meseret tmhrt

አጥርቶ ለማንበብ አጥርቶ ማሰብ
አጥርቶ ለማሰብ አጥርቶ ማንበብ
ምትኩ አዲሱ

ያለግድፈት፣ አጥርተው የሚያነብቡ አሉ። ጨማምረው ቀናንሰው እንጂ የማያነብቡ አሉ። ሲያነብቡ የራሳቸውን ድምፅ ማድመጥ የሚበልጥባቸው አሉ። የትኛው ዓይነት አንባቢ ነዎት?

በዚህ ዘመን ጥሩ አንባቢ ለማግኘት፣ ወይ ገዳም ወይም አርባ ዓመት ወደ ኋላ መቃኘት ያስፈልጋል። የዛሬ ዜና አንባቢዎች ባብዛኛው ራሳቸውን መሆን ያቃታቸው ናቸው። በሌላ ሰው ድምጽና ዘዬ ያነበንባሉ፤ በተውሶ ቅላፄ ማነብነባቸው መታመን እንደሚነሳ ያልገባቸው ናቸው።

ሀዲስ ዓለማየሁ፣ “ፍቅር እስከ መቃብርን እኔ ጻፍኩት፤ ወጋየሁ ነፍስ ዘራበት” ብለው አነባቡን አድንቀዋል። የወጋየሁ ንጋቱ ያነባበብ ምሥጢር ምንድነው? ምሥጢሩ፣ አድማጩን ወደ ራሱ ሳይሆን ወደ ታሪኩ መምራቱና ገጸ ባህርያቱን በራሳቸው ድምጽ ለመናገር ማብቃቱ ነው። አድማጭ በትረካው ላይ ሙሉ እምነት የኖረው ለዚህ ነው። የጥሩ አንባቢ ታማኝነት በቅድሚያ ለትረካውና ለአድማጭ ነው። ኢትዮጵያ ራዲዮ በተከታታይ ፍቅር እስከ መቃብርን በጧት ፕሮግራሙ ሲያሠራጭ በነበረ ዘመን ብዙዎች ከሥራ የሚያረፍዱበትን ምክንያት መገመት አያዳግትም። (ያኔ ባንዴ በቊሙ እንጂ እንደ ዛሬ አሳድሮ በ “ፖድካስት” በ “ሪፕሌይ” ማድመጥ አይቻል እንደ ነበር አንዘንጋ!)

ብዙዎች ዛሬ የወጋየሁን ፈለግ ተከትለው በንባብ ጋጋታ ዩቱብና ራዲዮ ጣቢያዎችን እያጣበቡ ነው። ከባለ ሙያ መማር በራሱ በደል የለበትም። ድርጊቱ ግን ወጋየሁ ንጋቱ ከመሠረተው የአነባብ መሥፈርት እንደ ወረድን አጒልቷል። እንዳለ መኮረጅ፣ በራስ ያለመተማመን፣ ለትርፍ የመሯሯጥ ምልክት ነው። የፈጠራ ችሎታ ማነስ ነው። አንዳንዴም የቅናትና የምቀኝነት። ወዳማረበት፣ ወደ ደራበት እስኪራከስ ይንጋጋል። በህወሓት ዘመን፣ የቋንቋ ፖሊሲ መዘባረቁና የትምህርት ጥራት መውደሙ ትውልዱን የፈጠራ መኻን አድርጎታል። ራስ ተኮር፣ ብሔርና ቅራኔ ተኮር ፖለቲካ እውነትን የመጠየፍ ባህል አበራክቷል። ከሠላሳ ዓመት ወዲህ፣ ባብዛኛው የፈጠራ ምድረ በዳ ውስጥ እየዳከርን እንገኛለን።

ያለግድፈት አጥርተው የሚያነብቡ ቊጥራቸው ቢመናመንም ጨርሶ አልጠፉም። “ሌሎች ብዙ ጒዳዮች በዚህ ሥር ይካተታሉ” የሚለውን ዐረፍተ ነገር እንደ ምሳሌ ብንወስድ፦ ይካተታሉ የሚለውን ይከታተሉ ብለው ያነበቡ አሉ። ሌሎች፣ ይከተታሉ ብለውታል። ይህ ዓይነት ስሕተት የሚከሰተው 1/ ከልምምድ ጒድለት ነው 2/ በተከፈለ ልብ ከማንበብ ወይም ከጥንቃቄ ጒድለት 3/ አንዳንዴም ከቃላት እውቀት ማነስ።

