ዜ  ና   ዕ  ረ  ፍ  ት

kedamo

ወንጌላዊ ኬዳሞ ሜቻቶ በ91 ዓመታቸው ሰኞ ጥቅምት 5/2011 ዓ.ም ወደ ጌታ ሄደዋል፡፡ ቀብራቸው ሐሙስ ጥቅምት 8/2011 ዓ.ም ከ7 ሰዓት ጀምሮ በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ይፈጸማል፡፡ እግዚአብሔር ያዘኑትን ሁሉ ያጽናና፡፡ "መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።" 2ኛ ጢሞ4፡7፣8

ከታች የተለጠፈው ጽሑፍ የተጻፈው ከ23 ዓመት በፊት ነው፡፡ መልእክቱ ዘመን ተሻጋሪ ስለሆነ በጥሞና እናንብብ። ወንጌላዊ ኬዳሞ፣ እግዚአብሔር በወንጌል ብርሃን አገራችንን ለመጎብኘት በብርቱ የተጠቀመባቸው አባት ናቸው። ስለ እርሳቸው እግዚአብሔርን እንባርክ። የሚጠቀሙባቸው የነበሩ ምሳሌዎች አገርኛና የማይረሱ ናቸው፤ ስለ በቅሎአቸው እና በስብከታቸው መሓል “ምን እንደ ዱባ ዝም ብላችሁ ትቀመጣላችሁ?” የሚሉት ለዛ የተሞላ ማነቃቂያ ዘዴአቸውን ብዙዎች ያስታውሳሉ። የቤተክርስቲያኑ ጌታና አዳኝ ፀጋና ሰላሙን ያብዛልን። ጥቅምት 6/2011 ዓ.ም. [October 16/2018] Ethiopianchurch.org

የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት አሳብ

በወንጌላዊ ኬዳሞ ሜቻቶ

በ1981ዓ.ም. ወደ አውሮጳና አሜሪካ በሄድኩበት ጊዜ በልዩ ልዩ ሁኔታ ያሸበረቁ አብያተ ክርስቲያናትን ለመጐብኘት ዕድል አጋጥሞኛል። ሆኖም በዚያ ያየሁት የሕንጻዎች ማማር እንጂ የክርስቲያኖችን በመንፈስ ቅዱስ የተቀጣጠለ አገልግሎት አልነበረምና ውስጤ አለቀሰ። እግዚአብሔርም የግሣጼ መልእክት ሰጠኝና ብዙዎች አልቅሰው ንስሓ ገብተዋል። ዛሬም እያንዳንዳችን ለመንፈስ ቅዱስ ባልታዘዝነው ነገር የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን በድለን ከሆነ ንስሓ መግባት ይኖርብናል። ሌሎቹን ነገሮቻችንን ሁሉ ሳንቆጥር እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ዕለት ዕለት የሚከብድብን የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ሊሆን ይገባል (1ኛ ቆሮንቶስ 1128)

የሃያኛዋ መቶ ክፍለ ዘመን ቤተ ክርስቲያን የጥንቷን ቤተክርስቲያን መለኰታዊ ውርስ መቀዳጀት ግድ ይኖርባታል። በውጫዊ መልኳ ማሸብረቅ፣ የአባላት ቁጥር ለመጨመር ዕቅድ መንደፍ፣ ድርጅታዊ መዋቅር መዘርጋት፣ ወዘተ፣ አስፈላጊ ተግባሮች ቢሆኑም እነዚህ የቤተክርስቲያን ዋናና አንገብጋቢ ጥያቄዎች አይደሉም። የጥንቷን ቤተክርስቲያን ቆራጥነት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መጐናጸፍ ነው በቅድሚያ የሚያስፈልጋት። ከሐሰት ትምህርቶች ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ የምትተናነቀዋ የዛሬዋ ቤተክርስቲያን ኃይልን በሚሰጡት በክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋ የምታድግ፣ በፍቅር የተቀጣጠለች፣ በጸሎት የምትጋደል፣ የምትሰጥና ምዕመናኖቿን “ወንጌልን ስበኩ” ብላ የምታሠማራ መሆን አለባት። እንደ ሐዋርያት ዘመን በፍቅርና በተጋድሎ እንዳትቀጣጠል ቅድስናዋን ያበላሸውንና አዚም ያደረገባትን ማስወገድ ይኖርባታል። እንደ አውሮጳ አብያተ ክርስቲያናት ኦና ከመሆን፣ ከመቀዝቀዝና በዓለማዊነት ከሚከሰቱ ችግሮች መከላከል ጊዜ የማይሰጠው ተግባራችን ሊሆን ይገባል።

