የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም

በእሸቱ አባተ 

drEshetu2የስሕተት ትምህርቶች ዋነኛው ምክንያት የተሳሳተ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ነው። ማንኛውም መጽሐፍ በደራሲው መንፈስና ለማስተላለፍ በፈለገው መልእክት መሠረት መተርጎም እንዳለበት ግልጽ ነው። ይህ ካልሆነ ለደራሲው ታማኝ አለመሆንና ያላለውን አለ፣ ያላሰበውን አሰበ ወደ ማለት ያደርሳል። ይህም ወደ ስሕተት ይመራል። 

መጽሐፍ ቅዱስ፣ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የጻፉት መጽሐፍ ነው [2 ጴጥሮስ 1፡ 21፤ 2 ጢሞቴዎስ 3፡ 16-17]። እንዲህ ከሆነ በዚያው መንፈስ አማካይነት ካልተተረጎመ ትርጉማችን የተሳሳተ ይሆናል።

አንድ ማስታወስ የሚገባን መንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል ያስተላለፈልን ሰዎችን በመጠቀም መሆኑን ነው። እንዲህ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔርንም የሰውንም እጅ (ጣት) እናያለን ማለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስም በሰዎች እጅና ቋንቋ የተጻፈ ፍጹም የእግዚአብሔር ቃል ነው። 

ከዚህ የተነሣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እግዚአብሔር ራሱን በነቢያቱና በሐዋርያቱ በኩል በተጻፈ ቃሉ ገለጠልን። እነዚህ ነቢያትና ሐዋርያት በተወሰነ ዘመንና ቦታ የነበሩ፣ የግል ስጦታ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ የነበራቸው ነበሩ። እግዚአብሔር በየዘመናቱ የተነሡትን የርሱን ባሪያዎች በዚህ መልክ በመጠቀም ፈቃዱን አስታወቀ። የብሉይ ኪዳን በዕብራይስጥ፣ ጥቂቱም በአራማይክ፤ የአዲስ ኪዳን ደግሞ በግሪክ ቋንቋ የተጻፈው፣ መጻሕፍቱ በተጻፉበት ዘመን የነበሩ ነቢያትና ሐዋርያት ሕዝቡንም ጨምሮ እነዚያን ቋንቋዎች ይጠቀሙ ስለነበረ ነው። 

ከዚህም ጋር ለተጻፉት መጻሕፍት ዘመን ቀረብ ብለው የነበሩ አባቶች የተጻፈውን ቃል በምን ዓይነት መንፈስ ተረዱት ወይም ተረጎሙት ብሎ መጠየቅ ይጠቅማል። ለምሳሌ ያክል ከጌታችንና ከሐዋርያት ዘመን አንሥቶ እስከ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ የግሪክ ቋንቋ በሜድቴራኒያን ባሕር አካባቢ በነበሩ የሮማ ግዛቶች ውስጥ የመግባቢያና የሥነ ጽሑፍ ቋንቋ ሆኖ ቆይቷል። በዚያን ዘመን የነበሩ ጌታን ያመኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቃሉን እንዴት ተረዱ ብሎ በመጠየቅ ከእነርሱ መማር፣ በዘመናት ሁሉ ያልተገለጠ የእግዚአብሔር እውነት ለኔ ተገለጠልኝ በማለት የሐሰት ትምህርት አስተማሪ ከመሆን ያድናል። ቃሉ “የእግዚአብሔር ቃል የተናገሩአችሁን ዋነኞቻችሁን አስቡ፣ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” ይላልና [ዕብራውያን 13፡ 7]። ስለዚህ ጤናማ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ለሁላችንም አስፈላጊ ነው። የስሕተት ትምህርቶች ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ነው። 

የሚከተሉትን መመሪያዎች ጤናማ በሆነ መንገድ ቃሉን ለመረዳትና ለመተርጎም ከጥንት ቤተ ክርስቲያን ጀምሮ የእግዚአብሔር ሰዎች ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ስለዚህ ሁላችንም በመመሪያዎቹ ብንጠቀም በማስተዋል፣ በጥበብና በትሕትና ቃሉን ለመረዳት ይጠቅመናል ብለን እናምናለን፦ 

1. ቃሉን ግልጽ በሆነ መሠረታዊ ትርጉሙ መረዳትና መተርጎም። ከላይ እንደገለጽነው የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ቃሉን ሲጽፉ ቋንቋቸውን ተጠቅመዋል፤ ቋንቋ ደግሞ የሰዋሰው ሕግና አገባብ አለው። ከዚህ የተነሣ አንድ ሰው የቃሉን ትርጓሜ ለማግኘት የተደበቀ ወይም የተሰወረ ነገር ከራሱ ሳይፈጥር በቀጥታ “ይህ የማነበው ቃል ምን ይላል?” ብሎ በመጠየቅ ግልጽ የሆነ ትርጓሜውን መውሰድ አለበት። የሚከተሉት ነገሮች መጽሐፍ ቅዱስን በመሠረታዊ ትርጉሙ በመረዳት ውስጥ ይጠቃለላሉ። 

