"ሰይጣን ይጥፋ! ጣሊያን ይጥፋ?"

ዛሬ አብባ የምናያት ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን ታሪኳ ምን ይመስል ነበር? መስዋእትነት ሲጠየቅ ብዙ የእግዚአብሔር ጸጋ አብሮ እንደሚሰጥ። ቅንነት፣ መሰጠት፣ ትጋትና ጥበብ ምን ውጤት እንደሚያስገኙ። ጸጋ ሲበዛ ለአገልጋይና ለአገልግሎት የሚያስፈልገው በረከት እንደሚበዛ። በመጨረሻም፣ የእግዚአብሔር ፍርድና ጥበቃ። እነዚህን በጥንቃቄ እናስተውል። 

በ 2000 ዓ.ም ከታተመው፣ "የመርኪና መጃ ግለ ታሪክ እና የወላይታ ቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን ታሪክ" መጽሐፍ፣ ከገጽ 21-24 የተወሰደ፤

“በ1930ዓ.ም. ጣሊያኖች አማኞችን ማሳደድ ጀመሩ። በጣሊያን ወረራ ጊዜ በአካባቢአችን ብዙ የቤተክርስቲያን መሪዎች ወንጌልን በመስበካቸው ስለ እምነታቸው ታሥረዋል፤ ተገርፈዋልም። ወንጌላውያኖቹም “ሰይጣን ይጥፋ” ብለው ያሉትን ጣሊያኖች፣ “ጣሊያን ይጥፋ” ብለው ስለ ተረጎሙት፣ ቁጣቸው በቤተክርስቲያን ላይ የከፋ ሆነ።

ቤተክርስቲያን በስደት ውስጥ እያደገች መሄዷን የተረዱ ጣሊያኖች ሃምሳ የቤተክርስቲያን መሪዎችን አሰሩ። በፖሊስ ተይዘው ወደ እሥር ቤት የተወሰዱት ክርስቲያኖች እያንዳንዳቸው አንድ መቶ ጅራፍ የተገረፉ ሲሆን፣ በሕይወት ቆይቶ ታሪኩን ያወራው ሰው አራት መቶ ጅራፍ ተገርፏል። ለወራት የታሰሩ ሰዎች በጀርባቸው መተኛት አይችሉም ነበር። የተገረፈው ሰውነታቸው ቆስሎ እንደ ጥሬ ሥጋ ሆኖ ይታይ ነበር። ሌሎቹ በእሥር ቤት እየማቀቁ በነበሩበት ወቅት አቶ ሳዋልዶ ሳጋሮ እና አቶ አላንቦ ሌቃ ሞተዋል። በእሥር ቤቱ ምንም ምግብ አይቀርብላቸውም ነበር። ምግብ የሚቀርብላቸው ከቤተሰቦቻቸውና ከወዳጆቻቸው ሲሆን፣ አንዳንዶቹም ከሩቅ ምግብ ተሸክመው ለታሠሩት ጓደኞቻቸው ያመጡላቸው ነበር…

ክርስቲያኖች በጣሊያኖች ይሰደዱ በነበሩ ጊዜ በአቶ ብሩ ቤት አጠገብ ተሠርቶ የነበረው ጸሎት ቤት በአገሩ ከሚገኙ በርካታ ጸሎት ቤቶች ጋር ተደምስሷል… አቶ ብሩ ቀን ቀን እየተደበቁ ይውሉና፣ ሌሊት ሌሊት ወንጌልን ለሦስት ወር ያህል አስተማሩ። በመጨረሻም “ሚስቴ በእኔ ምትክ ታሥራ እኔ እስከ መቼ ተደብቄ እኖራለሁ?” አሉ። ስለዚህም በሶዶ የጣሊያን ጦር አዛዥ ወደ ነበሩት ሻለቃ ቦዚ ዘንድ ሄዱ። የጦር አዛዡም አቶ ብሩን ወደ ቢሮአቸው አስገብተው፣ “የምትሰብከው ምንድነው?” ብለው ጠየቋቸው። አቶ ብሩም የሻለቃውን ዓይን በቀጥታ አትኩረው እየተመለከቱ ፣ “የምሰብከው የእግዚአብሔርን ቃል ነው” ብለው መለሱ። ሻለቃው ተናድደው “እንዴት አትኩረህ ታየኛለህ?” አሏቸው። አቶ ብሩም ጀርባቸውን ሰጥተው፣ “እንደዚህ ሆኜ እንዳናግርዎት ይፈልጋሉን” አሏቸው። ከዚያን ሻለቃው ከተቀመጡበት ብድግ ብለው በጥፊ መቷቸው። እየረጋገጡ እስኪዝሉ ድረስ ደበደቧቸው። “እንዲህ እንደ አሽከር በእኔ ላይ ትናገራለህን?” ካሉ በኋላ፣ ጥቂት ሲቆዩ በድንገት የሬድዮ ጥሪ ተደረገላቸውና “የአማጽያን ኃይል እያጠቃን ነውና በፍጥነት ወደ ሶሬ ዶጌ ወታደሮች ላኩልኝ” ተባሉ። ሻለቃውም ተጣድፈው እየወጡ፣ “ሌሊት መጥቼ እገድልሃለሁ” ብለዋቸው ወጡ። ከወታደሮቻቸው ጋር ወደ ተባለው አካባቢ ሲደርሱ፣ ድንገተኛ ጥቃት ከአማጽያን ተከፈተባቸውና ግንባራቸው ላይ ተመትተው አቶ ብሩን ተመልሰው የማየት ዕድል ሳያገኙ ሞቱ። አቶ ብሩም ሚስታቸው በነበሩበት እሥር ቤት ታሠሩ።

