የጸጋ ስጦታዎች ውጤታማ አሠራር እንዴት ሊሆን ይገባል?

የልምምድ አገልጋዮች ብቻ ሆነን እንዳንቀር …

በመርዕድ ለማ

በዚህ ክፍል የጸጋ ስጦታዎች አሠራር እንዴት እንደ ሆነ እናያለን። ጽሑፉ፦ መንፈሳዊ ልምምዶች፣ ሚዛናዊነት ወይስ አክራሪነት?፣ ጌታ ወይስ ስጦታው? በሚሉ ሦስት ዐበይት ክፍሎች ቀርቧል። በጽሑፉ ማጠቃለያም ፍቅር ከጸጋ ስጦታዎች ጋር ያለውን ትስስርና ተዛምዶ እንመለከታለን።

መንፈሳዊ ልምምዶች

መንፈሳዊ ልምምዶችን በሁለት መልኩ ማየት እንችላለን። የመጀመሪያው፣ ልምምዶችን ማክረር ነው። መንፈሳዊ ልምምድ በራሱ እራሱን የቻለ አገልግሎት ወይም ውጤት አይደለም። የአገልግሎት መድረኮች የተለያዩ መንፈሳዊ ልምምዶች ጎልተው ይታዩባቸዋል። ማሸብሸብ፣ እጅን ዘርግቶ መጸለይ፣ ዝግ ብሎ መናገር፣ ጮኾ መናገር፣ ወዘተ። እነኚህን የመሳሰሉ ልምምዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ቁም ነገሩና ዋነኛው ጉዳይ “በሰዎች ሕይወት ውስጥ ምን ሆነ? ተፈወሱ? በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ? ሕይወታቸው ተለወጠ? በምናስተናግደው ሕዝብ ሕይወት ውስጥ ምንድነው የሚታየው? ለውጡ፣ ፍሬው እንዴት ነው?” የሚለው ነው። አለበለዚያ የልምምድ አገልጋዮች ብቻ ሆነን እንቀራለን። የብዙዎች አገልግሎት ውጤት አልባ የሚሆነው የሰዎችን ልምምድ ስለሚኮርጁ ነው። እግዚአብሔር እያንዳንዳችንን እንዳለን ሆነን እንድናመልከውና እንድናገለግለው ይፈልጋል። እኛው በእኛነታችን ሆነን ብናገለግለው ለሰዎች ውብና ማራኪ እንሆናለን። ምክንያቱም እግዚአብሔር እኔን አንተን ወይም አንቺን የመሰለ ሌላ ሰው አልፈጠረምና።

ቀጥሎ፣ የልምምድ ተቃዋሚዎች ጉዳይ ነው። እነኚህ በጣም ወግ አጥባቂ ስለሆኑ አንድ ጊዜ የጨበጡትን ነገር እድሜ ዘመናቸውን መልቀቅ አይፈልጉም። ለልምምዱማ እነርሱም የራሳቸው ልምምድ አላቸው። ዳሩ ግን ካወቅሁት ሌላ ነገር እንዴት? ለምን? የሚል ግትርነት ያስቸግራቸዋል። መሠረታዊ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል አይለወጥ እንጂ አሠራሮችና ልምምዶችን ወጥ ይሁኑ አንበል። የጌታ ኢየሱስን የፈውስ አገልግሎት ስንመለከት እጁን ጭኖ ፈውሶአል፤ በቃል ብቻ ፈውሶአል፤ የዕውሩን ዓይን ጭቃ በመቀባት ፈውሶአል። የእግዚአብሔር ኃይል ትናንት በሠራበት መንገድ ብቻ አልነበረም በሚቀጥለው ቀን ሲሠራ የታየው። ሐዋርያው ጳውሎስም እጁን በመጫን ፈውሶአል፤ በለበሰው ጨርቅ አማካይነት ፈውሶአል። እነ ጴጥሮስ ጥላቸው እንኳ ሳይቀር ፈውሶአል። በብሉይ ኪዳን ኤልሳዕ በሞተው በሱነማዪቱ ልጅ ላይ ተዘርግቶበት ወደ ሕይወት መልሶታል። እስቲ በተለያዩ ጊዜአት እናንተም የተለማመዳችሁትን ልምምድ አስታውሱ። በዘመናችን እጅ በመጫን ሌሎች የመውደቃቸው ነገር አጠያያቂ ሆኗል። ምናልባት በኛም አገር የመንፈስ ቅዱስ መነቃቃት ሲጀምርና ለመንፈስ ቅዱስ ሙላት ስንጸልይላቸው፣ ከመንቀጥቀጥ፣ ከመጮኽም አልፈው የወደቁ ብዙዎች ናቸው። መውደቁ ብቻውን አገልግሎት መሆን አይችልም። ዳሩ ግን መንፈስ ቅዱስ በተለየ መንገድ ሲመጣ ልንወድቅ እንችላለን። የእጅ መጫን መነሻ አሳባችንን እንፈትሸው። ለመንፈሳዊ በረከት፣ ለመንፈስ ቅዱስ ሙላት፣ ለፈውስ ወይስ ሰዎችን ለመጣል? የእጅ መጫን ዓላማችን ትክክለኛ ከሆነ ምናለ ይውደቁ። እኛንም የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከጣለን እንውደቅ። በነጆን ዌስሊና ጆናታን ኤድዋርድስ አገልግሎት ብዙ ሰዎች ራሳቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ይወድቁ ነበር። ነገር ግን አሁንም ደግሜ እላለሁ፣ መውደቅ እራሱ ብቻውን አገልግሎት አይደለም። ስሚዝ ዊግልስወርዝ የሚባል ታላቅ የእምነት ሰው የታመሙ ሰዎችን የታመሙበትን ሥፍራ በቦክስ በመምታት ፈውሶአል። እሱ ይህን ስላደረገ እኛም እንድርግ ብንል ያለ ጥርጥር በወንጀል ተከሰን ፍርድ ቤት ልንቀርብ እንችላለን። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስን እናድምጠው፤ አገልግሎታችንም ይሠምራል።

