እግዚአብሔር ቃል ላይ ያልተደገፈ ልምምድ አደገኛ ነው

በመለሰ ወጉ

Mwogu9በኢየሱስ ስም የሚሰበኩት ስብከቶች ትክክለኛነታቸውን የመመርመርና የመጠየቅ እንዲሁም አንዳንድ እንግዳ ትምህርትና ልምምዶችን የሚያስተምሩ አስተማሪዎች ቢኖሩ ትምህርታቸውን የመቃወምና የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዳይደናገር የማስጠንቀቅ ክርስቲያናዊ ግዴታ አለብን። ሰዎችን አስደስተን እግዚአብሔርን ቅር ከምናሰኝ፣ ሰዎችን አሳዝነን እግዚአብሔርን ደስብናሰኝ ይሻለናል። ጳውሎስ ሌላው ቀርቶ ስም እየጠራ የሚቃወማቸው ሰዎች ነበሩ። “የእነርሱ ንግግር እንደማይድን ቁስል ይቦረቡራል፣ ከእነርሱም መካከል ሄምኔዎስና ፊሊጦስ ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች የሙታን ትንሳኤ ገና ድሮ ሆኖአል እያሉ በመከራከር ከእውነት መንገድ ወጥተዋል፣ የአንዳንዶችንም ሰዎች እምነት ያናውጣሉ” [2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡17-18]። በሌላ ሥፍራ ደግሞ “አንዳንድ ሰዎች ህሊናቸውን በመጣላቸው እምነታቸውን አጥፍተዋል። ከእነርሱ መካከል ሄምኔዎስና እስክንድር ይገኛሉ፤ እነርሱ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ከመናገር መቆጠብ እንዲማሩ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው ናቸው” ይላል [1ኛጢሞቴዎስ 1፡19-20]። ተወዳጁ ዮሐንስም እንኳ፣ ዲዮጥራጢስ የሐዋርያትን ትምህርት በመቃወሙ እንደ ወቀሰው እናነባለን [3ኛ ዮሐንስ 9-10]። መጽሐፍ ቅዱስ የሚመክረን አከራካሪ በሆኑት ነጥቦች ላይ እንዳንወያይ ሳይሆን፣ ውይይታችን በእውነትና በፍቅር እንዲሆን ነው [ኤፌሶን 4፡15]።

“ጌታ የቀባውን አትንካ” በማለት ለራሳቸው መከላከያ የሚያበጁ አሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሁሉን መመርመር እንዳለብን ይመክረናል [ዘዳግም 13፡1-5]። በነቢይነቱ የማይጠራጠር “በእግዚአብሔር ሕዝብ አልመረመርም” አይልም። መጽሐፍ ቅዱስም “በዓለም ላይ ብዙ ሐሰተኞች ነቢያት ስለ ተነሱ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፣ ይልቅስ መንፈሶች የእግዚአብሔር መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መርምሩ” [1ኛ ዮሐንስ 4፡1] ይለናል። እንግዲህ መታረም ያለባቸው ትምህርቶችና ልምምዶች እንዳሉ እያወቅን በፍርሃት ዝም ማለታችን ለምን ይሆን? ከላይ እንደ ገለጽነው ሌላ ነገር ሳይሆን “የመንፈስ ቅዱስ ተቃዋሚ” የሚል ስም ይሰጠኛል ብለን በመፍራት ብቻ ነው። “በእናንተ ላይ እንዳይፈረድባችሁ በማንም ሰው ላይ አትፍረዱ” የሚለው ቃል ምን ማለት ነው? [ማቴዎስ 7፡1] ትምህርታቸው ምንም ያህል ከመስመር የወጣ ቢሆንም “የተሳሳተ ትምህርታቸውን ያስፋፉ፣ ዝም በሉአቸው” ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይሄ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ ኤሊማስን “አንተ የዲያብሎስ ልጅ፣ የእውነት ሁሉ ጠላት፣ ማታለልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፣ ቀጥተኛውን የእግዚአብሔርን መንገድ ማጣመም አትተውምን? አሁንም እነሆ የእግዚአብሔር እጅ ይመታሃል፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ ለጥቂት ጊዜም የፀሐይን ብርሃን አታይም” ባላለውም ነበር [የሐዋ. ሥራ 13፡10-11]።

