ቅዱስ ዮሴፍ

ETnativity2

ዮሴፍ አንዴም ራሱን ሲያስተዋውቅ አናነብም። ጸራቢ እንደ መሆኑ የድርጊት ሰው  ነበረ። በጠቃሚነቱ ሠፈር የሚያውቀው ሰው ነበረ፤ ልጆቹን ጭምር ያውቋቸው ነበረ። [ማቴዎስ 13፡55-56] የመጀመሪያው የሕዝብ ቆጠራ አዋጅ ሲታወጅ እርሱም ሊቆጠር ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ወደ ቤተልሔም ተጓዘ [ሉቃስ1፡1-7]። ኢየሱስ በቤተልሔም እንደሚወለድ እግዚአብሔር በነቢያቱ አፍ ተናግሮ ነበር። [ሚክያስ 5:2] በቤተልሔም ሳሉ እጮኛው ማርያም ወለደች። የ”አይሁድ ንጉሥ” ተወለደን ሲሰማ፣ ንጉሥ ሄሮድስ ሥጋትና ቁጣ ያዘው። ሕፃናትን ለማስፈጀት ወሰነ። እግዚአብሔር ዮሴፍን በዚያው ወደ ግብፅ ሽሽ አለው፤ ዮሴፍ ከህጻኑ ኢየሱስ እና ከማርያም ጋር ሸሸ። ለቆጠራ ከቤቱ ከናዝሬት የወጣ፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነና ግብፅ ከረመ፤ ሄሮድስ እስኪሞት ወደ መንደሩ አልተመለሰም።[ማቴዎስ 2]

የእግዚአብሔር ቃል ዮሴፍን “ጻድቅ” ሲል ይገልጸዋል። ጻድቅ ሰው ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር የተስማማ፣ ልክ የሆነውን ማድረግ የሚወድ ነው። ቅኑና ልኩ ሲደረግ ማየት የሚወድ ነው። ልኩ ይደረግ እንጂ እርሱ በዚያ ውስጥ አለመታወቁ አይገደውም። ለጽድቅ ሥራ ምክንያት ሆኖ መገኘት ያስደስተዋል። ዝናቸውና ምግባራቸው የማይመሳሰል ስንቶች ናቸው? ዮሴፍ በዝምታ ዛሬም የሚናገረው አለው።

በእግዚአብሔር ዐይን ፊት ጻድቅ የሆነ ሰው ድምፁ ባይሰማም ይሰ-ማል። ዮሴፍ የሰውን ገበና ለመግለጥ የሚቸኩል ሰው አልነበረም። ሳይጋቡ ማርያም ፀነሰች። ይህ ምን ማለት ይሆን? የሚቀጥለው እርምጃ ምን ያመጣ ይሆን? ይህን ለሰሚው ማስረዳት እንዴት ይቻላል? ምስክር ማን ይጠራ? ዮሴፍ ለእጮኛው ለማርያም ጥልቅ ፍቅር ነበረው። ከእግዚአብሔር ዘንድ ገብርኤል ተገልጦ እንዲህና እንዲህ አለኝ ብላው ነበር። ይህን ያደረገ መንፈስ ቅዱስ ነው ስትለው ወዲያው ሊ-ረዳ አልቻለም፤ ኋላ ግን አመነ። መንፈስ ቅዱስ የእውነት መንፈስ ነዋ! መንፈስ ቅዱስ የተናገረውን መንፈስ ቅዱስ ያጸናዋል። እውነትን ለሚሹ ያበራላቸዋል፤ ከሰው አእምሮ በላይና ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ የሆነውን እንዲረዱ ይረዳቸዋል፦ ይህ ክፍል ተኣምራት ነው፤ ለሰው የማይቻል ለእግዚአብሔር ይቻላል ይላቸዋል። ለነገሩ፣ በተፈጥሮም በሚሆነው ፅንስ፣ እንዲህ ሠልጥነን እንኳ አጥንትና አጥንት እንዴት እንደሚጋጠም ገና አልደረሰንበትም። የሚታየውን ከማድነቅና ከማብራራት አላለፍንም። እንግዲህ፣ ይህንንም ያንንም ያደረገው እግዚአብሔር ነው!

እጮኛው ፀንሳ መገኘቷ ዮሴፍን ግራ አላጋባውም ማለት አይደለም። ራሱን ሁሉ ሳይጠራጠር አልቀረም። በአሳብ ሲጉላላ ሲገላበጥ ይመሽና እንቅልፍ ይወስደዋል። አንዱን ቀን ግን ወሰነ፤ ላያዋርዳት፣ ላይገልጣት በስውር ሊተዋት ወሰነ። የሚመጣውን ውርደት ሆነ ፈተና ለመጋፈጥ ቆረጠ። ዮሴፍ ጻድቅ ሰው ነበረ። ልኩን ይ-ረዳ እንጂ ያንን ማድረግ ፈቃዱ ነበረ። ይህን ጊዜ እግዚአብሔር መልአኩን ላከለት። መልአኩም፣ “አትፍራ፣ ያለህበትን ሁኔታ እግዚአብሔር አይቶታል፣ የልብህንም አሳብ ሰምቶአል” እያለ ቀረበ። አትፍራ፣ እመን። ማርያምን፣ ራስህን፣ እግዚአብሔርን አትጠራጠር። ይህ ነገር ከእግዚአብሔር ነው አለ።