ሚዛናዊነት ወይስ አክራሪነት?

ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ተሰሎንቄ 5፡19-22 ባለው ክፍል ሲናገር “መንፈስን አታጥፉ፤ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤ ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ” ይላል። በዚህ ክፍል ለሚዛናዊነት የሚረዱን አምስት ሃሳቦችን እናያለን።

  1. መንፈስን አታጥፉ፦ በብሉይ ኪዳን ለካህናት ከተሰጣቸው የአገልግሎት ድርሻ አንዱ ዘወትር በመሠዊያ ላይ እሳት እንዲነድ ማድረግ፣ እንዳይጠፋ መጠበቅ ነበር። መንፈስ ቅዱስ በእሳት ይመሰላል። ይህ እሳት የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ ከቤተክርስቲያናችንና ከግል ሕይወታችን ከጠፋ አገልግሎታችን ሁሉ ይጠፋል። ስለዚህ ዘወትር በመንፈስ ቅዱስ ጋር እንሥራ፤ በመንፈስ ቅዱስ እንመራ። በተለያዩ ችግሮች ምክንያት መንፈሱን አናዳፍነው። ይህም ሐዋርያው ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዳሳሰበው ማለት ነው። “ስለዚህ ምክንያት፣ እሳት እንደሚያቀጣጥል ሰው፣ እጆቼን በመጫኔ በአንተ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን ስጦታ እንድታነሳሳ አሳስብሃለሁ።” [2ኛ ጢሞቴዎስ 1፡6]
  2. ትንቢትን አትናቁ፦ የትንቢት አገልግሎት በሐዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን በጣም የታወቀ አገልግሎት ነው። ደግሞም ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ስጦታ ለማግኘት ፈልጉ ይላል። አንዳንድ ጊዜ በስመ ትንቢት ቤተክርስቲያን ችግር ሊገጥማት ይችላል። እውነተኞች ትንቢት ተናጋሪዎች እንደ መኖራቸው ሁሉ ሐሰተኞች ነቢያትም ይኖራሉ። ታዲያ ባንዳንድ በተሳሳተ ትንቢት ሳቢያ በሚመጣ ችግር “ከዛሬ ጀምሮ ትንቢት የሚባል ነገር አያስፈልገንም” በማለት ቤተክርስቲያን ይህንንም ጸጋ እንዳትጥለው ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
  3. ሁሉን ፈትኑ፦ መቸም የሰማነውንና ያገኘነውን ሁሉ አግበስብሶ መቀበል ጤናማ ሕይወታችንን ያውካል። ያለንበት ዓለም በብዙ ዓይነት የመናፍስት አሠራር የተሞላ ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ አለ፤ የሰይጣን መንፈስ አለ፤ የሰውም መንፈስ አለ። በምንሰማውና በምናየው ነገር አድናቆት ውስጥ ከመግባታችን በፊት ነገሩ ምን ይሆን? ብሎ የነገሩን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንሞክር። ከእግዚአብሔር ቃል ጋር እንዲሁም በውስጣችን ካለው መንፈስ ጋር እናመሳክረው።
  4. መልካሙን ያዙ፦ እግዚአብሔር እኛን ሲፈጥረን ተንቀሳቃሽ አሻንጉሊቶች አድርጎ አልሠራንም፤ የራሳችን ፈቃድ፣ ስሜትና ፍላጎት ያለን አድርጎ ነው። ደግሞም መልካሙን ከክፉው ለይተን እንድናውቅ አድርጎ አዘጋጅቶናል። እንዲሁም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ካደረገን በኋላ መንፈሱን በውስጣችን አስቀምጧል። ይህም መንፈስ የሚመራን ነው። በዚህም በእግዚአብሔር መንፈስ መሪነት መልካሙን ከክፉው ለይተን ከተረዳን፣ ክፉውን በመጣል መልካሙን በመያዝ መጽናት ይኖርብናል። “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና።” [ሮሜ 8፡14]
  5. ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ፦ እኛ የእግዚአብሔር ሰዎች ማንኛውንም ዓይነት ክፉ ነገር መጥላት ብቻ ሳይሆን ከዚያ መራቅ ግዴታችን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 12፡9 ላይ “ክፉውን ነገር ተጸየፉት” ይላል። አንድ የተጸየፍነውን ነገር በዓይናችንም እንኳ ልናየው አንፈልግም። በአእምሮአችንም ልናሰላስለው አንወድም። ክፉውን ነገር ተጸየፉት ካለ በኋላ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ ይላል። ስለዚህ ምንጊዜም ለበጎ ነገር ፈቃደኞችና ተባባሪዎች መሆን ይኖርብናል።

