እልልታ ስገዱለት

ከዘማሪ ተስፋዬ ጋቢሶ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ

gabissopic

ምህረቱ አያልቅምና / ለዘላለም ቸር ነውና

የማዳን ኃይሉን ላሳየን / በክንዱ ለሚጎበኘን

መልካሙን መዓዛ / በምስጋና አቅርቡለት

በእልልታ ስገዱለት፤

ይህ አዝማች በየአብያተ ክርስቲያናቱ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የታወቀ አዝማች ነው። ቃሉንም ዜማውንም የደረሰው ተስፋዬ ጋቢሶ ነው። ተስፋዬ በ65 ዓ.ም. ክርስቶስን አግኝቶና ተለውጦ ዛሬ በወንጌል ሥራ እግዚአብሔርን የሚያገለግል የ24 ዓመት ወጣት ነው። ዩኒቨርሲቲ ሊያስገባው በሚችል ውጤት የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን በ1969 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ አጠናቋል። ደብረ ዘይት ሆራ ዳር ከዛፍ ጥላ ሥር እለምለም ሣር ላይ ተቀምጠን በመዝሙር ስለሚሰጠው አገልግሎት አንዳንድ ጥያቄ ጠይቀነው ነበር። 

ዱሮ ዘፈን መዝፈን ትወድ ነበር? ይህን ያህል አይደለም። ሻይ ቤት ከጓደኞቼ ጋር ቁጭ ስንል የምንሰማውን ዜማ መልሼ አንጎራጉር ነበር።

ታዲያ ጓደኞችህ ድምጽህን ያደንቁ ነበር?  ይህን ያህል አይደለም

መዝሙር መዘመር እንዴት ጀመርክ? መጀመሪያ በኅብረት እንዘምር ነበር። ለኅብረት የማይመቹ አንዳንድ መዝሙሮችን ብቻዬን እንደዘምር ይገፋፉኝ ነበር። ነገር ግን ዘማሪ እሆናለሁ ብዬ አልገመትኩም።

መጀመሪያ አዘጋጅተህ ብቻህን የዘመርከው መዝሙር ምን የሚል ነበር? “ከእስራቴ ፈታኝ” የሚለው ይመስለኛል የመጀመሪያ መዝሙሬ። ብቻ ለመጀመሪያ ጊዜ እግዚአብሔር ባንድ ጊዜ በርከት ያሉ መዝሙሮችን ስለ ሰጠኝ በተለይ አላስታውስም፤

ከ”እስራቴ ፈታኝ” የሚለውን መዝሙርህን ቃሉን ታስታውሰዋለህ? አዎ፣ “የሠራዊት ጌታ ኃያሉ መድኅኔ |

ሲጠብቀኝ ሳለ ጽድቅና ኩነኔ | በኃጢአት አረግ ስኖር ተሳስሬ | ከእስራቴ ፈታኝ …”

ይህን መዝሙር እንድትጽፍ የገፋፋህ ምንድነው? የሕይወቴ መለወጥ ነው

መዝሙር የምታወጣው በምን በምን መንገድ ነው? ዮሐንስ [ራእይ] “በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርኩ” ይላል። እኔም በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ በመንፈስ ሆኜ ነው የማገኘው። ስጸልይ፣ ቃሉን ሳነብ፣  በመንገድ ስሄድ፣ ያን ጊዜ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር፣ ስለ እግዚአብሔር ሥራ አስባለሁ። ይህንን ወደ መዝሙር እለውጣለሁ፤ ብቻ ብዙ ጊዜ ብቻዬን ስሆን ነው የሚታየኝ። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ፣ አእምሮዬ በአንድ መልእክት ይሞላል።

በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነህ ካወጣሃቸው መዝሙሮች መካከል አንዳንዶቹን በምሳሌ ብትጠቅስልኝ?  እሺ፤

“እንባዬን አይተህ ጌታ | ለቅሶዬን ሰምተህ ጌታ | መሻቴን ስጠኝና፣ የሱስ ላመስግንህ | “ምስጋና የሚገባውን / እግዚአብሔርን እጠራለሁ / ከጠላቶቼ እድናለሁ” ቃሉን ሳነብ ነው።  “እግዚአብሔር ኃያል | በሰልፍም ደግሞ ኃያል | ከቶ እስከ ዛሬ፣ ለማን ተረቶ ያውቃል” በመንገድ ስሄድ ነው ያውጣሁት።