የእግዚአብሔርን ቃል በአግባቡ እንጠቀም, ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል በማስተማር በሥራው እንደማይነቀፍ ሠራተኛ ሆነህ፣ ፈተናን ማለፍህ በእግዚአብሔር ፊት የተረጋገጠ እንዲሆንልህ ትጋ” ሲል ይመክረዋል [2ኛ ጢሞቴዎስ 2፡15]። የእግዚአብሔርን ቃል በሚያጣምሙ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ክፉ ነገር ሐዋርያው ጴጥሮስ ሲገልጽ “በመልእክቶቹ ውስጥ አንዳንድ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጎደላቸው ወላዋዮች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደሚያጣምሙ፣ እነዚህንም ነገሮች ያጣምማሉ፤ ይህንንም በማድረጋቸው ይጠፋሉ” ይላል [2ኛ ጴጥሮስ 3፡16]። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ አስቸጋሪ የሆኑትን ሐሳቦች ለመረዳት ቤተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱስን የሚተረጉሙበት ዘዴ ወይንም ሳይንስ አዘጋጅተዋል። ይህንንም ሳይንስ “ኸርመኑቲክስ” ወይንም “የአተረጓጎም መመሪያ” ብለውታል። ይህን “የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም መመሪያ” በዓለም ዙሪያ ያሉ እውነተኛ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ይጠቀሙበታል። ለእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፣ ክርስቲያኖች ሁሉ የሚስማሙበት አንድ ዓይነት ትርጉም ይኖራቸዋል ብሎ መገመት ስህተት ነው፤ ይሁን እንጂ በዋና ዋና መሠረታዊ እምነቶችና ትምህርቶች ላይ ግን ይስማማሉ።

የኸርመኑቲክስን ሕግ ሳይከተሉ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ያለአግባብ እየቦጨቁ በመውሰድ “ጌታ የሰጠኝ ቃል” በማለት የሚጠቀሙበት አንዳንድ ሰዎች አሉ። አንድ ጊዜ በቴሌቪዥን በሚተላለፍ መንፈሳዊ ፕሮግራም ላይ እንዲሳተፍ የተጋበዘ አንድ ሰው እንዲህ አለ፤ “አገልግሎቴ የተመሠረተው በተሰጠኝ “የሕይወቴ ጥቅስ” ላይ ነው፤ ጥቅሱም የማቴዎስ ወንጌል 19፣29 “ለእግዚአብሔር ግን ሁሉ ይቻለዋል” የሚል ሲሆን የሕይወቴ ጥቅስ ብዬ ይህን የተቀበልኩት የተወለድኩት በ1929 ዓ.ም. ስለሆነ ነው” አለ።