ጌታ ወይስ ስጦታው?

ሁላችንም ከፍተኛ ጥንቃቄ የምናደርግበት ጉዳይ እንዳለ ለማሳሰብ እወዳለሁ። ዛሬ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራበት ወቅት እንደ መሆኑ መጠን ሰዎች መንፈሳዊ ጥማታቸውን ለማርካት ከአንዱ ቤተክርስቲያን ወደ ሌላው ሲሄዱ ያታያሉ። የተጠማነው ማንን ነው? ጌታን ነው ወይስ መንፈሳዊ ነገር? የመጀመሪያው ጥማታችንና ፍላጎታችን ጌታ ይሁን፤ ያኔ እንረካለን። “ማንም የተጠማ ቢኖት ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ” አለ ጌታ [ዮሐንስ 7፡37]

ለኃጢአተኞች፣ ለበሽተኞች ለተለያዩ ነፍሳት የሚሰበከው ምንድነው? ስብከታችን የሚያተኩረው ምን ላይ ነው? በጌታ ኢየሱስ ላይ መሆን ይገባዋል። ምክንያቱም የፈውስ፣ የመገለጥ፣ የተዓምራቶችና የድንቆች ሁሉ ምንጭ እራሱ ጌታ ኢየሱስ ስለሆነ። አገልጋዮች ምዕመናንን ልባቸውም ዓይናቸውም ከእኛ ላይ ተነሥቶ በክርስቶስ ላይ እንዲያርፍ እናድርግ። ይህን ብናደርግ ታማኝነታችን ይገለጻል። እንደገናም ትሕትና ነው። ሌላ ቀርቶ አንዳንድ በሽተኞች ወደ ቤተክርስቲያን ሲመጡ ፈውስን የሚቀበሉበትን መንገድ አዘጋጅተው ይመጣሉ። እግዚአብሔር ዛሬ በመገለጥ ተናገረኝ ይላሉ። ፈውስ በመገለጥ ብቻ አይመጣም። ምናልባትም ፈውስ ከሚመጣባቸው መንገዶች አንዱ ሊሆን ይችላል። ፈውስ በእግዚአብሔር፣ በእጅ በመጫን፣ በአምልኮ ውስጥ በመሆን ይመጣል። በፈለገው መንገድ ይምጣ ነገር ግን እኛ ባዶ ሆነን ጌታን እንፈልግ። የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ጌታ ኢየሱስን ማክበር ነው። “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፤ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ሁሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤ የሚመጣውንም ይነግራችኋል፣ እርሱ ያከብረኛል፣ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል።” [ዮሐንስ 16፡14] እዚህ ላይ የምንመለከተው መንፈስ ቅዱስ ተጠሪነቱ ለራሱ ሳይሆን ለጌታ ኢየሱስ ነው። ስለዚህ ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎቶች፣ የጸጋ ስጦታዎች፣ ልምምዶቻችን ሁሉ ለጌታ ክብር መዋል አለባቸው። እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ማሳየትና መግለጥ ይኖርባቸዋል።