ለዚህም የእውነተኛ ቤተክርስቲያንን መለያ ባህርያትና የጥንቷ ቤተክርስቲያን የነበራትን የኃይል ምሥጢር ለመጨበጥ “በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም” የሚለውን የእግዚአብሔርን ቃል መታዘዝ አለብን (ት. ዘካርያስ 46)። የእውነተኛ ቤተክርስቲያን ባህርያትም በምድራዊ አስተሳሰብ የሚለካ ሳይሆን ሰማያዊና ዘላለማዊ ነውና ቤተክርስቲያን ማን ናት? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለብን። 

*   ቤተክርስቲያን አንድ አካል ናት፣ ፍቅርም ምልክቷ ነው

እግዚአብሔር በክርስቶስ ደም የዋጃት ቤተክርስቲያን አንድ አካል ስለሆነች ከጥንት ጀምሮ አካሉ በሆኑት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ኅብረት አለ (1ኛ ቆሮንቶስ 12፤ ኤፌሶን 44)። የዛሬዎቹን አብያተ ክርስቲያናት አሕዛብ ምን እንደሚሉን በትክክል ባናረጋግጥም የጥንቶቹን እየተቃወሟቸው እንኳ “ተመልከቷቸው እርስ በርስ እንዴት እንደሚዋደዱ” በማለት ይቀኑባቸው ነበር። ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት የምትሆነው በአካላዊ ኅብረት ውስጥ ሲሆን የአንድነቷ ቁልፍም ፍቅር ነው (1ኛ ጢሞቴዎስ 315)። ፍቅር ለአብያተ ክርስቲያናት ኅብረትና ለመንፈስ አንድነትና ከልብ ለመስማማታችን ዋና ምልክት መሆኑን መርሳት የለብንም። እንዲያውም አሕዛብ በፍቅራችን አንድነታችንን ማረጋገጥ ከቻሉ ፍቅርን መለያችን ነው ልንል እንችላለን።

ቤተክርስቲያን በክርስቶስ አንድ አካል ናት ስንልም ቁም ነገሩ የድርጅታዊ አሠራር መመሳሰል አይደለም። የአምልኰ ሥነ ሥርዓት ልዩነት ሊኖር ይችላል። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አጠቃቀም ልዩነት ሊኖር ይችላል። የአመራርና የአስተዳደር ልዩነትም እንዲሁ ይኖራል (1ኛ ጢሞቴዎስ 31-13)። አንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን በሽማግሌዎችና በዲያቆናት ሲስተዳደር፣ ሌላው በመጋቢያንና በእረኞች መመራቸው የክርስቶስ አካል ከመሆን ያስቀራል? አንዳንዶች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ለሁሉም አማንያን መኖር አለባቸው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ለልዩ ልዩ አገልጋዮች ይሰጣል ብለው ቢያምኑ የክርስቶስ አካል አይደሉም ማለት ነው? አንዳንዶች በተሰበረ ልብና በጸጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ሲገናኙ ሌሎች በጭብጨባና ጮኽ ባለ ድምጽ ማምለካቸው ከክርስቶስ አካል ውጭ ያደርጋቸዋል?

በእነዚህ ነገሮች መመካትና መፎካከር የክርስቶስን አካል ከመጉዳት በስተቀር ለደህንነታችንም ሆነ ቤተክርስቲያንን ለማነጽ ምን ጥቅም ይኖረዋል? የልብ አንድነታችን የተመሠረተውም በአምልኰአችን ልምምድ ሳይሆን በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። ያጣመረን የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት እንጂ ልምምድ አይደለም። ያስተሳሰረን የምሥራቹ ቃል ነው። ያገናኘን የመንግሥተ ሰማያት ዜግነታችን ነው። ከዚህም የተነሳ ደስታችንንና መከራችንን እንከፋፈላለን፤ የአንዷ ቤተክርስቲያን ሕመም የሌላዋም በመሆኑ ችግራችንን እንጋራለን።

