ap news

ምርጫ 2013 አዲስ ተስፋ ይዞ መጥቷል! እንዲያብብ እናግዝ!

ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በብዙ መልኩ ታሪካዊ ነው። ባለፉት አምስት ምርጫዎች ህወሓት መራሹ ኢሕአዴግ መቶ በመቶ ሲያሸንፍ፣ ዜጋ በብሄሩ በኲል ለህወሓት ድምጽ ሲሰጥ ኖረ። ያለ እኔ ፈቃድ ሥልጣን አይታሰብም ብሎ ህወሓት ከጅምሩ አስታውቆ ነበር። ከብሔር ከርሸሌ ነጻ ያወጣኋችሁ ስለ ሆንኩ በዚህ ጉዳይ ጥያቄ ማንሳት ውለታ ቢስነት ነው አለ። በ97 የዲሞክራሲ ስልቱን ዓለም እንዲያይለት ብቻ በሩን ትንሽ ገርገብ ቢያደርግ ያልጠበቀው ሽንፈት ገጠመው፤ በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ ባፋጣኝ የሽብርተኛ ህግ ደነገገ፤ የተቃወምክ ሁልህም ወዮልህ አለ! ቀድሞውንም ዲሞክራሲ-ጠል ሆኖ ስለ ተፈጠረ፣ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” በሚል ወግ ማምታታቱን ተያያዘው፤ ሳያስበው በገዛ እጁ ፍጻሜውን አሳጠረው።

ያለ እኔ አገር ትበተናለች አለ፤ አገር በመበተን ተሠማራ፤ በ90 ለሁለት ተሠነጠቀ፤ 80 ሺህ ወጣት ተረፈረፈ። በ2002 መለስ ሞቱ፤ ከስምንት ዓመት በኋላ ህወሓት ተበተነ። ህወሓትን የበተኑት መተኪያ ያልተገኘላቸው የተባለላቸው መለስ ናቸው። ለሁሉም መልእክት ይሁን፦ የማይጋራ የማይደራደር ሥልጣን ፍጻሜው አያምርም!

አሜሪካኖች፣ አውሮጳውያን እና ህወሓት፣ በኮሮና ምክንያት ምርጫ 2013 መተጓጎል የለበትም ሲሉ ቆይተው፣ ትልቅ ረብሻ ስለሚፈጠር ጨርሶ መደረግ የለበትም ወደ ማለት ተሸጋገሩ። ከዚያ ምርጫው ላይ ታዛቢ አንልክም! ምርጫው ግን በሰላም ተጠናቅቋል። በህወሓት ዘመን ያልታየ ከፍተኛ የዜጋ ተሳትፎ ተመዝግቧል። ለመምረጥ ከተመዘገቡት 37 ሚሊዮን ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ ድምጽ ሰጥተዋል (በአሜሪካ በ2016፣ 61.4%፤ በእንግሊዝ 72.21% ጋር ያነጻጽሩ!)።

ምርጫ ያልተካሄደባቸው ጥቂት የኦሮምያ እና የትግራይ ክልሎች መስከረም ወር ሳይገባ ድምጽ ይሰጣሉ ተብሏል። ሦስት ጉዳይ መረሳት የለበትም፤ 1/ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተሰባጥሮ እንደሚኖር መዘንጋት የለበትም። ከዚህ የተነሳ ድምጽ ያልሰጠ ብሄር የለም፤ ይህ ትግሬ ወይም ኦሮሞ ስለ ሆኑ ድምጽ እንዳይሰጡ ተከለከሉ ለሚሉ እርምት ይሆናል፤ 2/ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 110 ሚሊዮን ነው፤ በየክልሉ ያሉትን ትግሬ እና ኦሮሞ ዜጎችን ጨምሮ በትግራይ ክልል እስከ 6 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች አሉ 3/ ከትግሬ ከኦሮሞ ከአማራ ወዘተ መምረጥ እየቻሉ ያልመረጡ ዜጎችም ይኖራሉ፤ መምረጥም አለመምረጥም መብት ነውና ይኸ ጥያቄ ሊፈጥር አይገባም።

የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ብልጽግና ፓርቲ ከ436 ውስጥ 410ሩን መቀመጫ አሸንፏል። ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና ፓርቲአቸው ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በድምጽ ብልጫ መሪነቱን ይይዛሉ። በዐይነ ቁራኛ እንከታተላቸው። ሥራ ካልፈጠሩ፣ በሰላም ገብተን እንድንወጣ መተማመኛ ካልሰጡን፣ ዜጋ በዐይኑ ቀለም ሳይሆን በዜግነቱ ብቻ አገሩ ላይ የትም ሄዶ ሠርቶ ለመኖር ካላስቻሉ፣ በተለይ የሕዝብን ንብረት መዝረፍ እና የህግ የበላይነትን ማዛባት ካበዙ በምርጫ 2018 ዓ.ም. እንደምንጠየፋቸውና የተሻለውን እንደምንመርጥ ከወዲሁ ይወቁ!

የዶ/ር ዐቢይ እና የፓርቲአቸው ማሸነፍ ሊገርም አይገባም። ምክንያቱ ሁለት ነው፤ ምርጫ 2013 ብዙዎች እንዳሰቡት ሳይሆን በህወሓት ላይ የዜጎች አቋም መግለጫ (ረፈረንደም) በመሆኑ። ባጭሩ፣ ከእንግዲህ የዘር ፖለቲካ ሰልችቶናል፣ ይብቃን! በክልል ሳንታሠር፣ ያልወከልናቸው ጥቂቶች ሳይሠለጥኑብን፣ በእኩልነት በነጻነት በአገራችን ላይ መኖር እንፈልጋለን ነው! በየመታወቂያችን ላይ “ኢትዮጵያዊነታችንን” ለድርድር አናቀርብም ነው!