የጸጋ ስጦታዎችና ፍቅር

በዚህ በመጨረሻ የማጠቃለያ አሳብ ላይ የጸጋ ስጦታዎች ከፍቅር ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ዝምድና መመልከቱ ይጠቅመናል። እንደገናም ለአገልግሎታችንም ሁሉ ማሠሪያ ይሆንልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራና ስጦታዎች በሰፊው የተናገረበት ክፍል ለቆሮንቶስ ሰዎች የጻፈው የመጀመሪያው መልእክቱ ነው። በዚሁ መልእክት በ12ኛው ምዕራፍ ላይ የጸጋ ስጦታዎችን ምንነትና የስጦታዎቹ ምንጭ ማን እንደሆነ የተናገረበት ክፍል ነው። በምዕራፍ 14 ላይ ደግሞ በማህበር፣ በጉባዔ ውስጥ እንዴት መጠቀም እንደሚኖርብን የተናገረበት ክፍል ነው። ምዕራፍ 13 ስጦታዎች አመርቂና ውጤታማ መሆን የሚችሉት በፍቅር ስንጠቀምባቸው ብቻ ነው በማለት ያስረዳል፤ ምዕራፍ 13 ስለ ፍቅር በስፋት የሚናገርበት ምዕራፍ ነው። ከቁጥር 1-3 ካለፍቅር የጸጋ ስጦታዎች ጠቃሚነት እንደሌላቸው ተገልጦአል፤ ከቁጥር 4-7 ደግሞ የፍቅርን የተለያዩ መግለጫዎች እንመለከታለን። ከቁጥር 8-13 የጸጋ ስጦታዎች እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ብቻ እንደሚሠሩና እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር ጸንተው እንደሚኖሩ ገልጦ ከሦስቱም የሚበልጠው ፍቅር እንደ ሆነ ተናግሯል። ብዙውን ጊዜ በዚሁ በምዕራፍ 13 ላይ የተገለጸውን ፍቅር ሰዎች በተሳሳተ መልኩ ይጠቀሙበታል።

አንዳንዶቹ የጸጋ ስጦታንና የመንፈስ ቅዱስን አገልግሎት ላለማጉላት የፈለጉ ሰዎች፦ ፍቅር ነው እንጂ የጸጋ ስጦታ ጠቃሚ አይደለም በማለት ለጸጋ ስጦታዎች ሥፍራ እንዳይሰጡና የመንፈስ ቅዱስን እሳት ለማዳፈኛ ሲጠቀሙበት ይታያል። ይህ ትልቁ ስሕተት ነው። አንድን እውነት ሌላውን እውነት ለማጥፊያ መጠቀም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስጠይቅ ስለሆነ እንጠንቀቅ። ሌሎች ደግሞ ከመጠን ባለፈ መልኩ የጸጋ ስጦታዎችን ብቻ በመግለጥ ስጦታዎችን ካለፍቅር የሚጠቀሙና የሚያስተምሩ አሉ። እነርሱም የትም አይደርሱም። ያለፍቅር ሁሉ ከንቱ ነውና። ከቁጥር 4-7 ባለው ክፍል 15 የተለያዩ የፍቅርን ባሕርያት እንመለከታለን።

ፍቅር ይታገሳል፦ አገልጋዮች ሰዎች አገልግሎታችንን ባይረዱ ችግር ቢገጥመን በዚህም ብንፈተን በትዕግስት እግዚአብሔርን መጠበቅ ፍቅር ነው።

ፍቅር ቸርነትን ያደርጋል፦ አገልግሎታችን እኛው ለኛው መሆን የለበትም፣ ለሌሎች ሰዎች ጥቅምና መታነጽ ምክንያት መሆን አለበት። ስለዚህ ለሌሎች ቸርነት ማድረግና ርህራሄን ማሳየት ፍቅር ነው።

ፍቅር አይቀናም፦ አገልጋዮች በምናገለግለው የጸጋ አገልግሎት ወደ ቅናት ውስጥ ከገባን ጸጋችንን በተሳሳተ መንገድ ተጠቅመንበታል ማለት ነው። ስለዚህ ከቅናት ነጻ መሆን አለብን።

ፍቅር አይመካም፣ አይታበይም፦ ትምክህተኛነት እግዚአብሔርን ያለማወቅ ነው። ማንም ሰው ትምክህቱ በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን የእግዚአብሔር ቃል ያዛል። “ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፣ ኃያልም በኃይሉ አይመካ፤ ባለጠጋም በብልጥግናው አይመካ፤ ነገር ግን የሚመካው፣ ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ፤ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፣ ይላል እግዚአብሔር።” [ኤርምያስ 9፡23-24]

