ቤተክርስቲያን ሥልጣን እስከ ምን ድረስ ነው?

lalibelacrossየቤተክርስቲያን መሪዎች፣ ሰዶማዊነትን በመቃወም ሊያስተላልፉት የነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ መጨናገፉ፣ ስለ ጥሪአቸው፣ ከመንግሥት ጋር ስላላቸው ግንኙነትና በተከታዮቻቸው ዘንድ ስላላቸው ተቀባይነት ለመመርመር ዓይነተኛ ምክንያት ይሆናል።

ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ሰዓቱ አሁን ነው። ቤተክርስቲያን የጽድቅ ወንጌል ለማስተማርና ኃጢአትን ለመቃወም የመንግሥት ፈቃድ ትጠይቅ ወይስ ጌታና አዳኝዋ ክርስቶስ ያዘዛት ይበቃታል? የኢትዮጵያን ሕዝብ በመላ የሚወክሉ የሃይማኖት መሪዎች ተቃውሞአቸውን በአግባቡ ሳያሰሙ እንዴት እንደ ዋዛ ሊበተኑ ቻሉ? ምእመን ድምጹን ለማሠማት ምን አማራጭ አለው? የመንግሥትና የሃይማኖት ድንበር በሕገ-መንግሥቱ በግልጽ ተገድቦ እያለ መንግሥት ለምን ተላለፈ? መንግሥት የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን በሕግ እንዳያጸድቅ ከእንግዲህ ምን ይከለክለዋል? የቤተክርስቲያን ሥልጣኗ እስከ ምን ድረስ ነው?

ቤተክርስቲያን የልደት፣ ጋብቻና ቀብር ሥርኣት መፈጸም እንጂ በአደባባይ ተቃውሞ ማሰማት ፖለቲካ ነው ብትባል፣ ከወንጌል ጋር የማይታረቅ ማኅበራዊ ጉድ እያየች ዝም ትላለች? ብርሃንዋን በመቅረዝ ላይ እንደማኖር በእንቅብ በታች ትሸሽጋለች? የምትሰብከው ወንጌል እንዳያስቆጣና በ”ነጻነት” እንድታመልክ የፈቀደላትን መንግሥት ውለታ እንዳታበላሽ ራሷን በራሷ ሳንሡር ታደርጋለች? የውጭ እርዳታ እንዳይቋረጥ፣ በ”ፍቅር” እንያያዝ የሚሉ ምክንያቶችን ትደረድራለች? “ከፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው” ብሎ ኢየሱስ ባጸናው ትእዛዝ ላይ መደራደርስ ትእዛዙን መሻር አይሆንም [ማር.10፡6]? ነገ የሚያነካክስ ሁኔታ ቢከሰት አቋም ለመውሰድ ምን አማራጭ አለ? የጌታ ሥራ “እንዳይተጓጎል” አንዳንዱ ጉዳይ ለጊዜው ወደ ጎን ይ-ተው?

መሪዎች ለክርስቶስ እና ለሕዝቡ ምን መልስ ሊሰጡ ተዘጋጅተዋል? ደርግ ቤተክርስቲያን ሲ-ዘጋና አንዳንዶችን ሲያሥር፣ ይህ ወቅት እስኪያልፍ መሰብሰብ ይቅር ያሉ እንደ ነበሩ፣ የተጠበቀው ወቅት ግን እንዳልደረሰ፣ እንዲያ ያሉትንም አንዳንዶችን አንድባንድ የፈሩት አውሬ እንደዋጣቸው እናስታውሳለን። አንድነት እኮ በጽድቅና በእውነት ላይ እንጂ በሰው ብልሃት አይጸናም። መሪዎች ቀኝና ግራውን የማያወቀውን ሕዝብ ወዴትና እንዴት ሊመሩት ነው?

ባለፉት ሃያ ዓመታት ሲካሄዱ የቆዩ ሁኔታዎችን እንደገና መመርመር ቤተክርስቲያን ከጥሪዋና ከተልእኮዋ ምን ያህል እንዳፈገፈገች ሊጠቁም ይችላል። ከቤተክርስቲያን ጥላ ሥር ወጥተው የሚንቀሳቀሱ ግለኛ “ሚኒስትሪዎች” እና ግለ ሰቦች የግላቸው ቤተክርስቲያን መሥራቾች ወደ መሆን ተሸጋግረዋል። ይህን ያነሳነው የሚታየውን ሐቅ ለመጠቆም እንጂ በጎ አካሄዶችን ሳንለይ ቀርተን አይደለም። ሁሉን አንድ ላይ መጨፍለቅ ባይቻልም፣ የሚታየው ሁኔታ ላለመያያዝና ለቤተክርስቲያን ሥልጣን መሸርሸር ምክንያት ሆኗል። በግለኛ ክርስትና ላይ ጎሠኛነት፣ መረን መጤ ባሕልና እየሰፋ የሄደው የኑሮና የትውልድ ክፍተት ተጨማምሮ ማኅበራዊ አመራሩን ያናጋው ይመስላል። በአንዳንዶች ዘንድ ተጠሪነት ከመዛባት አልፎ፣ በቤተሰብ እስከ መካለል ደርሷል። ባለፉት ሃያ ዓመታት የብልጽግና ወንጌል ሥር ሰድዶ ጥቂቱን ሲያዝናና፣ ብዙሃኑን ተመልካች አድርጎታል። በረከት መልካም ነው፤ የመልካም በረከት ምንጭ እግዚአብሔር ነው፤ ያም በረከት በቅድሚያ ሰማያዊ ነው፤ የሚያከብረውም ከሰው ይልቅ ሰጭውን ሊሆን ይገባል። ዓይናቸው በምድራዊ በረከት ለተያዘባቸው ግን መስዋእትነትም እንኳ ማትረፊያ ነው።