ግድፈቶች እንደ እንጒዳይ ፈልተዋል። ርቀን ሳንሄድ፣ ብሔራዊ ጋዜጦቻችን፣ አዲስ ዘመን እና ኢትዮፕያን ሄራልድ የሚያሳፍሩ በግድፈት የተበከሉ ጋዜጦች ሆነዋል። ይህ የሚያስረዳን እውነታ አለ፣ 1/ ለአንባቢ ዝቅተኛ አክብሮት መኖሩን 2/ በብቃት ሳይሆን በብሔር ኮታ ኃላፊነት ላይ መመደብ ያስከተለው 3/ የትምህርት ጥራት መውደቅ። ለተጨማሪ መረጃ፣ የኛን ከጎረቤቶቻችን ከኬንያና ከሱዳን እለታዊ ጋዜጦች ጋር ያስተያዩ።

አጥርቶ ማንበብ፣ ከኮሮና ባልተናነሰ ዘመቻና ክትትል ይሻል። በቃል አተረጓጎም ላይ የተለያየ መረዳት መኖር ወደ አለመግባባት ይመራልና፤ የመንግሥትን አመራር ያዛንፋል። በዜጋ መሓል አለመተማመንን ያባዛል፤ ፍትህን ያዛባል። ከወንጌል ሰባኪ እስከ አወያይና ዜና ዘጋቢ፣ የሚጠቀመው ጒራ (ማይሌ) እና አደንቋሪ ድግግሞሽ አድማስን የሚያፈካ ሳይሆን የሚያጨልም ነው! ትምህርት ቤቶች ከታች እስከ ላይ በንባብ፣ በእጅ ጽሕፈት፣ ምንባብን አስተካክሎ ለመረዳት በሚያስችሉ ጥናቶች ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል።

በኦዲዮ የተቀረጹ ምንባቦችን ያዳምጡ። የጥራት መሥፈርት ሊሆኑ የተገባቸው ሰነዶች (መጽሐፍ ቅዱስ፣ መዝገበ ቃላት፣ እና ህገ መንግሥት) በግድፈት የታጨቊ ሆነዋል። የፖለቲካ መሪዎችን፣ የሚኒስቴር መ/ቤቶችን መግለጫዎች፣ ሐተታዎችና መምሪያዎችን፤ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ምርምር ውጤቶችን ይመልከቱ። ኦድዮ አንባቢያን መጽሐፍ ቅዱስን በ “መንፈሳዊ” ድምፅ፣ እንደ መላእክት፣ እንደ እግዚአብሔር ሊያነብቡ ሲጥሩ መስማት ያስቃል፤ ያጀባቸው ሙዚቃ የሚነበበው ኲልል ብሎ እንዳይወጣ እየተሻማ እያዘናጋ እረፍት ይነሳል!

አንድ ድምዳሜ ላይ ደርሻለሁ፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ኦዲዮዎችን ማድመጥ ባስቸኳይ ይቊም። በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን (1954 ዓ.ም.) የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ይነበብ! በየእሑዱ አንዳንድ ምዕራፍ ከመዝሙረ ዳዊት ወይም ከተመረጠው ክፍል በተከታታይ ይነበብ፤ አጥርተው የሚያነብቡ ብቻ ተመርጠው በጒባኤ ያንብቡ (መጽሐፍ ቅዱስ ምእራፍ በምእራፍ ምንም ሳይጨመርበት በቀጥታ ከመድረክ ሲነበብ ከሰሙ ምን ያህል ጊዜ ሆነዎ?)። የአምልኮ መሪዎች፣ የአስተማሪዎች የቃላት ድግግሞሽ ለሕያው ቃል ሥፍራ ይልቀቅ! ሕዝቡን ከስሕተትና ከድንቊርና ማዳን ይቅደም! እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሁሉ ነው፣ ለሁሉ ነው፤ በሁሉ መነበቡም ተገቢ ነው። ባለቤትና በራሱ ሥልጣን እንደሌለው ተደርጎ ሊታሰብ አይገባም። ትንሽ ስሕተት ቢገኝበትም ኦዲዮ አንባቢው ስለ ጥረቱ ሊመሰገን ይገባል ማለት በእግዚአብሔርና በሰው ፊት በደል ነው።