ዮሴፍ መብቱን የማያውቅ ሰው አልነበረም። ማርያምን ማጋለጥ መብቱ ነበረ፤ እንደ ሙሴ ሕግ በአደባባይ ተወግራ እንድትሞት የመጀመሪያውን ድንጋይ መወርወር ይችል ነበር። ይህን ቢያደርግ ኖሮ አያስወቅሰውም ነበር። በዚህ ላይ፣ በኖረበት፣ በተከበረበት ከተማ ገና ስም ይወጣለታል። ከሌሎች ዮሴፎች ለመለየት፣ “እጮኛው ፀንሳ የተገኘችበት፣ ተወግራ የሞተች” አሽሙር ይባልለታል። በዚህ ሁሉ ራሱን ለማጽደቅ አልቸኮለም። እግዚአብሔር ሥራው ድንቅ ነው፤ የተወለደው ሕፃን ነቀፌታን የሚያስወግድ ሆነ።

መልአኩ፦ "ማርያምን መውሰድ አትፍራ አለው፤" ዮሴፍ እንደ ታዘዘው አደረገ። በባልነት መብቱ አልተጠቀመም፤ ተቆጠበ፤ ራሱን ገዛ። “የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም።” ዮሴፍ ለዚህ ዘመን ሰው የሚናገረው አለው። የአባትነት መብቱ ለተወለደው ሕፃን ስም ማውጣት ነበረ፤ መብቱን ለጌታ ለቀቀ። “ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ፣ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል። አማኑኤል ይሉታል፤ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።” ዮሴፍ ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ። ስሙንም ኢየሱስ አለው። ስምን መልአክ ያወጣዋል የሚባለው ለዚህ ነው? “በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ” …[ኢየሱስ በሥጋ ከመገለጡ በፊትም ነበረ፤] “ኢየሱስ” የኖረ፣ ሁሌ አዲስ እና የማይለወጥ ነው! ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው። [ሉቃስ 2፡21፤ዕብ.13፡8]

ኢየሱስ በተገኘበት ሄሮድስ አይገንም። ኢየሱስ በተገኘበት ዮሴፍ አይገንም፤ ማንም አይገንም። አንድ የሰማይ፣ አንድ የምድር ገዥ ብሎ የለም፤ አንድ ብቻውን የሰማይና የምድር ገዥ ነው። ሄሮድስ የኢየሱስ ስም እንዳይገን ታገለ፤ አልተሳካለትም፣ ታግሎ እራሱ ወደቀ። ዮሴፍ፣ ድምፁን አጥፍቶ፣ መብቱን ጥሎ ኢየሱስን አገነነ፤ ድርጊቱም ከሄሮድስ የአዋጅ ጡሩምባ ይልቅ በምድር ዳርቻና በዘመናት መካከል ተሰማ። ዮሴፍ እንደሚታዘዝ ስላወቀ፣ እግዚአብሔር ለማንም ያልነገረውን ታላቅ ምሥጢር ነገረው፣ ለማዳኑ ኃይል ምሥጢር ምክንያት አደረገው። ድምፃቸውን ሳያሰሙ በስውር የጌታን የኃይል ሥራ የሚሠሩ ብሩካን ናቸው። በሰዎች አፍ ብቻ ዝናቸው የሚቀድማቸው ግን ዋጋቸውን ከሰዎች ተቀብለዋል፤ የዮሴፍ አምላክ ይርዳቸው።

ዮሴፍ ቅዱስ ተባለ። እግዚአብሔር ለሥራ ለየው። እራሱ ቅዱስ ለሆነ፣ ለሚቀድስ አምላክ ራሱን ለየ፤ ለቅዱስ መንፈስ ተመቸ። ለጌታ ክብር ሲል ክብሩን ጣለ። ዮሴፍ የድርጊት ሰው ነበረ። ጸራቢ ነበረ። ብዙዎችን ይጠቅም ነበር። ኢየሱስ ጸራቢ ነበረ። ዓለምን እንዲያድን አባቱ ላከው። “የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፣ በስሙ ለሚያምኑት፣ ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው።” [ዮሐንስ 1"12] ኢየሱስ በተጠረበ እንጨት ላይ ተሰቀለ። በእንጨት ላይ የሚሰቀል ርጉም ይሁን እንደሚል፤ የሰውን ሁሉ እርግማን ይሸከም ዘንድ ተሰቀለ (ዘዳግም 21፡23)። “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።” [2ኛ ቆሮንቶስ 5፡21] ሰው ሁሉ አጎንብሶ እንዲያየው በግርግም ተወለደ፤ ሰው ሁሉ አቅንቶ እንዲያየው በጎልጎታ ተራራ ላይ ተሰቀለ። ያዩት ሁሉ ያመኑትም ከኃጢአት እዳና እስራት ነጻ ወጡ። እርሱ ለመሞት ተወለደ! ለበደል ሥርየት ሞተ፣ ኃጥኣንን ለማጽደቅ ከሙታን ተነሣ፤ በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ በቀጠረው ሰዓት ይመለሳል!

ማቴዎስ 1፡18-25። “የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ። እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤ የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።”

ሉቃስ 2፡8-15። “በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ። ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን! ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው። እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤”

የእግዚአብሔር ማዳን እነሆ፣ ተገልጧል፤ ማዳኑም ሰምተው እንዲታዘዙ ለሁሉ ተገልጧል። “መዳን በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” ያም ስም “ኢየሱስ” ነው። “አማኑኤል” ይሉታል፤ ትርጓሜውም፣ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ማለት ነው።

በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም … ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን … እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው። [ዮሐንስ 1:1-5፣ 14-18]