ምርጫ 2013 በህወሓት ላይ ረፈረንደም መሆኑን የሚጠቊመን፣ ብልጽግና በአዲስ አበባ ከ22 የፓርላማ ወንበር 21ዱን፣ በአማራ ክልል ደግሞ 114ቱን ማሸነፉ ነው። (አብን በገዛ ሠፈሩ 5 ብቻ ማሸነፉ፣ መሸነፉ!)። ሁለተኛ፣ ዶ/ር ዐቢይን ይነስም ይብዛም በእነዚህ ሦስት የመዓት አመታት አውቀናቸዋል፤ በህወሓት ዘመን ትንፍሽ ማለት ያቃተንን (በተልካሻ ምክንያት ከርሸሌ የወረድንበትን) ዛሬ እንዳሻን በዶ/ር ዐቢይና ባስተዳደራቸው ላይ ሳይቀር እያባረቅን እንገኛለን! የሌሎችን ፓርቲዎች ንግግራቸውን እንጂ ተግባራቸውን አላየንም! ለምሳሌ፦ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ (ኢዜማ) ሸር የማያውቁ አገር ወዳድ፣ ዘረኛ ፖለቲካን ለመዋጋት ያላሰለሰ ጥረት ያሳዩ ጎበዝ ኢኮኖሚስት ናቸው፤ አገር ሲያስተዳድሩ ግን አናውቃቸውም! የቅንጅት መሪ ሆነው መታሠራቸውን፤ ኋላ አገር ጥለው መውጣቸውን እናውቃለን። የተቀሩት ፓርቲዎች ከመሠነጣጠቃቸው ብዛት እንደ እብቅ ነፋስ ይዟቸው የሚሄዱ ያህል አንሰዋል። አጀንዳቸውን ለማስፋት ጥምረት ለመፍጠር ከተጠቀሙበት የአምስት ዓመት ጊዜ አላቸው።

የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ብልጽግና ፓርቲ በ94 ፐርሰንት ማሸነፉ እንዳፈቀደው ለማድረግ ይችል አይምሰለው። አይችልም። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በገለልተኛነት እስከ ፀና ድረስ፣ ሌሎቹ ፓርቲዎች እስከ ተጠናከሩ ድረስ፣ ከእንግዲህ የፖለቲካ ሂደቱ ዲሞክራሲያዊ ነውና፣ ሁሉ የሚጋራው የዲሞክራሲ ፍሬ መታየት ይኖርበታል። ገዥው ፓርቲ ለሁሉም እንዲብቃቃ ተግቶ በሥራ ማሳየት ይኖርበታል። የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ታግቶ ያለፍርኃት ድምጽ ማሰማት እንዳልቻለ አይተናል፤ በአማራም በኦሮምያም ግለ ሰቦች ተደራጀን በሚል ወግ ራሳቸውን የሕዝቡ ህጋዊ ወኪሎች አድርገው ሲያቀርቡ አይተናል፤ ምርጫ 2013 ወኪል ነን የሚሉትን ማንነትና አቅም ግልጽ አድርጓል። ወደ ታገተው ሕዝብ ለመድረስ የጠበበው ደጅ ይስፋ!

ሕዝብ ማረጋጋት ደግሞ የገዥው ፓርቲ ብቻ ኃላፊነት ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያውያን ይህን ትውልድ ማመስገን እና ከጎኑ መሠለፍ ግዴታ አለብን። ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ የብሔራዊ ምርጫ ቦርዱን ከአጋሮቻቸው ጋር በብቃት ሲመሩ ማየት እጅግ ተስፋ ሰጭ ነው። የኢትዮጵያ ወንዶች የመተናኮልና ደም የመፋሰስ ባህል፣ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ሴቶች ጥንቊቅ ስነ ምግባርና አብሮነት ተተክቶ ለማየት በቅተናል። ክብር ለአምላክ ይሁን። ዳኛ ብርቱካን ከከፈሉት መስዋእት አንጻር ታሪክ ተገልብጦ ይኸ ይሆናል ብሎ ያሰበ የለም። ሰው ላመነበት በጎ ዓላማ መታገሉ ዋጋ ቢያስከፍልም ፍጻሜው እንደሚሠምር ማስረጃ ነው።

አገር የሚመራው ፓርቲ ራእዩ እንዲሠምር ዜጋ ሁሉ ማገዝ እንጂ እንደ ሱሰኛ ጠበኛ ዘወትር መቃወም ጠልፎ ለመጣል በሃሰት ማጣጣል ፍሬ ቢስ ነው። ዶ/ር ዐቢይን ተኣምር ሠሪ አድርጎ ማየት ትልቁ ስህተት ነው፤ ህወሓት 30 ዓመት የጎነጎነውን በሦስት ዓመት ይፍቱ ማለት ጨርሶ ሚዛናዊነትን ማጣት ነው! ከእንግዲህ እርስ በርስ በአሳብ ዙሪያ መመካከር፣ መከራከርና ለአገር በሚጠቅም ሁሉ መያያዝ እንጂ እንደ ሰነፍ ልጅ በጎ ወደማይመኙልን ባዕዳን መሮጥ መቆም አለበት። እስካሁን ያተረፍነው ግራ መጋባት፣ እኩይ ዓላማ ላላቸው መግቢያ መፍጠር ነው። መሸነፍን የመቀበል ጸጋ፣ በሰላማዊ መንገድ ለማሸነፍ የመደራጀት ባህል ያብብ። እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ።

ምትኩ አዲሱ

ሰኔ 2013 ዓ.ም.

photo credit: ap news