ዜና ዕረፍት - ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ

Getatchew Haile

የቋንቋዎችና የጥንት መዛግብት ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በ90 ዓመታቸው በፈረንጆች ጁን 10/2021 በንውዮርክ አሜሪካ አርፈዋል። ዕውቀት የቀሰሙት፣ ከተወለዱበት ሸንኮራ፣ ከአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ፣ ከዚያ ግብጽ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና ዶክትሬት ካገኙበት ስመ-ጥር ቱቢንገን ዩኒቨርሲቲ ጀርመን ነው። ፕሮፌሰር ጌታቸው አገር ወዳድና የኢትዮጵያን ሥልጣኔ፣ ለዓለምና፣ ከግእዝና ከጀርመንኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም፣ ለኢትዮጵያውያን ያስተዋወቁ ናቸው።

ደርግ አቡነ ቴዎፍሎስን ከሥልጣን ለማውረድ ሲያሤር ፕሮፌሰር ጌታቸው ተቃውሞ ካሰሙት መሓል ነበሩ፤ በተኩስ ልውውጥ ወገባቸውን ተመትተው እግራቸው ሳይረግጥላቸው ኖረዋል። በ ሴንት ጆንስ ዩኒቨርሲቲ ሚኒሶታ አሜሪካ ሊፈጽሙት የጀመሩትን የአገራችንን የጥንት መዛግብት ሥራ አጠናቅቀው፣ ተተኪ አፍርተዋል። የልጅ ልጅ አይተዋል። መንፈሰ ብርቱና ለዓላማቸው የቆረጡ ግለሰብ ለመሆናቸው ይህ ብቻውን ትልቅ ምስክር ነው፤ በአገራችን ጉዳይ ተስፋ እንዳንቆርጥ ለቀረነው ትጋታቸው ሊያበረታታን ይገባል።

ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ተመራማሪና አስተማሪ ብቻ ሳይሆኑ በዘመኑ ፖለቲካም አክርረው አሳባቸውን በቃልና በጽሑፍ በየመድረኩ በማስረዳት ይታወቃሉ። አባባሎቻቸው አወዛጋቢ ያልሆኑባቸው ጊዜአት ጥቂት ናቸው። ለምሳሌ፦ እናንተ ጥገኞች እንጂ፤ ባለ መሬት እኛ ነን ማለታቸው። ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ተከፍላለች ለሚሉት “እናት ቤተ ክርስቲያናችን አልተከፈለችም” ማለታቸው ብዙ ቅሬታና ቁጣን ቀስቅሷል። “ዘ ሚሺኔሪ ፋክተር ኢን ኢትዮጵያ” (በፈረንጆች 1996) መጽሐፍ ላይ ከኦርቶዶክስ እምነት ውጭ ወንጌል አማኝነትን አገር ከመክዳት ጋር አመሳስለዋል፤ ክርስቲያን ማህበራት እንዲቃቃሩ ሰበብ ለሚሹ ሰበብ ፈጥረዋል። ከግእዝ ወደ አማርኛ በተረጎሙት “ደቂቀ እስጢፋኖስ” (1995 ዓ.ም.)፣ በ15ኛው ምእተ ዓመት በኢትዮጵያ የተከሰተው ኦርቶዶክሳዊ ተሃድሶ (ተጨናገፈ እንጂ) ገንኖ ከሚነገርለት ከፕሮቴስታንቱ አውሮጳዊ ተሃድሶ ይቀድማል የሚል አሳብ አዝሏል። ኢትዮጵያዊነትን ከደገኛነት እና ከኦርቶዶክስ አማኝነት ጋር እንዳያያዙ ብዙዎች ታዝበዋል።