ኃይልዋ ውጫዊና ድርጅታዊ አይደለም። ኃይሏ የሚመነጨው ከቤተክርስቲያን ሹማምንት፣ ከኰንፈረንስና ከኰሚቴ ሳይሆን ከመንፈስ ቅዱስ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን በሰው አስተዳደራዊ ጥበብ ብቻ ከተመራች ቤተክርስቲያን ለውድቀት ትዘጋጃለች። ለመንፈስ ቅዱስ ያልተገዙ ሊቃውንት የተሰበሰቡባት አካል ትቸገራለች። ለጸሎት ጊዜ የሌላትና የኰሚቴ ስብሰባ የበዛባት አካል ጫጫታና ጭቅጭቅ ይሰፍንባታል። የመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን የማይታይበት የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የጠረጴዛ ዙሪያ አንድነትን ቢያስገኝም የልብ አንድነትን አያመጣም። የአካል እንድነትና የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት የሌለበት የጋራ አምልኰ፣ የኅብረት ጸሎት፣ የአገልጋዮች ብዛት፣ የድርጅታዊ መዋቅር ኃይልና በረከትን ስለማያመጣ ቤተክርስቲያን ለሎዶቅያ ከተነገራት ማስጠንቀቂያ መማር አለባት (ራእይ 314-22)

በመንፈሳዊ ልምምዶች ልዩነት፣ በአምልኰ ሥነ ሥርዓት ልዩነት፣ በአስተዳደራዊ ጥበብ መበላለጥ ወይም በሌላ ምክንያት የክርስቶስን አካል ከመለያየትና ከመናናቅ በፍቅር አካሉን ብንገነባና ብናንጽ ይሻለናል። የአካል አንድነታችን ማረጋገጫ የሆነውን ፍቅር አጥብቀን እንከታተለን። ፍቅር ከሌለን የአካል አንድነቱ ምን ትርጉም ይሰጠናል (1ኛ ቆሮንቶስ 131-13)። በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ትምክሕትና ፉክክር ቤተክርስቲያንን መከፋፈል ትልቅ ኃጢአት ከመሆኑም በላይ ፍርድንና ቅጣትንም ስለሚያመጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። (ኤፌሶን 14)

*    ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት   

ይህ የቤተክርስቲያን መለያ ባህርይ ለብዙዎቻችን የሚሰጠው ትርጉም ቀላል ሊሆን ይችላል። ሆኖም ውድና ከባድ አባባል ነው። እግዚአብሔር “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ይለናል፤ መላእክትም “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ” ብለው ይጠሩታል። (1ኛ ጴጥሮስ 115-16፤ ኢሳይያስ 62) በቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉት የእግዚአብሔር ልጆች በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የጸደቁና በደሙ የታጠቡ፣ በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሱና ለቅዱሳን አገልግሎት የተለዩ ናቸው። የዘመናችን ቤተክርስቲያን በቅድስና ጉድለት የሚመላለሱ ሰዎችን ተሸክማ መጓዝ አይበጃትም። (1ኛ ቆሮንቶስ 69-10)

በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት በማገልገል ረጅም ልምድ ያላቸው ቢል ዋልድሮፕ የተባሉ ሰው በዚህ ዘመን ስላለችው የአሜሪካ ቤተክርስቲያን ምስክርነት ሲሰጡ በብዙ መልኳ ቅድስና ከጐደላት ከቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ጋር ትመሳሰላለች ብለዋል። “በጋብቻ ተበላሽታለች፤ በአኗኗርም ማቴሪያሊስት ሆናለች፤ ለምሳሌ ዛሬ በአሜሪካ አንድ ክርስቲያን ለቤተክርስቲያንና ለበጐ አድራጊ ድርጅቶች የሚሰጠው ከገቢው ውስጥ በአማካይ ሁለት በመቶ እንኳ አይሞላም፣” ይህ ምን ያህል ሰዎች ቁሳዊ ነገሮችን እንደሚወዱ ያመለክታል ብለዋል።  

መንፈስ ቅዱስ ለቤተክርስቲያን የተሰጠበት ዋና ምክንያት አማኞችን በመቀደስ ለእግዚአብሔር የተለዩ ሕዝቦች ለማድረግና ለአገልጋዮች ስጦታና ኃይል ለመስጠት ነው። (የሐዋርያት ሥራ 18፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 15) ቤተክርስቲያን የቅዱሳን ኅብረት እንጂ በኃጢአት የሚመላለሱ ክርስቲያኖች መሰብሰቢያ አይደለችም። ለአንዳንዶች እንደሚመስላቸው ቅድስናም ሃሳባዊና የማይታይ ነገር ሳይሆን በክርስቶስ ክቡር ደም በተቀደሱ ክርስቲያኖች ሕይወትና በዕለታዊ ኑሮአቸው የሚንጸባረቅ ውበት ነው። በመድረክ ላይ ስለ ቅድስና በመናገራቸው የሚረጋገጥ አይደለም። ቅዱስ ሰው ቅድስናን ያንጸባርቃል፤ መዓዛው ሊሸትት፣ ጣዕሙ ሊቀመስ ይችላል። የክርስቲያኖች የቅድስና ሕይወትም የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ማስረጃ ነው።