ሀ. የቃሉን ወይም የአረፍተ ነገሩን የመጀመሪያ ትርጉም መገንዘብ። የቃላት ትርጉም አብዛኛውን ጊዜ ከዘመኑና ከአካባቢው ጋር የተገናኘ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል መጀመሪያ በተነገረ ወይም በተጻፈ ጊዜ ለአድማጮቹና ለአንባቢያን ምን ትርጉም ሲሰጥ ነበረ ብሎ መጠየቅ አግባብ ያለው ነው። ስለዚህ የቃሉን ትርጉም በመረዳት ለራሳችን ያለውን መልእክት ከመውሰዳችን በፊት በተቻለ መጠን የተጻፈበትን ሁኔታና የመጀመሪያ ትርጉም ማወቅ አስፈላጊ ነው። 

ለ. የሥነ ጽሑፉን ዓይነት መለየት። መጽሐፍ ቅዱስ በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ዓይነቶች የተሞላ ነው። ስድ ንባብ፣ ቅኔ፣ ምሳሌዎች፣ ራእዮች፣ ታሪኮችና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘውን ቅኔ ወይም ራእይ አንድ የታሪክ ወይም የስድ ንባብ ክፍል እንደሚተረጎም መተርጎም አግባብ ያለው አይደለም። ከዚህም ሌላ ምሳሌያዊ አነጋገሮችንና ዘይቤዎችን ለየት ባለ መንገድ መተርጎም ያስፈልጋል። 

ሐ. ቃሉን ወይም አረፍተ ነገሩን በቅደም ተከተሉና በአገባቡ መሠረት መተርጎም። አንድ ቃል ወይም ጥቅስ ከመተርጎም በፊት የሚቀድሙትንና የሚከተሉትን ጥቅሶችና አንቀጾች ማንበብና ይዞታቸውን ማወቅ ጥቅሱን ለመተርጎም አስፈላጊ ነው። አንዳንዴም በጥቅሶችና በአንቀጾች ሳንወሰን ምዕራፎችንና መጽሐፉን በሙሉ በማንበብ መገንዘብ አስፈላጊ ነው። አንድ ጥቅስ የሚቆመው ብቻውን ሳይሆን በቅደም ተከተል ካሉ ጥቅሶች፣ አንቀጾችና ምዕራፎች ጋር በሐሳብ ተገናኝቶ ስለሆነ አገባቡን በቅርብም በስፋትም መመርመር ያስፈልጋል። አዚህ ላይ ማስታወስ የሚገባን አሁን በመጽሐፍ ቅዱሳችን የምናየው የምዕራፍና የቁጥር ክፍፍል መጀመሪያ ሲጻፍ እንዳልነበረ ነው። ብሉይ ኪዳን በምዕራፍና በቁጥር የተከፈለው በ1445 ዓ.ም ሲሆን አዲስ ኪዳን ደግሞ የተከፈለው በ1551 ዓ.ም ነው። ስለዚህ ከጊዜ በኋላ በተደረገው በምዕራፍና በቁጥር ክፍፍል ሳንገደብ ሐሳቡን ለማግኘት የሚቀድመውንም የሚከተለውንም ማንበብ ያስፈልገናል።

2. መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ይተረጉማል። በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጥቅስ ወይም አንድ ክፍል ትርጉሙ ግልጽ ካልሆነ ወይም ጥያቄ የሚፈጥር ከሆነ በሌሎች ግልጽ በሆኑ፣ በማያሻሙ ጥቅሶችና ክፍሎች አንጻር መተርጎም አለበት። ይህም የሚሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ አንድ አምላክ በመሆኑና በውስጡም የሚገኘው መንፈስና ሐሳብ አንድ ስለሆነ ቃሉ አንድነት እንጂ እርስ በርስ የመቃረን መንፈስ ስሌለው ነው። በዚህ ዓይነት ቃሉን መተርጎም፣ በማስተያየት የመተርጎም መንገድ ይባላል። በዚህ መልክ ሲተረጎም የሚከተሉትን ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይጠቅማል [1 ቆሮንቶስ 2፡13]። 

ሀ. በመጽሐፍ ቅዱስ ዓላማ መሠረት መተርጎም። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዓላማ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ወይም መልእክት ለሰዎች ማብሠር ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ዓላማ ስለ ክዋክብት፣ ስለ ከርሠ ምድር፣ ታሪክ፣ መልክዓ ምድርና የመሳሰሉትን ማስተማር ሳላልሆነ እነዚህን ለማጥናት የሚፈልግ ሌላ መጽሐፍ መፈለግ ይኖርበታል። ሐዋርያው የመጽሐፍ ቅዱስን ዓላማ ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ይጽፋል፦ “ከሕፃንነትህ ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፣ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅ ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” [2ጢሞ. 3፡ 16-17]