በ “አንድ አፍታ ላውጋችሁ” (2006 ዓ.ም.) የአተራረክን ውበት ያሳዩበት፣ ብዙ የተደራረቡ፣ ወደ ሰፊ አሳብ የሚጠቁሙ እይታዎችን፣ ለታሪክ ተመራማሪዎች ገና የሚቆፈር ማዕድን ትተውልን አልፈዋል። ለምሳሌ ያህል ሁለት ምንባቦችን እንጥቀስ፦ 1/ “ወደ ካይሮ መጣሁ። ያኔ ገና ትምህርቴን እየቀጠልኩ ነበር። ... ደክሞኝ ቁጭ ብያለሁ። ... አንድ በጣም ነጭ የሆነ ... የከሳ ሽማግሌ .. በዚያ ሲያልፍ አየሁ። ... በአረብኛ ነው፣ “ጀርመን ነህ ወይ?” አልኩት። ... “አይደለሁም” አለኝ። “አይ ይቅርታ እንደው ጀርመን ብትሆን ኖሮ የጀርመንኛ ቋንቋ እንድታስተምረኝ ለመጠየቅ ነው እንጂ ለክፋት አይደለም” አልኩት። “አይ ጀርመንም ባልሆን በርሊን ዩኒቨርሲቲ ነው የተማርኩትና ላስተምርህ እችላለሁ” አለኝ። ... ቁጭ ብለን ስናወራ፣ ... “ከየት ነህ?” አለኝ። “ከኢትዮጵያ” ስለው፣ “ከተፈሪ አገር? ያ ተፈሪ እኮ አባረረኝ ከኢትዮጵያ። እኔኮ የእቴጌ፣ የንግሥት ዘውዲቱ ፈረሰኛ ነበርኩ፣ ኮንት ‘እገሌ’ እባላለሁ” አለኝ፣ ኮንት እንግዲህ ባለ ሹም ማለት ነው አይደለም? አገረ ገዥ እንደ ማለት ነው፣ እንደ መስፍን ነው። “የራሺያ ሪቮሉሽን ሲመጣ ሁላችንም ተበታተንን። ያለቀውም አለቀ፣ የቀረነውም በየቦታው ስንሄድ እኔ ወደ ኢትዮጵያ ከሄዱት ውስጥ አንዱ ነበርኩ” አለኝ።

2/ [ደርግ ሥልጣን እንደ ያዘ ሰሞን] “የጠቅላይ ግዛቶች ምርጫ ደግሞ መጣ። ከዚያ ለሸዋ ሊመርጡኝ ... እባክህን ፓርላማ ሸንጎ እንድትገባ ተወዳደርልን አሉኝ። ... እሽ አልኩና እዚያው ውድድሩ ውስጥ ገባሁ። ... የነበረው ጭቅጭቅ ግራ አጋባኝ። ... ሁሉም ሪቮሉሽን ሪቮሉሽን እያለ ነበር የሚናገረው። ... ኮሎኔል አጥናፉ አባተ ... ጠራኝና፣ “ቤተክህነትና ቤተመንግሥት አብረው መሥራታቸው ቤተክህነትን የቤተመንግሥት ጥገኛ፣ የዚያ ተጠቂ አድርጓታልና በገንዘብ በኩል ራሷን ችላ እንድትተዳደር አንድ ዘዴ መፈለግ አለብንና እባክህ አንድ ኮሚቴ እናቋቁምና እዚያ ላይ አገልግልልን” አለኝ። ኮሚቴው ተቋቋመ።”

የምሑር ማወዛገብ፣ በተለይ በሶሻል ሳይንስ ምርምር፣ የተለመደ ነው። ውዝግቦቹን በማግነን ብዙ የሚጠቅሙ ፍሬዎችን እንዳናባክን እንጠንቀቅ። የብርቱ ምሑር ደግሞ ዝናና ተጽእኖ በአንድ ሕይወት ዘመን ብቻ አይገታም። ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ታላላቅ ምሑራን መሓል የሚደመሩ ናቸው። እግዚአብሔር ያዘኑትን ያጽናና።

የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን ያንብቡ