ከርሸሌ ለነቢያት?

በሃሰት የሚተነብዩ ሕዝብ የሚያስቱ በድንጋይ ተወግረው ከሕዝብ መሓል ይወገዱ ነበር፤ "ያላዘዝሁትን በስሜ በድፍረት የሚናገር ወይም በሌላ አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ፥ እርሱ ይገደል" (ዘዳግም 18፡20)። እውነተኞች ነቢያት ሁሌ ጥቂት እና ዓይነተኞች ናቸው። የጠራቸው እና የላካቸውን እግዚአብሔርን እንጂ ራሳቸውን አያውጁም። አኗኗራቸው አነጋገራቸውን ይመስላል፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስለሚናገሩ እግዚአብሔርን ይመስላሉ። እንደ ኤርምያስ ብዙ ግፍ ይደርስባቸዋል፤ እንደ ኤልያስ ሃሰተኞች ይቋቋሟቸዋል፤ ነገር ግን አያሸንፏቸውም!

ትንቢት የሚናገር ሁሉ በእግዚአብሔር መንፈስ ይናገራል ማለት አይደለም፤ በሟርት መንፈስ የሚናገሩ፣ በቴክስትና በሞባይል መንፈስ የሚሠሩ፣ ለትርፍ የሚሯሯጡ አሉ (የሐዋርያት ሥራ 16፡16)። ስንቶች መንፈስ ይለያሉ? ስንቶች መናፍስትን እንለያለን? የወቅቱ ዋነኛ ጥያቄ ይኸ ነው!

በዚህ ዘመን ሃሰተኞች ነቢያት በድንጋይ አይወገሩም። እግዚአብሔር አሳቡን ቀይሯል ወይም አይፈርድም ማለት ግን አይደለም! የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ነቢያት የነበሩ ዛሬም አሉ፤ የጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ነቢያት፤ የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ነቢያት አሉ። ሕዝብ የሚያታልሉ፣ ሽብርን ሰላም፣ ግፍን ነፃነት፣ ድህነትን ብልጽግና የሚሉ። ከዓመት በኋላ "ብዬ ነበር" እኮ የሚሉ፣ ከፊት ፊት እየሮጡ የሚሉላቸውን ተከታዮች ያፈሩ። በእኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ የሚተናነቊ፣ የሚናጠቊ። (ማቴዎስ 7፡15-20; 2ኛ ጴጥሮስ 2)

ከርሸሌ የሚያወርድ ቢሆን ኖሮ ስንቶች ጆሮአችንን በትንቢት ያደነቊሩ ነበር? ነቢይ ነን የሚሉትን የሚከታተል ህጋዊ ኮሚቴ ቢቋቋም (ጠ/ሚ ዐቢይ ያቋቋሙት የወንጌል አማኞች ካውንስል ማለቴ አይደለም!)። በሃሰት የተነበዩትን፣ ለትርፍ የሚሠሩትን አጣርቶ ወደ ከርሸሌ ቢያወርድ ምን ነበር!