ይህ አተረጓጎም ለመላው መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ለእያንዳንዱም ክፍል አስፈላጊ ነው። እያንዳንዱ ክፍል ለምን እንደዚያ እንደ ተፃፈ ዓላማውንና ሁኔታውን ማወቅ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ያዕቆብ በመልእክቱ “እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ ነው” ብሎ የጻፈው፣ እናምናለን እያሉ በግብረገባዊና ማኅበራዊ ኑሮ በግድየለሽነት ለሚኖሩት ሲሆን፣ በአንጻሩ ደግሞ በገላትያና በሮሜ ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገር ግን ለማይሠራ ኃጢአተኛውንም በሚያጸድቅ ለሚያምን እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርለታል” ሲል በግብረገብ ሥራቸው ብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ ተወዳጅነትንና ጽድቅን እናገኛለን ብለው ለተመጻደቁት ሰዎች ነበር። ሁለቱም ሐዋርያት የጻፉት ተነጣጥሎ ለየብቻ ሲታይ የሚቃረን ቢመስልም የተጻፈበትን ሁኔታና የሰዎቹን ዓይነት ስናይ የሚደጋገፉ እንጂ የሚለያዩ ወይም የሚቃረኑ ሆነው አናገኝም። 

ለ. ክፍሉን በተመሳሳይ ርእስ ላይ በሚናገሩ በሌሎች ክፍሎች አማካይነት መተረጎም። ለምሳሌ ያክል ራእይን ስንተርጉም ሌሎች የትንቢት መጻሕፍትና ክፍሎች ስላሉ ከእነርሱ ጋር እያገናዘቡ መተርጎም አስፈላጊ ነው። ስለ ጥምቀት፣ ስለ ቅዱስ ቁርባን፣ ደኅንነት፣ ንስሓ ወዘተ፣ የሚናገሩትን ክፍሎች ስለ እነዚህ አርእስት ከሚናገሩ ከሌሎች ክፍሎች ጋር እያመሳከሩ መተርጎም፤ አንዱን ጥቅስ ብቻ ወስዶ ሌሎችን ተመሳሳይ ጥቅሶች ከመርሳት ያድናል። 

ሐ. የቀደመውን በኋላኛውና ሙሉ በሆነው መገለጥ አማካይነት መተርጎም። አዲስ ኪዳን ከብሉይ ኪዳን በኋላ እግዚአብሔር ፍጹምና ሙሉ በሆነው ልጁ ራሱን የገለጸበት ነው። “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፣ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን…” [ዕብራውያን 1፡ 1-2]። “ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና…” [ዕብራውያን 10፡1]። 

ስለዚህ ብሉይ ኪዳን የሚተረጎመው እግዚአብሔር በአዲስ ኪዳን በገለጠው ፍጹምና ሙሉ መገለጥ መሠረት ነው። እንደዚሁም ሐዋርያት በመልእክቶቻቸው የወንጌላትና የትምህርቶቻቸው ይዘት ምን እንደሆነ አብራርተው አስተምረውናል። ስለዚህ መልእክቶቻቸው ወንጌላትን የሚያብራሩልን ናቸው። 

3. መጽሐፍ ቅዱስ ሊተረጎም የሚችለው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ቃል በጻፈው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ይተረጎማል። በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ምክሩንና ሐሳቡን ካልተገነዘቡ “ለፍጥረታዊ ሰው ሞኝነት” መስሎ ሊታየው ይቻላል።

በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ቃሉ መተርጎሙ በኛ በኩል ሊደረግ የሚገባው ዝግጅትና ጥናት ይቀራል ማለት አይደለም። በመንፈስ ቅዱስ በማሳበብ ቃሉን አንብበው ቅደም ተከተሉን፣ ባሕሉን፣ ታሪካዊ ይዞታውን ወዘተ ተመልክተው ትክክለኛ ትርጉሙን ለመረዳት ጥረትና ዝግጅት ሳያደርጉ የመጣላቸውን የሚናገሩና የሚሰብኩ አንዳንድ ሰዎች አሉ። ይህ ግን ስሕተት ነው። ማንኛውም ምእመንና አገልጋይ በጸሎት መንፈስ በመሆን የቃሉን ትርጉም ለመረዳት ከፍተኛ ጥረትና ጥናት ማድረግ አለበት። 