እግዚአብሔር አማኞችን “የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ” ብሎ ሲጠራን ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ “በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክሱ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” ይለናል (1ኛ ጴጥሮስ 29፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 71)። ክርስቶስን ከመከተላችን በፊት ሴሰኞች፣ አመንዝሮች፣ ሌቦች፣ ሰካራሞች፣ ተሰዳቢዎች፣ ነጣቂዎች፣ አድመኞች፣ ምቀኞች እንደነበርን መመላለስ አንችልም። ጳውሎስ “አገልግሎታችን እንዳይነቀፍ በአንዳች ነገር ማሰናከያ ከቶ አንሰጥም” እንዳለው በቅድስና ጉድለት ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን እንቅፋት መሆን የለብንም።

ዛሬም በቤተክርስቲያን ውስጥ ዕለት ዕለት ተጨባጭ በሆኑ የቅድስና ችግሮች ላይ መጸለይ፣ ትምህርት መስጠት፣ መምከር፣ መገሠጽና የእግዚአብሔር ቅጣት እንዳለ ማሳየት ቤተክርስቲያንን በዓለም ላይ ብርሃኗን እንድታበራ ይረዳታል።

*   ቤተክርስቲያን ዓለም አቀፋዊትና ዘላለማዊት ናት

ለአንዳንድ የቤተክርስቲያን ተቺዎች ቤተክርስቲያን የውጪ ኃይላት መሣሪያ ትመስላለች። ሌሎች ነቃፊዎች ደግሞ ቤተክርስቲያን የአሮጊቶች መሰብሰቢያ ናት ብለው ያስባሉ። ቤተክርስቲያን እንደ ማንኛውም ምድራዊ ድርጅት የአሠራር መዋቅር ብቻ እንደሆነች የሚቆጥሩም አሉ። ሁሉም ግን የተሳሳቱ አመለካከቶች ናቸው። ቤተክርስቲያን እነዚህ ነቃፊዎች እንደሚተቹዋት አይደለችም። በእውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ውስጥ የዘርና የወገን ልዩነት የለም። የልዩነት ግድግዳ በክርስቶስ ደም ስለ ፈረሰ ቤተክርስቲያን ከወገን ሁሉ፣ ከዘርም ሁሉ የተጠሩ አማኞች አካል ናት።

ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ሕዝቦች ሁሉ ለማዳን ስለመጣ በቤተክርስቲያን ውስጥም ያሉ አማኞች ያለ ምንም የዕድሜ ገደብ፣ ያለ ምንም የጾታ ልዩነት፣ ያለ አንዳች የትውልድ ሐረግና የዘር ልዩነት፣ ያለ ምንም የመብት ልዩነት በእኩልነት ይመላለሳሉ። በክርስቶስ “የግሪክ ሰው፣ አይሁዳዊም፣ የተገረዘም፣ ያልተገረዘም፣ አረማዊም፣ አስኩቴስም፣ ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፣ በሁሉም ነው።” (ገላትያ 311)

እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ከማንም ቡድን፣ ባሕል፣ መንግሥት፣ ድርጅት ጋር የተለየ ወገናዊነትን አታሳይም፤ ለማንም አታደላም። ድንበሯም በተባበሩት መንግሥታት፣ በአፍሪካ አህጉር፣ በኢትዮጵያ ክልሎች ወይም በየቀበሌያችን የተገደበ አይደለም። ቤተክርስቲያን ዘላለማዊትና ዓለም አቀፋዊት ስለሆነች አባላቶቿ ለደህንነታቸው ሲሉ ከማንም ሃይማኖታዊ ክፍል ጋር ያልተቆራኙ ለሁሉም በሆነው በአንዱ በክርስቶስ ኢየሱስ ሁሉም አንድ የሆኑበት ናት። የእውነተኛ ቤተ ክርስቲያን አባላት መዝገብም በምድር ላይ ሳይሆን በመንግሥተ ሰማያት በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ በመሆኑ ዛሬ የኢየሱስን ጌትነት በማመን አንድ አካል የሆንነው ሁላችን ዜግነታችን አንድ ነው።