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በተጨማሪ ሦስት ዋነኛ ነገሮችን ሊያደርጉ ይገባል፦ አንደኛ፣ የማያነብቡ እንዲያነብቡ፣ የሚያነብቡ አጥርተው እንዲያነብቡ (“መኃይምነት ከጌታ ቤት ይወገድ!” የሚል መፈክር አንግበው ይነሱ)። አጥርቶ ማንበብ የስህተት ትምህርቶችን ለመቋቋም ዓይነተኛ መሣሪያ ነው!! ሁለተኛ፣ ግድፈት የተገኘባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችና ኦዲዮዎችን ለይቶ ሕዝብ እንዳይጠቀምባቸው ያድርጉ። ሦስተኛ፣ እንደ ፖለቲከኞቹ ተካልለው የየራሳቸውን ኦዲዮ ከማተም፣ ጥምረት ፈጥረው ጥራት ያለውን ኦዲዮ መጋራት የተሻለ ነው። ብዙዎች ዩቱብ በሚያስገኘው ፍራንክ መሠማራታቸው እውን ነው! እንደ ኢየሩሳሌም ኤቫንጄሊካል ቤተ ክርስቲያን (ስዊድን) ኦዲዮውን ከቃሉ ጋር አጣምሮ ማናበብ ደግሞ ተጠያቂነትን ያበጃል፣ ግድፈቶችን ለማረም ይረዳል። በአንድ አንባቢ ብቻ መደረጉ ችግር የለውም። ኢየሩሳሌሞች እንዳደረጉት አስራ አራት አንባቢ ማሳተፍ (አንዲትን እህት ጨምሮ!) ግን ሸክሙን ከመጋራት አልፎ የብልቶችን አንድ አካልነት በማስታወሱ ሁለት ተልእኮ ባንዴ ተወጥቷል።

በኦዲዮ የለጠፉትን ማንነት ሳልጠቅስ ከብሉይ ኪዳን ሁለት ምሳሌ ልጥቀስ፦ ትንቢተ ሕዝቅኤል፤ 5፡11 “እኔ አሳንስሻለሁ” የሚለው፣ “እኔ አስነሳሻለሁ” ተብሎ ተነብቧል። የ “ከፍታ ዘመን” ወሬ እግዚአብሔር ማሳነስም እንደሚያውቅበት ሳያረሳሳን አልቀረም! ሕዝ 37፡18 “የሕዝብህም ልጆች። ይህ የምታደርገው ነገር ምን ማለት እንደ ሆነ አትነግረንምን?” የሚለው “የአሕዛብም ልጆች”፤ ወዘተ። እነዚህን ምሳሌዎች በሃምሳ ያባዙ፤ የግድፈቶቹን ገሚስ እንኳ አይሆኑም!

መልካም እረኛ በጎቹን በለመለመ መስክ ያሳድራቸዋል፣ በእረፍት ውኃ ዘንድ ይመራቸዋል። ይኸው እረኛ፣ ጥቃቅን እሾኾችና ደረቅ ሣሮች አልፎ አልፎ ቢገኙ ምንም አይደለም ቢል የማያስተውል፣ ሰነፍ፣ ጨካኝ አያደርገውም? የበጎች ሁሉ እረኛ ችላ የሚል ከመሰለን ገና አላወቅነውም ማለት ነው!

ከላይ የሚታየው ፎቶ፦ የኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም አስተዳደር ደርግ ከፈጸማቸው ታሪካዊ ሥራዎች መሓል የተምሮ ማስተማር ዘመቻ አንዱ ነው። የ1972 ዓ.ም. ዩኔስኮ (ተ.መ.ድ.) ተሸላሚ ነበር።