግ ባደረሰችው በደል ላይ ተጨማሪ እንዳይሆን የወንድሞቻችሁን ሃብትና ንብረት በመዝረፍ፥ እህቶቻችንን በመድፈር ተሳትፈዋል የሚባሉ አንዳንድ ጋጠ ወጥ ልጆች እንዳሉ ወሬ ስለምንሰማ ከመከላከያና ሰሞኑን ወደ ሥራ በመመለስ ላይ ካለው የፖሊስ ሃይል ጋር በመሆን መልካም ስማችሁን የሚያጎድፉትን እንዲታጠፉ ይሁን።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ከትግራይ ጋር የምትዋሰኑ የጎንደር፥ ወሎና ሌሎችም ህዝቦች ሆይ፤ የትህነግ የግፍ ፅዋ ቀዳሚ ቀማሾች እንደ ነበራችሁ ይታወቃል። ትህነግ ደግሞ ይህን በትግራይ ህዝብ ይሁንታ ወይም ድጋፍ እንዳደረገው ነጋ ጠባ ይለፈልፍ ስለ ነበረ ወንድሞቻችሁን በክፉ ዓይን አይታችሁ እንኳ ቢሆን ዛሬ ጥላቻን በፍቅር የማሸነፍ ጥሪ በእጃችሁ ላይ ወድቋል። ይህን ግዴታ መወጣት ታላቅነታችሁን ያጎላል። ዛሬ የትግራይ ህዝብ ፍቅራችሁን ማየት ቢችሉ ለዝንተ ዓለም ገንዘብ፥ እስከ ወዲያኛውም ድጋፍና መከታ እንደሚሆኑላችሁ ዕወቁ። በቁጣ ብዛትም ቢሆን፣ በነገሮች መደራረብ ጥቂት ጊዜ ዝም ብለንም ቢሆን አሁን የመነሻው ወቅት ነው። ቤተ እምነቶች፥ የህዝብ ድርጅቶች ፥ ወዘተ ቀድማችሁ አንቀሳቅሱን! 

photo credit: pride-ethiopia.org

የአገራችን እውነታ፣ ጸሐፊው ከላይ በዐይኑ አይቶ እንደመሰከረው ሆኖ ሳለ፣ በጥቂቶች ጩኸት የብዙሓኑ ድምጽ ታፍኖ እንመለከታለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጅምሩም እግዚአብሔርን ፈሪ፣ እንግዳ አክባሪ ነው። የሚጣሉና የሚያጣሉ ጥቂቶች ሕዝቡን አይወክሉም! ብዙዎቻችን ዝም ስላልን፣ አደባባዩን ጥለንላቸው ስለሄድን ብቻ ገነኑ። አገራችን የሁላችን እስከሆነች፣ የእኛንና የልጆቻችንን መብትና ቅርስ እያዘረፉ ያሉትን ጥቂቶች፣ እንዳይሠለጥኑብን ድምጻችንን አሰባስብን ተግተን ማሠማት አለብን። ስጋታችንን እያባባሱና ጥላቻ እየቆሰቆሱ የሚነግዱብንን ለይተን ልናውቃቸው ይገባል! መጣላት፣ መጠላላት አንፈልግም እንዳንል ምን ይከለክለናል? ከውስጥና ከውጭ በማህበራዊ ሚድያ አገር ወዳድ መስለው በስእብናችን ላይ ጦር የከፈቱብንን በቃን! ወጊዱልን አንፈልጋችሁም! እንዳንል ምን ያግደናል?! ዝምታ ያብቃ!! ይህን መሳይ ታሪክ ያላችሁ ላኩልንና ለብዙዎች እናዳርስ። ~ ኢትዮፕያንቸርች ዶት ኦርግ