በቴሌቪዥን ይተላለፍ የነበረውን መንፈሳዊ ፕሮግራም ይመራ የነበረውም ሰው “እስቲ የእኔንም የሕይወት ጥቅስ ልመልከት” በማለት የተወለደው በ1934 ዓ.ም. ስለሆነ የማቴዎስ ወንጌል 19፣34ን መፈለግ ጀመረ። ይሁን እንጂ ይሄ ምዕራፍ 34 ቁጥር እንደሌለው ተመለከተ። ፍለጋው በዚህ አላቆመም። እያገላበጠ መጽሐፍ ቅዱሱን ሲመለከት ሉቃስ 19፣34ን አገኘ፤ ጥቅሱም “ጌታ ስለሚያስፈልገው ነው” የሚል ስለነበር ደስ ብሎት “ጌታ እኔን ይፈልገኛል፣ በጣም ድንቅ ቃል ነው፣ ከዚህ በፊት የሕይወቴ ጥቅስ የምለው አልነበረኝም፣ አሁን ግን ጌታ ሰጠኝ፣ አመሰግንሃለሁ ሃሌ ሉያ!” ብሎ ጮኸ። የዚህ ሰው ሚስት ግን ቀጥላ፣ “ይህን ጥቅስ የሕይወቴ ጥቅስ ብለህ መጠቀም አትችልም፣ ምክንያቱም ይህ ጥቅስ የሚናገረው ስለ ውርንጫዋ አህያ ነው” አለችው። በዚህ ዓይነት “ጌታ ቃል ሰጠኝ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስን ያለአግባብ በመጠቀም፣ ከሚለው ውጪ እነርሱ እንደሚፈልጉት ትርጉም በመስጠት ራሳቸው ተሳስተው ሌሎችን የሚያሳስቱ አሉ።

ሌላ ሁላችንም የምናውቀው አንድ ታሪክ አለ። በሕይወቱ ከፍተኛ ውሳኔ ለማድረግ የተዘጋጀ አንድ ሰው “ጌታ ሆይ! ውሳኔ ለማድረግ እንዲረዳኝ ቃልህን ስጠኝ” ብሎ ከጸለየ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ከፍቶ ዓይኑን ጨፍኖ ጣቱን አሳረፈ። ጣቱ ያረፈው እንዳጋጣሚ ማቴዎስ 27፣5 ላይ ነበር። ቃሉም የሚለው “ሄዶም ታንቆ ሞተ” የሚል ነበር። ይሄ ጥቅስ “ምንም እኔን አልረዳኝም” ብሎ እንደገና መጽሐፍ ቅዱሱን ገለጥ አድርጎ ጣቱን በአንድ ሥፍራ ላይ አሁንም አሳረፈ። ጣቱ ያረፈበት ሥፍራ ሉቃስ 10፣37 ላይ ነበርና፣ “እንግዲያውስ ሂድ፣ አንተም እንዲሁ አድርግ” የሚለውን ቃል አነበበ። ተስፋ ሳይቆርጥ ለሦስተኛ ጊዜ እንደገና እንደተለመደው ገለጥ ቢያደርግ ያነበበው ቃል “ለማድረግ ያሰብከውን ቶሎ ብለህ አድርግ” የሚል ነበር። በዚህ ዓይነት ዘዴ የእግዚአብሔርን ቃል መጠቀም ካልጠበቅነው ዓይነት ስህተት ላይ ስለሚጥለን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል።