ከመዝሙሮችህ መካከል የተለየ ትርጉም የሚሰጥህ አለ? ከጊዜ ወደ ጊዜ ይለዋወጣልና ይሄ ነው ማለት አልችልም

ታዲያ አሁን ባለህበት ሁኔታ በተለይ የምታስበው አለህ? ይህን ጥያቄ እለፈኝ [አለ ሳቅ እያለ]

ሌሎች ሰዎች ቃል ጽፈው ሰጥተው ዜማ አውጥተህ ዘምረህ ታውቃለህ? አዎ፣

እስቲ ለምሳሌ አንድ ጥቀስልኝ፤ ይህን ያህል የተለመደ አይደለም። በሕብረት ነው እንጂ በግሌ አልዘመርኩም

መዝሙር ምንድነው? ምን እንደምል አላውቅም። መዝሙር ግን እወዳለሁ፤

ስትዘምር ምን ይሰማሃል? በገዛ ራሴ ተነሳስቼ ስዘምር የመዝሙሩን ቃል እንደምዘምረው ይሰማኛል። ሰዎች ግን ሳይሰማኝ ዘምር ሲሉኝ እዘምራለሁ፣ ግን ላይሰማኝ ይችላል። በቦታውና በሁኔታው ሲሆን ነው ደስ የሚለኝ፣ የሚሰማኝም

እስከ ዛሬ ስንት ካሴት መዝሙር አውጥተሃል? አራት

እንዴት ጀመርክ በካሴት ማውጣት? የመዝሙሮቹ መልእክቶች ተቀርጸው ከበዙ ለብዙዎች ትምህርት እንደሚሆን ብዙዎች ስላመኑበት ቤተክርስቲያን አዘጋጅታ አወጣች። እኔ መዘመር ብቻ ነው። የቀረውን ሁሉ የምታደርገው ቤተክርስቲያን ነች።

በአገልግሎት ላይ ችግር ይገጥምሃል? ችግሩ ችግር መስሎ ስለማይታየኝም እንደሆን እንጃ ችግር አለብኝ ማለት አልችልም

በአጠቃላይ እንዲተላለፍ የምትፈልገው መልእክት አለ? አዎ፣ በብሉይም በሐዲስም እግዚአብሔር ለመዝሙር ታላቅ ቦታ ሲሰጠው እናያለን። እግዚአብሔር በመዝሙር የሕዝቡን ጠላቶች ድል እንዳደረገ እናነባለን። ሕዝቡ ባመሰገኑ ጊዜ የሚታየውና የማይታየው ጠላት ወድቋል። የኃጢአት ሰንሰለት ተበጣጥሶአል። ወኅኒ ቤት ተከፍቷል። ከዚህም በላይ መዝሙር ምድራዊ ብቻ ሳይሆን ሰማያዊም ነው። ስለዚህ መዝሙር ክቡር ነውና አክብረን መያዝ አለብን። ሁለተኛው ሃሳቤ በተለይ ወጣቶች የሆንን ቃሉን ከማጥናት ይልቅ መዝሙርማጥናት እናዘወትራለን ይመስለኛል። የተስተካከለ ሕይወት እንዲኖረን ለቃሉም በቂ ጊዜ መስጠት ይገባናል እላለሁ። ሦስተኛው ሃሳቤ ደግሞ እግዚአብሔር አሁን ካለነው ዘማሪዎች የተሻሉ እንዲያስነሳ ምዕመናን መጸለይ እንዳለባቸው ማሳሰብ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመዝሙር የተሠሩ ሥራዎች ሊሠሩ ይችላሉ። አራተኛና ማጠቃለያ ሃሳቤ ደግሞ እኛ ዘማሪዎች ሰማያዊ የሆነ መልእክት እንዲኖረን ምዕመናን በጸሎት እንዲደግፉን ማሳሰብ ነው።  

3/5/2010                    ከብርሃን መጽሔት .43 1971 .. ከገጽ 6 እና 13 የተወሰደ።