ጣሊያኖቹም በእንግሊዝ እርዳታ ከተሸነፉና አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ አገራቸው እንደ ተመለሱ አቶ ብሩ ከሚስታቸውና በጣሊያኖች ከታሠሩ ሌሎች በርካታ ክርስቲያኖች ጋር ሲፈቱ፣ አቶ አላንቦ ግን በእሥር ቤት እንዳለ ታሞ ሞተ። የቀሩት የቤተክርስቲያን መሪዎች በጥፊና በእርግጫ ከመደብደባቸው በስተቀር በጌታ ጥበቃና እንክብካቤ ሁሉም በሰላም ተፈቱ።

ከስደቱ በኋላ የቤተክርስቲያን መሪዎች ወደ ዋንቼ ላኩኝ። ልጅ በመሆኔ ጣሊያኖች ወደ እሥር ቤት አስገብተው ቢደበድቡት ይሞታል ብለው ተወያዩ። ቢሆንም፣ በብርቱ ተጨነቅሁና ለራሴ “እቤት ተቀምጬ የጌታን ሥራ ላቆም ነው?” አልኩና ወደ ዋንቼ ሄጄ የቤተክርስቲያን ሰዎችን፣ “ትልቅ አዳራሽ ብትሠሩ ሕፃናትን ሰብስቤ አስተምራለሁ” ብዬ አሳብ አቀረብኩላቸው። እነርሱም ደስ አላቸውና ሰፋ ያለ አዳራሽ ሠሩ። እኔም ቀጨሞ ከሚባል ዛፍ ፍሬ ለቅሜ በውሃ ውስጥ ዘፍዝፌ ሳማስለው ቀለሙ ወጣ። የቀርከሃ ስንጥቅ ወስጄ እንደ እስክሪብቶ አድርጌ በማሾል ከሠራሁት በኋላ፣ እያጠቀስኩ በጥጥ ጨርቅ ላይ መጻፍ ጀመርኩኝና ማስተማሬን ቀጠልኩ። የትምህርት ዝና በፍጥነት ወደ ተራራማው አካባቢ ሁሉ ተሠራጭቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማንበብና መጻፍ የተጠሙ 250 ልጆችን አገኘሁ። የሚከፈለኝ ነገር ባይኖርም፣ እኔ ግን በልቤ ለጌታ ካለኝ ጥልቅ ፍቅር የተነሣ በደስታ አስተምራቸው ነበር። ስብሰባችንን የምናካሄደው በተቻለን መጠን በሥውር ቢሆንም፣ የጣሊያን ሃይሎች ግን የወንጌልን ሥራ ለማፍረስ የሚቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ ነበርና በአቶ ጉንታ ቤት መግቢያ ላይ የነበረውን ትንሽ የጸሎት ቤት አፈረሱት። እኛም መሰብሰቢያችንን ወደ ሻንካ አባ ቤት ለማዛወር በፈለግን ጊዜ፣ አቶ ሻንካ “ጣሊያኖች በቤቴ ውስጥ መሰብሰባችሁን ካወቁ ቤቴን ያፈርሱብኛል፣ ስለዚህ ሌላ ቦታ ፈልጉ” አለን።