በየዘመናቱ የሚነሱ የቤተክርስቲያን ተቃዋሚዎች ቤተክርስቲያንን በቋንቋ፣ በወገንና በሃብት ልዩነት በጾታ ለመለያየትና ለመከፋፈል ያደረጉት ጥረት ሊሳካላቸው ያልተቻለው ለዚሁ ነው። ቤተ ክርስቲያን የአዛውንትና የድሆች ብቻ አይደለችም። የፈረንጆችም ብቻ አይደለችም። በአገራችን እንደምናስተውለው አንዳንዶች አንድን ቤተክርስቲያን ጥንታዊ ሌላውን “መጤ” በማለት እንደሚከፋፍሉትም አይደለችም። ቤተክርስቲያን አስቀድሞ በእግዚአብሔር ዕቅድና ዓላማ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተመሠረተች ናት። እውነተኛዋን ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር በስተቀር ማንም አላቋቋማትም። የገሃነም ደጆች የማይቋቋሟት፣ ዘላለማዊት፣ ሰማያዊትና ጥንታዊት አድርጐ የፈጠራት እግዚአብሔር ነው። (ማቴ. 1618)

ስለዚህ ቤተክርስቲያን በመካከልዋ የወገንና የዘር ልዩነቶችን ማሳየትና ማስተናገድ ፈጽሞ አይገባትም። በኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ አምነው መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ የእግዚአብሔር ልጆች በሙሉ በክርስቶስ አንድ ናቸው። የጥንቶቹ ሐዋርያትና ነቢያት፣ የአሁኖቹ አማኞችና አገልጋዮች ወደ ፊትም በክርስቶስ አምነው መዳንን የሚያገኙ አማኞች ሁሉ ያለ ልዩነት አንድ ናቸው። (ኤፌሶን 220፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 311፤ 1ኛ ጴጥሮስ 25)

*    ቤተክርስቲያን በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጸች ናት (ማቴ417፤ የሐዋ.ሥ238፤ ሮሜ 51፣ 41-6፣ 321-24)

የዘመናችን ቤተክርስቲያን ከመቸውም ይልቅ ራሳቸውን ነቢያትና ሐዋርያት ነን የሚሉ አሳቾች የሚነሱባት ሆናለች። በቅርቡ በአገራችን ከተከሰቱት ተጨባጭ ምሳሌዎች መካከል አንዳንድ “መንፈስ ነን” የሚሉ ወገኖች የቤተ ክርስቲያንን ህልውና በመቃወም ራሳቸውን “እውነተኛ” ነቢያትና ደቀ መዝሙር አድርገው ሾመዋል። ለቤተክርስቲያን የማይታዘዙና ህልውናዋን የማያምኑ ናቸው፤ ከቤተክርስቲያን ኃላፊነትና ፈቃድ ውጪ በስመ ሐዋርያነትና ደቀ መዝሙርነት ዟሪዎችና አመጸኞች በመሆን በዚህም የእግዚአብሔርን ስም አሰዳቢዎች መሆናቸውን እንኳን አይገነዘቡም።

ወጣቶች የክርስትና ሕይወታቸውን እንደ እግዚአብሔር ቃል ለወላጆቻቸው ማስመስከርና መታዘዝ ሲገባቸው “ለወንጌል ሲል አባቱን፣ እናቱን፣ ወንድሞቹንና እህቶቹን፣ ቤቱንና ንብረቱን ያልተወ የእግዚአብሔር ሊሆን አይችልም” ይላል እያሉ ለገዛ ፍላጐታቸው ቃሉን ሲያጣምሙ አያፍሩም። “ነቢያት መቸ ቤተ ክርስቲያን አቋቋሙ? ደቀ መዛሙርትስ መቸ በቤታቸው እያደሩ ወንጌልን ሰበኩ?” እያሉ ራሳቸው ስተው እያሳቱ ስለሆነ ቤተ ክርስቲያን በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ እንዴት እንደ ታነጸች ማስተማር ተገቢ ነው።

ሌሎችም የእግዚአብሔርን ልጆች ቋንቋ ኰርጀው ራሳቸውን እውነተኛ ሐዋርያት በማስመሰል ቤተክርስቲያንንና መንጋውን ለማመሰቃቀል ጥረት እያደረጉ ናቸው። በቅርቡ አንድ ሰው ወደ ቤተክርስቲያን ሾልኰ በመግባት የራሱን ተኩላነት ክዶ ክርስቶስ በደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያን ስም ለማጥፋት መሞከሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ይህም ድርጊት አብያተ ክርስቲያናት ራሳቸውን ነቢያትና ሐዋርያት ነን ከሚሉ አሳቾች እንዲጠብቁ የማሳሰቢያ ደወል ነው። ለመንጋውና ለራሳችንም እንድንጠነቀቅ ጥሩ ትምህርት ሊሆነን ይገባል። (የሐዋርያት ሥራ 2020)

