ስጦታህን እወቅ

እግዚአብሔር ስጦታ ሰጥቶኛል? ስጦታዬስ ምንድነው? የተፈጥሮ ችሎታዬን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው ማለት እችላለሁ? ስጦታ ያድጋል አያድግም? … ሌሎች ሌሎች ጥያቄዎች ይኖሩህ ይሆናል። ረጋ ብለህ እያስተዋልክ ይህንን ጽሑፍ ካነበብክ ማን ያውቃል መልስ ታገኝ ይሆናል። 

እያንዳንዱ ክርስቲያን አንድ ወይም ከዚያ የበለጠ ስጦታ አለው 

በክርስቶስ ደም በተዋጀው ቤተሰብ ውስጥ እያንዳንዱ በእግዚአብሔር ቃል የተወለደ ሕጻን ስጦታ ተቀብሏል። “ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ እያንዳንዳችሁ እያሳስበናል (1ኛጴጥ. 410)። እያንዳንዱ ክርስቲያን ስጦታውን የማወቅና የማሳደግ ኃላፊነት አለበት። ልክ እንደ ዘር ወይም አዲስ እንደ ተወለደ ሕጻን መንፈሳዊ ስጦታዎችም ከትንሹ ይጀምሩና በጥንቃቄ ከተያዙ ያድጋሉ። በፍቅርና በመንፈስ ቅዱስ በመመካት ሳናቋርጥ ከተጠቀምንባቸው ግባቸውን የሚመቱ ጠንካራ መሣሪያዎች ይሆናሉ። ስጦታውን ባሳደገ መጠን የእግዚአብሔር ባሪያ ራሱ ጠቃሚ ሰው መሆን ይጀምራል። ስጦታው ከተቀባዩ አኳኋን፣ ባሕርይና ካለፈበት ልምምድ ጋር ይስማማል። ስጦታው የወደ ፊት ኑሮውን እንኳ ሊወስን ይችላል። ምክንያቱም ስጦታዎቹ መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱ ክርስቲያን በሕይወት ዘመኑ ሊፈጽማቸው የሚገባቸውን ሥራዎች የሚያሳዩ ጠቋሚዎች ስለሆኑ ነው። ስጦታ ላንተ በግልህ የሚያስደስትህና ስሜት የሚያሳድርብህ የራስህ ስጦታ ምን ምን መሆኑን ለይተህ ስታውቅ ነው። ስጦታህን ለማወቅ ከሚረዱህ ነገሮች አራት ያህል እንጠቅሳለን። 

በተፈጥሮ ችሎታህ ጀምር፣ በዚያ ግን አትቁም 

የተፈጥሮ ችሎታና መንፈሳዊ ስጦታ አንድ ባይሆኑም እንኳ የተያያዙ ነገሮች ናቸው። እንድ ሰው እንዳለው ስጦታዎቹ “… በውስጥ የተደበቀ የተፈጥሮ ችሎታን ይጠቁማሉ”። እንግዲህ ስጦታን ለማወቅ ከሚደረጉ የመጀመሪያ እርምጃዎች አንዱ የተፈጥሮ ችሎታን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጠቀም መጀመር ነው። በዚህ ዓይነት መንገድ አንዱን ስጦታዋን ያወቀች አንዲት ሴት አውቃለሁ። ፍቃዱ ኦርጋንና ፒያኖ የመጫወት ችሎታ አለው። በአምልኰ ጊዜ፣ በወጣቶች ስብሰባና በሌሎችም ስብሰባዎች መጫወት ይወዳል። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት ሰዎች ሙዚቃውን ከመውደዳቸውም በላይ ሌላም የሚናገሩት ነገር አለ። የአምልኰ የመክፈቻ መዝሙር ሲጫወት አእምሮዬ ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል። ከዚያም መንፈሴ ለአምልኰ ይዘጋጃል። የሙዚቃውን ቃላት እከተላለሁ፤ ጌታም በዚያ ውስጥ ለልቤ ይናገራል። እንግዲህ የመንፈሳዊ ስጦታን አንድ መለኪያ በጸሎት ይመነዝሩታል። በእምነት ላይ በተመሠረተ ጽኑ ጸሎት አንጻር ያስቀምጡታል። ይኸም ጸሎት እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን እንዲሰጠን አንዴ ጠይቀነው የጠየቅነውን ነገር ለማግኘት በትዕግስት የምንጠባበቅበት ጸሎት መሆኑን የእግዚአብሔር ሰዎች ይናገራሉ። ለእግዚአብሔር አንዴ ከነገርነው ሰምቶታል ማለት ነው። ያንኑ ነገር መልሶ መላልሶ መንገሩ ጆሮን የፈጠረው ታላቅ ጌታ ጆሮ የለውም እንደ ማለት ይሆናል። 