መንፈስ ቅዱስ በምእመናን ሁሉ ውስጥ የሚኖር የኅብረት ወይም የጋራ መንፈስ ነው [1ቆሮንቶስ 12፡ 12]። ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር በቃሉ ለብቻዬ ያስተምረኛል እያልን በቤተ ክርስቲያን በኩል የሚሰጠውን ትምህርትና አገልግሎት መናቅ የተሳሳተ አካሄድ ነው። በቤተ ክርስቲያንም በእውነትና በትክክል ተጠርተው በማስተማር የሚደክሙትን አገልጋዮች አለመስማትም ትክክል አይደለም። መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለያዩ ስጦታዎችን እየሰጠ ምእመናንን በጋራ የሚያንጽ ስለሆነ እውነቱ ለኔ ብቻ ተገለጸልኝ ብለን ሳንኩራራ ከእርስ በርስ በተሰጠን ጸጋ መጠን ልንማማር ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ለመተርጎም መቻላችን ከሌሎች መሰል ክርስቲያኖች ጋር ኅብረት እንዳይኖረን የሚያደርግ አይደለም። መንፈስ ቅዱስ የአንድነት የፍቅርና የትሕትና መንፈስ ነውና። 

4. ቃሉ አሁን ለኔ (ለኛ) ምን ይላል? መንፈስ ቅዱስ ሕያው መንፈስ ስለሆነ በቃሉ አማካይነት እያንዳንዳችን አሁን ላለንበት ሁኔታ ይናገራል። ያነበብነው ቃል መጀመሪያ በተነገረበት ወይም በተጻፈበት ጊዜ ምን ትርጉም ነበረው? በአገባቡና በመላው መጽሐፍ መሠረት ምን ትርጉም አለው? ብለን ከጠየቅን በኋላ ዛሬስ ለእኔ (ለእኛ) ምን ይናገራል? ለማኅበረ ምእመናናችንስ ምን መልእክት አለው ብለን መጠየቅ ይገባናል። ማንኛውም ተቀዳሚ ዝግጅት ቃሉን ለሕይወታችን ወደምንሰማበትና ወደምናዋህድበት ደረጃ እንዲያደርሰን ያስፈልጋል። ቃሉ ዛሬ ለእኛ በሚናገርበት መልእክት መሠረት ስንሄድ እግዚአብሔርን የምንከተል፣ ከስሕተት ትምህርት የተጠበቅን በብርሃን የምንጓዝ መልእክተኞች እንሆናለን። 

/ እሸቱ አባተ በኮንኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ ካሊፎርኒያ የሥነ መለኮት ትምህርት መምህር የነበሩ ሲሆን፣ ታህሳስ 18/2004 . ወደ ጌታ ተሻግረዋል። ይህ ክፍልትምህርተ ሥላሴበሚል ርእስ 1987 .. ካሳተሙት መጽሐፍ በደራሲው ፈቃድ የተወሰደ ነው። 

ከጥቂት ወራት በፊት በቃሉ አተረጓጎም ዙሪያ የሚታየውን መዘበራረቅ እንዴት ማረም ይቻላል ብዬ ለመመካከር ስልክ ደውዬለት ነበር። የሰጠኝ ምላሽ አልተረሳኝም። “ከቃሉ ጋር ያልተገናኙ ይሉ ይሉና ባዶ ሲሆንባቸው ይመለሳሉ” የሚል ነበር። በተጨማሪ፣ ታህሳስ 1/2004 እንዲህ የተጻፈ መልስ ያላገኘ ኢ-ሜል ልኬለት ነበር።

ወድ ወንድሜ ዶክተር እሸቱ አባተ፣ 

የጌታ ጸጋ ይብዛልህ።

ራሱን ስላጠፋው የኔሰው ስለ ተባለው መምህር ዜና ሳትሰማ አልቀረህም ብዬ እገምታለሁ። ይህንኑ ከስነ መለኮት አስተምህሮ አንጻር መመርመር አስፈላጊና ወቅታዊ ስለሆነ በዚህ ላይ ሊጽፍ የሚችል ማን ይሆን ብዬ ሳስብ አንተ ትዝ አልከኝ። ለብዙዎች ጥያቄ የፈጠረ ሁኔታ ነውና ብትፈቅድ ባጭሩም እንኳ ቢሆን ጽፈህ ብትልክልን ድረ ገጻችን ላይ እለጥፈዋለሁ። ጌታ ይባርክህ። አደራህን ይህ እንደ ደረሰህ መልሱን አስታውቀን። ምትኩ

----------------------------------------------------

እግዚአብሔር ቤተሰቡን ያጽናና። “ከሰማይም። ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ። አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።” [ራእይ 14፡13]

አብያተክርስቲያናት ይህን እጅግ ጠቃሚና ወቅታዊ የሆነ ትምህርት አባዝተው ለየምዕመኑ እንዲያዳርሱ በጌታ ስም እናሳስባለን።