ሽማግሌዎች ደግሞ ሌላ ቦታ የማግኘት ችግር ነበረባቸው። ከዚያም አባቴ ተነሣና፣ “እግዚአብሔር የሰማይና የምድር ጌታ እስከ ሆነ ድረስ፣ ለእርሱ ምንም ቦታ የለውም ማለት እንችላለን ወይ? የእኔን ቤት ውሰዱና ግን ለመኖሪያዬ ትንሽ ጎጆ ሥሩልኝ” አለ። ክርስቲያኖችም እጅግ ደስ አላቸው። ሁሉም አባቴን አመስግነው እንደ ንብ ተረባርበው ቤቱን ከግቢያችን ውጪ በአንድ ጀምበር ሠርተው አጠናቀቁ። ከሳምንት በኋላም፣ ስብሰባቸውን በቀድሞው ቤታችን ውስጥ አደረጉ። የቤታችን ዙሪያ 50 ጫማ የሚሆን ቢሆንም፣ ተሰብሳቢዎቹን ሁሉ ለመያዝ ብቁ አልነበረም። ስለዚህም አባቴ ከመጀመሪያው ቤት ጋር አያይዞ አራት ማዕዘን ቤት ጨምሮ በሠራ ጊዜ፣ ሁሉም ተዝናንቶ መሰብሰብ ቻለ። ዋና አስተማሪያችን አቶ ጐዳቶ ጩቦ ነበርና በግቢያችን ውስጥ ለእርሱ መኖሪያ የሚሆን ቤት ተሠራለት። እርሱ በዱጉና ያስተምር ነበር። አቶ ጐዳቶ እዚያ ሆኖ ታላቅ ረዳት የሆነችውን ወ/ሮ ማሚቴን አገባ። በእርሱ አገልግሎት ብዙዎች ወደ ቤተክርስቲያን ተጨምረዋል። ቤተክርስቲያን ለአባቴ የሠራችው ቤት አነስተኛ ስለ ነበር፣ ለእኛና ለከብቶቻችን በቂ አልሆነም። ስለዚህ አባቴ በግቢያችን ውስጥ ደስ የሚል ትልቅ ቤት ለእንግዳ ማረፊያ እንዲሆን ሠራ። አንዳንዶቹ ልጆች መኝታቸውን በአዲሱ ቤት ውስጥ አደረጉ። አንዳንዶቻችን ደግሞ በከብቶች ቤት ውስጥ ስንተኛ፣ ሌሎች በጸሎት ቤት ይተኙ ነበር።

በዋንቼ ፊደል ሳስተምር፣ የማስተምራቸው የተወሰኑ አማኞች እስከ ሌሊት ይቆዩ ነበር። ሴቶችና ልጃገረዶች በውስጠኛው [በጓዳ] የሚተኙ ሲሆን፣ ወንዶች ልጆች በጸሎት ቤት ወለል ላይ ይተኙ ነበር። ለዚያ ሁሉ ሰው አልጋ ስለሌለ ቄጠማ ቆርጠው መሬት ላይ አንጥፈው በላዩ ላይ ቁርበት ዘርግተውበት ወፍራም ከጥጥ የተሠራ ቡልኮ ለብሰው ይተኙ ነበር። ሁላችንም በአንድነት እንመገባለን፤ ሴቶች ምግብ ያበስላሉ፣ ውኃ ይቀዳሉ፣ ሣር ያጭዳሉ። ወንዶች ደግሞ አትክልት ያመርታሉ፤ እንጨት ይፈልጣሉ፣ አንዳንዴ ደግሞ ሣር ያጭዳሉ። በወላይታ የእኛ አካባቢ ለም እንደ መሆኑ መጠን፣ ምግባችን በቆሎ፣ ስኳር ድንች፣ ድንች፣ አደንጓሬ፣ የእንሰት ቂጣ፣ ገብስ፣ ቅጠላ ቅጠል፣ አተር፣ ባቄላ፣ ሽንብራ፣ ዱባ፣ ማሽላ፣ ሥጋ፣ ቅቤ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ዐይብ፣ እና የተለያዩ ፍራፍሬዎች ሁሉ ይመረታሉ። ቀኑን የምናሳልፈው መጻፍና ማንበብ እየተለማመድን፣ ቃሉን በማጥናት፣ መዝሙሮችን በመዘመር፣ እንዲሁም ለታሠሩት መሪዎቻችን ምግብ በማቀበልና ባጋጠመን ጊዜ በመመስከር ነበር።