የተፈጥሮ ችሎታን በሥራ ላይ ስናውል በውጤቱ አንድ ከተፈጥሮ ውጪ (መንፈሳዊ) የሆነ ለውጥ በሰው ላይ መምጣቱ ነው። ይህም ማለት ሰዎች ወደ ጌታ ኢየሱስ ሲሳቡ ወይም በእምነታቸው ሲታነጹ ነው። ይህ መታነጽ ያለ መንፈስ ቅዱስ አይመጣም። ሆኖም አንድ ሰው የተፈጥሮ ችሎታ ኖሮት ከዚህ ጋር የተያያዘ መንፈሳዊ ስጦታ ላይኖረው ይችላል። ለምሳሌ ስድስት ዘማሪዎች ሁሉም በሙዚቃ ችሎታቸው እኩል የሆኑ በተለያዩ ጊዜአት ይዘምራሉ። አድማጮችም በሰሙት ሙዚቃ በጣም እንደ ተደሰቱ በማድነቅ ይናገራሉ። ነገር ግን ከስድስቱ አንዱ ከተፈጥሮ ችሎታው ጋር መንፈሳዊ ስጦታም አለው። እሱ ሲዘምር የእግዚአብሔር ህልውና በአዲስ መንገድ ይከሰታል። ሰዎች ወደ ጌታ ይጠጋሉ። መንፈስ ቅዱስ በመዝሙሩ ቃላት ውስጥ ለሕይወታቸው የሚያስፈልገውን መልእክት ያስተላልፋል። ብቻ … አንድ መለኰታዊ ነገር ይፈጸማል። እኩል የተፈጥሮ ችሎታ ካላቸው ከሌሎቹ ከአምስቱ በተለየ ሁኔታ ያ አንድ ዘማሪ መንፈሳዊ ስጦታውን በሥራ ላይ እያዋለ ነው። 

አንዳንድ መንፈሳዊ ስጦታዎች “ከተሰወሩ” የተፈጥሮ ችሎታዎች ጋር የተያያዙ ናቸው። ኤልሳቤጥ የሕጻናት አስተማሪ ነች። ልጆች ትወዳለች፣ ግን በየቤታቸው እየሄደች ወላጆቻቸውን ማጽናናት አትወድም፤ እንዲያውም እንደዚህ ዓይነት ሥራ ሸክም ነው የሚመስላት። ለርሷ ከችሎታዋ ከጠባይዋም ጋር የማይጣጣም ነገር እንደሆነ ነው የምታስበው። ነገር ግን ከመንፈሳዊ የኃላፊነት ስሜት የተነሣ በየቤቱ እየሄደች ሰዎችን መጐብኘት ጀመረች። በጥቂት ጊዜ ውስጥ እግዚአብሔር ባልጠበቀችው መንገድ ሲጠቀምባት አስተዋለች። ራሷን “ከሰው ጋር የማይገጥም ባሕርይ ያለኝ” ብላ የምትጠራው ኤልሳቤጥ በያንዳንዱ ጊዜና ሁኔታ ለጊዜውና ለሁኔታው አስፈላጊ የሆኑ ቃላት ከአንደበቷ ሲወጡ አየች። ወላጆች የቤተሰባቸውን ችግር ግልጽ አድርገው ያካፍሏት ጀመር። የክርስቶስ እርዳታ አስፈላጊነት ስለተሰማት ድምጿን አሰምታ አብራቸው እንድትጸልይ ጠየቀቻቸው። ከዚህ በፊት ጌታ ኢየሱስን ከማያውቁ ቤተሰቦች ጋር መጸለይ የምትፈራው ኤልሳቤጥ አሁን ቃላቱ ከአፏ ይፈተለኩ ጀመር። ሳታስብ የምትጸልይባቸው ነገሮች አእምሮዋን መሙላት ጀመሩ። መንፈስ ቅዱስ በውስጧ ይጸልይ ነበር። ኤልሳቤጥ ከጸለየች በኋላ በብዙ እናቶች ፊት ላይ እንባ ይታይ ነበር። የክርስትና ሕይወታቸው መታደስ ለመንፈሳዊ ስጦታዋ ምስክር ነበር።