ልምምዳችን በእግዚአብሔር ቃል መመዘን አለበት

የግል መንፈሳዊ ልምምዳችን መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል መሆን አለመሆኑን የምንለካበት ሚዛን አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል ከስህተት ሁሉ ነጻ ስለሆነ የሰው ሚዛን ወይንም መለኪያ አያስፈልገውም። የእኛ የሰዎች ልምምድ ግን ብዙ ጊዜ የተሳሳተ ስለሚሆን፣ በጥንቃቄ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ትክክለኛነቱ መመዘን አለበት። ልምምዳችን ምንም ያህል አስደናቂ ቢሆን እንደ እግዚአብሔር ቃል ካልሆነ ወይንም የእግዚአብሔርን ቃል የሚቃረን ከሆነ እውነት አይደለም። አንዲት ሴት ውሻዋ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በልዩ ቋንቋ ማመስገን እንደ ቻለ መሰከረች። ከላይ የሰማነውን ዓይነት ተዓምር እግዚአብሔር ማድረግ ቢፈልግ አይችልም ማለታችን ሳይሆን ጥያቄያችን በእርግጥ እግዚአብሔር ያደርጋል ወይ? የሚል ነው። አንዳንዶች ይህን ዓይነት ምስክርነት የሚሰጡበት ምክንያት በሌሎች ዘንድ እግዚአብሔር በልዩ መንገድ የሚጠቀምባቸው ብርቱዎች መስለው ለመታየት በመፈለግ ይመስለናል። አንድ ጊዜ አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ የካቶሊክ ቄስ ሲመሰክር “መቁጠሪያዬን ይዤ እየቆጠርኩ ስጸልይ ማሪያም በቋንቋ የመናገር ስጦታ ሰጠችኝ” አለ። ስብሰባውን ይመራ የነበረው የቤተ ክርስቲያኒቱ መጋቢ ተነስቶ “እንዴት ዓይነት አስደናቂ ምስክርነት ነው! እግዚአብሔር እኛ ልክ ነው ብለን በምንለው መመሪያ ሐሳብ የማይታሠርና የማይመራ መሆኑን ስታዩ ደስ አይላችሁም? አንዳንድ ሰዎች የወንድማችንን ምስክርነት ሲሰሙ ከእነርሱ ሐሳብ ጋር ስለማይስማማ ብቻ ምስክርነቱን አይቀበሉትም ይሆናል። በመንፈስ ቅዱስ መሞላታችን እንጂ እንዴት እንደተሞላን ማወቁ ይህን ያህል አስፈላጊ አይደለም” አለ። ይህን ሕዝቡ ሲሰማ በደስታ ተሞልቶ አጨበጨበ። መንፈስ ቅዱስን ሊሰጥ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ያወቁት አይመስለንም። ለዚህ ይሆናል ከዚያ ሕዝብ መካከል አንድም ሰው “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” የሚል ጥያቄ ያልጠየቀው። ልምምዳቸው የእግዚአብሔርን ቃል ቢቃረንም ይህን ያህል ግድ ያላቸው አይመስለንም።

የግል “ልምምዳችን” ከእግዚአብሔር ቃል በላይ ወይንም እምነታችን የሚታነጽበት መሠረት መሆን የለበትም። ልምምዳችን በቃሉ ላይ የተመሠረተ እንጂ በሚለዋወጠው ስሜታችን ላይ መሆን የለበትም። እምነታችን የተገነባው በእግዚአብሔር ቃል ባልተደገፈ ልምምድ ላይ ከሆነ ብዙ የስህተት ትምህርቶች መፈጠራቸው ግልጽ ነው። አንድ ጊዜ አንድ ክርስቲያን ፎቶግራፍ አንሺ ከአንድ የክርስቲያን ጋዜጣ ላይ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ማስታወቂያና እንዲሁም ልምምዱን አወጣ፤ “አንድ ማታ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ላይ በውስጤ አንድ መንፈስ ያስጨንቀኝ ነበር። ሂድና ፀሐይ ስትወጣ ፎቶግራፍ አንሳ የሚል ጥሪ በውስጤ ይሰማኝ ጀመር። ከዚያም ከአንድ ወንዝ አጠገብ ካሜራዬን አዘጋጅቼ የፀሐይዋን መውጣት መጠባበቅ ጀመርኩ። በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር ቅርበት ተሰማኝ፤ ልቤም በልዩ ሰላም ተሞላ። ፀሐይዋ ልክ መውጣት ስትጀምር ካሜራዬን አስተካክዬ ሳነሳ እጁን ዘርግቶ ሲባርክ በውሃ ላይ እንደሚታየው ዓይነት ጥላ ይታየኝ ነበር። ይሄኛው ግን ከማንኛቸውም ዓይነት ጥላዎች ፍጹም የሆነና የተለየ ነበር። እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል መልኩን አይቼ ከእናንተ ጋር ያየሁትን እንዳካፍላችሁ ራሱን ገለጸልኝ” አለ። የዚህ ሰው ምስክርነት እዚህ ላይ አላበቃም “$9.90 ብትልኩ ይህን መጠኑ 8 በ 10 ኢንች የሆነ የእግዚአብሔርን ምስል ፎቶግራፍ እልክላችኋለሁ” ይላል። የእግዚአብሔር ቃል “እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም” (ዮሐንስ 1፣18) እና “ማንም እኔን አይቶ መኖር አይችልም” (ዘጸአት 33፣20) ቢልም ይህ ሰው የሚያምነውና የሚቀበለው ሰው እስካገኘ ድረስ ግድ የለውም። የሚፈልገው ፎቶግራፉን ሽጦ ገንዘብ ማግኘቱን ብቻ ነው። እንደነዚህ ዓይነቶቹን ነው ጳውሎስ “እንዲህ ያሉት ሰዎች ሃይማኖት የሀብት ማግኛ ዘዴ መስሎ ይታያቸዋል” ያላቸው (1 ጢሞ. 6፣5)።