በዮሐንስ ራእይ ለትያጥሮን ቤተክርስቲያን እንደ ተጻፈው “ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣኦት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያቺን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ” እንዳንባል መንቃት አለብን፤ ይልቁንም እንደ ኤፌሶን ቤተክርስቲያን “ሐዋርያት ሳይሆኑ ሐዋርያት ነን የሚሉትን መርምረን ሐሰተኞች እንደሆኑ” መለየት ይጠበቅብናል። (ራእይ 22፣20)

ቤተክርስቲያን በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጸች ናት ሲባል በሐዋርያት እምነት ላይ የተመሠረተች፣ ባስተማሩት፣ በሰበኩትና በጻፉት መጽሐፍት ላይ ታነጸች ማለት እንጂ ዛሬ በተነሱት ነቢያትና ሐዋርያት ነን ባዮች ላይ ተመሠረተች ማለት አይደለም። እውነተኛ ቤተክርስቲያን እግዚአብሔር ለነቢያትና ለሐዋርያት የሰጣትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምስክርነት ሥራ ላይ በማዋል ትታወቃለች። “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፣ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” (1ኛ ቆሮንቶስ 311) አንዲት ቤተክርስቲያን እውነተኛ ልትባል የምትችለው የቤተክርስቲያን የእምነት አቋም፣ መሠረታዊ የደህንነት ትምህርቷና ሥነ ሥርዓቷን በተሟላው የእግዚአብሔር ቃል ላይ ከመሠረተች ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ የሆነ የእምነት አቋም ስህተት ነው።

እነዚህን አራቱን ዋና ዋና የቤተክርስቲያን መለያ ባህርይ ዘወትር ማሰብ አለብን። አንዳንዶች እንደሚያደርጉት ቤተክርስቲያን አንድ አካል መሆኗን እየተናገሩ ሌሎችን መናቅና መንከስ ተገቢ አይደለም። (ገላትያ 514-15) ሌሎችም ብዙ ግልጽና ድብቅ ኃጢአቶችን እየፈጸሙ ቅድስናቸውን አለመጠበቃቸው ለቤተክርስቲያን ነቀርሣ በመሆኑ ንስሃ መግባት አለባቸው። አንዳንዶችም ቤተክርስቲያንን በወገንና በዘር ከፋፍለው የወገን አገልጋዮችና መጥፎ ምሳሌ ሆነዋልና ሊስተካከሉ ይገባል። አንዳንዶች ደግሞ የሐዋርያትን ቃል ማቃለል ይፈልጋሉና ሊታረሙ ያስፈልጋል፤ “ከተጻፈው አትለፍ” ይላልና። (1ኛ ቆሮንቶስ 46) ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት፤ ቤተክርስቲያን ቅድስት ናት፤ ቤተክርስቲያን ዘላለማዊት ናት፤ ቤተክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት።

ከሕይወት መጽሔት፣ ቁጥር 24/1988 ዓ.ም./ገጽ 4-5። ጽሑፉ በመጠኑ ታርሟል። ጥቅምት 6/2011 ዓ.ም. እንደገና ታተመ [October 16/2018]

የውይይት ጥያቄዎች

  1. አንድነት እንዳይኖር የሚያደርጉ ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ምንድናቸው?
  2. በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሦስት ዓይነት ሰዎችን ጥቀስ።
  3. አራት የቤተክርስቲያን መለያ ምልክቶች ምንና ምንድናቸው?
  4. ለቤተክርስቲያናት የተሰጠውን የአምልኰና የጸጋ ስጦታዎችን አጠቃቀም ዘርዝር።
  5. “መንፈስ ነን” የሚሉ ሰዎችን እንዴት መለየት ይቻላል?
  6. የጥንት ነቢያትና ሐዋርያት ከዘመኑ ነቢያትና ሐዋርያት የሚለዩበትን አንድ ነጥብ ጥቀስ።
  7. ስለ ቤተክርስቲያን የሚሰሙ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ዘርዝር፤ ልኩ አመለካከት የቱ ነው?
  8. “ፍርድና ቅጣትን” የሚያመጣ ምንድነው?