ክርስቲያን ጓደኞችህ የሚሉህን አድምጥ 

ሌሎች ከአዲስ አንጻር ያዩናል። እኛ ራሳችንን ከምናውቀው በተለየ መንገድ ያውቁናል። በግል መለኪያችን ብቻ ራሳችንን ከመዘንን ስለ ራሳችን የማናውቃቸውን ድብቅ ነገሮች ሳናስተውል እንቀራለን። የተቀበልነውን ስጦታ እንድናስተውል ሌሎች ሊረዱን ይችላሉ። ስጦታህን ለማወቅ እንዲረዱህ ጥቂት ጓደኞች ቢኖሩህ ጥሩ ነው። ጊዜ ውሰዱና እየጸለያችሁ ተነጋገሩ። ይህ አንዱ የሌላውን ስጦታ በመግለጽ እንዲተባበር ሊረዳ ይችላል። ይህ መንገድ ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በቂ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት ቢኖርበት ግቡን ይመታል። የእግዚአብሔር ሕዝብ ኅብረት በሌላም መንገድ ሊጠቅመን ይችላል። የቤተ ክርስቲያን አባሎች ወይም መሪዎች አንዳንድ ኃላፊነቶችን እንድንቀበል ወይም የተለያዩ ሥራዎችን እንድንፈጽም ሊጠይቁን ይችላሉ። የሰንበት ትምህርት እንድናስተምር ከተጠየቅን ምናልባት የማስተማር ስጦታ ኖሮን ይሆናል። በቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አገልግሎት ውስጥ ሥራ ቢሰጠን ከብዙ ስጦታዎች አንዱን ሊጠቁመን ይችላል፤ ማበረታታት፣ እርዳታን ማድረግ፣ አስተዳደርን ወይም ሌላ ስጦታን። 

አንድ ሰው ያለ መንፈሳዊ ስጦታ የማስተማርን አገልግሎት ጀምሮ ይሆናል። ሌላው ደግሞ ያለ ስጦታው በኰሚቴ ውስጥ ሊያገለግል ይችላል። ግን ምንም ያህል የሚያበረክቱት ጠቃሚ ነገር አይኖርም። አገልግሎት ቢኖረንም መንፈሳዊ ስጦታ እለን ማለት ማረጋገጫ አይሆንም። ይህ የሚያሳየን ሥራውን እንድናደርግ ዕድል እንደ ተሰጠን ብቻ ነው። ክርስቲያን በተሰጠው አገልግሎት ውስጥ ምንም መንፈሳዊ ስጦታ ካላየበት የአገልግሎቱ ጊዜ እስኪያልቅ ጠብቆ ወደ ሌላ አገልግሎት ቢዛወር ይሻላል። ስጦታን ማሳደግ ብዙ ጥረትና መውደቅና መነሳት የሚጠይቅ ሥራ ነው። ነገር ግን ሰው ከሾመን ሹመት ይልቅ እግዚአብሔር የሰጠን አገልግሎት ይበልጣል። 

በመውደቅ በመነሳት ተማር 

ስጦታህ በሌሎች ላይ ያመጣውን ለውጥ ለማስተዋል ሞክር። ምን እንደሚሰማቸው ለማወቅ ሞክር። እግዚአብሔር ያንን ችሎታ ሌሎችን ከመውደቃቸው ለማንሳት እየደጋገመ ከተጠቀመበት ምናልባት እሱ ስጦታህ ይሆናል። አንድ የቤተ ክርስቲያን መጋቢ አባሎችን በማማከር አገልግሎቱ ብዙ አይሳካለትም ነበር። ነገር ግን ጥቂት ለየት ባለ መንገድ የሰጣቸው ምክሮች በጣም ግባቸውን የመቱ ነበር። ነገሩን ለማጤን ሲሞክር እነዚህ ግባቸውን የመቱ የማማከር ጊዜዎች ሁሉ በማስተማር መልክ የቀረቡ ነበሩ። መጋቢው ስጦታው ማማከር ሳይሆን ማስተማር መሆኑን ተገነዘበ። 