ፍቅር የማይገባውን አያደርግም፦ አንድ አገልጋይ በአነጋገሩ፣ በአሳቡ፣ በሚያደርገው ነገር ሁሉ ጠንቃቃና አስተዋይ ሊሆን ይገባዋል። ሰዎች በጸጋ ስጦታዎች የምናገለግላቸውን አገልግሎቶች ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ሕይወታችንንም ይከታተላሉ። ስለዚህ ጨዋና የተከበረ ጭምትና ነውር የሌለበት ከክፋትም የራቅን ልንሆን ይገባል።

ፍቅር የራሱን አይፈልግም፦ ብዙውን ጊዜ የአገልጋዮች ድካም እዚህ ላይ ነው። ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ መልኩ የተለያዩ ፈተናዎችና ችግሮች ሲገጥሙን፣ ለምን ተነካሁ? በማለት የያዝነውን አደራ መጣል የፍቅር ጉድለት ነው። አገልጋይ ሳይነካ ማገልገል ጨርሶ አይችልም። ለምን ተነካሁ? ከሚል መራራነት ነጻ ወጥተን የራሳችንን በመተው የጌታን በመፈለግ፣ ጌታን ብናገለግለው ከዕለት ዕለት እየተባረክን እንሄዳለን።

ፍቅር አይበሳጭም፦ ብስጩ አገልጋይ ገና ያላደገና ነገሮችን አርቆ ማስተዋል የተሳነው ነው። አገልጋይ ከተበሳጨ በጸጋ አያድግም። ዘወትር በቅርብ ያለውን ብቻ ስለሚያይ በርቀት ያለውን የእግዚአብሔርን አሳብ አይረዳም። ስለዚህ በሆነው ባልሆነው መበሳጨት በአንድ አገልጋይ የሚታይ የፍቅር ጉድለት ነው።

ፍቅር በደልን አይቆጥርም፦ አገልግሎታችን ከተለያዩ ሰዎች ጋር የተያያዘ ነው። በመሆኑም ከሰዎች ጋር እስከ ተያያዘ ድረስ ደግሞ ሰዎችን መጉዳትና በሰዎችም መጎዳት ሊያጋጥም ይችላል። ጎዳንም ተጎዳንም ዘወትር ይቅር ለማለትና በይቅርታ ለማስተካከል ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። ይኸን ብናደርግ የፍቅር ሰዎች ሆነናል ማለት ነው።

ፍቅር ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ አመጻ ደስ አይለውም፦ የፍቅር ሰው የሌሎች ሰዎች አገልግሎትና የመንፈሳዊ ሕይወት እድገት ያስደስተዋል። እንዲሁም ውድቀታቸውንና ችግራቸውን በራሱ እንደ ደረሰ አድርጎ ይቆጥረዋል፤ ይሰማዋል።

ፍቅር ሁሉን ይታገሳል፦ የሌሎችን ሰዎች ስሕተት ለማጋለጥ አይቸኩልም፤ ወይም ትክክለኛነቱንና ሀቀኛነቱን ለማሳየት አይጥርም። በሚቃወሙትና በሚተቹት ሰዎች ሁሉ ፊት እራሱን ይገዛል። ሁሉን ያምናል፣ የፍቅር ሰው በሚሰማውና በሚያየው ነገር ልቡ አያፈገፍግም፤ ዳሩ ግን በአምላኩ ይታመናል።

ፍቅር ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፦ በፍቅር የሚያገለግል ሰው ዛሬ በጨለማ ያለ ቢመስለውም የነገው ብርሃን እንደሚሆንለት በአምላኩ ተስፋ ያደርጋል። በሙሉ ተስፋም ይወጣል ይገባልም።

ፍቅር በሁሉ ይጸናል፦ አንድ የጌታ አገልጋይ ብዙ ሰልፍና ጦር የሚገጥመው ሰው ነው። ከወጀቡና ከማዕበሉ የተነሳ ሥፍራውን በመልቀቅ የሚሸሽ ሳይሆን በአምላኩ ተማምኖ ተደግፎ ቀጥ ብሎ የሚቆም መሆን አለበት። እንግዲያስ እውነትን በፍቅር እያገለጥን ከጌታ የተቀበልነውን አገልግሎት በፍቅር መጠቀም እንድንችል እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን።

መጋቢ መርዕድ ለማ የወንጌልን እሳት በምድራችን ለማቀጣጠል እግዚአብሔር ከተጠቀመባቸው አንጋፋ የጌታ ባሪያዎች መሃል አንዱ ናቸው። ጽሑፉ መጠነኛ እርምት ተደርጎበታል። የተወሰደው ከቀንዲል መጽሔት ቁ.10/1989 ዓ.ም. ከገጽ 15-18 ላይ ነው።