በልምምዳቸው ላይ እምነታቸውን የሚመሠርቱ ሰዎች አልፎ አልፎ ሲቸገሩ ይታያሉ። መጽሐፍ ቅዱስን እናምናለን፣ የእግዚአብሔርን ቃል መቃረን አንፈልግም ይላሉ፤ በሌላ በኩል ግን ልምምዳቸውን ከእግዚአብሔር ቃል እኩል አድርገው ለመያዝ ሲፈልጉ ይታያሉ። “በልምምድና” በእግዚአብሔር ቃል መካከል የሚፈጠረውን ግጭት ለማስታረቅ ቻርለስ ፋራ የተባለው ሰው አንድ አስታራቂ ሐሳብ ወይንም ትርጉም አመጣ። አንደኛው “ሎጎስ” ሁለተኛው ደግሞ “ሬማ” የሚል። በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ሲያስረዳ “ሎጎስ የሚለው ቃል ታሪካዊ የሆነው ቃል ሲሆን “ሬማ” ደግሞ አማኞች በግል ሕይወታቸው ሲለማመዱት ነው። ሎጎስ ወደ ሬማነት የሚለወጠው አንባቢው ሲነካው ብቻ ነው፤ ሎጎስ ሁልጊዜ ሬማ ወይንም ለአንባቢው የእግዚአብሔር ቃል አይሆንም። ሎጎስ፣ ሬማ የሚሆነው አንባቢውን ሲነካ ብቻ ነው” ይላል። በዚህ ዓይነት ሎጎስ ወደ ሬማነት ካልተቀየረ የሰውን ሕይወት የመለወጥ ኃይል የለውም ይላል። ይህ ዓይነት አተረጓጎም በጣም አደገኛ ነው። በዚህ ዓይነት የእግዚአብሔር ቃል እውነተኛ ቃል መሆን የሚችለው እኛን ሲነካን ብቻ ይሆናል፣ ካልነካን ግን የእግዚአብሔር ቃል አይደለም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር መንፈስ የተሞላ መሆን አለመሆኑን ወሳኙ ሰው በሚሰማው ስሜት አይደለም። የሰዎች ልምምድ መጽሐፍ ቅዱስ ልክ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጫ መስጠት አይችልም። ሰው ቢቀበለውም ባይቀበለውም “ቅዱስ መጽሐፍ በሙሉ በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው” የሚለው ቃል አይለወጥም (2ጢሞ. 3፣16)።