ስታገለግል በሚሰጥህ እርካታ ስጦታህን ለማወቅ ሞክር 

መንፈሳዊ ስጦታህን በቤተ ክርስቲያን ክልል ብቻ አትወስነው። እግዚአብሔር የሚሰጥህ ማንኛውም የሥራ ስሜት ለመንፈሳዊ ስጦታ ፍንጭ እንደሆኑ ለማየት ሞክር። ዘነበ በእጅ የሚሠራ ነገር ማድረግ ይወዳል። መኪና መጠገን፣ የተሰባበሩ ነገሮችን ማስተካከል…፤ ዘነበ ከዚህም ሌላ ከሰዎች ጋር መሥራት በጣም ይወዳል። ከተፈጥሮ ችሎታው ጋር የመርዳት ስጦታም አለው ማለት ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 1228)። ሰዎች ዘነበ እንዲረዳቸው ሁልጊዜ ይጠሩታል። ይህም የመርዳት አገልግሎት ክርስቶስን ከማስከበሩም ሌላ ዘነበንም በጣም ያረካዋል። አስተውል፦ መንፈሳዊ ስጦታን መጠቀም ደስታንና እርካታን ያመጣል። እርግጥ አንዳንዶቹ ይህንን ደስታና እርካታ በሙላት አያገኙም፣ መንፈስ ቅዱስን ስለሚያሳዝኑ ነው። ስጦታ ከእግዚአብሔር ቢሰጥም ተቀባዩ ለራሱ ክብር ሲያደርገው ሊያበላሸው ይችላል። ነገር ግን የአካሉ ራስ ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ሲኖር የአካሉ ብልቶች ሁሉ በስጦታው ይደሰታሉ። 

ስጦታችንን ለማወቅ በምናደርገው ጥረት የውድድር መንፈስ ጨርሶ መወገድ አለበት። ከሌሎች ጋር ራሳችንን ማስተያየትም ሆነ ማወዳደር ፍጹም አልተፈቀደም። ይህን ማድረግ ሁሉም ቻይና ሁሉን አዋቂ የሆነውንና ስጦታውንም የሚሰጠውን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን አለማክበር ነው። ከዚህ ይልቅ ሌሎች ስጦታቸውን እንዲለዩ ያንተንም እንዲያሳዩህ እርዳቸው። በስጦታቸው መደሰትንና መጠቀምን ተማር። ስለነርሱ እግዚአብሔርን አመስግን። በሌሎች ስጦታ መደሰት ስለ ሌሎች ያለንን መጥፎ አስተያየት ለማስወገድ የክርስቶስን አካል አንድነት ለመጠበቅና ለመረዳዳት ይጠቅማል። መንፈሳዊ ስጦታዎች በፍቅር ካልተሠራባቸው ምንም አይጠቅሙም (1ኛ ቆሮንቶስ 13)። ፍቅር የጐደለውን ይሞላል። ያለመረዳትንና ውድቀትን ያስወግዳል። ፍቅር ይቅርታ ያደርጋል፤ ያማክራል፤ ያስተካክላል።  ፍቅር የመንፈስ ስጦታዎችን ማሰናከያዎች ሳይሆኑ ማስተካከያዎች ያደርጋቸዋል። ደስ የሚልና ጠቃሚ ሕይወት እንዲኖርህ መንፈሳዊ ስጦታዎችህን እወቅ። በክርስቶስ አካል ውስጥ ያለህን የአገልግሎት ድርሻ አሳድግ። ለሌሎች መታነጽ ስጦታህን በፍቅር ለመጠቀም በሙሉ ኃይልህ ሥራ። “ልዩ ልዩ የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ።”

[ብርሃን መጽሔት ቁጥር 51፣ 1972፣ ገጽ 10-11 እና 20]