ራሳቸውን ሲሾሙና ሲሿሿሙ፣ እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ ሲሉ አንዳንዶችን የተነሡበት መሬት ርቃቸዋለች። እነዚህም የሚናገሩትና የሚሆኑት ከቤተክርስቲያን በስተውጭ ካሉት እምብዛም አልተለየም። “ሚኒስትሪ” ለሚያካሄዱና የብልጽግና ነገር ለሚያሳሳቸው ለአንዳንዶች፣ ግልጽ አቋም ከመውሰድ ይልቅ በዘመኑ መንፈስ ተስማምቶ ተመሳስሎ መኖርና ፍትኅ የማያውቅ “ፍቅር” መስበክ ይቀናቸዋል። የሚጠላለፉ መቸውንም በጽድቅ ነገር አይደፍሩም። የክርስቶስ መስቀል መካከለኛነቱ ሲዛነፍ ውጤቱ የ“ተቻችሎ፣ ተቀባብሎ፣ ተመሳስሎ” ማደር ወንጌል ነው።

ቤተክርስቲያን የራሷን ቤት ሳታጸዳ መቆምና አመጽን መቋቋም አይቻላትም። የጸና አቋም ያላቸው መሪዎች የሌለ ስም ቢሰጣቸው፣ ያንን እንኳ ለመቀበል የተዘጋጀ አእምሮ ካልኖራቸው ውጤቱ አሁን እንደታየው መፍረክረክ ይሆናል። የጠላት ዒላማ ያነጣጠረው በመሪው ላይ ነው፤ መንጋውን ለመበተን መሪውን መምታት ዓላማው ነው። አሳልፈው ለመስጠት የማይመለሱ ከመካከል እንዳሉ አውቀው፣ መሪዎች ይበልጥ መያያዝ ይኖርባቸዋል። የማይደራደሩባቸውን እውነቶች ለይተው ማወቅና ኢየሱስ በሰጠው ሥልጣን ላይ ቆሞ ይህንኑ ማወጅ ይጠበቅባቸዋል። የክርስቲያን ፍልሚያ አዲስ ፍልሚያ አይደለም፤ በኢየሱስ ላይ የተደረገበት ለእውነተኛ ተከታዮቹ አይቀርላቸውም። ከሁሉ ይልቅ፣ የእረኞች አለቃ የሆነው ኢየሱስን የሚቋቋመው እንደሌለ፤ ለሕዝቡ የሰጠው መንፈስ ደግሞ ሕያውና ብርቱ፣ ወደ ጥበብና ወደ እውነት እንደሚመራ ማስታወስ ኃይል ይጨምራል።  

ቤተክርስቲያን የክርስቶስን ፈለግ እንድትከተል ተጠርታለች። ኢየሱስ ሲሰድቡት አልተሳደበም፣ ፊቱን ግን እንደ ባልጩት ድንጋይ አጠነከረ። የእግዚአብሔር ጽድቅ በእርሱ ይከናወን ዘንድ አላፈገፈገም። እርግጥ መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለም፤ የጦር ዕቃችንም ሥጋዊ አይደለም። በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሳውን ሁሉ ለማፍረስ ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው [ኤፌሶን 6፡12፤ 2ቆሮንቶስ 10፡3-6]። የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ልበሱ፣ አንሡ፣ ተጫሙ፣ ቁሙ፣ ያዙ የተባልነው ጦርነት በታወጀበት ዓለም ውስጥ ስለምንገኝ ነው፤ አለመዘጋጀት ከሚያስከትለው መዘዝ እንድንድንና እንድናድን ነው። ስንዝር ብንለቅለት ጠላት ክንድ ይጠይቀናል። በዓለም ውስጥ መኖራችን ጨውና ብርሃን እንድንሆን እስከሆነ ድረስ የምንገኝበትን ሥርኣተ ማኅበር መጨመሩ የግድ ነው። እያንዳንዱ በግሉና በቤቱ የወንጌልን ዕዳ እንዴት ልወጣ ብሎ ልቦናውን መመርመርና አብዝቶ መጸለይ ይኖርበታል። ቤተክርስቲያን፣ ይህንና የመሳሰሉትን እርም ነገሮች ከምድሪቱ ላይ እንዲነቅል በጌታ ጸባዖት ፊት የጾም አዋጅ ማወጅ ይኖርባታል። የወንጌል ነገር የድምጽ ብልጫ ጉዳይ አይደለም። ኢየሱስ፣ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሠጠኝ ሲል፣ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ ሲል፣ ይኸንኑ ማለቱ ነው። ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ ሲል ከኔ ሌላ ጌታ የለም ማለቱ ነው። ኢየሱስ በሁሉ ላይ ጌታ ነው? እንግዲያስ፣ እውነት ይዞ መሸሽ ይቁም!