እግዚአብሔር ዕውቀትን አይጠላም

የአንዳንድ ሰዎች የግል ልምምድ የእግዚአብሔርን ቃል የሚቃረን ከመሆኑም ሌላ ተራና በጣም የሚያስቅ ነው። እግዚአብሔር “አእምሮአችሁን አትጠቀሙ” ያለን ይመስላል። ጳውሎስ እግዚአብሔር በሰጣቸው አእምሮ በሚገባ ስለማይጠቀሙ አንዳንድ ሰዎች ሲጽፍ፣ “በትክክለኛ ዕውቀት አለመሆኑ ነው እንጂ እነርሱ ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ ቅንዓት እንዳላቸው እኔ ራሴ እመሰክርላቸዋለሁ” ይላል (ሮሜ 10፣2)። እዚህ ላይ መንፈሳዊ ቅንዓት ያለ ዕውቀት በቂ እንዳልሆነ ጳውሎስ ይገልጻል። ስለሆነም ከአእምሮ ውጪ በሆነ ልምምድ እንድናልፍ አይፈልግም። አእምሮን መጠቀም ባያስፈልግ ኖሮ “አእምሮአችሁ ታድሶ ሕይወታችሁ ይለወጥ” (ሮሜ 12፣2) እንዲሁም “አእምሮአችሁም በመንፈስ ይታደስ” (ኤፌሶን 4፣23) ባላለም ነበር። በጣም አስቸጋሪ በሆነው በመንፈሳዊ ነገር ቀርቶ በዕለታዊ ነገሮች ላይ እንኳን መቶ በመቶ መስማማት አይቻልም። ስለዚህ እኛ ከምናምነውና ከተቀበልነው እምነት ውጪ የሆነ ነገር ስንስማ አንበሳጭ፣ አንቆጣም። መንፈሳዊ የሆነውን ነገር የምንመዝንበት አንድ ሚዛን አለን። ያም የእግዚአብሔር ቃል ነው። በእግዚአብሔር ቃል መዝነን “ገለባ” ከሆነብን መጣል “ፍሬ” ያለው ከሆነ ደግሞ መቀበል መብታችን ነው። ማንም “ይህን ካልዋጣችሁ” ብሎ ጉሮሮአችን ውስጥ በግድ መክተት የሚችል የለም። በዚህ ትምህርት ውስጥ የቀረቡትን ሐሳቦች በእግዚአብሔር ቃል መዝነን ልክ ሆነው ካላገኘናቸው ላለመቀበል መብታችን ነው። በሌላ በኩል ግን እኛ ባንቀበለው ሌሎች የሚቀበሉት ሊኖሩ ይችላሉና “ለምን ይሄ ነገር ተነካ” በማለት የሌሎችን የመማር ዕድል ላለመንካት መጠንቀቅ እንዳለብን አንርሳ።

ከእኛ ትንሽ ለየት ያለ ሐሳብ በማቅረባቸው እንደ ጠላት ወይንም “እንደ መንፈስ ቅዱስ ተቃዋሚዎች” የማይታዩ መሆናቸውን ሲያውቁ፣ ያለ ፍርሃት የሚሰማቸውን ለመናገርና ለመጻፍ ብዙዎች ድፍረት ያገኛሉ። ስለዚህ እኛ ከምናምነውና ከተቀበልነው ውጪ የተለየ ሐሳብ ኖሮት ሐሳቡን ለመግለጽ ለሚፈልግ ሰው መብቱ ነውና አንከልክለው፤ አእምሮአችንን ሰፋ አድርገን የሚለውን በጥንቃቄ እንስማ። ካልተስማማን እንተወው። ሌሎች ብዙ የምንስማማባቸው ነገሮች ይኖሩናልና በአንድ ነገር ብቻ ስላልተስማማን የተለየ አድርገን አንቁጠረው። ሆደ ሰፊዎች ለመሆን ራሳችንን እናለማምድ። በሌላ አቅጣጫ የጌታን ልጆች የሚያንጽበት ከጌታ የተቀበለው ስጦታ ይኖረዋልና በስጦታው እንገልገልበት።

ዶክተር መለሰ ወጉ የኢትዮጵያውያን የወንጌል አገልግሎት መሥራችና መሪ ናቸው። አገልግሎታቸውን ለመጎብኘት እዚህ ይመልከቱ፦ http://www.eomusa.org/ ይህ ጽሑፍ ከብርሃን መጽሔት፣ ቁጥር 29/1989 ዓ.ም.፣ ገጽ 21-23 የተወሰደ ነው።